Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በተክለ ብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን በ708 ሚሊዮን ብር ሲገነባው የነበረ አዳሪ ትምህርት ቤት ለንዑስ ተቋራጮች ተሰጠ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በቡራዩ ከተማ በተክለ ብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን ድርጅት አማካይነት በ708 ሚሊዮን ብር ሲያስገነባው የነበረውን የልዩ ተሰጥኦ አዳሪ ትምህርት ቤት፣ ኮንትራክተሩ ባለበት ማስቀጠል ባለመቻሉ በሥሩ ለነበሩ ንዑስ ተቋራጭ ኩባንያዎች መተላለፉ ተገለጸ፡፡

የቀድሞው ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በአገሪቱ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ተማሪዎች እንዲማሩበትና ጥሩ አስተሳሰብ ይዘው እንዲያድጉ ይረዳል ተብሎ በ2010 ዓ.ም. ከተክለ ብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን ድርጅት ጋር ውል በመግባት፣ በ540 ቀናት ሕንፃው እንደሚጠናቀቅ ቢገለጽም እሰካሁን አለመጠናቀቁ ተገልጿል፡፡

በ2011 ዓ.ም. የሕንፃ ግንባታው ተጠናቆ ተማሪዎችን በመቀበል አገልግሎት እንደሚሰጥ፣ የቀድሞው ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ጌታሁን መኩሪያ (ኢንጂነር) ተናግረው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የአሁኑ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጅ ሚኒስቴር የበላይ ኃላፊዎች ሕንፃው እሰካሁን እንዳይጠናቀቅ ካደረጉት ምክያቶች መካከል ባለፉት ዓመታት በቡራዩ አካባቢ በነበረ የፀጥታ ችግር፣ እንዲሁም ተክለ ብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን ድርጅት አሁን ባለበት ሁኔታ ግንባታውን ማስቀጠል የሚችልበት አቅምና ሁኔታ ላይ እንደማይገኝ አስረድተዋል፡፡

የኢድና ሞል ባለቤት አቶ ተክለ ብርሃን አምባዬ በስማቸው የተቋቋመውን የኮንስትራክሽን ድርጅት (ተክለ ብርሃን አምባዬ ኮንክትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር) ዋና መሥሪያ ቤትና ኢድና ሞልን በመያዣነት በመጠቀም፣ ከባንክ የወሰዱትን ብድር ባለመመለሳቸው፣ ብድሩን የሰጠው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የብድሩ መያዣ የሆኑትን ሕንፃዎች በሐራጅ መሸጡ ይታወሳል፡፡

በቡራዩ ከተማ 1,000 ተማሪዎችን እንዲይዝና ሁለት የተማሪዎች መኝታ ቤት፣ ላይብረሪ፣ ካፊቴሪያ፣ ላቦራቶሪና ቢሮዎች የተካተቱበት የሕንፃ የግንባታ ሒደት ተሰርዞ፣ አዲስ ጨረታ ቢወጣ ቀድሞ በነበረበው ዋጋ ሕንፃውን ማስጨረስ የማይቻል በመሆኑ፣ በመጀመርያው የጨረታ ውልና ዋጋ ዋና ኮንትራክተሩ የቀጠራቸው ተቋራጮች ሕንፃውን እንዲጨርሱ መደረጉን የሚኒስቴሩ የሀብት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ዓባይነህ ሙሉጌታ ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ የንዑስ ተቋራጮቹን ስም ከመጥቀስ ተቆጥበዋል፡፡

ሊቋቋም ለታሰበው አዳሪ ትምህርት ቤት የማቋቋሚያ አዋጅ እንደሚወጣለት የተነገረ ቢሆንም፣ ከሕንፃው አለመጠናቀቅ ጋር ተያይዞ እስካሁን የተባለ ጉዳይ የለም፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በ2012 ዓ.ም. ተመድቦለት የነበረውን የመደበኛና ካፒታል በጀት ለታቀደለት ዓላማ ማዋሉን አስመልክቶ ያካሄደውን የኦዲት ግኝት፣ ጥር 30 ቀን 2014 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳድርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለውይይት  አቅርቧል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ፎርማሊቲ ሳይሟላ የተፈጸመ ግዥ፣ የወጪና ገቢ ማስረጃ ያልተገኘላቸው የገንዘብ መዝገቦች፣ ከመመርያ ውጪ የተከናወነ ግዥ፣ የንግድ ፈቃድ ከሌላቸው አቅራቢዎች የተከናውኑ ግዥዎች፣ በቂ ምክንያት ያልቀረበባቸው ግዥዎች፣ ከአንድ አቅራቢ ብቻ ግዥ መፈጸምና በመሰል የሕግ ግድፈቶች ተፈጸመ ያለውን በቢሊዮን የሚቆጠር የፋይናንስ ኦዲት ክፍተት ለቋሚ ኮሚቴው አቅርቧል፡፡

በተጨማሪም በሚኒስቴሩ ለዓመታት ያለ ሥራ የተቀመጡ አዳዲስና የአገልግሎት ጊዜያቸው እየተጠናቀቁ ያሉ 92 የአዳራሽ ወንበሮች፣ 92 ላፕቶፖች፣ 13 ጄኔሬተሮች፣ የፎቶ ኮፒ ማሽኖች፣ የመኪና ጎማዎች እንዲሁም በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ የተለያዩ ለቢሮ አገልግሎት የሚውሉ መሣሪያዎች ያለ ሥራ ተከማችተው እንደሚገኙ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ሪፖርት አመላክቷል፡፡

ይሁን እንጂ አብዛኛው ክፍተት ሊፈጠር የቻለው ከዚህ ቀደም የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ወደ አንድ ሲዋሀዱ፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከመባሉ በፊት በሁለቱ ተቋማት የነበረው ሀብት በሚገባ ተቆጥሮ፣ በኦዲት ተረጋግጦ ባለመቀመጡና ለአዲሱ ተቋም ባለመተላለፉ የተፈጠረ ክፍተት እንደሆነ የመሥሪያ ቤቱ ኃላፊዎች ተናግረዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች