Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበአማራና በአፋር ክልሎች ለወደሙ የጤና ተቋማት መልሶ ግንባታ እስከ 36 ቢሊዮን ብር...

በአማራና በአፋር ክልሎች ለወደሙ የጤና ተቋማት መልሶ ግንባታ እስከ 36 ቢሊዮን ብር ሊያስፈልግ ይችላል ተባለ

ቀን:

ከአንድ ዓመት በላይ በዘለቀው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በአማራና በአፋር ክልሎች ውድመት የደረሰባቸውን የጤና ተቋማት ወደ ነበሩበት ለመመለስ፣ እስከ 36 ቢሊዮን ብር ሊያስፈልግ ይችላሉ ሲሉ የጤና ሚኒስትሯ ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) ገለጹ።

የወደሙ የጤና ተቋማትና አገልግሎቶችን በአጭር ጊዜ በዝርዝር የሚያሳይ የተጠና ነገር ባይኖርም፣ በዳሰሳ ሲታይ በመንግሥት የተመደበው የድጎማ በጀት ተቋማትን መልሶ ለመገንባት በጣም አነስተኛ እንደሆነ ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

ሊያ (ዶ/ር) ይህንን የተናገሩት የተቋማቸውን የስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ዓርብ ጥር 27 ቀን 2014 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት ነው፡፡ በጦርነቱ ሳቢያ በአፋርና በአማራ ክልሎች 42 ሆስፒታሎች፣ 523 ጤና ጣቢያዎችና 2,359 የጤና ኬላዎች መውደማቸውንና 234 አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ አምቡላንሶች መዘረፋቸውን አስታውቀዋል።

የደረሰውን ጉዳትና ውድመት እንደገና በመንግሥት የመልሶ ግንባታ ፕሮግራም እስኪጀመር ድረስ፣ የጤና ሚኒስቴር  ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ መድኃኒቶች፣ የሕክምና መሣሪያዎችና ገንዘብ ጦርነቱ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ለሕክምና ተቋማትና ለተጎጂዎች ድጋፍ መደረጉን አብራርተዋል።

በልማት አጋሮችና በለጋሽ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በኩል ለተፈናቀሉ ዜጎች የመድኃኒት፣ የአልሚ ምግብና ለጤና ተቋማት የሕክምና ግብዓቶች ከ4.6 ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ቁሳቁሶች ለአማራ፣ ለአፋር፣ ለኦሮሚያና ለቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎች ድጋፍ መደረጉን አክለው ገልጸዋል

ባለፉት ስድስት ወራት ለጤና ተቋማት የሚያገለግሉ የጤና ግብዓቶች ከ10.4 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ከውጭ አገር፣ ገዝቶ ማስገባቱን፣ በጤና ሚኒስቴር ሪፖርት ተመልክቷል።

በዚህም ባለፉት ስድስት ወራት የአገሪቱን የሕይወት አድንና መሠረታዊ የጤና መድኃኒቶች አቅርቦት ወደ 80 በመቶ ማሳደግ እንደተቻለ፣ የጤና ሚኒስትሯ ሊያ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

በግማሽ ዓመቱ 13.1 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ መድኃኒቶች፣ የሕክምና መገልገያዎች መሣሪያዎች፣ እንዲሁም ሌሎች ግብዓቶች መሠራጨታቸውን ገልጸዋል።

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሕመም የመያዝና ከተያዙም የመታመም ዕድልን በእጅጉ ለሚቀንሰው ክትባት ኅብረተሰቡ ያለው አመለካከት ዝቅተኛ በመሆኑ፣ ተከትቦ ሞትን መቀነስ እየተቻለ ባለመሆኑ ግን የሞት መጠን እየጨመረ መሆኑን ሚኒስትሯ አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ ክትባት መሰጠት ይፋ ከተደረገበት ቀን ጀምሮ ወደ ሁለት ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ዋጋ ያላቸው ሲኖፋርም፣ አስትራዜኒካ፣ ጆንሰን ኤንድ ጆንሰንና ፋይዘር የተባሉ ክትባቶችን ከ9.3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች መሰጠቱን ሊያ (ዶ/ር) ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ከ30 ሚሊዮን በላይ የኮቪድ-19 ክትባት በመጋዘን እንዳለ አስረድተው፣ ‹‹በቀጣይ ሰፋ ያለ የቅስቀሳ ዘመቻ በማድረግ ዜጎች እንዲከተቡ እናደርጋለን፤›› ብለዋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...