Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከበረራ ታግዶ የከረመው ማክስ አውሮፕላን አራት ሰዓት በፈጀ የአገር ውስጥ የሙከራ በረራውን ማድረጉ ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሦስት ዓመታት ገዳማ በኋላ የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን አራት ሰዓት የፈጀ የአገር ውስጥ የሙከራ በረራውን በተሳካ ሁኔታ ማጠናቀቁን አስታወቀ፡፡

አየር መንገዱ ማክሰኞ ጥር 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ለሪፖርተር በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው የድርጅቱ የቦርድ ሊቀመንበር፣ ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የቦይንግ ኩባንያ ሥራ አስፈጻሚዎች፣ አምባሳደሮች፣ ጋዜጠኞችና ሌሎች አካላትን በማካተት በኢትዮጵያ የሚገኙ ታወቂ የቱሪስት ቦታዎችን ለአራት ሰዓታት ያህል በአየር ቃኝቶ በስኬት ማረፉ ተገልጿል፡፡

የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም ‹‹የደኅንነት ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጠውና ኩባንያው ለሚያደርጋቸው ማናቸውም ውሳኔዎችና እንቅስቃሴዎች መነሻ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡ በመሆኑም ኩባንያው የአውሮፕላኑን ሥሪትና ውቅር ለ20 ወራት ያክል  ሲገመግም መቆየቱን አስታውቋል፡፡

በአፍሪካ በትልቅነቱ ቀዳሚ ሆኖ የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያሉትን ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖቹን ከበረራ ውጪ ያደረገው ከመጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በዕለቱ ከአዲስ አበባ ወደ ኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ 149 ሰዎችን ይዞ ይጓዝ የነበረ የበረራ ቁጥር ET302 ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን የበረራ ቁጥር በመከስከሱ ነበር፡፡ በዚህ አደጋ የበረራ ሠራተኞቹን ጨምሮ 157 ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል፡፡

አደጋውን ተከትሎ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ በተጨማሪ በዓለም ላይ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች ካለባቸው የደኅንነት መቆጣጠሪያ ችግር ጋር በተያያዘ በረራ እንዲያቆሙ ተደርገው ቆይተዋል።

በቦሌ አየር ማረፊያ የሙከራ በረራውን ያጠናቀቀው አውሮፐላኑ ከዛሬ ጥር 25 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በዚሁ አውሮፕላን  መደበኛ የመንገደኞች በረራ ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ አየር መንግድ አራት የቦይንግ 737 አውሮፕላኖች ያሉት ሲሆን፣ በትዕዛዝ ላይ ከሚገኙት 25 ተመሳሳይ ማክስ አውሮፕላኖች ውስጥ የተወሰኑትን በ2022 እንደሚረከብ አስታውቋል፡፡

 

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች