Sunday, May 19, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የአፍሪካ ኅብረት ፋይዳ በቅጡ ይታወቅ!

የአፍሪካ የነፃነት እንቅስቃሴዎች ተጋግመው በርካታ የአፍሪካ አገሮች ከቅኝ ገዥዎቻቸው ነፃ ለመውጣት ሲቃረቡ፣ እ.ኤ.አ. በ1959 ምዕራባውያን ቅኝ ገዥዎች፣ ‹‹አፍሪካውያን ለነፃነት ዝግጁ ናቸው ወይ?›› የሚል አስገራሚ ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡ ይህ ጥያቄ መቅረቡ የከነከናቸው የታንዛኒያ መሥራች አባት በመባል የሚታወቁት ጁሊየስ ኔሬሬ፣ ‹‹ቤቴ መጥተህ ጃኬቴን ከሰረቅከኝ በኋላ፣ እኔ ጃኬቴን መልሼ ለመውሰድ ዝግጁ መሆኔን ለመጠየቅ ምንም ዓይነት መብት የለህም፡፡ …ምናልባት አለባበሱን አሳምሬ ዘናጭ ላልሆንበት እችል ይሆናል፣ ነገር ግን ጃኬቱ የእኔ ነው…›› ነበር ያሉት፡፡ በተለይ አፍሪካን እንደ ቅርጫ ሥጋ የተቀራመቱት ቅኝ ገዥዎቹ እንግሊዝና ፈረንሣይ፣ ከአፍሪካ ሲያግዙት የነበረውን የተፈጥሮ ሀብት በቀላሉ ከእጃቸው እንዳይወጣ ሲሉ ነበር የአፍሪካውያኑን ለነፃነት ብቁ መሆን ጥያቄ እንዲነሳበት ያደረጉት፡፡ ይህ ጥያቄ ግን እንደ ዘበት የቀረበ ሳይሆን፣ በእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ የተለመደውን ዘረፋ ያለ ከልካይ ለማካሄድ የተጠነሰሰ ሴራቸው አካል ነበር፡፡ ዛሬም የቀድሞዎቹ ቅኝ ገዥዎች ቀብረውት የሄዱት የተንኮል ቦምብ በየጊዜው እየፈነዳ፣ አፍሪካን ሰላም በማሳጣትም ይታወቃል፡፡ አፍሪካውያንን በጥንካሬ የሚያስተባብራቸው ኅብረት ባለመኖሩ  ነው ይህ ሁሉ ፍዳ የሚታየው፡፡

ኢትዮጵያ የቀድሞውን የአፍሪካ አንድነት ድርጅትም ሆነ የአሁኑን የአፍሪካ ኅብረት ዕውን ለማድረግ የከፈለችውን መስዋዕትነት ለመዘርዘር መሞከር፣ ለቀባሪው ማርዳት ስለሆነ ዝርዝሩ ውስጥ አንገባም፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያዊያን ለአፍሪካውያን ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ታላቅ ተምሳሌት እንደነበሩ፣ በታላቁ ፀረ ኮሎኒያሊስት የዓድዋ ጦርነትና ከዚያም ከወራሪው የፋሽስት ኃይል ጋር ያደረጉዋቸው ተጋድሎዎች አይረሱም፡፡ ለፓን አፍሪካኒዝም ጥንስስ መሠረት የሆኑት ኢትዮጵያዊያን ጀግኖች አፍሪካውያን ወገኖቻቸው ከቅኝ አገዛዝ ለመላቀቅ ያደረጉትን ትግል ከማገዝ ጀምሮ፣ የጋራ መሰባሰቢያ የሆነ ድርጅት የመመሥረት ሐሳብ በማፍለቅና ከግብ በማድረስ ታላቅ ተጋድሎ ማድረጋቸውም አይዘነጋም፡፡ ባለ ራዕዮቹ ኢትዮጵያዊያን ይህንን የመሰለ መስዋዕትነት የሚጠይቅ ግዳጅ ተወጥተው የአፍሪካውያን መሰባሰቢያ ቢፈጥሩም፣ ይህ ተቋም ግን ለኢትዮጵያ ያለው ፋይዳ ምንድነው? ኢትዮጵያዊያንስ ከዚህ ተቋም ተጠቃሚ ለመሆን ያደረጉት ጥረት ምንድነው? ተቋሙስ ይበልጥ ተጠናክሮ ለሁሉም አፍሪካውያን የጋራ ተጠቃሚነት እንዲሠራ ምን አድርገዋል? እያደረጉስ ነው? የአፍሪካ ኅብረት በትክክል የአኅጉሪቱ መሠረታዊ ፍላጎቶችና ችግሮች ላይ እየሠራ ነው? ወይስ እዚህ ግባ በማይባሉ ፋይዳ ቢስ ጉዳዮች ነው የሚወጠረው? የመሳሰሉ ወቅቱን የሚዋጁ ጥያቄዎች ማንሳት የግድ ይላል፡፡

ከአፍሪካ ኅብረት አፍሪካውያን በጋራ፣ ኢትዮጵያ ደግሞ በተናጠል ያገኘችው ጥቅም ምንድነው? የአፍሪካ ኅብረት የሰጠው ጥቅም አለ ከተባለስ ምን ይሆን? ያጎደለውስ ምንድነው መባል ይኖርበታል፡፡ የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ በአዲስ አበባ ሲካሄድ እንግዶችን በሰላም ተቀብሎ ማስተናገድ፣ የኢትዮጵያውያን የተለመደና የተመሠገነ ባህል ነው፡፡ ከዚህም አልፎ ተርፎ መንገዶች ሲዘጋጉ የሚደርሰው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳትም ይታወቃል፡፡ በሌላ በኩል እንግዶች ይዘው ከሚመጡት አበል የሚቆነጥሩት ገቢ እንዳለም አይዘነጋም፡፡ ነገር ግን ኅብረቱ ለአፍሪካ በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ደግሞ እንደ አስተናጋጅነቷ በተናጠል ያለው ፋይዳ ሲመዘን፣ አሁንም የሚያነጋግሩ በርካታ እንከኖች አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል አንዱ አፍሪካን ከውጭ ተፅዕኖ በማላቀቅ ራሷን እንድትችል አለማድረግ ነው፡፡ በአፍሪካ የጠመንጃ አፈሙዝ ፀጥ የሚለው ፍትሕ፣ ነፃነትና እኩልነት ሲሰፍን ነው፡፡ ከመፈክር የማያልፍ አጃንዳ ይዞ መምጣት ፋይዳ የለውም፡፡ በምርጫ ብቻ ሥልጣን ላይ የሚወጡ መሪዎች መብዛት ሲገባቸው፣ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ከሱዳን እስከ ማሊና ቡርኪና ፋሶ ድረስ ፋሽን ሆኗል፡፡ ኅብረቱም ለጊዜው አገሮችን ከአባልነት ከማገድ ያለፈ አቅም ስለሌለው፣ አምባገነኖች በብዛት ሥልጣን እየያዙ ነው፡፡

አፍሪካውያን በተባበረ ድምፅ የእኛ ነው የሚሉት ተቋም ለመሆን ብዙ ይቀረዋል፡፡ የውጭ ዕርዳታ እየተማፀነ በለጋሾች ፍላጎት ከሚዘወር፣ በአባል አገሮች ቁርጠኝነት ራሱን ነፃ አውጥቶ ተቋማዊ ነፃነቱን ካላስጠበቀ ፋይዳ ቢስ ነው፡፡ ከአጠቃላዩ የአፍሪካ ችግር ወደ ኢትዮጵያ ጉዳይ ስንመለስ ሁለት መሠረታዊ ችግሮችን እናነሳለን፡፡ የመጀመርያው የአፍሪካ ኅብረት ለኢትዮጵያ ያለው ፋይዳ ሲሆን፣ ሁለተኛው ኢትዮጵያዊያን በአፍሪካ ኅብረት ለመጠቀም ያደረጉት ጥረት ነው፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካውያንን የጋራ ቤት ለመገንባት በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ያለፈችበትን ውጣ ውረድ ታሪክ በሚገባ ከትቦታል፡፡ ይህንን የተቀደሰ ዓላማ ለማሳካት ታላቅ ተጋድሎ ያደረጉ ኢትዮጵያዊያን በሚገባ ይታወቃሉ፡፡ አፍሪካውያን የጋራ የሆነው ተቋማቸው በተለያዩ ጊዜያት የመፍረስ አደጋ ሲያጋጥመው፣ ባለ ራዕዮቹ ኢትዮጵያዊያን እንዴት እንደታደጉት አይረሳም፣ ታሪክም ምስክር ነው፡፡ በተለይ ምዕራባውያን የአፍሪካውያን በአንድ ኅብረት ጥላ ሥር መሰባሰባቸው ሥጋት ሲፈጥርባቸው፣ በኮርፖሬት ሚዲያዎቻቸው አማካይነት በሚነዙት ፕሮፓጋንዳና በአባል አገሮች መሀል በሚፈጥሩት ቅራኔ በተደጋጋሚ ሊያፈርሱት ጥረት አድርገዋል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ዋናዋ አክሻፊ ኢትዮጵያ ነበረች፡፡

ነገር ግን ኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች ችግር ሲገጥማት፣ ይህ ተቋም ከንፈር ከመምጠጥ የዘለለ ያደረገላት ምንም ነገር የለም፡፡ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ድንበሯ ተጥሶ ስትወረር፣ ቻርተሬ ተጥሷል ብሎ ጥብቅና ሲቆም አይታወቅም፡፡ ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር ጥሳ ገብታ ሰፊ መሬት ከያዘች ከአንድ ዓመት በላይ ቢሆናትም፣ የአፍሪካ ኅብረት አንዴም አጀንዳ ሲያደርገው አልታየም፡፡ ሁሉም የአፍሪካ አገሮች በቅኝ ግዛት ወቅት ባለው ድንበር መፅናት አለባቸው የሚለው ቻርተር በብዙ አገሮች ተጥሶ፣ የበርካታ ንፁኃን ሕይወት እንዲያልፍ መደረጉም አይዘነጋም፡፡ በጎረቤት አገሮች የውክልና ጦርነት በተደጋጋሚ የተከፈተባት ኢትዮጵያን ደግፎ ሲቆም አልታየም፡፡ ሌላው ቀርቶ የኅብረቱ ዋና መሥሪያ ቤት ባለበት አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያውያን ከጥቂቶች በስተቀር አብዛኞቹ ማለት ይቻላል፣ ከጥበቃና ከጉልበት ሠራተኝነት የተሻለ ሥራ ማግኘት እንኳ አይችሉም፡፡ በዚህ ላይ በበላይ አለቆቻቸው የሚፈጸምባቸው ግፍ ብዙ የተባለበት ነው፡፡ የአፍሪካ ኅብረት ዘመናዊ ሕንፃ በመዲናዋ ቢገተርም፣ ልጆቿ ግን ከሩቅ የማየት የዘለለ ተሳትፎ የላቸውም፡፡ ይህም ለምን መባል አለበት፡፡

ኢትዮጵያ 500 ሚሊዮን ሕዝብ ያህል ይኖርበታል በሚባለው የዓባይ ተፋሰስ ውስጥ፣ ለዓባይ ወንዝ 86 በመቶ የውኃ ሀብት የምታበረክት አገር ናት፡፡ በታሪኳ ለመጀመርያ ጊዜ በዓባይ ወንዝ ላይ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጭ ግድብ ለመገንባት ስትነሳ፣ እስካሁኗ ሰዓት ድረስ እየገጠማት ያለው ፈተና ይታወቃል፡፡ ውኃውን በፍትሐዊነት የመጠቀም መርህ መሠረት በታችኞቹ የተፋሰስ አገሮች ላይ ጉልህ ጉዳት ሳታደርስ፣ ከድህነት ለመውጣት በምታደርገው ፍትሐዊ እንቅስቃሴ ታላቁን የህዳሴ ግድብ እየገነባች አሥር ዓመታት ቢቆጠሩም፣ በተለይ ከግብፅ ጋር የምታደርገው እልህ አስጨራሽ ድርድር እየፈተናት ነው፡፡ የሦስትዮሽ ድርድሩ ከአቅም በላይ ሆኖ ለኅብረቱ ቢመራም፣ ድርድሩ እንዲህ በዋዛ የሚቋጭ አይደለም፡፡ በዚህ ሁሉ ፈተና ውስጥ ያለችው ኢትዮጵያ በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት እንዴት ፍትሐዊ ውሳኔ ታጣለች? ይህ ጥያቄ የአፍሪካ ኅብረትንና የኢትዮጵያ ባለሥልጣናትን ይመለከታል፡፡ ‹‹አፍሪካውያን ችግራቸውን በራሳቸው መፍታት አይችሉም›› እየተባሉ መሳለቂያ ከሚደረጉባቸው ማሳያዎች አንዱ ይህ ነው ቢባል ስህተት ይሆናል? ኢትዮጵያውያን ‹‹በቅኝ ግዛት ዘመን ሕግ አንገደድም፣ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን የሚቃረን ስምምነት መስማት አንፈልግም፣ የመልማት መብታችን ይከበር…›› ሲሉ የአፍሪካ ኅብረትስ ምን ይላል? የእኛ ባለሥልጣናትስ ኅብረቱን ምን እያሉት ነው? መቋጫ ያጣው ድርድር ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ቢያመራ መመለሻው ምን ይሆን? አፍሪካውያን ተፈጥሮ በሰጠቻቸው ሀብት መስማማት አቅቷቸው ጦር እስኪማዘዙ ነው ወይ የሚጠበቀው? ይህም መልስ የሚፈልግ ጥያቄ ነው፡፡ ለዚህም ነው የአፍሪካ ኅብረት ፋይዳ በቅጡ መታወቅ ያለበት!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...

በስድስተኛው ዙር ጠቅላላና ድጋሚ ምርጫ የሚሳተፉ ፓርቲዎች በገዥው ፓርቲ ላይ ተቃውሞ እያቀረቡ ነው

በ2013 ዓ.ም. ስድስተኛው ምርጫ ባልተካሄደባቸው ክልሎች በጠቅላላና በድጋሚ ምርጫ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት ብትችል፣ ከበርካታ ታዳጊ አገሮች የተሻለ በዕድገት ጎዳና የመገስገስ እምቅ አቅም እንዳላት የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ይህንን የመሰለ...

የመግባቢያ አማራጮችን ተባብሮ መፈለግ ከጥፋት ይታደጋል!

በአሁኑ ጊዜ ሕዝብና አገርን ጤና የሚነሱ በርካታ ችግሮች በየቦታው እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ ችግሮቹ ከመጠን በላይ እየተለጠጡ ቅራኔዎች ሲበረክቱ ሰከን ብሎ ከመነጋገር ይልቅ፣ የጉልበት አማራጭ...

አገርን ከቀውስ ውስጥ ማውጣት ብሔራዊ አጀንዳ ይሁን!

የአገራቸው መፃኢ ዕድል የሚያሳስባቸው በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ወገኖች፣ በየቀኑ የሚሰሟቸው ማቆሚያ ያጡ ልብ ሰባሪ የግጭትና የጦርነት ዜናዎች እንቅልፍ ይነሷቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ማንኛውም...