Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየአገሪቱ ማስተር ፕላን በመንግሥት ባለሥልጣናት እየተጣሰ ነው ተባለ

የአገሪቱ ማስተር ፕላን በመንግሥት ባለሥልጣናት እየተጣሰ ነው ተባለ

ቀን:

በከተሞች የሚተገበረው የአገሪቱ ማስተር ፕላን ከላይኛው እስከ ታችኛው የመንግሥት ዕርከን ባሉ ባለሥልጣናት እየተጣሰ መሆኑ ተገለጸ፡፡

አገሪቱ ከምትከተለው የፖሊሲና የዕድገት አቅጣጫ ጋር የተጣጣመና የተቀናጀ የልማት ፕላን እንዲኖር ማድረግ፣ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ከተሞች የከተማ ገጠርና የከተማ ከተማ ትስስርን ማጠናከር፣ እንዲሁም ተመጋጋቢና የተመጣጠነ የአከታተም ሥርዓት መፍጠር የሚል የከተሞች ፕላን በ2000 ዓ.ም. መውጣቱ ይታወሳል፡፡

ይሁን እንጂ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የወጣው ማስተር ፕላን ከአመራሮች ትኩረት ማነስ የተነሳ በበርካታ ከተሞች ተጥሶ፣ የከተማ መሬት እየተሸነሸነ ለተለያየ ዓላማ እያዋለ መሆኑን የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ፣ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት፣ በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የከተሞች አሰፋፈር ምቹነት ላይ ያካሄደውን የ2012 እና የ2013  በጀት ዓመት የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ላይ ጥር 18 ቀን 2014 ዓ.ም. ውይይት አካሂዷል፡፡

በውይይቱ በመሬት አጠቃቀም  ላይ አመራሮች ምንም እንኳ በሕግ የተሰጣቸው ኃላፊነት ቢኖርም ከአሠራር ውጪ መሬትን እንደፈለጉ የመጠቀም አዝማሚያ እንዳላቸው በሚኒስቴሩ የከተማ ፕላን ዝግጅትና ትግበራ ክትትል ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ገነት ገብረ እግዚአብሔር ተናግረዋል፡፡

ለአብነትም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ለገሃር አካባቢ ኤግል ሂልስ የተባለ የቤቶች ፕሮጀክት በመሬት ባንክና ማስተላለፍ ጽሕፈት ቤት በኩል የተላለፈው የቦታ ስፋት 11.1 ሔክታር ሆኖ እያለ፣ ኩባንያው ባዘጋጀው የከተማ ዲዛይን 33.9 ሔክታር ሆኖ መገኘቱን የኦዲት ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡

ይሁን እንጂ የቦታ ስፋቱ ከሚፈቅደው ውጪ በከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ፣ የሕዝብን ጥቅም ለማስከበር በሚል ሰፊ ቦታ መስጠቱን ኃላፊዋ ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ ቤተ መንግሥት አካባቢ የተገነባውና የወዳጅነት ፓርክ የሚል ስሜ የተሰጠው የመዝናኛ ቦታ በማስተር ፕላኑ መሠረት የንግድ ማዕክል እንደነበር፣ ፓርኩ ሲገነባ በፕላኑ መሠረት ለማዕከሉ ማካካሻ የሚሆን ቦታ እንዳልተዘጋጀ አክለው ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም የተለያዩ ከተሞች መሬትን በጊዜያዊነት በሚል እየሸነሸኑና እያጠሩ፣ የተሻለ ኢንቨስትመንት ሲመጣላቸው ፕላኑን በመጣስ ለሌላ ተግባር እየሰጡ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በመሆኑም የመንግሥት ኃላፊዎች የሚፈልጉትን ቦታ ኮሚቴ አቋቋመው በጋራ ሆነው ለሚፈልጉት ተግባር እንደሚወስኑ የገለጹት ኃላፊዋ፣ ይህን ድርጊት ምክር ቤቱ ለምን ብሎ መጠየቅ አለበት ብለዋል፡፡

በበርካታ ከተሞች ከፕላን ውጪ ሕገወጥ የመሬት ወረራ ስለመበራከቱ  የገለጹት ወ/ሮ ገነት፣ ከተሞቹ ሲጠየቁ ጥናት እያደረግን ነው የሚል መልስ እንደሚሰጡና ይህ እንቅስቃሴ ከወዲሁ ካልተገታ ችግሩ እንደማይቆም ገልጸዋል፡፡ ምክር ቤቱ ያወጣው የከተማ ፕላን ምን ላይ እንዳለ መገምገምና መጠየቅ ካልቻለ፣ በቀጣይ ልማት የሚባል ነገር ከፕላኑ ውጪ ይሆናል ብለዋል፡፡

የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ አባላት በክልልም ሆነ በታችኛው የመንግሥት መዋቅር ላይ መሠረታዊ ማስተር ፕላኑ ሳይፈቅድ፣ ከተሞች እንደፈለጉ በራሳቸው እየተነሱ ሕግና መመርያ ሲጥሱ የ‹‹ሥርዓተ አልበኝነት›› እንቅስቃሴ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሊያስቆም እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽነር ሳሙኤል ኡርካቶ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የአዲስ አበባ ከተማ የአፍሪካ መዲና እየተባለ ፕላኑ በማይፈቅደው መንገድ መሬት እንደተፈለገ የሚሸነሸን ከሆነ፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በቀላሉ ሊያልፈው እንደማይገባ አስረድተዋል፡፡

ኮሚሽነሩ አክለውም ሕግ በግለሰቦች እንደተፈለገ እየተጠመዘዘ የሚጣስ ከሆነና ለሕዝብ ጥቅም በሚል ሕግ ጥሶ ልማት እንደሌለና የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በቅንጅት መሥራት እንዳለበት ጠቁመው፣ ‹‹ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አያያዙ አላማረኝም፤›› ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለፀረ ሙስና ትግል ያለው ተነሳሽነት ዝቅተኛና በመሆኑ የሙስና ተጋላጭነቱ ከፍተኛ በመሆኑ፣ ከተማው ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንዳለ ኮሚሽነሩ አክለው ገልጸዋል፡፡

 ከጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አጠቃላይ ጉዳዩን በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት ወ/ሮ ትብለጥ ቡሽራ በበኩላቸው፣ ኤግል ሂልስ ለተባለው ፕሮጀክት በመሬት ባንክ 11 ሔክታር ተብሎ ተመዝግቦ ወደ 33 ሔክታር ከፍ መደረጉ፣ በፖለቲካ አመራሩ ለሕዝብ ጥቅም በሚል የተወሰነው ውሳኔ የመሬት ባንክ ሳያውቀው ነው ብለዋል፡፡ የሚመለከተው ተቋም ሳያውቀውና ንግግር ሳይደረግበት፣ በፖለቲካ አመራሩ ብቻ መወሰኑ አግባብ ባለመሆኑ ሊስተካከል እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡

በርካታ ተቋማት ላይ የሚታየው የኦዲት ችግር በሕግ በተሰጣቸው አግባብ ሥራን አለመሥራት እንደሚስተዋል፣ ለዚህም ፓርላማው ተጠያቂነትን ለማረጋጋጥ በቁርጠኝነት ሊሄድበት እንደሚጋባ ወ/ሮ ትብለጥ ጠቁመዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ስብሳቢ አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ ‹‹ግለሰቦች ከተማን ያህል ነገር በዚህ ልክ ሕግን በመጣስ ለፈለጉት ዓላማ ሲያውሉና የትውልዱን የወደፊት ዕጣ ፋንታ ሲያበላሹ ለምን ይፈቀድላቸዋል?›› ሲሉ ወቀሳ አቅርበዋል፡፡

‹‹የከተማ ምክር ቤቶች የሕዝብ ወኪል ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ከተሞች ግን የፖለቲከኞች ብቻ አይደሉም ከተሞች የነዋሪዎች ናቸው፡፡ ፖለቲከኞች የሕዝቡ አንድ አካል እንጂ ብቸኛ ወኪል አይደሉም፡፡ በመሆኑም ሁሉም ነዋሪዎች በከተማቸው ጉዳይ ሲሠሩ ሥራዎችን የማወቅ፣ የመሳተፍና ባለቤትነታቸውን የማረጋገጥ መብት አላቸው፡፡ በመሆኑም የሕዝብ ተሳትፎ በፖለቲከኞች ተሳትፎ ብቻ እየተመዘነና እየተለካ አሳትፈናል ተብሎ መሄድ ስለሌለበት ግልጽ ሥርዓት መዘርጋት ይገባዋል፤›› ሲሉ አሳስበዋል፡፡

አክለውም ራሰን በራስ የማስተዳደር መብትን በማስታከክ ለሕዝብ ጥቅም እየተባለ ውሰን ግለሰቦች ሌብነትን እንዲያበረታቱ አይፈቀድም ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...