Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናፓርላማው በታሪክ ከፍተኛ የተባለውን 90 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት ለአገር መከላከያ አፀደቀ

ፓርላማው በታሪክ ከፍተኛ የተባለውን 90 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት ለአገር መከላከያ አፀደቀ

ቀን:

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአገሪቱ ታሪክ ከፍተኛ የተባለውን የ90 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት ለአገር መከላከያ አፀደቀ፡፡

ምክር ቤቱ ዓርብ ጥር 20 ቀን 2014 ዓ.ም. ባደረገው 3ኛ ልዩ ስብሰባ የ2014 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግሥት ተጨማሪ በጀት 122 ቢሊዮን ብር ሆኖ እንዲፀድቅ ከሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበለትን ረቂቅ፣ በዘጠኝ ተቃውሞ፣ በሰባት ተዓቅቦ፣ በአብላጫ ድምፅ አፅድቆታል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰኔ 28 ቀን 2013 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ፣ የፌዴራል መንግሥት የ2014 በጀት ዓመት 561.7 ቢሊዮን ብር አድርጎ ሲያፀድቅ፣ ለአገር መከላከያ ሚኒስቴር 22 ቢሊዮን ብር መመደቡ ይታወሳል፡፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ታኅሳስ 20 ቀን 2014 ባካሄደው ስብሰባ በአገሪቱ በተከሰተው ጦርነት ምክንያት ተጨማሪ ወጪ በማስፈለጉና ከኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አኳያ የሚሰበሰበው ገቢ አሁን ያለውን የክፍያ ጥያቄ ለማስተናገድ አስቸጋሪ ሁኔታ በመፍጠሩ፣ እንዲሁም ወቅቱ የፈጠረውን የተጨማሪ ወጪ ፍላጎት በበጀት ሽግሽግ ለማስተናገድ ያልተቻለ በመሆኑ፣ የተጨማሪ በጀት ጥያቄ ቀርቦ ውይይት ከተካሄደበት በኋላ ለዝርዝር ዕይታ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መመራቱ አይዘነጋም፡፡

በፓርላማ በአብላጫ ድምፅ የፀደቀው ተጨማሪ በጀት 90 ቢሊዮን ለመከላከያ ሚኒስቴር የትጥቅና ቀለብ ወጪ፣ ስምንት ቢሊዮን ብር ለዕለት ደራሽ ዕርዳታ፣ ስምንት ቢሊዮን ብር ለመጠባበቂያ፣ ሰባት ቢሊዮን ብር ለካፒታል ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ፣ እንዲሁም ዘጠኝ ቢሊዮን ብር ለወጪ አሸፋፈን ማስተከካከያ ተብሎ ቀርቧል፡፡

ከዚህ በፊት ባልተለመደ ሁኔታ ወጪው በአገር ውስጥ ብድር እንደሚሸፈን የተገለጸ ሲሆን፣ የበጀት አመዳደቡም ከምክር ቤት አባላት ጥያቄዎች ተነስተውበታል፡፡

አቶ መለሰ መና የተባሉ የምክር ቤቱ አባል ለአገር ዋጋ ለከፈለው መከላከያ 90 ቢሊዮን ብር ቢያንስ እንጂ አይበዛም ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ በጦርነቱ ለተጎዱትና ለዘመናት ገበሬው ሲገለገልባቸው የነበሩ የግብርና ተቋማት በመውደማቸው እንደገና ለማቋቋም የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል አቶ አብዱልከሪም አብዲ የተባሉ ተወካይ በሶማሌ ክልል ያለውን የድርቅ ሁኔታ የማይገልጽ በጀት በመሆኑ፣ እንደገና እንዲከለስ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

በተመሳሳይ ከሰሜኑ ጦርነት ባልተናነሰ በቦረና፣ በጉጂ፣ በሶማሌና በተወሰኑ የአፋር አካባቢዎች እንስሳት እየሞቱና ሰዎች እየተሰደዱ፣ ሕፃናትና እናቶች በከፍተኛ ሁኔታ ችግር ውስጥ ገብተው በተወሰነ መጠን የበጀቱ አጠቃቀም እነዚህን አካባቢዎች ያጠቃለለ ቢሆን ዜጎችን በአግባቡ መታደግ ይቻል እንደነበር የገለጹት ከፈና ኢፈ (ዶ/ር) የተባሉ የምክር ቤት አባል ናቸው፡፡

ሌላ የምክር ቤት አባል ደግሞ በአማራና በአፋር ክልሎች በጦርነቱ ምክንያት በርካታ ንብረቶች መውደማቸውን፣ የትምህርትና የጤና ተቋማት ወደ አገልግሎት እንዲመለሱ ከተፈለገ የበጀት ድጎማው ለእነዚህ አካባቢዎች ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ውድመት የደረሰባቸውን አካባቢዎች እንደገና መልሶ ለማቋቋም አምስት ቢሊዮን ብር ተብሎ መቅረቡ፣ ዘመን ተሻጋሪ በሆኑ የምርምር ተቋማት የደረሰውን ውድመት በብዙ ቢሊዮኖች መመለስ እንደማይቻል ሌላ የምክር ቤት አባል ጠይቀዋል፡፡

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ፓርቲ ተወካይ ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር)፣ ‹‹ለአገር መከላከያ 90 ቢሊዮን ብር ተብሎ መቅረቡ ተገቢ ቢሆንም፣ በመንግሥት ተረስቷል ወይም ተዘሏል ብዬ የምለው፣ አማራና አፋር ክልሎች በተለየ ሁኔታ የፀጥታ መዋቅራቸውን እያሰፉ መሆናቸውንና የልዩ ኃይል ቁጥራቸውም ሰፊ በመሆኑ፣ በሰሜኑ ጦርነት በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ አውጥተው ጦርነት ውስጥ በመቆየታቸው፣ መንግሥት ይህንን ወጪ ካልተካላቸው ወጪያቸው እንዴት ታስቦ ነው?›› የሚል ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ለቀረቡት ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ፣ በተለይ ከአማራና ከአፋር ክልሎች የሚደረገው የመልሶ ማልማት ግንባታ በማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴና በየደረጃው ካሉ ተቋማት ውይይት ተደርጎበት፣ በምን ዓይነት መንገድ መከናወን እንዳለበት ተወስኗል ብለዋል፡፡

ዓለም አቀፍ ልምድ ባላቸው የጥናት ባለሙያዎች የሚደገፍ የመልሶ ማልማት ፕሮጀክት መፅደቁን፣ እስከ መጪው መጋቢት 2014 ዓ.ም. ድረስ ዝግጅት ተጠናቆ ወደ ሥራ እንደሚገባ አክለው ተናግረዋል፡፡

ለዚህ ይረዳ ዘንድ ከዓለም ባንክ 300 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን፣ በመጪዎቹ ሳምንታት የሚጠናቀቅ መስመር ላይ ያሉ 150 ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ መገኘቱን ጠቁመዋል፡፡

በሌላ በኩል የአማራና የአፋር ክልሎች የፀጥታ ተቋማትን በበጀት መደገፍ በተመለከተ ለቀረበው ጥያቄ፣ መንግሥት ድጋፍ የሚያደርገው ለመከላከያ ሠራዊትና ለፌዴራል የፀጥታ ተቋማት በመሆኑ እነዚህ የክልል የፀጥታ መዋቅሮች በክልል በሚመደብ በጀት እንደሚደገፉ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...