Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየሙስና ሥጋት ተጋላጭነትን የሚገመግም አገር አቀፍ የፀረ ሙስና ፎረም ሊቋቋም ነው

የሙስና ሥጋት ተጋላጭነትን የሚገመግም አገር አቀፍ የፀረ ሙስና ፎረም ሊቋቋም ነው

ቀን:

በኢትዮጵያ የፀረ ሙስና ትግሉን በመከታተል አገራዊ የፀረ ሙስና መከላከል ፖሊሲ አፈጻጸም የሚገኝበትን ደረጃ እየገመገመ፣ ቀጣይ የሥራ አቅጣጫ ሊያስቀምጥ የሚችል አገራዊ ፎረም ሊመሠረት መሆኑ ተሰማ፡፡

ሪፖርተር ለፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ቅርብ ከሆኑና ስማቸው እንዳይጠቀስ ከፈለጉ ምንጮች ባገኘው መረጃ መሠረት፣ የአገሪቱ መንግሥታዊ ተቋማት የሙስና ተጋላጭነት ከፍተኛ በመሆኑ፣ የፀረ ሙስና ትግል ግልጽና የሚተገበር ፖሊሲና ስትራቴጂ ከመቅረፅ ባሻገር፣ ለትግበራ ውጤታማነቱ በጠንካራ ድጋፍና ክትትል በማስፈለጉ ፎረሙን መመሥረት የግድ ሆኗል፡፡

በቅርቡ በይፋ ተመሥርቶ ወደ ሥራ እንደሚገባ የተገለጸው ይህ ፎረም፣ የመንግሥት ተቋማትን፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን፣ የሚዲያ ተቋማትን፣ የሃይማኖት ተቋማትን፣ ሕዝባዊ ድርጅቶችን፣ የማኅበራት ተወካዮች፣ እንዲሁም ታዋቂ ግለሰቦችን ያካትታል ተብሏል፡፡ የፀረ ሙስና ትግል ግልጽና የሚተገበር ፖሊሲና ስትራቴጂ ከመቅረፅ ባሻገር፣ የትግበራ ውጤታማነት በጠንካራ ድጋፍና ክትትል መጠናከር እንዳለበት ታምኗል፡፡

 አገራዊ ፎረሙ የራሱ ሰብሳቢና ምክትል ሰብሳቢ ተሹሞለት በየስድስት ወራት እየተገናኘ በሚቀርብ የጥናት መረጃ መሠረት የመንግሥት ተቋማትን፣ የሕዝባዊ ድርጅቶችንና የልማት ድርጅቶችን የሙስና ተጋላጭነት ደረጃን፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ የፀረ ሙስና ፖሊሲና ስትራቴጂ አፈጻጸም ደረጃን እየገመገመ አቅጣጫ በማስቀመጥ መንግሥትን የማማከር ኃላፊነት እንደሚሰጠው ከምንጮች ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በተጨማሪም በመልካም ሥነ ምግባር ግንባታና በሙስና መከላከል ተግባር የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ግለሰቦችና አካላት ዕውቅና መስጠት፣ በፎረሙ የሚቀመጡ አቅጣጫዎች በየተቋማት መተግበራቸውን መከታተል፣ እንዲሁም የአፈጻጸም ሪፖርት እንዲቀርብለት የማድረግና ሒደቱንም ይቆጣጠራል ተብሏል፡፡

የሚቋቋመው አገራዊ ፎረም በመረጃ ላይ የተደገፉ ጥቆማዎች እንዲቀርቡ ከማስቻሉም ባላፈ፣ በፀረ ሙስና ትግል አገር አቀፍ ቅንጅት ለመፍጠር ወሳኝ የሆነ ሚና ይኖረዋል ተብሎ እንደሚታሰብ ተጠቁሟል፡፡

ፎረሙ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትንና የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽንን ጨምሮ ከሰባት ተቋማት የተውጣጡ የሥራ አስፈጻሚ አባላት እንደሚኖሩበት የሥራ ማስኬጃ ወጪው በፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና እንደሚሸፈን ተገልጿል፡፡

የፌዴራል የሥነ ምግባርና  ፀረ  ሙስና  ኮሚሽን  እስከ  2008  ዓ.ም.  ድረስ  ተሰጥተውት  የነበሩ   የሙስና  ወንጀልን  የመመርመርና  ክስ  የመመሥረት  ኃላፊነቶች  ተወስደው ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ከተሰጡ ወዲህ፣ ኮሚሽኑ በአመዛኙ ሥራዎቹን በማስተማር ላይ አድርጓል፡፡ በዚህም የኮሚሽኑ የበላይ ኃላፊዎች ኮሚሽኑ ሙስናን ለመከላከል  በሚያደረገው  ጥረት  እንደ  ዋነኛ  መሣሪያ  የነበሩ፣  በተለይም  የሙስና  ወንጀልን  መመርመርና በተጠርጣሪ ላይ ክስ የመመሥረት ኃላፊነቶች እንዲመለሱላቸው በተደጋጋሚ ሲጠይቁ ይሰማል፡፡

በቅርቡ ተቋቁሞ ሥራ ይጀምራል የተባለው ፎረም፣ በተለይ በመንግሥታዊ ተቋማትና በሕዝብ ሀብት ላይ ተንሰራፍቷል ለሚባለው የሙስና ወንጀል አንድ የመፍትሔ ሐሳብ ያመነጫል ተብሎ እንደሚጠበቅ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...