Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ በአዲስ አበባ መካሄዱ ትልቅ የዲፕሎማቲክ ስኬት እንደሆነ ተገለጸ

የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ በአዲስ አበባ መካሄዱ ትልቅ የዲፕሎማቲክ ስኬት እንደሆነ ተገለጸ

ቀን:

በአዲስ አበባ በሚገኘው የአፍሪካ ኅብረት ዋና ጽሕፈት ቤት በየዓመቱ የሚካሄደው የኅብረቱ የመሪዎች ስብሰባ፣ ላለፉት ሁለት ዓመታት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በበይነ መረብ ሲካሄድ የነበረው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ፣ ከጥር 25 እስከ  29 ቀን 2014 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ በአካል ሊካሄድ መሆነ ትልቅ የዲፕሎማሲ ስኬት ነው ተባለ፡፡

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በርካታ መሪዎች ወደ አዲስ አበባ መምጣት ባለመቻላቸው፣ 33ኛውና 34ኛው ዓመታዊ የኅብረቱ ጉባዔ ጥቂት መሪዎች በአካል በተገኙበት በበይነ መረብ መካሄዱ ይታወሳል፡፡

በተያዘው ዓመት የኮቪድ-19 እና የፀጥታ ሥጋቶችን እንደ ምክንያት በማድረግ ዓመታዊ ጉባዔው በኢትዮጵያ እንዳይካሄድ ወይም እንዲሰረዝ የተወሰኑ አገሮችና አካላት ውትወታ ሲያደርጉ የቆዩ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ከተለያዩ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ ከፖለቲከኞችና ከአጋር አገሮች ጋር በመሆን በተደረገ የማግባባት ሥራ ጉባዔው በአዲስ አበባ መሪዎች በተገኙበት እንዲካሄድ መወሰኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲ (አምባሳደር) በሳምንታዊ መግለጫቸው ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስተር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከቀናት በፊት በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው፣ ‹‹አፍሪካዊ ወንድማማችነታችንን ከመቼውም ጊዜ በላይ ማጠናከር በሚያስፈልገን በዚህ ወሳኝ ወቅት፣ የአፍሪካ ኅብረት አባል አገሮች መሪዎች ተስማምተው የኅብረቱ ጉባዔ በአዲስ አበባ እንዲደረግ በመወሰናቸው በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ምሥጋናዬን አቀርባለሁ፤›› ማለታቸው ይታወሳል፡፡

ይህ በርካታ መሪዎች ይሳተፉበታል ተብሎ የሚጠበቀውን ዓመታዊ የመሪዎች ጉባዔ በአዲስ አበባ ሰላም አንደሌለ በማስመሰል ሲሰብኩ፣ የሐሰት መረጃ ሲያሠራጩና እንዳይካሄድ ሲወተውቱ የነበሩት አካላት፣ ኢትዮጵያ በታሪክ በተቀናቃኝነታቸው የምታውቃቸውና የኅብረቱ መቀመጫ ከአዲስ አበባ እንዲነሳ ላለፉት በርካታ ዓመታት ሲሠሩ የነበሩ እንደሆኑ ቃል አቀባዩ ገልጸዋል፡፡

የኅብረቱን ዓመታዊ ጉባዔን ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ መዛወርን በተመለከተ በኅብረቱ ቻርተር ላይ ምንም የተጠቀሰ ነገር ባይኖርም፣ ከውትወታው በኋላ ጉባዔው በአዲስ አበባ እንዲካሄድ መወሰኑ ለአዲስ አበባ የምፀዓት ቀንን ሲሰብኩ ለነበሩ አካለት ከባድ የመልስ ምት ነው ብለዋል፡፡

‹‹የአፍሪካ አኅጉርን የሥርዓተ ምግብ አቅምና የሰው ሀብት ልማት መገንባት፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ልማትን ማፋጠን››  በሚል መሪ ቃል የሚካሄደው ጉባዔ በአዲስ አበባ  እንዲሆን መወሰኑ፣ ለኢትዮጵያ ከገጽታ ግንባታዋ ባሻገር የተረጋጋች አይደለችም የሚለውን ትርክት ከሥረ መሠረቱ ነቅሎ የሚጥል አንደሆነ ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ጉባዔውን ለማስተናገድ ብሔራዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ፣ ከወትሮው በተለየ በተሻለ ሁኔታ እንዲከበር እየተሠራ እንደሆነ አክለው ገልጸዋል፡፡

ከመሪዎቹ ጉበዔ ቀድሞ የሚካሄደው 43ኛው የአፍሪካ ኅብረት የቋሚ ተወካዮች ኮሚቴ ስብሰባ ጥር 12 ቀን 2014 ዓ.ም. በበይነ መረብ ለሁለት ቀናት የተካሄደ ሲሆን፣ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙሳ ፋቂ ማህማት፣ የኮሚቴው ሰብሳቢና የኅብረቱ አባል አገሮች አምባሳደሮች ተሳትፈውበታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...