Thursday, April 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኋላ ቀር የደን አጠቃቀምን ለማዘመን

ኢትዮጵያ ያላትን የደን ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም እንድትችል መንግሥታዊ ተቋማት ይነስም ይብዛም እየሠሩ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በተለይ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ አማካይነት የደን ሀብትን በመጠቀም ረገድ እምብዛም መሆኑ ይታወሳል፡፡ የተለያዩ ተቋሞች ብቅ ብቅ እያሉ ይገኛል፡፡ ከእነዚህም መካከል ሶዞ ኮንሰልቲንግ ይገኝበታል፡፡ የሶዞ ኮንሰልቲንግ ሥራን በተመለከተ ተመስገን ተጋፋው ከዋና ሥራ አስኪያጇ ወ/ሮ አሜን ሆሉስትረም ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- ሶዞ ኮንሰልቲንግ እንዴት ተመሠረተ?

ወ/ሮ አሜን፡- ሶዞ ኮንሰልቲንግ መቀመጫውን ስዊድን አድርጎ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ የሚገኝ ድርጅት ነው፡፡ ድርጅቱም የዛሬ ሰባት ዓመት ገደማ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ማንኛውንም ዘላቂ የሆኑ ለውጦችን ያመጣሉ የተባሉ ሥራዎች ላይ በመሳተፍ እየሠራ ይገኛል፡፡ በጤናና በደን አጠቃቀም ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ የደን አጠቃቀም ላይ ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ አግባብ ባለው መልኩ ለመሥራት የዕውቀት ሽግግሮችን በመስጠትና ጥሬ ዕቃዎችን በማቅረብ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል፡፡ በኢትዮጵያ እንደዚህ ዓይነት ልማድ እንዲኖር በአሁኑ ወቅት አሥራ ሦስት ሰዎችን አስመርቆ በዘርፉ ላይ እንዲሠሩ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፡፡ ለተመረቁትም አስፈላጊውን ግብዓት በማቅረብ እዚህ ሥራ ላይ እንዲሰማሩ የምናደርግ ይሆናል፡፡ ይኼ ከሆነ በኢትዮጵያ እየታየ ያለው የኋላ ቀር የደን አጠቃቀምን ማዘመን ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ዓይነት አገልግሎቶችን እየሰጣችሁ ነው?

ወ/ሮ አሜን፡- አብዛኛው ሥራችን ለውጥ ተኮር የሆኑ ነገሮች ላይ ነው፡፡ ማኅበረሰቡም የተለያዩ የሥራ ፈጠራ ሐሳቦችን እንዲያመነጭ መንገዶችን እንከፍታለን፡፡ ለዚህም የተለያዩ ሥልጠናዎችን እየሰጠን እንገኛለን፡፡ በኢትዮጵያም የተለያዩ ዕድሎች እንዳሉ ለማየት ችለናል፡፡ እነዚህንም ዕድሎች በመጠቀም በርካታ ወጣቶች ወደ ተለያየ ሥራ እንዲሰማሩና አቅማቸውን አውጥተው እንዲሠሩ መንገድ የምንከፍት ይሆናል፡፡ በተለይም ደግሞ ለሥራው የሚሆን ማቴሪያሎችን በማቅረብ አገልግሎቶችን ተደራሽ በማድረግ የምንጥር ይሆናል፡፡ በተለያዩ አገሮች ላይም ይኼ ልምድ ይታያል፡፡ ገበያ ተኮር የሆኑ የደን አወጋገድ ሥራዎችን በማምጣትና ለተቋሞች የተለያዩ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ዘርፉ ላይ ለመሥራት እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ በዚህ ጊዜም በየዓመቱ 400 ሚሊዮን ዶላር የሚያክል የእንጨት ምርቶችን ኢትዮጵያ በአግባቡ እንድትጠቀምበት ለማድረግ በተቋማችን በኩል የምንሠራ ይሆናል፡፡ ይኼን ማድረግ ከተቻለ በዘርፉ ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡ በተለይም ደግሞ ዘመናዊ የሆነ አሠራር በመዘርጋት አገሪቱ ያላትን ሀብት እንድትጠቀም ዕድል ይከፍታል፡፡

ሪፖርተር፡ከሌሎች ተቋሞች ጋር በጋራ ለመሥራት ምን አስባችኋል?

ወ/ሮ አሜን፡- በእርግጥ ከተለያዩ ተቋሞች ጋር በመሥራት በራችን ክፍት ነው ማለት ይቻላል፡፡ በአሁኑ ወቅት ገበያ ተኮር የሆነ የደን አጠቃቀም ሥርዓት እንዲኖር እየሠራን ይገኛል፡፡ አገሪቱም ያላትን የደን ሀብት ለመጠቀምና ኢንዱስትሪውን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ የምንሠራ ይሆናል፡፡ አሁን ላይ ሥልጠናዎችን በመስጠት ከዘርፉ እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች እያስተማርን ነው፡፡ በተለይም ደግሞ ያለውን የደን አቅርቦት ለማጣጣም ከመንግሥት ጎን ቆመናል፡፡ ያስመረቅናቸውን ኢንተርፕረነር ወደ ሥራው ለመግባት ዝግጅት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ በተለይ በአገሪቱ በአብዛኛው ሥራዎች በቴክኖሎጂ የታገዙ አይደሉም፡፡ ተቋማችንም እንደ አንድ ሥራ ብሎ የያዘው ነገር በገጠር አካባቢ የሚገኙ አርሶ አደሮች የደን ውጤት አገልግሎቱ ምን እንደሆነ አያውቁትም፡፡ ይህንን እንዲያውቁትና ኢትዮጵያ ላይ ያሉ ሀብቶች ለመጠቀም እንዲቻል ተቋማችን እየሠራ ይገኛል፡፡ ይህ ከሆነ የተሻለ ለውጥን ማምጣት ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ የሚታየው የደን ሀብት አያያዝ ችግርን ለመቅረፍ ምን እየሠራችሁ ነው?

ወ/ሮ አሜን፡- ከደን ሀብት ጋር ተያይዞ ሰፊ ችግሮች እንዳሉ ተቋማችን ባደረገው ጥናት ለመለየት ችለናል፡፡ ነገር ግን እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ በዘርፉ ከሚሳተፉ ባለሙያዎችና ተቋሞች ጋር በቅንጅት እየሠራን ነው፡፡ መንግሥትም ያለውን ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም መሥራት ይኖርበታል፡፡ ዋና መቀመጫችን ስዊድን ቢሆንም፣ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር እንሠራለን፡፡ የደን ጥቅምን በማወቅ ጤነኛ ሥራን መሥራት ይገባል፡፡ በተለያዩ ቦታዎች የደንን ጥቅም በማወቅና ያለውን ነገር በመለየት አርሶ አደሮች በከፍተኛ ሁኔታ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ በኋላም መንግሥት የተለያዩ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ዘርፉ ላይ መሥራት ይኖርበታል፡፡ ከዚህ በፊት አብዛኛውን ጊዜ የተተከሉ ደኖች ያለምን ምክንያትና ጥቅማቸው ሳይታወቅ እንደነበር ባደረግነው ጥናት ለመመልከት ችለናል፡፡ አብዛኛውን የሚተከሉ ደኖች እንክብካቤ ሳይደረግላቸው ሲወድቁና አገልግሎት ላይ ሳይውሉ ለማየት ችለናል፡፡ ከዚህ በኋላ ግን የሚተከሉ ተክሎች ጥቅማቸውን በማወቅ መንከባከብ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሲሆን የደን ሀብት አያያዛችን የተቀላጠፈና ዘመናዊ የሆነ አሠራር የጎላበት መሆን ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- ግንዛቤ ከመፍጠር አኳያ ምን ሠርታችኋል?

ወ/ሮ አሜን፡- የእኛ ተቋም ትኩረት አድርጎ የሚሠራው የደን ሀብት አያያዝና ጤና ላይ ነው፡፡ የደን አያያዝ ላይም ሆነ ጤና ላይ የሚሠሩ ሥራዎች ዘመናዊነትን የተላበሱ ለማድረግ የተለያዩ ግንዛቤዎችን ፈጥረናል፡፡ አሁንም እየፈጠርን ነው፡፡ በደን ሀብት አያያዝ ላይ መንግሥት ትኩረት እንዲሰጥበትና አርሶ አደሮችም ያላቸውን አቅም ተጠቅመው መጠነ ሰፊ ሥራ እንዲሠሩ በተለያዩ ነገሮች የምናግዝ ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታትስ ምን አስባችኋል?

ወ/ሮ አሜን፡- በእርግጥ የተለያዩ ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም ጋር ተያይዘው ብዙ ችግሮች ይነሳል፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት በቀጣይ ፕሮግራማችን አንድ የቴክኖሎጂ ማዕከል ለማቋቋም ዕቅድ ይዘናል፡፡ የደን ሴክተሩን የሚደግፉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በማምጣትና በማስተማር በዘርፉ ላይ የሚታየውን ችግር በተወሰነ መልኩ የምንቀርፍ ይሆናል፡፡ ከዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጋር ተያይዞ የሠራናቸው ሥራዎች ነበሩ፡፡ ይህም ሥራ የብዙ አርሶ አደሮችን አቅም ማጎልበት ተችሏል፡፡ አሁንም ይህንኑ ለማጠናከር የቴክኖሎጂ ማዕከሉን ለማቋቋም ቅድመ ዝግጅቱን አጠናቀናል፡፡

ሪፖርተር፡- በቀጣይ ምን ለመሥራት አስባችኋል?

ወ/ሮ አሜን፡- እንደ ሶዞ በቀጣይ ብዙ ነገሮች ለመሥራት ዕቅድ ይዘናል፡፡ በማንኛውም ቋሚ ለውጥ በሚያመጡ ፕሮጀክቶች ላይ ለመሥራት በተጠንቀቅ ቆመናል፡፡ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችም ዘመናዊ አሠራርን እንዲከተሉ የምንሠራ ይሆናል፡፡ በዚህ ነገር  ላይም በደንብ ከተሠራ የደን ሀብት አያያዝ ያድጋል፡፡ የነበሩ ችግሮችም ወዲያውኑ ይቀየራሉ ብለን እናምናለን፡፡ መንግሥትም የነበሩትን ችግሮች በመቅረፍ ወዲያውኑ ለውጥ ማምጣት ይኖርበታል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹በአሁኑ ወቅት ከ21 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ሰብዓዊ ዕርዳታ ይፈልጋል›› አቶ አበራ ሉሌሳ፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ምክትል ጸሐፊ

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ላለፉት 89 ዓመታት በመላ አገሪቱ የሰብዓዊነት አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ በድርቅ፣ በበሽታና በግጭት ምክንያት ለተጎዱ ወገኖች የምግብ፣ የመጠለያ፣ የመድኃኒትና የ24 ሰዓት...

ከቢሻን ጋሪ እስከ ዶባ ቢሻን እንክብል

ዶባ ኢንዱስትሪያል ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር መጋቢት 24 ቀን 2016 ዓ.ም. ከሦስት ዓመታት በላይ ጥናትና ምርምር ያደረገበትንና ለገበያ ያበቃውን ዶባ-ቢሻን እንክብል የውኃ ማከሚያ...

ለሴቶች ድምፅ ለመሆን የተዘጋጀው ንቅናቄ

ፓሽኔት ፎር ኤቨር ኢትዮጵያ ከተመሠረተበት እ.ኤ.አ. ከ2011 ጀምሮ በፆታ እኩልነት፣ በእናቶችና ሕፃናት ጤና እንዲሁም የሴቶችን ማኅበራዊ ችግር በማቃለል ዙሪያ በተለያዩ ክልሎች ሲሠራ ቆይቷል፡፡ በአሁኑ...