Saturday, April 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አሊባባና የአቶ ኤርሚያስ አመልጋ ኩባንያ ኤሌክትሮኒክስ ግብይት በቅርቡ ሥራ ሊጀምር መሆኑ ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያን የበይነ መረብ ግብይት ከሥሩ ይቀይራል ተብሎ የሚጠበቀው፣ የአሊባባና የአቶ ኤርሚያስ አመልጋ አዲስ ኩባንያ የኤሌክትሮኒክስ ግብይት (ኢ-ኮሜርስ)፣ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ውስጥ ወደ ትግበራ ሊገባ መሆኑ ታወቀ፡፡

በታዋቂው የቻይና ኩባንያ አሊባባ ባለቤት ሚስተር ጃክማና በኢትዮጵያዊው የቢዝነስ ሐሳብ አመንጪ አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ትብብር እየተቋቋመ ያለው አዲሱ የኢ-ኮሜርስ ቴክኖሎጂ፣ ከሁለቱ የተውጣጣ ጥምር ስም እንደሚሰጠውም ታውቋል፡፡

ድርጅቱ በበይነ መረብ ቴክኖሎጂው ላይ ሁሉንም በኢትዮጵያ የሚገኙ የግብይት ምርቶች መገኛ ዋጋ የሚያሳውቅ መሆኑንና የበይነ መረብ ግዥ ትዕዛዝ፣ የዲጂታል ክፍያና የአቅርቦት አገልግሎትን ያስችላል ተብሏል፡፡ አዲሱ ድርጅት የአቅርቦት (Delivery) አገልግሎቱን ለ‹‹እሺ›› ኤክስፕረስ ለመስጠት ስምምነት ላይ መድረሱን ሪፖርተር አረጋግጧል፡፡

‹‹ወደ ትግበራ ለመግባት ቀጣይ ስድስት ወራት ያስፈልጉናል፣ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያትም የዘገዩብን ሥራዎች አሉ፤›› ሲሉ አቶ ኤርሚያስ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርም በኢትዮጵያ ያሉ ቻይናውያን ያገለግላል የተባለ አገልግሎት ሊጀምር መሆኑ ታውቋል፡፡ በኮቪድ-19 እና ብሔራዊ ባንክ የወረቀት ገንዘብ ዝውውርን ለመቀነስ በወሰዳቸው ዕርምጃዎች ምክንያት፣ የበይነ መረብ ግብይት ፍላጎት እያደገ መምጣቱና መንግሥት የቴሌኮም ዘርፉን ለውድድር መክፈቱ አጠቃላይ የዲጂታል ሽግግር ለውጡን እያፋጠነው መሆኑ ተነግሯል፡፡

በአሁኑ ጊዜም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሕግ ክፍተቶችን ይሞላል ተብሎ የሚጠበቀውን የኤሌክትሮኒክ ግብይት ደንብ አጠናቋል፡፡ ‹‹ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አርሞ ጨርሶ ለጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ሰጥቷል፡፡ የደንቡ መውጣት ዲጂታል ግብይትን ሙሉ ያደርጋል፤›› ሲሉ ማንደፍሮ እሸቴ (ዶ/ር) በሚኒስቴሩ የሕግ ጉዳዮች አማካሪ አስረድተዋል፡፡

በተመሳሳይ የገቢዎች ሚኒስቴርም የኤሌክትሮኒክ ደረሰኝ ለማተም የሚያስችል ቴክኖሎጂ እያስገባ መሆኑ ታውቋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ያሉ የኢ-ኮሜርስ ድርጅቶች ቁጥር ወደ ሰላሳ የሚጠጋ ሲሆን፣ አብዛኞቹ ባለፉት ሦስት ዓመታት የተፈጠሩ ናቸው፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች