Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናመንግሥት ክስ ስላቋረጠበት ምክንያት ግልጽ ማብራሪያ እንዲሰጥ ተጠየቀ

መንግሥት ክስ ስላቋረጠበት ምክንያት ግልጽ ማብራሪያ እንዲሰጥ ተጠየቀ

ቀን:

 ከድምፃዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር በተያያዘ ከተፈጠረው ሁከትና ግድያ፣ እንዲሁም በሰሜን ኢትዮጵያ በተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት በቁጥጥር ሥር ውለው ክስ ተመሥርቶባቸው፣ በሕግ ጥላሰ ሥር የነበሩ ግለሰቦች ከሰሞኑ በመንግሥት ክሳቸው ተቋርጦ በመፈታታቸው፣ አገር ቤት የገቡ የዳያስፖራ አባላት ውሳኔው እንዳስቆጣቸው ገልጸው  መንግሥት ግልጽ ማብራሪያ እንዲሰጥበት ጠየቁ፡፡

 የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መንግሥት ጥሪ አድርጎላቸው ወደ አገር ቤት ከገቡ የዳያስፖራ አባላት ጋር ‹‹የዳያስፖራው ሚና ለፓን አፍሪካን ንቅናቄ›› በሚል ርዕስ ጥር 3 ቀን 2014 ዓ.ም. ሲምፖዚየም በአዲስ አበባ አካሂዷል፡፡

በሲምፖዚየሙ ተሳታፊ የነበሩ ከአሜሪካና ከአውሮፓ የመጡ የዳያስፖራ አባላት፣ ጉዳያቸው በሕግ እየታየ የነበረ ነገር ግን ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር እንዲፈቱ በመንግሥት የተላለፈውን ውሳኔ በተመለከተ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

አቶ ኤርሚያስ መኮንን የተባሉና ከአሜሪካ አገር የመጡ ትውልደ ኢትዮጵያዊ፣ ‹‹ሰዎቹ ተፈቱ ሲባል በሕልሜ ነው ወይስ በእውነት ነው እስከምል ድረስ በጣም ደንግጬ ነበር፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ነገር ግን እየቆየሁ ራሴን ካረጋጋሁ በኋላ ሳስበው፣ መንግሥት ጉዳዩን በአንድ ቀን ምሽት የሚወስነው ነገር አይደለም፣ በደንብ አጢኖበት መሆን አለበት በሚል ራሴን እዚያ ውስጥ ከትቼ ለማየት እየሞከርኩ ነው፤›› ሲሉ ስሜታቸውን ገልጸዋል፡፡

በተለይ ፖለቲከኞች ሁልጊዜም ሁለትና ሦስት ርቀት ከሕዝቡ ቀድመው መሄድ አለባቸው ያሉት አቶ ኤርሚያስ፣ ምንም እንኳ ፖለቲከኞች የሚወስኗቸውን ሁሉንም ውሳኔዎች ሕዝብ ይወቅ ባይባልም፣ መነገር ያለባቸው ነገሮች ለሕዝብ በግልጽ መነገር እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ ኤርሚያስ ገለጻ፣ በመንግሥት ግብዣ ወደ አገር የገቡ የዲያስፖራ አባላት፣ የመንግሥትን የክስ ማቋረጥ ውሳኔ ሲሰሙ በርካታዎቹ ደንግጠዋል፣ ተከፍተዋል፡፡ በዚህም ብዙዎቹ አኩርፈው ተመልሰው መሄዳቸውን ጠቁመዋል፡፡

በመሆኑም መንግሥት እንዲህ ዓይነት ቅሬታዎችን ለመፍታት ከሁሉም አካላት ጋር፣ በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አድርገውላቸው ከመጡ ዳያስፖራ አባላት ጋር ግልጽ ውይይት በማድረግ መተማመን መፍጠር ይገባዋል ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ ወ/ሮ ፍሬወይኒ ዘሚካኤል የተባሉና ከቦስተን የመጡ የዳያስፖራ አባል፣ መንግሥት ባደረገው ጥሪ መሠረት ኢትዮጵያን ለመርዳት በርካታ ዓይነት ድጋፎችን ይዘው እንደመጡ ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ መንግሥት ከሰሞኑ ያሳለፈው ውሳኔ በተለይም በአማራና በአፋር ክልሎች ለተከሰተው ጦርነት እንዲሁም፣ በኦሮሚያ ክልል ለደረሰው ሞትና መፈናቀል ምክንያት የነበሩ ሰዎች መፈታት በርካታ ሰዎችን እንዳስደነገጠ አስረድተዋል፡፡

ለአብነትም ከሰሞኑ በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን ለመጎብኘት አቅደው የነበሩ የዳያስፖራ አባላት የክስ ውሳኔውን ሲሰሙ፣ ለመጎብኘት ካቀዱት ቢያንስ ግማሹ አኩርፈው ከጉብኝቱ መቅረታቸውን ገልጸዋል፡፡

የኮሎራዶ ግዛት ‹‹የበቃ ንቅናቄ›› (No More) ተወካይ ወ/ሮ ሒሩት በቀለ፣ የመንግሥትን የክስ ማቋረጥ ውሳኔ ‹‹በጣም ያማል›› ሲሉ ገልጸውታል፡፡ ‹‹ጓደኞቼ ውሳኔውን እንደሰሙ ወደ መጡበት አገር ትኬት ቀይረው ተመልሰዋል፣ እኛ ግን ወገባችንን አስረን ቆይተናል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹በአማራና በአፋር ክልሎች ግፍ የፈጸሙ ወንጀለኞች፣ የ85 ዓመት መነኩሴ ያስደፈሩና በርካታ ለመናገር የሚያም ግፍ እንዲፈጸም ያደረጉ አመራሮች መፈታት፣ ትግሉንም፣ የእኛንም መምጣት ሆነ የበቃ ንቅናቄን ዜሮ የሚያደርግ ነው፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡

‹‹ሁልጊዜም ቢሆን ዳያስፖራዎች ከአገራችን ጎን መቆም እንፈልጋለን፤›› ያሉት ወ/ሮ ሒሩት፣ ‹‹መንግሥት ወደ አገራችሁ ኑ ብሎ በጠራን መሠረት የሚፈለግብንን ለመወጣትና ለማበርከት መጥተናል፡፡ ነገር ግን ስህተቶች ሲፈጠሩ መታረም እንደሚገባቸውና መንግሥት ከአሜሪካ ተወካዮችም ሆነ ከሌሎች አካላት ጋር የሚያደርገው ስምምነት ገልጽ መሆን አለበት፤›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

አክለውም ዳያስፖራው አገር ጠራችኝ ብሎ ሥራውን፣ ቤቱንና ልጁን ጥሎ ወደ አገር ሲገባና መንግሥት የጉዳይ ባለቤት አድርጎት ሊወያይና ሊደመጥ ሲገባው፣ በእንዲህ ዓይነት ድንገተኛ ውሳኔ ዳያስፖራው ተበሳጭቶ ሲሄድ ለአገር ኪሳራ ነው ብለዋል፡፡

አሸባሪ ተብሎ የተሰየመውን ሕወሓት ማባበልም ሆነ አብሮ መሥራት እደማይቻል የገለጹት ወ/ሮ ሒሩት፣ ‹‹አሁንም ድጋሚ ስህተት እንዳይሠራ ከሕዝብና በአገር ጥያቄ ላይ መንግሥት ሁላችንም እንደ ዜጋ ሊያወያየን ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

በእንግሊዝ የዲፌንድ ኢትዮጵያ ግብረ ኃይል ተወካይ የሆኑት አቶ ዘለዓለም ጌታሁን፣ ‹‹ምንም እንኳ መንግሥት የሚወስናቸውን ውሳኔዎች ለሕዝብ ግልጽ ያለማድረግ ችግር ቢኖርም፣ ሕዝብ ደግሞ እንደ ሕዝብ የተመረጠ መንግሥት የሚወስናቸውን የተለያዩ የፖለቲካ ውሰኔዎች የመቀበል ኃላፊነት አለብን፤›› ብለዋል፡፡

በዳያስፖራው ዘንድ ግራ መጋባትና የመናደድ ዓይነት ስሜቶች መንፀባረቃቸውን የገለጹት ተወካዩ፣ መንግሥት ማለት ለአገር የሚጠቅም ውሳኔ የሚያስተላልፍ አካል በመሆኑ፣ የመንግሥትን ውሳኔ መቀበል ካልተቻለና ሁሉም ውሳኔ የሚሰጥ ከሆነ ግራ የተጋባ አገር ነው ሊፈጠር የሚችለው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...