Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናብሔራዊ መግባባት ላይ ለመድረስ በታሪክ ውስጥ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት እንዲቆም ተጠየቀ

ብሔራዊ መግባባት ላይ ለመድረስ በታሪክ ውስጥ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት እንዲቆም ተጠየቀ

ቀን:

በኢትዮጵያ ብሔራዊ መግባባት ለማምጣትና  የጋራ ትርክት ለመፍጠር እየተሄደበት ያለውን ዕርቀት ውጤታማ ለማድረግ፣ ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት የፀዳ  ውይይት እንደሚስፈልግ የታሪክ ምሁራን ጠየቁ፡፡

በኢትዮጵያ ባለፉት ዘመናት በነበሩ የመንግሥት ሥርዓቶች ውስጥ ፖለቲካና ታሪክ ተጠላልፈው አንድ ላይ እንዲቆሙ በመደረጋቸውና ከመንግሥት ጫና ነፃ ባለመሆናቸው፣ አገሪቱ የጋራ ትርክት መፍጠር እንደተሳናት የታሪክ ተመራማሪዎች ገልጸዋል፡፡

የሰላም ሚኒስትር ከአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ‹‹የታሪክ አበርክቶ ለብሔራዊ መግባባትና የታሪክ ሚና›› በሚል ርዕስ፣ በርካታ የታሪክ ተማራማሪዎችን ያሳተፈ ውይይት ታኅሳስ 27 ቀን 2014 ዓ.ም. ተካሂዷል፡፡

በውይይቱ የመነሻ ጹሑፍ ያቀረቡት ባህሩ ዘውዴ (ኤመሬተስ ፕሮፌሰር) በታሪክ ውስጥ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ባለፉት ሥርዓቶች በሙሉ የተለመደ እንደነበርና የሚያግባባ የጋራ ትርክት መፍጠር አቅቶ ታሪክን ከፖለቲካ ተገዥነት ማላቀቅ እንዳልተቻለ ተናግረዋል፡፡

በዚህም የፖለቲካ ድርጅቶች ለራሳቸው በሚያመች መንገድ ጠምዝዘው የፖለቲካ መሣሪያ አድርገው እንደተጠቀሙበት፣ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ከእንዲህ ዓይነት ጫና መውጣት ካልተቻለና ታሪክ ከፖለቲካ ጋር እስከተያያዘ ድረስ፣ አሁንም እያበጣበጠ ወደፊትም በዚሁ ሁኔታ መቀጠሉ እንደማይቀር ተናግረዋል፡፡

‹‹ታሪክ ብዙ ነገር አስተማሪ ሆኖ ትምህርት ቤት መሆን ሲገባው እስር ቤት መሆን የለበትም፣ በመሆኑም ባለፈና በተሠራ ታሪከ  መነቋቆር የለብንም፤›› ብለዋል፡፡

ለዚህም ያመች ዘንድ የታሪክ ምሁራን በጥሩ የታሪክ አጻጻፍ መመዘኛዎች የተመዘኑ፣ በመረጃ የተጠናከሩና የተመሳከሩ እንዲሁም ሚዛናዊነትን በጠበቀ መንገድ ታሪክን ሊያቀርቡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡  

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በታሪክ አጻጻፍ ረገድ የደረጃ ማሽቆልቆል አለ ብለው፣ በተለይም ከአገሪቱ ትምህርት ሥርዓት ጋር በተገናኘ ብዙ ሰዎች ምንም እንኳ ዕውቀቱ ቢኖራቸውም የቋንቋ ችግር መኖር፣ ነፃ አውጪ ነን የሚሉ የፖለቲካ ድርጅቶች አንድ ጫፍ ብቻ ያለው ትርክት ይዘው የኢትዮጵያን ታሪክ በተጨባጭ ማረጋጋጥ በማይቻል ትርክት ለመፍጠር የሄዱበት ርቀት፣ ለታሪክ መዛባት አስተዋጽኦ እንዳደረገ አስረድተዋል፡፡

በሌላ በኩል በትውስታና በታሪክ መካካል ያለውን ልዩነት አለመረዳት፣ ታሪክን በተሳሳተ መንገድ መናገር እንደ ችግር ሊጠቀሱ እንደሚችሉ ባህሩ (ፕሮፌሰር) ተናግረዋል፡፡

ወደፊት ለሚደረጉ የብሔራዊ መግባባት ውይይቶች ሚዛናዊና ንቁ አንባቢ ዜጎችን መፍጠርና ሀቅና ዕርቅን የያዙ ታሪኮችን ማቅረብ እንደሚገባ፣ በታሪክ የተደረጉ ሁነቶች ክፉም ሆኑ መልካም መሆናቸውን፣ አብሮ ለመኖር ከተፈለገ ግን በመጥፎ ታሪክ  ላይ መቆዘምና ማላዘን የትም ሊያደርስ አይችልም ብለዋል፡፡

ምንም እንኳ በታሪክ የተለያየ አመለካከት የሚኖር ቢሆንም እየታየ ባለው ሁኔታ  ግን፣ መሠረታዊ ስምምነት በሚያስፈልገው ታሪክ እንኳ ለመግባባት እንዳልተቻለ ተናግረዋል፡፡ ለአብትም በአፍሪካ አገሮች ዘንድ አንደ ትልቅ ጉዳይ የሚታየውን የዓድዋ ድል፣ በኢትዮጵያውያን ዘንድ አልፎ አልፎ የሚተረጎምበት ሁኔታ ትክክል አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለምሳሌ ያህል ዓድዋን በትግራይ አካባቢ የትግራይ ድል በተለይም የራስ አሉላና የራስ መንገሻ ድል አድርጎ የማግዘፍና የመቀበል፣ በቅርቡ ደግሞ በኦሮሞ ብሔርተኞች በኩል የሚወጡ ጽሑፎች ለዓድዋ ያን ያህል ግምት አለመስጠት እንደሚስተዋል ጠቅሰዋል፡፡

‹‹በዓድዋ ካልተስማማህ በምን ልትስማማ ነው? ዓለም ሁሉ ከመስማማት አልፎ የሚያመልከውና የሚያከብረውን ዓድዋ፤›› ሲሉ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡

አቶ አበባው አያሌው (ረዳት ፕሮፌሰፈር) በበኩላቸው፣ ስለብሔራዊ መግባባት ሲነሳ ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ ሰዎች በማንነታቸው ስለመንገላታታቸው፣ የታቀደበት የማፈናቀል ሥራ በመቀጠሉና ይህም አልበቃ ብሎ ደግሞ ባለፉት አምስት ዓመታት ሁኔታው እየበረታ መሄዱን አስታውሰዋል፡፡

የብሔራዊ መግባባት ጉዳይ ሲነሳ ፍፁማዊ ስምምነት ሊኖር እንደማይችል፣ አወዛጋቢው ጉዳይ ላይ እየተነጋገሩ በሚያስማማው ላይ ደግሞ ተስማማቶ መኖር የተሻለ አማራጭ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለብሔራዊ መግባባት ታሪክ ሁነኛው መሣሪያ ሆኖ መነሳት እንዳለበት የጠቆሙት አቶ አበባው፣ የፖለቲካው ዋና መነሻ ከትናንት ሳይሆን ዛሬ ላይ ተመሥርቶ ግቡን ነገ ማድረግና ነገን የተሻለ ማድረግ ላይ ማተኮር እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

‹‹ይሁን እንጂ እንዳለመታደል ሆኖ የእኛ ፖለቲከኞች አካሄድ ስለነገ ግብና ዛሬ ስላለው ተጨባጭ ነባራዊ ሁኔታ ሳይሆን፣ የዛሬ 300 ዓመት እንደዚህ ስላደረግከኝ በሚል የንትርክ ጉዞ ላይ ይገኛሉ፤›› ብለዋል፡፡

የፖለቲካው መነሻ ከመሠረቱ ትክክል ያልሆነ ታሪክን ወደኋላ ሄዶ በመቀስቀስ የተነሳ በመሆኑ፣ የጋራ ትርክት ለመፍጠር ታሪክ አንድ የብሔራዊ መግባቢያ ውይይት መነሻ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

የታሪክ ክፍፍል፣ የታሪክ ሽሚያ፣ የጀግና ሽሚያ፣ ሀቅን ማዛባት፣ የተጻፈውን ሁሉ ታሪክ ነው ብሎ መውሰድ፣ አንቂዎች ነን የሚሉ እንኳን ሊያነቁ ራሳቸው እንኳ የማያነቡ በመሆናቸው በታሪክ አለመግባባት እንዲፈጠር አስተዋጽኦ ስለማበርከታቸው አክለው ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ፖለቲካ የፈጠራቸው የተጋነኑና የተፈበረኩ ታሪኮች መበራከት፣ አንዳንዴም ባልተከናወነ የውሸት ታሪክ ግጭት በመፍጠር ሕዝብን ማራራቅና በሊቃውንት መካከል ክፍፍል መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ መልካም አስተዳደርና ከዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ በበለጠ አለመግባባት የተፈጠረው በሕገ መንግሥቱ፣ አገሪቱ የምትወከልበት ምልክት ባለመኖሩና በታሪክ መዛባት በመሆኑ፣ ለዚህም ውይይት ማካሄድ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያን በሚወክሉ ኤምባሲዎችና የቆንጽላ  ጽሕፈት ቤቶች፣ ኢትዮጵያ ማነች ቢባል ሊቀርብ የሚችል ብሔራዊ ትርክት መፍጠር እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡

የሰላም ሚኒስትር ደኤታ  አቶ ታዬ ደንደአ፣ ስለታሪክ ሲነሳ ትናንት የተሠሩት ሁሉም ታሪኮች መልካም ወይም ሁሉም መጥፎ ሊሆኑ እንደማይችሉ በመጥቀስ፣ የሚጻፉ ታሪኮች መማርያና ወደ ተሻለ አቅጣጫ ሊወስዱ እንደሚገባ ተናገረዋል፡፡

ሌሎች አገሮች ታሪክን እንደሚማሩበትና ዛሬያቸውን እንደሚተነትኑበት፣ እንዲሁም ነጋቸውን የተሻለ ለማድረግ እንደሚጠቀሙበት የገለጹት አቶ ታዬ፣ በርካታ የአውሮፓ አገሮች ለረዥም ዓመታት በጦርነት ያለፉበትን ታሪካቸውን መማርያ አድርገው ድሮ ጠላት የነበሩት አሁን ወዳጅ ስለመሆናው ጠቅሰዋል፡፡

አቶ ታዬ አክለውም፣ ‹‹ኢትዮጵያ ሌሎችን የሚያስቀና በርካታ ታሪክ ያላት ሆና እያለ ለታሪክ የተለያየ አተረጓጎም በመስጠት ወደፊት መሄድ ሲገባን፣ ወደኋላ እየጎተተን እርስ በእርሳችን የምንነታረክበት አጋጣሚ በርካታ ነው፤›› ብለዋል፡፡

አገሪቱ በሁሉም አካባቢ ያለባት ችግር ተመሳሳይ ቢሆንም የግጭት መነሻው ግን ታሪክ የሚተረጎምበት፣ የሚታይበትና የሚተረክበት ሁኔታ እንጂ ተጨባጭ የሆነ አሁናዊ ምክንያት እንዳልሆነም አስረድተዋል፡፡

‹‹ስለሆነም በታሪክ ላይ ያለን ግንዛቤና አስተሳሰብ በማስተካከል ምሁራኑ ታሪካችን መማርያና የዕድገት ምንጭ እንዲሆን ሊሠሩ ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹በኢትዮጵያ ዓለምን ያስደነቁ ቅርሶች አሉን፣ አክሱም ያለ ኢንጂነሪንግ ዕውቀት የተሠራ አይደለም፣ ያን ዕውቀት መዝግበን ይዘን ቢሆን ኖሮ ዛሬ የት በደረስን ነበር፤›› ያሉት አቶ ታዬ፣ ‹‹ላሊበላንና ጎንደርን የሠራው አዕምሮና የተሠራበት የሒሳብ ሥሌት በታሪክ ውስጥ በደንብ ቢመዘገብ፣ ታሪክን ስናስብ ዛሬ ትልቅ ጉልበት ሊሆነን ይገባ ነበር፤›› ብለዋል፡፡

በመሆኑም በታሪክ አተረጓጎም ምክንያት ይኼ የእኔ ነው፣ ያ የእገሌ ነው፣ እኔ የለሁበትም በሚል ባልተገባ ፉክክር በጣም ብዙ ሀብቶች በከንቱ ስለመቅረታቸውና ለአብነትም፣ ‹‹በእጅ የያዙት ወርቅ እንደሚባለው ዓድዋን ስንመለከት እኛ የምናይበትና ሌሎች የአፍሪካ አገሮች የሚመለከቱበት ሚዛን እኩል አይደለም፣ ስለአበበ ቢቂላ በጃፓን በሚተረክለት ልክ፣ አቡነ ጴጥሮስ ስለፈጸሙት ገድል እኛ በሚገባው ልክ ለትውልዱ አላስተማርንም፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...