Monday, April 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የጨርቃ ጨርቅና የቆዳ ኢንዱስትሪዎች የውጭ ምንዛሪ ቅድሚያ እንዲያገኙ ይደረጋል ተባለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ በጨርቃ ጨርቅና ቆዳ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶች ያሉባቸው ችግሮች እንዲቃለሉ በቅድሚያ እንዲያገኙ እንደሚደረግ ተገለጸ፡፡

ይህ የተገለጸው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ታኅሳስ 3 ቀን 2014 ዓ.ም. በሞጆና በአዳማ ከተማ የሚገኙ የጨርቃ ጨርቅና የቆዳ ፋብሪካዎችን የሥራ እንቅስቃሴ በተጎበኘበት ወቅት ነው፡፡ ፍሬንዲሺፕ ቆዳ ፋብሪካ፣ ኮልባ ቆዳ ፋብሪካ፣ ኢቱር ቴክስታይል፣ ሰንሻይንና ኪንግደም ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች የተጎበኙ ፋብሪካዎች ናቸው፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል እንደ ገለጹት፣ ኢንዱስትሪዎቹ ጥሬ ዕቃ ተጠቅመው የሚያመርቱ ስለሆኑ ድጋፍ ካገኙ ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ምርት በማቅረብ የውጭ ምንዛሪና ሰፊ የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ፡፡

በኢንዱስትሪዎቹ ውስጥ የሚታዩና የመንግሥትን ድጋፍ የሚፈልጉ ጉዳዮች እንዳሉ በጉብኝቱ ወቅት መረዳታቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ከእነዚህ ውስጥ አንደኛው የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ችግር ነው፡፡ ኢንዱስትሪዎቹ ለመለዋወጫና ለጥሬ ዕቃ የሚሆን የውጭ ምንዛሪ እንደሚፈልጉ ሚኒስትሩ አስታውቀው፣ በፍላጎታቸውም መሠረት የቅድሚያ ቅድሚያ እንዲሰጣቸው እንደጠየቁ አስረድተዋል፡፡

በሌላ በኩል ከጥሬ ዕቃ አቅርቦትና ከኮቪድ ወረርሽኝ ጋር በተገናኘ ቀደም ሲል የነበሯቸው የገበያ መዳረሻዎች ላይ መድረስ እንዳልቻሉ፣ በዚህም ምክንያት ገቢያቸው በመቀነሱ ተለዋጭ የገበያ መዳረሻ እንደሚፈልጉ ድርጅቶቹ ካቀረቧቸው ጥያቄዎች መካከል ይገኝበታል፡፡ ጥያቄዎቹ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትን በማስተባበር የሚፈታ እንደሆነ የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ በአጠቃላይ ጉብኝቱ ምን ዕድልና  ምን ችግር አለ የሚለውን የተለየበት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የተነሱትን ችግሮች ለኢንዱስትሪዎቹ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ኢንዱስትሪዎችን ታሳቢ በማድረግ፣ የቅድሚያ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው እንዲፈቱ የማድረግ ሥራ አንደኛው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ተግባር እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡  ኢንዱስትሪዎቹ ሥራቸው በውጭ ምንዛሪ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ፣ ከውጭ ምንዛሪ ጋር በተገናኘ ያለውን ችግር አሁን ከሚያሳዩት አፈጻጸም ጋር ተያይዞ፣ ከብሔራዊ ባንክ ጋር በመነጋገር የሚፈታ እንደሆነ አቶ መላኩ ተናግረዋል፡፡

ከተጎበኙት ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ውስጥ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ተበድሮ ብድሩን በአግባቡ መክፈል ሳይችል በመቅረቱ፣ ባንኩ በራሱ ማስተዳደር የጀመረውና በቱርካውያን ባለቤትነት የተመሠረተው ኢቱር ቴክስታይል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ይጠቀሳል፡፡

አቶ መላኩ እንዳስታወቁት፣ በውጭ ባለሀብቶች ተይዘው የነበሩ አንዳንድ ኢንዱስትሪዎች ከብድር አመላለስ ችግር ጋር በተያያዘ በዚህ ወቅት የልማት ባንክ እያስተዳደራቸው ነው፡፡ ከእነዚህ ድርጅቶች ውስጥ ኢቱር አንደኛው ነው ያሉት አቶ መላኩ፣ ፋብሪካው የተራረፉ የጨርቃ ጨርቅ ግብዓቶችን በጥሬ ዕቃነት የሚጠቀምና ይህንንም ወደ ክርና ልብስ የሚቀይር መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ድርጅቱ በአገሪቱ አዲስና ልዩ ተብሎ የሚወሰድ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፣ ምናልባትም በአራትና በአምስት ዓመታት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ወጪውን መሸፈን የሚችል አዋጭ እንደሚሆን፣ ነገር ግን ባለሀብቶቹ የሚጠበቁባቸውን ግዴታዎች ስላልተወጡ የልማት ባንክ ተረክቦታል ብለዋል፡፡

ባንኩ ድርጅቱን ከተረከበው በኋላ ከማምረት አቅሙ በግማሽ ያህል እያመረተ መሆኑን፣ ይህም ባንኩ እስከ መጨረሻው ድረስ ፋብሪካውን ይዞ ለመቀጠል ባለው ፍላጎት መሠረት አይደለም ያሉት ሚኒስትሩ፣ ነገር ግን የፋብሪካው ሠራተኞች እንዳይበተኑ እየተመረተ ያለው ምርት ለአገርም የሚያስፈልግ እንደሆነ ታምኖበት ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

‹‹በዚህ ወቅት ፋብሪካው በ50 በመቶ አቅም የሚያመርትበትን እንቅስቃሴ ወደ 75 በመቶ ከፍ እንዲያደርግ በዚህ ወቅት ከሚያስተዳድረው ማኔጅመንት ጋር ተግባብተናል፤›› ያሉት አቶ መላኩ፣ ፋብሪካውም ኤክስፖርቱን እንዲያሳድግና አዳዲስ የገበያ መዳረሻዎችን እንዲፈልግ ይደረጋል ብለዋል፡፡

አንድ ድርጅት እየሠራ ሲሸጥና ቆሞ ወይም ተዘግቶ ሲሸጥ የዋጋ ልዩነት አለው ያሉት ሚኒስትሩ፣ ፋብሪካውን ለመግዛት የሚመጡ አዳዲስ ባለሀብቶች ሠራተኞቹ ሳይበተኑ፣ የምርት ሰንሰለቱ ሳይቋረጥ ፋብሪካውን ገዝተው ወደ ሥራ የሚገቡበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይቻላል ብለዋል፡፡

ባንኩ ድርጅቱን ለጊዜው ይዞት በጥሩ ሁኔታ እያስተዳደረው ይገኛል ያሉት አቶ መላኩ፣ ነገር ግን በዋናነት እንደሚፈለገው አዳዲስ ባለሀብቶች በሚመጡበት ጊዜ ፋብሪካው ሳይቆም ተረክበውት እንዲያስቀጥሉ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

ፋብሪካው 1,100 የሚደርሱ ሠራተኞች እንዳሉት ተገልጿል፡፡ በልማት ባንክ በኩል በጊዜያዊነት እንዲመሩት የተሾሙት ኃላፊዎች ለሚኒስትሩ እንደገለጹት፣ ፋብሪካውን ባንኩ ከተረከበ በኋላ ምንም ዓይነት ለማሽኖቹ መለዋወጫ የሚሆኑ ቁሶችን በመጋዘን አላገኙም፡፡ ማሽኖቹ የመለዋወጫ ዕቃዎች ስለሚያስፈልጋቸው የአገር ውስጥ ወኪሎችን ፈልገው እንደሚያሟሉ ተናግረዋል፡፡

ሆኖም መለዋወጫዎችን በቀጥታ ለማምጣት የባንክ ኤልሲ ለመክፈት የፋብሪካው ስም መዘዋወር ስላለበት ሒደቱን እንደ ጀመሩ ገልጸው፣ ማሽኖቹ የምርት ጊዜያቸው ትንሽ ቆየት ያለ ስለሆነ የመለዋወጫ ዕቃዎቻቸውን ማግኘት አስቸጋሪ እንደሆነባቸው አስረድተዋል፡፡

ፋብሪካውን ለመሸጥ በመስከረምና በጥቅምት ወራት ጨረታ እንደወጣ የተገለጸ ሲሆን፣ ግምቱ ወደ 1.4 ቢሊዮን ብር በመሆኑ በጨረታው ሊወዳደር የፈለገ ባለሀብት እንዳልቀረበ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች