Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊኦሚክሮን በኢትዮጵያ ስለመግባቱ የማጣራት ሥራ ይከናወናል ተባለ

ኦሚክሮን በኢትዮጵያ ስለመግባቱ የማጣራት ሥራ ይከናወናል ተባለ

ቀን:

ከስምንት ሚሊዮን በላይ ሰዎች የኮቪድ መከላከያ ተከትበዋል

ኮቪድ-19 ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ ቀውሶችን እንዳስከተለ ይታወቃል፡፡ የወረርሽኙ አስቸጋሪ ሁኔታ ደግሞ የዝርያውና የባህሪው መቀያየር ሲሆን፣ ይህም ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት አስቸጋሪና ፈታኝ አድርጎታል፡፡

የጤና ሚኒስቴር ኅዳር 22 ቀን 2014 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ሚኒስትሯ ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ዴልታና ሌሎች የኮቪድ ዝርያዎች በዓለም ተከስተዋል፡፡ እነዚህ የመጨረሻ ዝርያ አይደሉም፡፡ አሁንም ወረርሽኙ እስካልቆመ ድረስ ሌሎች ዝርያዎች ይመጣሉ፡፡

በአሁኑ ሰዓት በተለይም በበርካታ የዓለም አቀፍ ሚዲያ አውታሮች እያነጋገረ ያለውና በዓለም ጤና ድርጅት ‹‹ኦሚክሮን›› የሚል ስያሜ የተሰጠው አዲሱ የኮቪድ ዝርያ ከተከሰተ ወዲህ ዓለም ዳግም ተደናግጧል፡፡

በኦሚክሮን መከሰት ሳቢያ የአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮችና ሌላውም ዓለም ከደቡብ አፍሪካ ብቻ ሳይሆን ከመላው ደቡባዊ አፍሪካ አገሮች ለሚመጡ መንገደኞች ድንበሮቻቸውን የመዝጋት ውሳኔ አሳልፈዋል፡፡ አንዳንድ ግዛቶችም የአስቸኳይ ጊዜ ድንጋጌ እስከማወጅ ደርሰዋል ሲሉም የፈጠረውን ድንጋጤ ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡

የኦሚክሮን ወረርሽኝ ሁኔታ ገና ሳይታወቅ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ሲባል የመግቢያ በሮችንና ድንበሮችን መዝጋት መፍትሔ ባይሆንም፣ በየመግቢያ በሮች ላይ ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ በየመግቢያው በር እየተካሄደ ያለው የመቆጣጠር ሥራ ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል፣ በዚህም ተገቢውን ክትባት የወሰዱ እንዲገቡ፣ ያልተከተቡ ከሆነ ደግሞ በየመግቢያ በሮች እንዲከተቡ እንደሚደረግና የመከላከያ መንገዶችም የተለየ መረጃ እስካልመጣ ድረስ አሁን እየተተገበሩ ያሉት መንገዶች መቀጠል እንዳለባቸው አክለዋል፡፡

ክትባቱን መከተብ በቫይረሱ የመያዝን፣ ከተያዙም በኋላ በበሽታው የመሞትን ዕድል በከፍተኛ ደረጃ እንደሚቀንስ ያስታወሱት ሚኒስትሯ፣ አዲሱ የቫይረስ ዝርያ መከሰቱ የተሰማው የአውሮፓና ሌሎችም አገሮች የኮቪድ-19 ወረርሽኝ አራተኛው ዙር ማዕበል ውስጥ ባለበት ወቅት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡  

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በአገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ አሳሳቢ የጤና ሥጋት እንዲሆን ያደረገውም አራተኛው ዙር ማዕበል በመምጣቱ፣ አደገኛ የሆነው ዴልታ በመስፋፋቱ፣ አዲሱ ኦሚክሮን ዝርያ በመከሰቱ ምክንያት መሆኑን ሚኒስትሯ አመልክተዋል፡፡

ይህ ሁኔታ እንደተደበቀ ሆኖ የመከላከያ ክትባትን በበቂ ደረጃ አለመወሰድ፣ በክትባቱ ዙሪያ የሚነሱ አሉባልታዎች፣ የተሳሳቱ አመለካከቶችና ኢሳይንሳዊ መረጃዎች ተጨምረውበት ሥጋቱን እንዳወሳሰበው ተናግረዋል፡፡

ኦሚክሮን በተለያዩ አገሮች ቢገኝም በአገራችን ገብቷል ወይስ አልገባም የሚለውን ለመለየት የሚረዳ የማጣራት ሥራ እንደሚከናወን፣ የባህሪውን ሁኔታና ሌሎችም የዝርያውን ተያያዥ ነገሮች ለማወቅ የሚያስችል ጥናት በመከናወን ላይ መሆኑን አክለዋል፡፡

እንደ ዶ/ር ሊያ፣ በመላው ዓለም እስካሁን ከ3.3 ቢሊዮን በላይ ወይም 42 በመቶ ያህል ሰዎች የኮቪድ-19 መከላከያ ተከትበዋል፡፡ በኢትዮጵያ ደግሞ የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት መሰጠት ከጀመረበት አንስቶ እስከ ኅዳር 22 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ  8,106,497 ሰዎች የተከተቡ ሲሆን፣ 9,555,907 ዶዝ ክትባት መሰጠቱን፣ ከዚህ ውስጥ 4,225,378 ያህል ዶዝ ካለፉት ሁለት ሳምንታት ጀምሮ በአገር አቀፍ ደረጃ በመካሄድ ላይ ባለው የክትባት ዘመቻ ላይ ውሏል፡፡ ይህም ክትባቱ በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን ማመላከቱን አስረድተዋል፡፡

ከዚህም ሌላ እስካሁን ድረስ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ 761 ሚሊዮን፣ በአፍሪካ 8.6 ሚሊዮን፣ በኢትዮጵያ ከ370 ሺሕ በላይ ሰዎች በቫይረሱ እንደተያዙ፣ ከእነዚህም መካከል እንደ ቅደም ተከተላቸው ከ5.2 ሚሊዮን፣ ከ222 ሺሕ፣ 6,771 ሰዎች እንደሞቱ፣ በርካቶችም በፅኑ ሕሙማን መታከሚያ ክፍል ገብተው በሕክምና ላይ እንደሚገኙ ሚኒስትሯ ጠቁመዋል፡፡

በተለያዩ የዓለም ክፍሎች፣ በአፍሪካና በኢትዮጵያ በወረርሽኙ ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች ብዛት ሊታወቅ የቻለው በየጤና ተቋማት ውስጥ ሲታከሙ በቆዩት እንጂ በየቤቱ የሞቱትን እንደማያካትት ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በደቡብ አፍሪካ አገሮች የታየው አዲሱ የኮሮና ቫይረስ ዓይነት እስካሁን ከታዩት የኮሮና ቫይረስ ዓይነቶች እጅግ የተለየ ነው ተብሏል፡፡ በበርካታ ብዙ የዘረመል ለውጥ ውስጥ በማለፍ በአንድ ሳይንቲስት ‹‹አሰቃቂ›› ተብሎ ሲገለጽ በሌላው ደግሞ እስካሁን ከታዩት የከፋ ዝርያ ተብሏል፡፡

ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች በደቡብ አፍሪካ በአንድ ግዛት ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፣ የበለጠ ሊስፋፋ እንደሚችል ግን ፍንጮች አሉ፡፡ ቫይረሱ በምን ያህል በፍጥነት እንደሚሠራጭ፣ ክትባቶችን የመቋቋም አቅሙና በሌሎችም ላይ ጥናት እየተደረገ መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...