Thursday, April 18, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ግብር ከፋዮች መሠረታዊ የታክስ ሕጎችን እየተማሩ መሆኑ ተጠቆመ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የገቢዎች ሚኒስቴር ከትግራይ ክልል በስተቀር በሁሉም ባሉት አሥር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶቹ፣ በሳምንት ሁለት ቀናት ለስድስት ሰዓታት መሠረታዊ የታክስ ሕጎች ትምህርት በፓወር ፖይንት (Power Point) መስጠት ጀመረ፡፡

ሚኒስቴሩ እንዳስታወቀው ግብር ከፋዮች 90 ሰዓታት መማር ያለባቸው ሲሆን፣ ፈተናዎችን ካለፉ ሠርተፍኬት ወስደው ራሳቸውንም ከግብር ቅጣቶች ያድናሉ ተብሎ ታስቧል፡፡  

‹‹አብዛኞቹ የግብር ቅጣቶች ተደጋጋሚና ባለማወቅ የሚከሰቱ ናቸው፡፡ የ100 ሺሕ ብር ፍሬ ግብር ባለመክፈል የሚሊዮን ብር ቅጣት ይጣልባቸዋል፤›› ሲሉ፣ በሚኒስቴሩ የታክስ ከፋዮች ትምህርት ዳይሬክተር አቶ በፍርዱ መሠረት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ የከፍተኛ ደረጃ የታክስ ሕጎች ሥልጠና (አድቫንስድ ሌቭል ትሬኒንግ) ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን፣ 90 ክሬዲት ሰዓታት የጨረሱ ብቻ ወደዚያ እንደሚያልፉ አስረድተዋል፡፡

አሁን እየተሰጠ ያለው ትምህርት በሦስት የተከፈለ ሲሆን እያንዳንዱ አንድ ወር ከግማሽ ወይም በአጠቃላይ 90 ሰዓት ይፈጃል፡፡ ሦስቱም የቀጥተኛ ታክስና ቀጥተኛ-ያልሆነ ታክስ አስተዳደር ሲሆኑ፣ በአጠቃላይ 13 ሞጁሎች ተዘጋጅተዋል ተብሏል፡፡ በእነዚህ በሦስቱ ምድቦች ውስጥ አሥር ዙሮች እንዳሉ፣ ግብር ከፋዮች አንዱን ዙር በፈተና ሲያልፉ ብቻ ወደ ቀጣይ ዙር ይመዘገባሉ፡፡

ከግንቦት 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ሲሰጥ በቆየውና አሁን አሥረኛ ዙር በደረሰው የቀጥተኛ ታክስ ከፋዮች ትምህርት 3,500 ታክስ ግብር ከፋዮች ተፈትነው ማለፋቸው ታውቋል፡፡

‹‹ግብር ከፋዮች እንደ ማንኛውም ተማሪ ተመዝግበውና መታወቂያ ወስደው ተምረውና ተፈትነው ነው የሚያልፉት፡፡ በጣም ብዙ መመርያዎች፣ ደንቦችና አዋጆች በሞጁሎች ውስጥ ተካተዋል፡፡ ትምህርቱን የትልልቅ ድርጅቶች ባለቤቶች፣ አካውንቶቻቸውና የፋይናንስ ኃላፊዎቻቸው እየተማሩ ነው፡፡ ለውጭ ዜጎች በሌሎች ቋንቋዎች ሞጁሎቹ እየተረጎሙ ነው፡፡ ዋናው ትምህርት የትኞቹ ወጪዎችና ገቢዎች በታክስ እንደሚመዘገቡ ማሳወቅ ነው፡፡ በተለይ የንግድ ገቢ ግብር ሕግ ውስብስብ ስለሆነ እሱ ከበድ ብሏቸዋል፤›› ሲሉ አቶ በፍርዱ አስረድተዋል፡፡

ሠርተፊኬት የወሰዱ ግብር ከፋዮች አዲስ የግብር ሕግ ካልወጣ በስተቀር ከእንግዲህ የግብር ግንዛቤ ማስጨበጫ ሳያስፈልጋቸው እንደሚከፍሉ፣ ሚኒስቴሩም ራሳቸው አምነው የከፈሉትን የግብር መጠን ኦዲታቸውን ብቻ ቼክ በማድረግ ያረጋግጣል ሲሉ አክለዋል፡፡

ትምህርቱ ተደጋጋሚ የግብር ክስ ጉዳዮች በመብዛታቸው የተጀመረ ቢሆንም፣ በመደበኛ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ የታክስ ትምህርት ባለመኖሩ የተፈጠረ ክፍተት ውጤት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ገቢዎች ሚኒስቴር ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመሆን 81 ገጽ ያለው ሰነድ አዘጋጅቶ በመደበኛ ትምህርት ሥርዓት ውስጥ እንዲገባ ያስረከበ ቢሆንም፣ አዲሱ ካሪኩለም ባለፈው ዓመት ይጀመራል ተብሎ በመዘግየቱ፣ ገቢዎች ሚኒስቴር የራሱን ሞጁል አዘጋጅቶ ትምህርቱን መጀመሩን ገልጸዋል፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር አፅድቆት የነበረው ሰነድ የታክስ ትምህርት ከቅድመ መደበኛ (ከኬጂ) ጀምሮ እንዲሰጥ ይፈቅዳል፡፡

‹‹ሕፃናት በመጫወቻና በትንንሽ ነገሮች እንዲጀምሩ ተደርጎ ከፍ ሲሉ ግንዛቤያቸው እንዲዳብር ይደረጋለ፡፡ ግብር የከፋይ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ዜጋ ጉዳይ መሆን አለበት፤›› በማለት ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

የክልሎችን ሳይጨምር በፌዴራል ደረጃ የሚታወቁ ወደ 48,000 የሚጠጉ ግብር ከፋዮች መኖራቸውን፣ እየተሰጠ ያለው ትምህርት አስመጪዎችን ባለማካተቱ ለእነሱ ሌላ ሞጁል ከጉምሩክ ኮሚሽን ጋር እየተዘጋጀ ነው፡፡

በአገሪቱ 628 ትልልቅ ግብር ከፋዮች (Large Tax Payer) ሲኖሩ አብዛኞቹ ትምህርቱን እየወሰዱ ነው ተብሏል፡፡ በሚቀጥለው ዓመት የሚጀመረው ትምህርት ዘርፍን መሠረት ያደረገ ሲሆን፣ ለምሳሌ በግንባታ ወይም በቱሪዝም ዘርፍ ያሉ ድርጅቶች ለየብቻ እንደሚማሩ ተጠቁሟል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች