Saturday, May 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

በቀደም ዕለት መሀል ቦሌ አንድ ዘመናዊ ካፌ በረንዳ ላይ ሆኜ ጋዜጣ እያነበብኩ ማኪያቶዬን ስጠጣ፣ ድንገት በቁጣ የሚጮህ ሰው ድምፅ ይሰማኛል፡፡ ቀና ስል ከፊት ለፊቴ በኩል አንድ ሰው በተንቀሳቃሽ ስልኩ እየተነጋገረ ነው፡፡ ዓይኖቹ ቀልተው በንዴት የሚነጋገረው ይኼው ሰው ጉንጮቹ እየተንቀጠቀጡ በኃይለ ቃል በስልኩ ከሚያናግረው ሰው ጋር እየተጨቃጨቀ ነው፡፡ ንዴቱ ከመጠን በላይ በመናሩ ማንም ቢሰማው ደንታ የሚሰጠው አይመስልም ነበር፡፡ ሰውዬው በርካቶች አፍጥጠን ስናየው እንኳ ግድም አልሰጠው፡፡ እኛ ዓይናችንን ያፈጠጥንበት እሱ ስለጮኸ ሳይሆን ከአፉ በሚወጡት አስፈሪ ኃይለ ቃሎች ምክንያት ነበር፡፡

‹‹የፈለገ ሥልጣን ይኑረው የማውቀው ነገር የለም፡፡ እንኳን የክፍለ ከተማ አይደለም ለምን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት አይሆንም? ከፈለገም ለምን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አይሆንም?›› እያለ ሲጮህ ነበር የደነገጥነው፡፡ ‹‹እሱ በሥልጣኑ ተመክቶ የፍርድ ቤት ውሳኔ አላከብርም ብሎ ሕገወጥ ተግባር ሲፈጽም ዝም የምለው መሰለህ?›› ሲል በልቤ ማንን ይሆን በማለት ማሰብ ጀመርኩ፡፡ ሰውዬው ቀጥሏል፡፡ ‹‹ሕግ ባለበት አገር ውስጥ ከሕግ በላይ ነኝ ካለ በሬሳዬ ላይ ተራምዶ ሕገወጥ ተግባሩን ያስፈጽማል፤›› አለ፡፡ የባሰው መጣ፡፡ ‹‹ባለሥልጣንም ይሁን የድርጅት ካድሬ እኔን የሚያገባኝ ነገር የለም፡፡ ሁለታችንም በሕግ ፊት እኩል ነን፡፡ ይህም ሕገ መንግሥቱ ያጎናፀፈኝ መብት ነው…›› እያለ በጩኸት ሲናገር አንዳንድ ሰዎች ሒሳባቸውን እየከፈሉ ውልቅ ማለት ጀመሩ፡፡

ሰውዬው ከካፌው በረንዳ ላይ ወርዶ በስልኩ ውስጥ ከሚያናግረው ሰው ጋር መጨቃጨቁን ቀጥሏል፡፡ የሰውዬው ኃይለ ቃል ሲጨምር ሌሎች ደንግጠው ከአካባቢው ቢሰወሩም፣ እኔ ግን እዚያው ቁጭ ብዬ የሰውዬውን አካላዊ እንቅስቃሴ እያየሁ ነው፡፡ ሰውዬው በኃይል እየተወራጨ አስፋልት መንገዱ ላይ ወጪ ወራጁ እየተመለከተው በጩኸት መነጋገሩን ቀጥሏል፡፡ አንዳንዶች ወፈፍ ያደረገው እየመሰላቸው ይሸሹታል፡፡ ሌሎች ደግሞ በርቀት ፈንጠር ፈንጠር ብለው በድንጋጤ ይመለከቱታል፡፡ በዚህ መሀል ሰውዬው ለየለት፡፡ ስልኩን አስፋልት ላይ ከስክሶ በእግሩ እየረጋገጠ ድምጥማጡን አጠፋው፡፡ ራሱን በእጆቹ እየደበደበ መሄድ ጀመረ፡፡ በቃ ለየለት ማለት ነው፡፡

- Advertisement -

ሰውዬው በፍጥነት መንገዱን ይዞ ሲሸመጥጥ፣ እኔ ወዲያው ሒሳቤን ከፍዬ እከተለው ጀመር፡፡ ከመንገዱ ማዶ ተሻግሮ ሄዶ አንድ ነጭ ላንድክሩዘር ውስጥ ገብቶ ሞተሩን አስነሳ፡፡ መኪናውን በፍጥነት እየነዳ ወደ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን አቅጣጫ ሲያከንፈው፣ እኔም መኪናዬ ውስጥ ገብቼ ፊትና ኋላ እየበረርን መድኃኔዓለም ደረስን፡፡ ከመኪናዬ ወርጄ ሰውዬው መኪናውን ወዳቆመበት ጠጋ ብዬ ማየት ጀመርኩ፡፡ የመኪናው መሪ ላይ ፊቱን ደፍቶ ያለቅሳል፡፡ እስኪጨርስ በማለት ወደ ፈጣሪ ፀሎት ማድረስ ጀመርኩ፡፡ የምድሩ ግሳንግስ ነገር አስጠልቶ መመነን ያስመኛል፡፡ ለበርካታ ደቂቃዎች የፈጣሪ በር ላይ ካተኮርኩ በኋላ ዓይኖቼን ወደ መኪናው መለስ ሳደርግ፣ ሰውዬውም ከሰማዩ አድማስ ጋር የገጠመው ሰማይ ላይ ዓይኖቹን ሰክቷቸዋል፡፡

ስፈራ ስቸር ወደ መኪናው ተጠግቼ በአንገቴ ሰላም አልኩት፡፡ ትኩር አድርጎ ካየኝ በኋላ እሱም በአንገቱ ሰላም አለኝ፡፡ ጠጋ ብዬ፣ ‹‹ቅድም በንዴት ስትናገርና ከዚያም ስልክህን ስትሰባብር ዓይቼህ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ እዚህ መጥተህ ቆመሃል፡፡ ምን ገጠመህ?›› በማለት ጥያቄ አቀረብኩለት፡፡ ግራ በተጋባ ስሜት እያየኝ፣ ‹‹ታዲያ አንተን ምን ያገባሃል?›› አለኝ፡፡ መረጋጋት እያሳየሁ፣ ‹‹በእርግጥ የሚያገባኝ ነገር የለም፡፡ የሰው ልጅ እንዲህ በከባዱ ሲበሳጭ ስለማልወድ ያጋጠመህን ላዋይህ ነው፤›› አልኩት፡፡ ፊቱን ቅጭም አድርጎ ከመኪናው ወርዶ፣ ‹‹ወንድሜ አይጠቅምህም፣ እኔም ለፈጣሪዬ አልቅሼ ስለነገርኩት ካሁን በኋላ የሰው አፅናኝ አልፈልግም፤›› ብሎኝ ደህና ዋል በሚል ስሜት መኪናው ውስጥ ገብቶ ሞተሩን ማስነሳት ጀመረ፡፡

እኔም ፊቴን አዙሬ ወደ መጣሁበት ስመለስ ሰውዬው መኪናውን አቁሞ፣ ‹‹አንድ የክፍለ ከተማ ባለሥልጣን ነኝ የሚል ሰው በፍርድ ቤት የተፈረደልኝን አላስፈጽምም ከማለቱ በተጨማሪ፣ እኔን ለማሳሰር ፖሊስ አሰማርቷል የሚል ማስፈራሪያ ሲደወልልኝ ነው የተናደድኩት፡፡ የደወለልኝ ዘመዴ የሰውዬውን አስፈሪነት እያጋነነ የሕግ የበላይነት ዋጋ እንደሌለው በፍርኃት ተርበድብዶ ሲነግረኝ አበድኩኝ፤›› ብሎ መሪውን በቡጢ እየጠለዘ ሳቀ፡፡ ‹‹አሁን ግን ተረጋግቻለሁ…›› አለኝ፡፡ ‹‹ታዲያ አሁን ምን አሰብክ?›› በማለት ጥያቄ አቀረብኩለት፡፡ በጣም በተረጋጋ መንፈስ፣ ‹‹ፈጣሪ አምላኬ እያለልኝ የደካማ ፍጡር ማስፈራራት ምን ያመጣል ብለህ ነው? ለጊዜው ወፈፍ ቢያደርገኝም ከፈጣሪ በላይ ማንም ኃይል እንደሌለው አውቃለሁ እኮ፤›› ብሎኝ መድኃኔዓለም ግቢ ውስጥ ተሰናበተኝ፡፡ እኔም ለእኛም ሆነ ለኢትዮጵያ ችግር መፍትሔው ያለው ፈጣሪ እጅ ውስጥ ስለሆነ፣ ‹‹ሠልፍ የጀግና ነው፣ ድል የእግዚአብሔር ነው›› ብለን ከተነሳን የማንም ወንበዴ አያሸንፈንም፡፡

(ዕድሉ አስፋው፣ ከገርጂ)  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ