Thursday, April 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊከ12 ዓመት ዕድሜ ጀምሮ የሚከተቡበት አዲሱ አገራዊ የኮቪድ-19 ክትባት ንቅናቄ

ከ12 ዓመት ዕድሜ ጀምሮ የሚከተቡበት አዲሱ አገራዊ የኮቪድ-19 ክትባት ንቅናቄ

ቀን:

  • ‹‹ዛሬውኑ ይከተቡ ጤናዎትን ይጠብቁ!››

ኅብረተሰቡን ከአስከፊው የኮሮና ወረርሽን ለመጠበቅ መንግሥት የተለያዩ ዕርምጃዎችን ሲወስድ ቆይቷል፡፡ በቀጣይም የመከላከሉን ሥራ ውጤታማ ለማድረግ በክትባቱ ላይ የሚፈጠሩ የተሳሳቱ አመለካከቶችን፣ አሉባልታዎችንና ኢሳይንሳዊ የሆኑ መረጃዎችን ወደ ጎን በመተው፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥራታቸው የተረጋገጡ ክትባቶችን በመውሰድ ጤንነቱን መጠበቅ እንደሚኖርበት ያሳሰቡት የጤና ሚኒስትር ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

የአገር አቀፍ የኮቪድ-19 ክትባት ዘመቻ መርሐ ግብር ኅዳር 7 ቀን 2014 ዓ.ም. ሲጀመር ሚኒስትሯ እንደገለጹት፣ መንግሥት በተከታታይ ተጨማሪ ክትባቶችን ወደ አገር ውስጥ በማስገባት እስካሁን ከ3.6 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተከትበዋል፡፡

ሆኖም ግን ክትባቱን ተደራሽ ለማድረግ ከታለመው አንፃርና ኢትዮጵያ ካላት የሕዝብ ቁጥር አንፃር አፈጻጸሙ አነስተኛ እንደሆነና በዚህም የተነሳ የዘመቻ ሥራ ማከናወን አስፈላጊ ሆኖ እንደተገኘ ነው የተናገሩት፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ክትባቱንም በአጭር ጊዜ ለታላሚው ኅብረተሰብ ተደራሽ ለማድረግ ለሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታትና ከዚያ በላይ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ ለሆኑ ዜጎች ክትባቱ እንደሚሰጥ ዶ/ር ሊያ ጠቅሰው፣ ከአሁን ቀደም እየተሰጡ ካሉት ‹‹የአስትራዜኒካ››፣ ‹‹ስይኖፋርም›› እና ‹‹ጆንስ ኤንድ ጆንሰን›› ክትባቶች በተጨማሪ የ‹‹ፋይዘር›› ክትባት ወደ አገር ውስጥ መግባቱን በመግለጽ ነው፡፡ የፋይዘር ክትባቱንም ዕድሜያቸው ከ12 ዓመት በላይ ለሆናቸው ከነገ ጀምሮ በአዲስ አበባ እንዲሁም ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ በክልሎች መሰጠት እንደሚጀምር ተናግረዋል፡፡

ዶ/ር ሊያ እንዳስታወቁት፣ በዘመቻው በአጠቃላይ 20 ሚሊዮን ዜጎችን ተደራሽ ለማድረግ ታቅዷል፡፡ ለዚህም ከስምንት ሚሊዮን ዶዝ በላይ ክትባት በእጅ የሚገኝ ሲሆን፣ ተጨማሪ ክትባቶች ወደ አገር እየገቡ ነው፡፡ ለዕቅዱ መሳካት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የየድርሻውን መወጣት ይኖርበታል፡፡

የኮቪድ-19 በሽታ ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ጀምሮ ባሉት ጊዜያት 368,979 ሰዎች ቫይረሱ እንደተገኘባቸው በምርመራ የተረጋገጠ ሲሆን፣ 6,630 ሰዎች ደግሞ በበሽታው ተይዘው ሕይወታቸው ማለፉን ከሚኒስትሯ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተመሳሳይ የሆነ የክትባት ዘመቻ መርሐ ግብር ከኅዳር 6 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በማካሄድ ላይ ነው፡፡ ‹‹ዛሬውኑ ይከተቡ ጤናዎትን ይጠብቁ!›› በሚል መሪ ቃል ለአሥር ቀናት በሚካሄደው በዚሁ መርሐ ግብር፣ አንድ ሚሊዮን ሰዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱን የአስተዳደሩ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዮሐንስ ጫላ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

ክትባቱ በዘመቻ እንዲካሄድ ያስፈለገበት ምክንያት ቀደም ሲል ከአጠቃላዩ የከተማ ነዋሪዎች መካከል ቢያንስ 20 ከመቶ ያህሉን ለመከተብ ተይዞ የነበረው ዕቅድ ባለመሳካቱ የተነሳ ነው፡፡ እስከ ኅዳር 15 ቀን ድረስ በሚካሄደው በዚሁ ዘመቻ ላይ ግን ዕድሜቸው 12 ዓመትና ከዚያም በላይ የሆኑ እንዲከተቡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ክትባቶቹ ከዚህ በፊት እንደሚሰጡት በጤና ተቋማት ብቻ ሳይሆን በተቋቋሙት ጊዜያዊ የክትባት መስጫ ጣቢያዎች ጭምር ሲሆን፣ እነዚህም በርካታ ሰዎች በሚገኙባቸው የኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ ትልልቅ የገበያ ቦታዎች፣ ሞሎች፣ የማሠልጠኛ ማዕከላት፣ በግልና በመንግሥት ትምህርት ቤቶች፣ እንዲሁም ሌሎች ለማኅበረሰቡ ይበልጥ አመቺና ቅርብ በሆኑ ቦታዎች ላይ እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡

በአሁኑ ጊዜ አራት የክትባት ዓይነቶች ማለትም አስትራ ዜኒክ፣ ሲኖፋርም፣ ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን እና ፋይዘር በማስገባት ኅብረተሰቡ በነፃ ተጠቃሚ እንዲሆን እየተሠራ እንደሚገኝ፣ ክትባቶቹንም ለሚገባቸው ለማድረስ ይቻል ዘንድ 777 የክትባት ቡድኖችን በማንቀሳቀስ አገልግሎቱን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ ጥረት እንደተደረገ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ለተከታታይ አሥር ቀናት በመካሄድ ላይ ባለው በዚህ ዘመቻ ላይ ከቀረቡት ክትባቶች መካከል ‹‹ፋይዘር›› የተባለው ክትባት የሚሰጠው በጤና ተቋማት ብቻ እንደሆነ፣ ክትባቱንም የሚጠቀሙ ዕድሜያቸው 12 ዓመትና ከዚያም በላይ የሆኑ ልጆችና አዋቂዎች እንደሆኑ ነው የገለጹት፡፡

ለልጆች የሚሰጠው ይህ ክትባት በመንግሥትና በግል ትምህርት ቤቶች ብቻ ቢከናወን ችግሩ ምንድነው? ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ዮሐንስ ጫላ (ዶ/ር) ሲመልሱ፣ ‹‹የክትባቱ ባህርይ የሙቀቱ መጠን በጣም ዝቅተኛ የሆነ ቅዝቃዜ ያለው ቦታ በማስፈለጉና ከጤና ተቋማት ውጪ ማውጣትም ውጤቱን ስለሚቀንሰው ነው፤›› ብለዋል፡፡

እንደ ዮሐንስ ጫላ (ዶ/ር) ማብራሪያ፣ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የገቡት እነዚህ ክትባቶች ፍቱንነታቸውና ደኅንነታቸው በዓለም ጤና ድርጅትና በጤና ሚኒስቴር የተረጋገጡ፣ በምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ዕውቅናና ፈቃድ ያገኙ ናቸው፡፡ በእነዚህም ክትባቶች አንድ ሚሊዮን የከተማው ነዋሪዎችን ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ታስቧል፡፡

ከእነዚሁ ክትባቶች መካከል ‹‹ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን›› ክትባት የሚሰጠው አንድ ዶዝ ብቻ ሲሆን፣ የቀሩት ግን ሁለት ዶዝ መሆን እንዳለባቸው፣ በዚህም መሠረት የመጀመርያው በተወሰደ በወሩ ሁለተኛውን ዶዝ መከተብ እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት ኃላፊው፣ ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ክትባትን የተለየ ያደረገው በአንድ ዶዝ ብቻ ውጤታማ መሆኑ በዓለም ጤና ድርጅት በመረጋገጡ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

እንደ ኃላፊው አባባል ዕድሜያቸው 12 ዓመትና ከዚያም በላይ ከሆኑ ታዳጊ ልጆች በስተቀር ሁሉም አዋቂዎች የፈለጉትን ዓይነት ክትባት የመጠቀም/የመከተብ መብት አላቸው፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን የጤናው ዘርፍ ማንኛውንም ጥረት ያደርጋል፡፡ ይሁን እንጂ የማኅበረሰብ ጤና ችግር በዘርፉ እንቅስቃሴ ብቻ የሚገታ አይደለም፡፡ ከዚህ አኳያ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የጋራ ኃላፊነት እንዳለበት አውቆ የመከላከያ ዘዴዎች በአግባቡ መተርጎም ይኖርበታል፡፡

በተለይ የወረርሽኙ ሦስተኛው ማዕበል በአዲስ አበባ በስፋት በመከሰቱ በርካታ ሰዎች በወረርሽኙ እንደተያዙ፣ የሕክምና ማዕከሎቹ አልጋዎች በአንድ ወቅት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ለፅኑ ሕሙማን ታካሚዎች ብቻ እስኪሆኑ ደርሰው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ብዙዎችን በሞት እንዳጣናቸው፣ ከዚህ በፊት በቫይረሱ ተይዘው ሕመሙ ይፀናባቸው ከነበሩ ዕድሜያቸው የገፋና ተጓዳኝ የጤና ችግር ካለባቸው በተጨማሪ በታዳጊ ወጣቶች ላይ የከፋ ጉዳት እያደረሰ እንደሚገኝም ኃላፊው ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...