Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊተደራሽነቱን እንዳያሰፋ ፋይናንስ እጥረት ማነቆ የሆነበት የዓይን ባንክ

ተደራሽነቱን እንዳያሰፋ ፋይናንስ እጥረት ማነቆ የሆነበት የዓይን ባንክ

ቀን:

ከዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ ሐኪሞች ቁጥር አናሳ መሆን፣ በኅብረተሰቡ ግንዛቤ እጥረትና በፋይናንስ ችግር የተነሳ ተደራሽነቱን በአገር አቀፍ ደረጃ ለማስፋፋት እንዳልቻለ የሚናገረው የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ ነው፡፡

የባንኩ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ለምለም አየለ እንደገለጹት፣ ባንኩ በአሁኑ ጊዜ ያሉት የዓይን ንቀለ ተከላ ሐኪሞች ቁጥር ዘጠኝ ብቻ ሲሆኑ፣ አንድ ሌላ የዓይን ሐኪም ደግሞ በንቅለ ተከላ የሰብ ስፔሻሊቲ መርሐ ግብር በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዓይን ሕክምና ትምህርት ክፍል በመከታተል ላይ ነው፡፡

የፋይናንስ ችግሩን ግን በጤና ሚኒስቴር በኩል መፍትሔ ያገኛል የሚል ተስፋ መኖሩን ዋና ዳይሬክተሯ ጠቅሰው፣ ባንኩ እነዚህ ችግሮች ባሉበት ሁኔታ ሁሉ በብሌን ጠባሳ ምክንያት ብርሃናቸውን የተነጠቁ ሰዎችን ከለጋሾች የዓይን ብሌን በመሰብሰብ ብርሃናቸውን እንዲያገኙ በማድረግ ኃላፊነቱን እየተወጣ ያለ ሰብዓዊ ተቋም መሆኑን ገልጸዋል፡፡  

ብርሃን እንዲያገኙ የማድረግ ሥራውንም የሚከናወነው የዓይን ብሌኑ ንፅህና እና ጥራቱን በማረጋገጥ ሲሆን፣ በዚህም መሠረት ከተቋቋመበት 1995 ዓ.ም. ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ 2,678 ወገኖች በንቅለ ተከላ ሕክምና ዘዴ ብርሃናቸው እንደተመለሰ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

‹‹የዓይን ብሌን ማለት ከዓይናችን ፊት ለፊት የሚገኝ መስታወት መሰል ሆኖ ጥቁሩን የዓይናችንን ክፍል የሚሸፍን ነው፡፡ ብርሃን አስተላላፊ የዓይን ክፍል ከመሆኑም ባሻገር መጠኑም ከ12 እስከ 14 ሚሊ ሜትር ነው፡፡ ይህም በልምድ የአንድ ሰው የአውራ ጣት ጥፍርን ያህል ነው፤›› ሲሉም ዋና ዳይሬክተሯ አብራርተዋል፡፡

አንድ በሕይወት ያለ ሰው የኢትዮጵያን የዓይን ባንክን ዓላማ በመርዳትና በማወቅ ከሕልፈቱ በኋላ የዓይን ብሌኖቹን ለዓይን ባንክ መለገስ እንደሚቻል፣ ለዚህም ዕውን መሆን በዓይን ባንኩ በመገኘት ቃል ኪዳን ሰነድ ላይ መፈረምና መታወቂያ ካርድ መውሰድ እንዳለበት ነው የገለጹት፡፡

አንድ ሰው ሕይወቱ ባለፈ በስምንት ሰዓት ጊዜ ውስጥ የዓይን ብሌኑ መሰብሰብ እንደሚኖርበት፣ ዕድሜያቸው ከሁለት ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑ ወገኖች ሕልፈት ሲያጋጥማቸው የቅርብ ዘመድ በሚሰጠው ፈቃድ የዓይን ባንኩ ብሌናቸውን መሰብሰብ እንደሚችል ከዳሬክተሯ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ባንኩ የዓይን ብሌኖቹንም የሚሰበስበው በሦስት መርሐ ግብሮች በመታገዝ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል አንደኛው ሆስፒታልን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ፕሮግራም ሰው ሕይወቱ በሆስፒታል ውስጥ በሚያልፍበት ወቅት የሟች የቅርብ ቤተሰብን በማማከርና ፈቃድ በመጠየቅ የሚሰበሰብበት መንገድ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ሁለተኛው መርሐ ግብር በሕይወት እያሉ ቃል ከገቡ ወገኖች የሚሰበሰብበት አካሄድ ሲሆን፣ ተግባራዊ የሚሆነውም ለቤተሰቦቻቸው በሚደረግ ጥሪ አማካይነት መሆኑን ዋና ዳይሬክተሯ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ሦስተኛውና የመጨረሻው መርሐ ግብር በማንኛውም ሁኔታ በቤት ውስጥ ሕይወታቸው አልፎ በቤተሰቦቸው አማይነት በሚደረግ ጥሪ የዓይን ብሌን መሰብሰብ እንደሚቻል፣ የዓይን ባንኩ ሠራተኞችም ለጋሽ ያለበት ቦታ ድረስ በመገኘት የዓይን ብሌን እንደሚሰበስቡ ተናግረዋል፡፡

‹‹የዓይን ብሌን እንደተሰበሰበ ‹አፕቲዞልጂ ኤስ› የሚባል ማስቀመጫ ውስጥ ይቀመጣል፡፡ ማስቀመጫው ብሌኑን በሕይወት ያለ ሰው ላይ እንደሆነ ሁሉ ለ14 ቀናት ጊዜ ውስጥ ንጽህናውንና ጥራቱን በማረጋገጥ ለታካሚዎች እንዲደርስ ይደረጋል፤›› ብለዋል፡፡

እንደ ወ/ሮ ለምለም ማብራሪያ፣ የዓይን ብሌን የመሰብሰብ ሒደት ከ30 እስከ 40 ደቂቃ ብቻ የሚወሰድ ሲሆን፣ በቀብር ሥነ ሥርዓት ላይም ተፅዕኖ አያመጣም፡፡ የሚሰበሰበው የዓይን ብሌኑ ብቻ በመሆኑ በለጋሽ የፊት ገጽታ ላይ የሚያመጣው ምንም ዓይነት ለውጥ የለም፡፡

የዓይን ባንኩ ባለሙያዎች ብሌን ከመሰብሰባቸው በፊት የተለያየ የአካል ምርመራ፣ እንዲሁም ለጋሽ ከተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች ነፃ መሆናቸውን በላቦራቶሪ ምርመራዎች፣ የዓይን ብሌኑ ጥራት ለታካሚው የሚያመጣውን የዕይታ ለውጥ መጠን በዓይን ባንክ ላቦራቶሪ ውስጥ በሚደረግ ፍተሻ ይረጋገጣል፡፡ 

የዓይን ብሌን ጠባሳ ዓይነ ሥውርነት በተለያዩ የዓይን ምርቃዜዎች (ኢንፌክሽኖች)፣ በኩፍኝ በሽታ፣ በቫታሚን ኤ እጥረት፣ በተለያዩ ድንገተኛ አደጋዎች በተፈጥሮ፣ እንዲሁም ከሞራ ግርዶሽ ሕክምና በኋላ ሊከሰት እንደሚችል ከወ/ሮ ለምለም ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ በ1998 ዓ.ም. በተደረገ ጥናት ከ300 ሺሕ በላይ ወገኖች በብሌን ጠባሳና ተዛማጅ ችግሮች ተጠቅተዋል፡፡ ይህ ሕመም በአብዛኛው ወጣቱን የሚያጠቃ ሲሆን፣ የሚድነውም በብሌን ንቅለ ተከላ ሕክምና ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

‹‹ዓይን በሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ ትልቅ ሚና ያለው አባላተ ስሜት ነው፡፡ ተፈጥሮው ትንሽ ቢሆንም ከርቀት ያለውን ነገር ማየትና መለየት ይችላል፡፡ የምናየውንም ነገር ወደ አዕምሮ በመላክ መልዕክቱን ወደ ምሥል በመቀየር እንድንረዳ ያደርጋል፡፡

ዓይን የውበት መገለጫ ከመሆኑ የተነሳ ‹‹ስንቶች በሰዎች የዓይን ፍቅር ወድቀዋል›› ያሉት ወ/ሮ ለምለም፣ ‹‹ግጥሞች፣ ተረቶች፣ ታሪኮች፣ ልብ ወለዶች፣ ድራማዎች፣ ቴአትሮች፣ ፊልሞች፣ ወዘተ ሌላ ሌላም ነገር በዓይን ዙሪያ መሠራቱ ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ዓይን ከሁሉም የሰውነት ክፍል ጋር በቅንጀት የሚሠራ ነው፤›› ሲሉም አስምረውበታል፡፡

ከዋና ዳይሬክተሯ ማብራሪያ ለመረዳት እንደተቻለው፣ ያም ሆነ ይህ ከሁሉም የሰውነት ክፍሎች ጋር በጥምረት የሚሠራ በመሆኑ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል፡፡ ሌላው ልዩ የሚያደርገው በተፈጥሮው ጉዳትን መቋቋም የማይችል መሆኑን ነው፡፡ ‹‹ሌሎች የሰውነታችን ክፍሎቻችን ሲጎዳ ዓይናችንም አብሮ ሊጎዳ ይችላል፡፡ ለዚያም ይመስላል ‹አፍንጫ ሲመታ ዓይን ያለቅሳል› የሚባለው፤›› ያሉት፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...