Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የሕይወት ተሞክሮ የተንፀባረቀበት የጡት ካንሰር ማስገንዘቢያው መድረክ

የጥቅምት ወር ዓለም አቀፍ የጡት ካንሰር ግንዛቤ ማስጨበጫ ወር ነው፡፡ ይህንንም ምክንያት በማድረግ ኢትዮጵያ ውስጥ ከጥቅምት 15 እስከ ጥቅምት 19 ቀን 2014 ዓ.ም.  ድረስ የጡት ካንሰር ምርመራ፣ ምክር አገልግሎትና የሕይወት ተሞክሮ ማንፀባረቂያ ቀን ሆኖ ይሰነብታል፡፡ ከእነዚህ መካከል የሕይወት ተሞክሮ ማንፀባረቂያ ቀን የተከናወነው ጥቅምት 16 ቀን 2014 ዓ.ም. ሲሆን፣ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሕክምና ኮሌጅ በተካሄደው በዚህ ዕለትም አራት የጡት ካንሰር ሕሙማን የሕይወት ተሞክሮዋቸውን አካፍለዋል፡፡ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሕክምና ኮሌጅ ዋና ፕሮቮስት ወንድምአገኝ ገዛኸኝ (ዶ/ር) በመድረኩ መክፈቻ ላይ ባሰሙት ንግግር ‹‹በጡት ካንሰር ላይ ትኩረት ያደረገ ምርመራና ሕክምና ቶሎ ማድረግ በራሳችን፣ በቤተሰባችንና በማኅበረሰቡ ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ ማቅለል ይቻላል›› ብለዋል፡፡ ኮሌጁ እያስገነባ ካለው የካንሰር ሕክምና ማዕከል ግንባታ በቅርቡ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃም አመልክተዋል፡፡ በመድረኩ ላይ የተገኘው ታደሰ ገብረማርያም የሕሙማኑን ተሞክሮ እንደሚከተለው አጠናቅሮናታል፡፡

ሲስተር ፩፡- የሕክምና ክትትል አድርገው ሕይወታቸውን ካተረፉና የሕይወት ተሞክሮዋቸውን ካካፈሉትም መካከል ያጋጠማቸውን ነገር በማንሳት ተሞክሮዋቸውን ያካፈሉ አንዲት ሲስተር ይገኙበታል፡፡ ሲስተሯ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሕክምና ኮሌጅ ለብዙ ዓመታት ካገለገሉ በኋላ በክብር ጡረታ ወጥተዋል፡፡ የካንሰር ሕመም ከተገኘባቸው 11 ዓመታት እንደሆናቸው ሳይናገሩ አላለፉም፡፡

‹‹የካንሰር ሕመምን አስመልክቶ በኅብረተሰቡ ላይ ግንዛቤ መፍጠር ጥሩ ነው፡፡ ይህ ግን ድሮ አልነበረም፡፡ አሁን ግን በስፋት መጀመሩ ጥሩ ከመሆኑም ባሻገር እኛም ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ጡቶቻቸውን ከሚታመሙት ሴቶች መካከል ብዙዎቹ መናገር አይፈልጉም፡፡ ከዚህ በመነሳት ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብዬ አስባለሁ፤›› ብለዋል፡፡

ሕክምናውን በወቅቱ ከተወሰደ መዳንና መኖር እንደሚቻል እሳቸው የጡት ካንሰር ካደረባቸው 11 ዓመት እንደሞላቸው በተለይም ምንም ሳያፍሩ መናገርና ሌሎችንም ማስተማር እንደቻሉ ከተንፀባረቁት ተሞክሮዋቸው ለመረዳት ተችሏል፡፡

አንድ ሰው በካንሰር ከተያዘ ታከመም አልታከመም መሞቱ አይቀርም በሚል የተሳሳተ ምክንያት ምንም ዓይነት ሕክምና ሳያገኙ ብዙ ሰዎች ለሕልፈተ ሕይወት መዳረጋቸውን እንደሚያውቁ ገልጸው፣ መታከሙ ግን እሳቸውን እንዳኖራቸው ከብዙ ዓመት አገልግሎት በኋላ ለጡረታ እንዳበቃቸው ነው የተናገሩት፡፡

ካንሰር የሚመጣው በኃጢዓት ወይም በእርግማን እንዳልሆነ ሰው ላይ በተለያዩ ምክንያት ሊያጋጥም እንደሚችል፣ ስለዚህ ሕክምናውን በወቅቱ መከታተልና ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ከከፋ ጉዳት ለመዳን እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

እንስት ፪፡- አሜሪካ ከሚገኘው የዓለምፀሐይ የጡት ካንሰር ፋውንዴሽን የመጡት ሦስተኛዋ እንስት በስማቸው ፋውንዴሽን የተቋቋመላቸው ሴት ትንሽ እህታቸው መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በጡት ካንሰር ምክንያት እህታቸው ሕይወታቸው እንዳለፈ፣ ፋውንዴሽኑም ለሟች እህታቸው መታሰቢያና የጡት ካንሰር ያለባቸውን ሴቶች ለመርዳት ታስቦ የተቋቋመ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

እሳቸውም ከሦስት ዓመት በፊት የጡት ካንሰር እንዳለባቸው በሕክምና ማረጋገጣቸውና ይህም በሽታ በዘር የመጣና እሳቸውን ጨምሮ ከሦስት እህታማቾች መካከል ሁለታቸው የጡት ካንሰር እንደያዛቸው ነው የተናገሩት፡፡

‹‹እኔ ዕድለኛ ሆኜ ባለሁበት አገር ጡቴን ተመርምሬ በሽታው ሥር ሳይሰድ ቶሎ ደርሼበታለሁ፡፡ ኬሞ ብዙም አላደረኩም፡፡ ግን ለአሥር ዓመት የሚወሰድ ሆርሞናሊ ትራፒ ጀምሬያለሁ፡፡ ይህንንም ሳደርግ አሁን ሦስተኛ ዓመቴ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በካንሰር የተያዘው አንደኛው ጡታቸው ብቻ ቢሆንም እሳቸው ግን ሁለቱንም ጡቶቻቸውን እንዳስወጡ ይህንንም ያደረጉበት ምክንያት የጡት ካንሰር ከኦቫሪ ጋር እንደሚገናኝ በማወቃቸው እንደሆነ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

በመገናኛ ብዙኃን በጡት ካንሰር ዙሪያ የሕይወታቸውን ተሞክሮ በስፋት በማካፈል፣ የካንሰር ሕመም ሊድን እንደሚችል በማስተማር ላይ የሚገኙት ሌላም ወይዘሮ ለተለያዩ ሕክምና ወደ ጤና ተቋማት ያዘወትሩ እንደነበር፣ ነገር ግን በእነዚህ ቀናት ሁሉ ምንም ዓይነት የጡት ካንሰር እንዳልተገኘባቸው ነገር ግን በ2011 ዓ.ም. የጡት ካንሰር ያለባቸው መሆኑን እንደተነገራቸው፣ ካንሰሩም ደረጃ ሦስት ላይ እንደነበር በዚህም የተነሳ ምንም ሕይወት እንደሌለ አድርገው ይቆጥሩ እንደነበር አስረድተዋል፡፡

እንስት ፫፡- ‹‹ካንሰር መጣ ማለት ሞት መጣ ማለት አይደለም፡፡ መዳን ይቻላል፤›› ያሉት ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ደግሞ ከደረጃ ሦስት የጡት ካንሰር እንደዳኑ፣ ለዚህም ተገቢውን የሕክምና ክትትል ማድረግ በእጅጉ አስፈላጊ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የጤና ሚኒስትሯ ማስገንዘቢያ፡-  ለአሥር ወራት ያህል ተገቢውን ሕክምናና ክትትል ሲያደርጉ እንደቆዩ፣ እንድናለሁ የሚል እምነትና ጽናትን ጨምሮ ከሕክምና ጋር በመታገዝ ከሞት ተርፈው ሌሎቹን ለማስተማር እንደበቁ አስረድተዋል፡፡

የጤና ሚኒስትር ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) ‹‹የዓለም ጤና መርጃዎች እንደሚያሳዩት የጡት ካንሰር በዋናነት ሴቶችን ነው በከፍተኛ ደረጃ የሚያጠቃውና የሚገድለው፡፡ ባደጉትም ሆነ ገና በማደግ ላይ በሚገኙት አገሮች ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ የሚፈጥር የካንሰር ዓይነት ነው፡፡ በየዓመቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ 2.1 ሚሊዮን ሴቶች በጡት ካንሰር እንደሚያዙ ያሳያል›› ብለዋል፡፡

ካሉትም የካንሰር ዓይነቶች መካከል ሴቶችን በመግደል የሞት መጠን ትልቁን ድርሻ የሚይዘው የጡት ካንሰር እንደሆነ፣ እ.ኤ.አ. በ2020 በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ684,000 በላይ ሴቶች በጡት ካንሰር ሕይወታቸውን እንዳጡ መረጃዎች ማሳየታቸውን ነው የተናገሩት፡፡

ባደጉት አገሮች በከፍተኛ ደረጃ የሚታወቅ ቢሆንም በሁሉም አገሮች ሥርጭቱ እየሰፋ የመጣ የካንሰር ዓይነት መሆኑን ገልጸው በአገራችንም የጡት ካንሰር እንደዚሁ በከፍተኛ ደረጃ ከሚገኙት የካንሰር ዓይነቶች አንዱ ሲሆን፣ በአጠቃላይ በአገሪቱ ከሚከሰቱ የካንሰር ዓይነቶች አንድ ሦስተኛውን የሚይዝ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ካለው የማኅበረሰቡ ግንዛቤ ማነስ አንፃርም የጤና ተቋማቱ በበቂ ሁኔታ አለመጠናከር ጋር ተያይዞ 65 በመቶ የሚሆኑት ታካሚዎች ወደ ጤና ተቋም የሚደርሱት ዘግይተው ወይም ደረጃ አራት ላይ ሲደርሱ ነው፡፡ ይህም ሁኔታ የሕክምናውን ውጤት አነስተኛ እንደሚያደርገውና የመኖር ዕድልን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚቀንስ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ ለጡት ካንሰር ተጋላጭ የሚያደርጉና ይበልጥ የሚታይባቸው የተለያዩ ሁኔታዎች እንዳሉ የጡት ካንሰር ሴቶችንም ወንዶችንም የሚያጠቃ ሲሆን፣ በዋናነት ግን የሚከሰተው በሴቶች ላይ እንደሆነና ዕድሜ እየጨመረ በሄደ ቁጥርም በካንሰር የመያዝ ዕድል እንደሚጨምርም አስረድተዋል፡፡

የዚህን ዓመትና ያለፈውን ዓመት ለየት የሚያደርገው በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ውስጥ መሆናችን ሲሆን፣ ይህም በአጠቃላይ ሕክምና ላይ የራሱን ተፅዕኖ መፍጠሩን፣ በዚህ ጊዜ ጤና ተቋማትን ለማጠናከር በጋራ መሥራት አስፈላጊ መሆኑንና ከዚህም በመነሳት በአሁኑ ሰዓት በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ 17 ሆስፒታሎች ውስጥ የካንሰር ሕክምና የሚሰጡ ሐኪሞችን በማሠልጠን ሕክምናውን ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

 የጨረር ሕክምናን በተመለከተ ግን እጥረት እንዳለ ይህንንም ለመለወጥ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አዲስ የጨረር ሕክምና መሣሪያ እንዲተከል፣ በተጨማሪም በሌሎቹ ስድስት የጤና ተቋማት ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተሠራባቸው የሚገኙ መሣሪያዎች እንዲገቡ የማድረግ ሥራ በሒደት ላይ መሆኑን ነው ያመለከቱት፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ብዝኃ ትምህርቱን ‹ስቴም› ለማስረፅ

ስሜነው ቀስቅስ (ዶ/ር) የስቴም (Stem) ፓውር ግብረ ሰናይ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተርና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የቴክኖሎጂ አማካሪ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የማስተርስና የፒኤችዲ...

‹‹እውነታውን ያማከለ የሥነ ተዋልዶ ጤና ግንዛቤን ማጠናከር ያስፈልጋል›› ደመቀ ደስታ (ዶ/ር)፣ በአይፓስ የኢትዮጵያ ተወካይ

በሥነ ተዋልዶ ጤና ጉዳዮች ላይ በመሥራት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሰው አይፓስ፣ የኢትዮጵያን ሕግ መሠረት አድርጎ በሴቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና ከጤና ሚኒስቴርና ከክልል ጤና ቢሮዎች...

የልጅነት ሕልም ዕውን ሲሆን

‹‹ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው›› የሚል በብዙዎች ዘንድ የሚዘወተር አባባል አለ፡፡ አባባሉ የተጎዳን ሰው ለመርዳት፣ የወደቁትን ለማንሳት፣ ያዘኑትን ለማፅናናት፣ ከገንዘብ ባሻገር ቅንነት፣ ፈቃደኝነት፣...