Tuesday, March 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየፌዴራል ፖሊስ ባልደረባ በከፈተው ተኩስ አንድ ሰው ገድሎ ዘጠኝ ማቁሰሉ ተጠቆመ

የፌዴራል ፖሊስ ባልደረባ በከፈተው ተኩስ አንድ ሰው ገድሎ ዘጠኝ ማቁሰሉ ተጠቆመ

ቀን:

በዮናስ አማረ

በአዲስ አበባ በተለምዶ ኮተቤ ብረታ ብረት ሲቪል ሰርቪስ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ አንድ የፌዴራል ፖሊስ ባልደረባ በከፈተው ተኩስ አንዲት ሴት ስትሞት፣ በሌሎች ዘጠኝ ሰዎች ላይ ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት ማድረሱ ተጠቆመ፡፡

እሑድ ጥቅምት 7 ቀን 2014 ዓ.ም. ምሽት በደረሰው በዚህ አደጋ በቡና ቤቶችና በመደብሮች ላይም ጉዳት መድረሱን፣ ሪፖርተር በቦታው ተገኝቶ ደረሰ የተባለውን ጉዳት ተመልክቷል፡፡

ፖሊስ በከፈተው ተኩስ ነፃነት አረጋ የተባለች የማህሌት ሆቴል አስተናጋጅ ወዲያውኑ ስትሞት፣ በአካባቢው ኅብረተሰብ በማግሥቱ የቀብር ሥርዓቷ መፈጸሙን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ጥቃት አድራሹ ተኩሱን በጀመረበት ማህሌት ሆቴል ውስጥ በወቅቱ እንደነበረች የተናገረችው ቢሊሴ ገመቹ፣ ጥቃት አድራሹ እዚያው ሆቴል ሲጠጣ እንዳመሸ ገልጻለች፡፡ ‹‹ቡና ቤቱ ውስጥ እኔም ነበርኩ፣ ብዙ ሰዎች እየጠጡ ነበር፡፡ ከፌዴራል ፖሊሱ ጋር ጓደኛዬ አብራው ነበረች፡፡ በድንገት ፎቶ አነሳሽኝ ብሎ በእርግጫ ከመታት በኋላ ሰድቦ አባረራት፡፡ ምን ተፈጠረ ብዬ ስጠይቃት ፎቶ አነሳችሁኝ ብሎ መማታቱን ስለነገረችኝ ሄጄ ፎቶ ያነሳው አለመኖሩን ነግሬ ይቅርታ ልጠይቀው ሞከርኩ፤›› ትላለች፡፡

‹‹እኔንም እየሰደበኝ ጭንቅላትሽን ሳልበትነው ዞር በይ ብሎ በቁጣ መለሰኝ፡፡ ደግሜ ይቀርታ ስጠይቀው እሷን ነው የምፈልገው አንቺ ዞር በይ አለኝ፡፡ ጓደኛዬን ነይ እንውጣ ብላትም እንቢ ስላለችኝ ተነስቼ ወደ ደጅ ወጣሁ፡፡ ጥቂት ቆይቼ ስመለስ ግን እሷ እሱ የተቀመጠበት መቀመጫ ላይ ተቀምጣ ነበር፡፡ ውስጥ ቁጭ ብዬ ሳለሁ ትንሽ ቆይቶ ወደ ውጭ ወጣ ብሎ ከተመለሰ በኋላ ሒሳቡን ከፍሎ ድጋሚ ሲወጣ ተመለከትኩ፡፡ ከፍሎ ከወጣ በኋላ በአሥር ደቂቃ ውስጥ አደጋው ደረሰ፤›› በማለት ቢሊሴ የተፈጠረውን አደጋ ከእነ መነሻው ተናግራለች፡፡

‹‹ሙሉ ትጥቁን ይዞ መጥቶ አስተናጋጅና ደንበኛ ሳይል በሁላችንም ላይ ጥይት ያዘንብብን ጀመር፤›› የምትለው ቢሊሴ፣ ከሦስት ቢራ በላይ ያልጠጣና ለቂም በቀል የሚያበቃ ግጭት የሌለው ሰው ለምን እንደዚያ እንዳደረገ ግራ መጋባቷን ታስረዳለች፡፡ ‹‹እሱ የተጣላት አስተናጋጅ ሥራ ከጀመረች ሦስት ቀኗ ነው፤›› የምትለው ቢሊሴ፣ ነገር ግን በእዚያ አደጋ ለሞት የበቃችው ለአሥር ዓመታት ያገለገለችው ነፃነት አረጋ የተባለች ጓደኛዋ መሆኗን በሐዘን ስሜት አስረድታለች፡፡

‹‹እኔና ጥቂት ሰዎች ጥግ ላይ ወዳለ መጋዘን ዘለን ገብተን ነፍሳችንን አተረፍን፡፡ ጓደኛችን የተመታችው ግን መጥፎ ቦታ ነበር፡፡ ደሟ ፈሶ እጄ ላይ ተዝለፈለፈች፡፡ ሆስፒታል ብትወሰድም በር ላይ ትንፋሿ አለቀ፡፡ ይህች ልጅ ማንነቷ አይታወቅም፣ ቤተሰቧ አልተገኘም፣ መታወቂያ የላትም፣ ከየት እንደመጣች አይታወቅም፡፡ የዚህ ሠፈር ሰው ደግነት ባይኖር ኖሮ አስከሬኗን በሥነ ሥርዓት ለመቅበር እንኳን ባልተቻለ ነበር፤›› ስትል ቢሊሴ ገልጻለች፡፡

‹‹በሌላ ጊዜ ሰዎች ሲጣሉና ጠርሙስ ኮሽ ሲል ሮጠው የሚመጡት ፌዴራል ፖሊሶች የዚያን ቀን ዝር አላሉም፡፡ ጓደኛችን ተገድላና የሰው ደም ፈሶ ምንም ያሉን ነገር የለም፡፡ ለልጅቷ ድንኳን ጥለን ለቅሶ እንዳንቀመጥ አድርገውናል፤›› ስትልም በአካባቢው በሠፈሩ ፌዴራሎች ላይ ያላትን ቅሬታም ተናግራለች፡፡

በወቅቱ ቀላልና ከባድ የመቁሰል አደጋ ገጥሟቸው በሕክምና ላይ የሚገኙ ተጎጂዎች እንደተናገሩት፣ ጉዳት አድራሹ የፌዴራል ፖሊስ ባልደረባ ደብረ ብርሃን ከተማ መያዙን ቢሰሙም፣ የፍትሕ ሒደቱንም ሆነ የሕክምናቸውን ጉዳይ በቅርበት የሚከታተል የመንግሥት አካል እንዳላናገራቸው በተለይ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ጣቶቹን ያቆሰሉ የጥይት እርሳሶችን በእጁ የያዘው ገብረ ወልድ አደራው የተባለ ተጎጂ፣ ‹‹አደጋው ሲከሰት ከወንድሜ ጋር ከሆቴሎቹ ጎን ያለውን ሱቃችንን እንጠብቅ ነበር፤›› ብሏል፡፡ ‹‹ተኩሱ ሲጀምር ምንድነው ብለን በድንጋጤ በሩን ዘጋነው፡፡ ጋብ ብሎ ድጋሚ ሲጀምር በሩን ከፈትኩት፡፡ አካባቢው በተኩስ እሩምታና በጥይት ብልጭታ የተሞላ ነበር፡፡ ወዲያው በሩን ዘጋንና ሱቁ ወለል ላይ ተኛን፡፡ በድንገት እጄን ነዘረኝ፡፡ ልክ እንደ ኤሌክትሪክ እጄን ሲነዝረኝ ተመትቻለሁ ብዬ ለወንድሜ ነገርኩት፡፡ ከፍተኛ ደም ይፈሰኝ ስለነበር ወዲያው እጄን በጨርቅ አሰርነው፤›› በማለት ገብረ ወልድ እንዴት አደጋው እንደደረሰበት አስረድቷል፡፡

‹‹ሰውየው ለረዥም ጊዜ መንደሩን በተኩስ ሲቆጣጠር የከተማው ፖሊሶች መጥተው እስኪያስቆሙት ድረስ ጓደኞቹ የፌዴራል አባላት ምንም አላደረጉም፡፡ እኛን ለማዳን ከግቢ የወጣው ወንድማችንን ደርሶበት ካስቆመውና እንዲተኛ ካዘዘው በኋላ፣ የጠብመንጃውን ቃታ ሲስብ ጥይት አለቀበት፡፡ አዲስ የጥይት ካርታ ለመቀየር ሲሞክር ነበር ወንድማችን ሮጦ አስፋልት ተሻግሮ ወደ ራሳቸው ካምፕ በመግባት ያመለጠው›› ሲልም ወንድሙ ከሞት የተረፈበትን አጋጣሚ ገብረ ወልድ ተናግሯል፡፡

‹‹ጣቶቼ ወደ መደበኛ ይዞታቸው የመመለስ ዕድላቸው 50 በመቶ መሆኑን ሐኪሞች ነግረውኛል፡፡ መጥቶ ያናገረኝ አካል የለም፣ ላሳክምህ ያለኝም አካል የለም፡፡ ይጠብቀኛል ብለህ በምታምነው ሰው በጥይት መደብደብ ሐዘኑ ከባድ ነው፤›› ሲልም ቅሬታውን አስረድቷል፡፡

አደጋ አድራሹን ፖሊስ በሰዓቱ መተኮሱን እንዲያቆም ሲጠይቀው እንደነበር የተናገረው ቢንያም ታደሰ በበኩሉ፣ በማያውቀው ምክንያት ወደ እሱ አለመተኮሱን ተናግሯል፡፡ ተኳሹን ተጠግቶ ለማናገርና ጥቃቱን እንዲያቆም ለመጠየቅ እንዴት እንደደፈረ ለቀረበለት ጥያቄ በሰጠው ምላሽ፣ ‹‹እኔም የቀድሞ ወታደር ነኝ፡፡ በቅርቡ የክተት ጥሪ ሲደረግ በድጋሚ ዘምቼ ከሰሞኑ ነው ከወሎ ግንባር የተመለስኩት፡፡ አደጋው ከጠላት ጋር የሚደረግ ውጊያ መስሎኝ ልረዳው ነበር የወጣሁትና ቀርቤ ችግሩን እንዲያስረዳኝ የጠየኩት፤›› በማለት ቢንያም የነበረውን ሁኔታ አስረድቷል፡፡

ተኳሹ ከማህሌት ሆቴል ጥቃቱን መጀመሩንና መደዳውን ባሉ ሆቴሎችና ሱቆች ላይ ሲተኩስ ለአንድ ሰዓት መቆየቱን ቢንያም መስክሯል፡፡ ‹‹የተኩስ ድምፅ በአካባቢው ሲቀልጥ እኔ ከነበርኩበት ሦስተኛ ቤት ወደ ውጭ ወጣሁ፤›› የሚለው ቢንያም፣ ‹‹ተኳሹ በርቀት የማውቀው ‘ዳኛቸው ወርቁ’ የተባለ የፌዴራል ፖሊስ ባልደረባ መሆኑን አረጋገጥኩ፤›› ይላል፡፡ ‹‹አጠገቡ ሄጄ ለምን እንደሚተኩስ ችግሩን ጠየቅኩት፡፡ ነገር ግን በሠፈር ስሜ ‘አፋሩ’ ብሎ ጠርቶ፣ እኔ ተስፋ ቆርጫለሁ አንተም ተስፋ ቁረጥ በማለት ሌላ ምላሽ ሳይሰጠኝ ተኩሱን ቀጠለ፤›› ይላል የነበረውን ድንገተኛ ክስተት ሲያስረዳ፡፡

‹‹እኔ አጠገብ ሆኖ ካርታ ሲቀይር ዓይቻለሁ፡፡ በኋላ ላይ ከደረሱ ፖሊሶች ጋር ፈልገን ሦስት ካርታ አግኝተናል፡፡ ይህን ሁሉ ጥይት መደዳውን ባሉ ቤቶች ላይ ሲያርከፈክፍ፣ ሰዎች ሲያቆስልና ሲገድል ለአንድ ሰዓት ያህል ማንም አልደረሰልንም፤›› በማለት ቢንያም የአደጋውን ሁኔታ ገልጾታል፡፡ ‹‹አስፋልት ተሻግሮ ካምፕ ያላቸው የፌዴራል ፖሊሶች የጥይቱን ጩኸት ሲሰሙ ምላሽ አለመስጠታቸው ይገርማል፡፡ ቢያንስ ወደ ሰማይ እንኳ ቢተኩሱ አደጋ አድራሹን አስደንግጠው ያስቆሙት ነበር፤›› ብሏል የቀድሞ ወታደር ቢንያም፡፡ ‹‹በስተመጨረሻ በአካባቢው የደረሱት የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊሶች የተኩስ ምላሽ ሲሰጡት ነው ሮጦ ወደ ካምፕ የገባውና ያመለጠው፤›› ሲልም አደጋ አድራሹ ከአካባቢው የተሰወረበትን ሁኔታ ተናግሯል፡፡

ሪፖርተር ያናገራቸው በምኒልክ ሆስፒታል ተኝተው ሕክምና ከሚደረግላቸው መካከል አንዱ ዳዊት ኑር በበኩሉ ሦስት ቦታ በጥይት መመታቱን ተናግሯል፡፡ በሰዓቱ ማህሌት ሆቴል ውስጥ ይዝናኑ ከነበሩ ደንበኞች አንዱ እንደነበር የተናገረው ዳዊት፣ ‹‹እግሬን፣ እጄንና ሆዴን ሦስት ጊዜ ተመትቻለሁ›› ሲል ጉዳት የደረሰበትን አካል በማሳየት ተናግሯል፡፡ ‹‹ማህሌት ቡና ቤት ውስጥ የእሩምታ ተኩስ ሲከፈት ወደ ውጭ ለመውጣት ስሞክር ጥይት ተቀበለኝና ወደቅኩኝ፡፡ ከዚያ በኋላ ራሴን ስለሳትኩ ምን እንደሆነ አላውቅም፤›› በማለት ያጋጠመውን አደጋ ገልጿል፡፡ ‹‹ምኒልክ ሆስፒታል በግል እየታከምኩ ሲሆን፣ ትናንት ፖሊሶች መጥተው ቤተሰብ አናግረዋል፡፡ እኔ ተኝቼ ስለነበር ምን እንዳሉ አላውቅም፤›› በማለት አሁን በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ አስረድቷል፡፡

በምኒልክ ሆስፒታል ሕክምና የምትከታተል ሌላኛዋ ተጎጂ ሴና ሰለሞን በበኩሏ፣ አደጋው ዱብ ዕዳ እንደሆነባት ገልጻለች፡፡ ‹‹በጊዜው በሆቴሉ ውስጥ በሥራ ላይ ነበርኩ፡፡ ተኩስ ብቻ ነው የሰማሁት፡፡ ዕቃ ለመመለስ ወደ ውስጥ ስገባ ጥይት እግሬን አገኘኝ፡፡ ተኩስ ለረጅም ጊዜ ስለነበር እጅግ ያስፈራል ጩኸቱ፡፡ አተኳኮሱ ለአንድ ሰው የመጣ አይመስልም ነበር፡፡ ወደ ሁሉም ሰው ነበር የተተኮሰው፤›› ስትል የተፈጠረውን ሁኔታ አስረድታለች፡፡

“የሞተችዋ ጓደኛዬ ናት፤” የምትለው ሴና ‹‹ከተመታሁ በኋላ ለብዙ ደቂቃዎች ወድቄ ራሴን ስቼ ስለነበር ሰዎች ናቸው ወደዚህ ያመጡኝ፤›› ትላለች፡፡ ‹‹ማስታገሻ እየሰጡኝ ነው፡፡ አልትራሳውንድ እንደምነሳ ነግረውኛል፡፡ ፖሊሶች መጥተው ጠይቀውኛል፡፡ በተረፈ ግን የሠፈር ሰውና ጓደኞቼ ናቸው ያገኙትን እያመጡ እያሳከሙኝ ያሉት፡፡ ማንም የቅርብ ዘመድ የምለው ሌላ ሰው ከጎኔ የለም፤›› በማለት አደጋው ያደረሰባትን ጉዳትና የምትገኝበትን ሁኔታ ተናግራለች፡፡ 

በአደጋው አካባቢ የሚገኙ ቤቶችን፣ ሆቴሎችንና ሱቆችን ለመመልከት እንደተቻለው በበርካታ ጥይቶች ተበሳስተዋል፡፡ በአካባቢው ያሉ ቤቶች አንዱ ከሌላው ሳይለዩ መደዳውን እንደ ተተኮሰባቸው የጥይት አረሮቹ የፈጠሩትን ቀዳዳ በመመልከት ማረጋገጥ ተችሏል፡፡

ጉዳት አድርሶ ከተሰወረ በኋላ ደብረብርሃን ከተማ ላይ ተይዟል ስለተባለው ተጠርጣሪ የምርመራ ሒደትን በሚመለከት ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ለማግኘት ሪፖርተር ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...