Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት በመውሰድ ሕይወትን ማትረፍ እየተቻለ በተሳሳቱ መረጃዎች መጎዳት አይገባም›› ሚኪያስ ተፈራ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኮቪድ-19 ድንገተኛ አደጋ ማስተባበሪያ ቢሮ ምክትል ኃላፊ

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መላውን ዓለም እያተራመሰ፣ ሰዎችን ለጤና መታወክና ለሕልፈት ሕይወት እየዳረገና የሥርጭት አድማሱን እያሰፋ ነው፡፡ ወረርሽኙ የመጀመርያውንና ሁለተኛውን ወጀብ አጠናቅቆ ሦስተኛው ወጀብ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ዓይነቱ ወጀብ ከሌሎቹ ለየት የሚያደርገው ‹‹ዴልታ›› የተባለውን አዲስ የቫይረስ ዝርያ መፍጠሩ ወይም ማስከተሉ ነው፡፡ የዴልታ ቫይረስ ዝርያ በሰው ሕይወት ላይ የሚያስከትለው ጥፋት ወይም ዕልቂት በእጅጉ የከፋ ነው፡፡ ይህ ዝርያ  በኢትዮጵያ ከታየ ውሎ አድሯል፡፡ በአጠቃላይ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝና ከዴልታ ዝርያ ጋር በተገናኘ ታደሰ ገብረ ማርያም ከኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኮቪድ-19 ድንገተኛ አደጋ ማስተባበሪያ ቢሮ ኃላፊ ሚኪያስ ተፈሪ (ዶ/ር) ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡- ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተከሰተ ሁለት ዓመት ሊሞላው እየተቃረበ ሲሆን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የሞት መጠኑ እየጨመረ ነው፡፡ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ይታወቃል?

ዶ/ር ሚኪያስ፡- ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ኢትዮጵያ ውስጥ ከገባ ሁለት ዓመታት ገደማ ሊሆነው ነው፡፡ በወረርሽኙ ምክንያት ከዚህ በፊትም ብዙ የምንወዳቸውን ወገኖቻችንን አጥተናል፡፡ የአሁኑ መጠን ግን በተለየ ሁኔታ ማሻቀቡ ይታያል፡፡ ይህ የሆነበት አንደኛው ምክንያት የቫይረሱ ዝርያ የተለየ በመሆኑ ነው፡፡ ይህም በቅርቡ በተሰጡ መግለጫዎች በተደጋጋሚ ተነግሯል፡፡ ዴልታ የሚባለው የኮቪድ-19 ቫይረስ ዝርያ በአገራችን ከተከሰ ወዲህ የፅኑ ሕሙማን ክፍሎች ብዛት ያላቸውን ታካሚዎች እያስተናገዱ ነው ያሉት፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ባለፉት ሁለት ዙር ወጀቦች በቀን ከተከሰተው ሞት ይልቅ በአሁኑ ወጀብ በብዛት ተከስቷል፡፡ ይህም የሚያሳየው ነገር ቢኖር ዴልታ ከተባለው ዝርያ ጋር ተያይዞ የመጣ የሞት ብዛት ከፍተኛ መሆኑንና ወደ ፅኑ ሕሙማን ክፍል የሚገቡ ታካሚዎች ቁጥር እያሻቀበ መምጣቱን ነው፡፡   

ሪፖርተር፡- ዴልታ የተባለው ዝርያ መነሻው ከየት እንደሆነ ይታወቃል? በኢትዮጵያስ ዝርያውን የመለየት ሥራ ተከናውኗል ወይ?

ዶ/ር ሚኪያስ፡- የተለያዩ ዝርያዎች በተለያዩ አገሮች ይከሰታሉ፣ ወይም ይታያሉ፡፡ እነዚህ የተለያዩ ዝርያዎች እንደሚያስከትሉ ጉዳት እንዳላቸው፣ የሥርጭትና የሞት መጠን፣ እንዲሁም ሰዎችን ለፅኑ ሕመም ከመዳረጋቸው አኳያ ሲታይ የተለያየ ደረጃ አላቸው፡፡ ወይም ደረጃ ይሰጣቸዋል፡፡ እንደ ዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት ከሆነ ዴልታ የተከሰተው ህንድ ውስጥ ነው፡፡ ለብዙ ሰዎች ሞት ምክንያት ሆኖ በመገኘቱ ክትትል ሲደረግበት ቆይቷል፡፡ አሁን በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ተሠራጭቷል፡፡ በአገራችንም በቅርቡ የቫይረሱን ዝርያ የመለየት ሥራ መከናወኑ ይታወቃል፡፡ በሦስተኛው ወጀብ ከተያዙት ሰዎች አብዛኞቹ ዴልታ በሚባለው ዝርያ ምክንያት መሆኑ ተደርሶበታል፡፡

ሪፖርተር፡- ኮቪድ-19 ቫይረስን ለመከላከል የሚያስችል መመርያ ቀደም ሲል ወጥቷል፡፡ አሁን ደግሞ መመርያው ተሻሽሏል፡፡ ነገር ግን ተፈጻሚነቱ ላይ ክፍተት ይታይበታል፡፡ በዚህ ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድነው?

ዶ/ር ሚኪያስ፡- የመጀመርው መመርያ ቁጥር 30/2013 ይባላል፡፡ በመመርያው በተቀመጠው መሠረት የተከናወኑ ሥራዎች በየጊዜው ይዳሰሳሉ፡፡ አሁን ግን የመጀመርያውን መመርያ ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ መመርያ 803/2013  ወጥቷል፡፡ መመርያው የሚያሳው ነገር ቢኖር በአገር አቀፍና በክልል ደረጃ ራሱን የቻለ አስፈጻሚ አካል ወይም ግብረ ኃይል አለው፡፡ ግብረ ኃይሉ የማስፈጸምና የማስገደድ ኃላፊነት እንዳለውና ይህም የሚመራውም በየደረጃው ባሉ ከፍተኛ ኃላፊዎች ነው፡፡ ይህም ሆኖ የተለያዩ ዘርፎች አካላት በግብረ ኃይሉ ውስጥ የሥራ ድርሻ አላቸው፡፡ በዚህም ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ከዘርፎቹ አካላት መካከል የሕግ አስፈጻሚና የጤናው ዘርፎች ይገኙበታል፡፡ መመርያውን ተግባራዊ ለማድረግ ከሚረዱ መንገዶች መካከል አንደኛው ይኼው አወቃቀር ነው፡፡ ሌላው ደግሞ መመርያውን ለሚመለከታቸው ክፍሎች ማስተዋወቅ ነው፡፡ ክፍሎቹም በዚያው መሠረት ክትትል ያደርጋሉ፡፡ ለዚህም ዕውን መሆንና ምቹ ሁኔታ የመፍጠር ጉዳይ በጤና ሚኒስቴርና በኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በኩል እየተሠራ ነው፡፡ ለማስተዋወቁም የሚረዱ መድረኮች እንደተዘጋጁና ውይይትም እንደተካሄደ ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህም ሌላ በየሳምንቱ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫዎች እየተሰጡ ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- የመጀመርያውን መመርያ ቁጥር 30/2013 ማሻሻል ለምን አስፈለገ?

ዶ/ር ሚኪያስ፡- ኅብረተሰቡን የማስተማሩ ሥራ በተለያዩ መንገዶች በተጠናከረ መልክ እየተከናወነ መሆኑን መዘንጋት የለበትም፡፡ የመጀመርያው ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሲከሰት ቫይረሱ የተገኘበት ሰው ሲነገር የነበረው የኅብረተሰበ መደናገጥ፣ የመከላከያ መንገዶች ትግበራ ሲታይ ከፍተኛ የሚባል ነበር፡፡ በመካከሉ መዘናጋቶችና መቀዛቀዞች መታየት ጀመሩ፡፡ በዚህም የተነሳ መጀመርያ ላይ የታየው ጥንቃቄ አሁንም በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀጥል ለማድረግ ብቸኛው መንገድ የተሻሻለ መመርያ ማውጣት ሆነ፡፡ በተሻሻለው መመርያ ውስጥ የተካተቱና ኃላፊነት የተሰጣቸው ባለድርሻ አካላትም፣ በየደረጃው የሚፈለጉ ትግበራዎችን መከታተልና ማስፈጸም አንዱ የሥራ ድርሻቸው ሆኖ በውል ተለይቶ እንዲቀመጥ ተደርጓል፡፡   

ሪፖርተር፡- በመመርያው የተቀመጡ የመከላከያ መንገዶች ትግበራ ላይ ክፍተት ይታያል እየተባለ ነው፡፡ ይህ ክፍተት ለምን ተፈጠረ?

ዶ/ር ሚኪያስ፡- የተሻሻለው መመርያ የወጣው አንደኛ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በማየትና የበሽታውን አስከፊነት ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡ ይህም ቢሆን ግን የመከላከያ መንገዶች ትግበራ ላይ ክፍተት መስተዋሉ አይካድም፡፡ ይህ የሆነባቸው በርካታ ምክንያቶችን ማንሳት ይቻላል፡፡ ከምክንያቶቹም መካከል አንደኛው በመመርያው የታቀፉ ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን በትክክል አለመወጣት ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ለትራንስፖርት ዘርፍ የወጡ ቅጣቶች መነሳትና መጫን ከሚገባቸው ግማሽ ያህሉን ብቻ እየጫኑ እንዲያሽከረክሩ መደረጉ መቅረቱ፣ ማስክ ማድረግ እየተዘነጋ መምጣቱ ለመከላከያ መንገዶች ትግበራ ክፍተት መፍጠር መንስዔ ሆነዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በአገር ውስጥ በሰው ሠራሽና በተለያዩ ምክንያቶች ከቀዬአቸው ተፈናቅለው በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖችን ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመታደግ ምን እየተሠራ ነው?

ዶ/ር ሚኪያስ፡- በአገር ውስጥ የተፈናቀሉ ወገኖችን ከወርሽኙ ለመጠበቅ ሲባል ከዚህ በፊት ያልነበረ ራሱን የቻለ አንድ ክፍል ተቋቁሟል፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ ቅድሚያ ሰጥቶት እየተሠራ ካለው መካከል ተፈናቃዮች ቶሎ ምርመራ እንዲያገኙ ማድረግ ነው፡፡ ለዚህም ፈጣን የላቦራቶሪ ምርመራና ክትባት ተፈናቃዮች ባሉባቸው አካባቢዎች ማቅረብም ይገኝበታል፡፡  

ሪፖርተር፡- የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል ከሚያስችሉ ጥንቃቄዎች መካከል አንዱና ዋነኛው ክትባት ነው፡፡ ሰዎች ግንዛቤ ያስፈልጋቸዋልና የክትባቱን ጠቃሚነት አጠር አድርገው ቢያብራሩልን?

ዶ/ር ሚኪያስ፡- ክትባት በየጤና ተቋማት ለኅብረተሰቡ እየተሰጠ ነው፡፡ ክትባት መውሰድ በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡ አብዛኞቹ የአውሮፓ አገሮች በኮቪድ-19 ምክንያት ጥለዋቸው የነበሩት ገደቦችን እያነሱ ነው፡፡ በየስታዲዮሞቻቸው በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ደጋፊዎች በአንድነት ተፋፍገው ውድድሩን ሲመለከቱ እናያለን፡፡ ይህ ሁሉ ሊሆን የቻለው ኅብረተሰቡ ተገቢውን ክትባት በመውሰዱ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ከኢትዮጵያ ሁኔታ አንፃር ሲታይ ሦስት ዓይነት ክትባቶች እንዳሉ ነው፡፡ እነርሱም ‹‹አስትራዜኒካ››፣ ‹‹ሲኖፋርም›› እና ‹‹ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን›› ይባላሉ፡፡ እስካሁን 3.9 ሚሊዮን ዶዝ ክትባት ነው ለኅብረተሰቡ የተሰጠው፡፡ ከዚህ አኳያ ያልተከተበ ማንም ሰው በየአቅራቢያው በሚገኘው ጤና ተቋም እየቀረበ መከተብ ይኖርበታል፡፡ ክትባት መውሰድ በወረርሽኝ ላለመያዝ ይረዳል፡፡ ከተያዘም ወደ ፅኑ ሕሙማን ክፍል የመሄድ መጠንን በብዛት ይቀንሳል፡፡      

ሪፖርተር፡- ክትባቱ በኅብረተሰቡ ዘንድ ምን ያህል ተቀይባነት አለው?

ዶ/ር ሚኪያስ፡- እዚህ ላይ ሁለት ነገሮች መታየት አለባቸው፡፡ አንደኛው ክትባቱን ለማዳረስ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ነው፡፡ ከፍ ያለ የክትባት መጠን ወደ አገራችን እንዲገባ ለማድረግ ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ እስካሁን የገቡ ብዙ ክትባቶች እንዳሉ እንረዳለን፡፡ እነዚህንም ክትባቶች ኅብረተሰባችን ተቀብሎ እንዲከተብ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ የመጀመርያው ክትባት በቅድሚያ ለጤና ባለሙያዎች፣ እንዲሁም ዕድሜያቸው ከ55 ዓመት በላይ የሆኑና ተጓዳኝ በሽታ ላለባቸው ብቻ የሚሰጥ ነበር፡፡ በዚህም በርካታ ማኅበረሰቦች በየጤና ተቋማቱ እየቀረቡ ተከትበዋል፡፡ ቀጥሎ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆኑ ማኅበረሰቦች በየአቅራቢያቸው በሚገኝ ጤና ተቋማት እየቀረቡ እንዲከተቡ ጥሪ ቀርቧል፡፡ በዚህም የክትባት እጥረት አላጋጠመም፡፡ በየጊዜው ከአጋር ድርጅቶች በጤና ሚኒስቴር በኩል ክትባቶች ወደ አገር ውስጥ እየገቡ ነው፡፡ አሁን በከፍተኛ ደረጃ አስቸጋሪ ሆኖ የተገኘው ለመከተብ ያለው ፈቃደኝነት ዝቅተኛ መሆኑ ነው፡፡ እስካሁን የተከተበው ማኅበረሰብ ሦስት በመቶ ብቻ  ነው፡፡ ይህ ምን ያህል አነስተኛ እንደሆነ ያሳያል፡፡

ሪፖርተር፡- ክትባቱን አስመልክቶ የተጋረጠውን እንቅፋት ወይም ሥጋት እንዴት ነው የሚገልጹት?

ዶ/ር ሚኪያስ፡- ክትባቱን በተመለከተ አሁንም ፈተናዎች እየገጠሙን ነው፡፡ አንደኛ ሰዎች ወደ አቅራቢያቸው ጤና ተቋም እየቀረቡ ክትባቱን መውሰድ አለመፈለጋቸው ነው፡፡ ሁለተኛው ተግዳሮት ደግሞ ክትባቱን አስመልክቶ ምንም ማስረጃና መጨበጫ ያልተገኘላቸው የተሳሳቱ መረጃዎችን ማሠራጨት ነው፡፡ ከእንዲህ ዓይነት መረጃዎች መካከል ‹‹ኮቪድ የለም፣ መከተቡ የደም መርጋትን ያስከትላል፣ ወዘተ›› የሚሉ የተሳሳቱ መረጃዎች በግንባር ቀደምነት ይሰማሉ፡፡ ሕፃን ልጅ ሚዝል ሲከተብ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ትንሽ የትኩሳት ስሜት ሊኖር ይችላል፡፡ ይህም ማንኛውም ክትባት ላይ ሊከሰት ይችላል፡፡ አንድ ሰው በኮቪድ-19 ቢያዝ የደም መርጋት ሊያጋጥመው ይችላል፡፡ በክትባት ሳቢያ ግን የሚመጣ ችግር የለም፡፡ በዓለም አምስት ቢሊዮን ሕዝብ ቢከተብም እኛ በተቃራኒ ክትባቱን እየወሰድን አይደለም፡፡ ኮቪድ-19 የለም የሚሉ ሰዎች ደግሞ ሚሊኒየም የኮቪድ-19 ሕክምና ማዕከል ገብተው ቢያዩ ጉድ ይላሉ፡፡ የጤና ባለሙያዎች ከጭንቅላታቸው እስከ መጫሚያቸው ድረስ ከባድ የመከላከያ አልባሳት አድርገውና የሚያስከትለውንም ኃይለኛ ሙቀት ችለው አገልግሎት ሲሰጡ መመልከትና የታካሚዎችን ጭንቀት መረዳት፣ ኮቪድ-19 ገዳይ ብቻ ሳይሆን ምን ያህል ዘግናኝ እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት በመውሰድ ሕይወትን ማትረፍ እየተቻለ በተሳሳቱ መረጃዎች መጎዳት አይገባም፡፡  

ሪፖርተር፡- የባህል መድኃኒትን ከክትባቱ ጋር አያይዞ ለመጠቀም የታሰበው በምን ደረጃ ላይ ነው ያለው?

ዶ/ር ሚኪያስ፡- አንድ መድኃኒት ሲመረት ራሱን የቻለ ክሊኒካል ሙከራዎች አሉ፡፡ እዚህን ሙከራዎች ከታለፉና የመጨረሻው ውጤቱ ይፋ ከተደረገ በኋላ ነው ወደ ትግበራ የሚገባው፡፡ ከዚህ አኳያ ለኮቪድ-19 መከላከያ ይውላል የተባለው የባህል መድኃኒት በኢንስቲትዩቱ ባለሙያዎች እየተጠና መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ የውጤቱ መጨረሻ ከታወቀ በኃላ ይፋ ይሆናል፡፡ ይህ ገና ጥናት ላይ ያለ ስለሆነ አሁን መነካካቱ አይጠቅምም፡፡  

ሪፖርተር፡- በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተይዘው ፅኑ ሕሙማን ክፍል ገብቶ ድኖ የመውጣት ተስፋ እየታየ ነው? ወይስ ተስፋ አስቆራጭ ነው?

ዶ/ር ሚኪያስ፡- የሦስተኛውን ወጀብ ትንሽ ለየት የሚያደርገው ከፍተኛ የፅኑ ሕሙማን ቁጥር መኖሩ ነው፡፡ በሁለተኛ ወጀብ ጊዜ በአንድ ቀን ወደ 120 ፅኑ ታካሚዎች ነበሩ፡፡ አሁን እስከ 145 ድረስ የሚጠጉ ሰዎች ፅኑ ሕሙማን ክፍል ገብተው አገልግሎት አግኝተዋል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ሁለተኛው ወጅብ ላይ ትንሽ አጋጥሞን የነበረው የኦክስጅን አቅርቦት ላይ የታየው እጥረት ነበር፡፡ አሁን ግን ይህ እጥረት እስካሁን ባለው በሦስተኛ ወጀብ አላጋጠመንም፡፡ ከዚህ በኋላ እንግዲህ የፅኑ ሕሙማን ቁጥር እየጨመረ ሊሄድ ይችላል፡፡ ከዚህ በፊት የነበሩ ክፍቶችን በመሸፈንና አሠራሮችን በማጠናከር አዳዲስ የኦክስጅን ማምረቻዎች በማቋቋም ችግሩን ለመወጣት ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ በየቀኑ በርካታ ሕሙማንን የሚያስተኛው ሚሊኒየም ሆስፒታል በሁለተኛው ወጀብ ወቅት በሰዓት 50 ኪዩቢክ ሜትር ኦክስጅን ማምረት የሚችል ፕላንት ነበረው፡፡ አሁን ግን በሰዓት 100 ኪዩቢክ ሜትር ኦክስጅን ማምረት የሚችሉ ሁለት የኦክስጅን ፕላንቶች ተገጥመውለት ቀጥታ ለታካሚዎች እንዲደርስ ተደርጓል፡፡ በተመሳሳይ ሌሎች የግል ጤና ተቋማትም ኦክስጅን ወደ ማምረት እየገቡ ነው፡፡     

ሪፖርተር፡- በኮቪድ-19 ወረርሽኝ መያዝና መሞት በየትኛው የኅብረተሰብ ክፍል ላይ ነው ጎልቶ የሚታየው?

ዶ/ር ሚኪያስ፡- በየቀኑ በምናያቸው መረጃዎች ምን ያህል ሰዎች እንደተጠቁ፣ በየትኛው የዕድሜ ክልል ላይ ያሉትን ነው ወረርሽኙ እያጠቃ ያለው? ለሞት የሚዳረጉትስ በየትኛው የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉት ናቸው? የሚለውን በየቀኑ ነው የምንከታተለው፡፡ በየሳምነቱ በምንሰጣቸው መግለጫዎችም ጎላ አድርገን እናቀርባቸዋለን፡፡ ከዚህ አኳያ ወረርሽኙ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ አብዛኛው በበሽታ ከፍ ያለ የመያዝ ምጣኔ የሚያሳየው ከ15 እስከ 34 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ ባሉ ወጣቶች ላይ ነው፡፡ የሞት ምጣኔው ሲታይ ደግሞ ዕድሜያቸው ከ55 ዓመት በላይ በሆኑ ሰዎች ላይ ነው፡፡ ነገር ግን በየጊዜው የነበሩትን ወጀቦች ስናይ ለምሳሌ በሦስተኛው ወጀብ ላይ ለየት ያለው ነገር በበሽታው የመያዝ ምጣኔ በሁሉም የዕድሜ ክልል ላይ ያረፈ ነው፡፡ በአጠቃላይ የሞት ምጣኔው ወይም ከፍተኛ የሞት መጠን ያስመዘገበው ሦስተኛው ወጀብ ነው፡፡ የዕድሜ ጣሪያውም በሚታይበት ጊዜ በወጣቶች ላይ ሞት በዛ ብሏል፡፡  

ሪፖርተር፡- የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ኢትዮጵያ ውስጥ ከገባበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ ምን ያህል ሰዎች ሞተዋል? ይህ ችግር ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጋር ሲነፃፀር እንዴት ይታያል?

ዶ/ር ሚኪያስ፡- ወረርሽኙ ከተከሰተበት ዕለት ጀምሮ እስከ አሁኗ ሰዓት ድረሰ በኮቪድ የሞቱ ወገኖችን ብዛት ከ6,000 በላይ ነው፡፡ ይህም ከአፍሪካ አምስተኛ ሲያደርገን፣ በቫይረሱ የተያዙ ወገኖችን ስናነፃፅር ደግሞ አራተኛ ነን፡፡ በኮቪድ የተያዙ ወገኖች ቁጥር እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አይደለም፡፡ በአገራችን በቅርቡ የተካሄዱት የአደባባይ በዓላት ለቫይረሱ አጋላጭ መሆናቸው መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ወረርሽኙ ለመጀመርያ ጊዜ እንደተከሰተ በቀን አንድ ሰው ብቻ መሞቱ ነው ሪፖርት የተደረው፡፡  አሁን ግን ወደ 40 አሻቅቧል፡፡ ይህም ሊያሳስበን ይገባል፡፡ ቁጥሩን ብቻ አይደለም ማየት ያለብን፡፡ የምንወዳቸውና የምንሳሳላቸውን ወገኖችንን ማጣታችንን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ በየቀኑ የሚሰጡት መረጃዎችም ቁጥሮች አይደሉም፣ ሰዎች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመርያ ጊዜ በኮቪድ-19 የተያዘ ሰው መገኘቱ ሲሰማ ከተማው በአንድ ጊዜ ነው ፀጥ እረጭ ያለው፡፡

ይህ ዓይነቱ አስፈሪ ድባብ የተከሰተው በሕግ አስገዳጅነት ሳይሆን፣ ውስጣችን በጭንቀት በመሞላቱና ለራሳችን ብለን ነው፡፡ ለረዥም ጊዜ ቤት ውስጥ መቀመጥ ይቻላል፡፡ ነገር ግን አስገዳጅ የሆኑ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ሊያጋጥሙን ይችላሉ፡፡ እነዚህን ችግሮች ማጣጣም ያስፈልጋል፡፡ የመከላከያ መተግበሪያ መንገዶች በእጃችን ነው ያሉት፡፡ ዋጋ አያስከፍሉም፡፡ እነሱም አላስፈላጊ ከሆኑ እንቅስቃሴዎች ራሳችንን መገደብ፣ አላስፈላጊ የሆኑ ስብሰባዎች ላይ አለመገኘት፣ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ፣ እጅን በሳሙና ደረጃውን በጠበቀ መንገድ መታጠብ ከመተግበሪያ መንገዶች መካከል ተጠቃሾች ናቸው፡፡  

ሪፖርተር፡- የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሰውን ለበሽታና ለሞት መዳረጉ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የጤናውን ዘርፍ እንዲጠናከር አድርጎታል ለማለት ይቻላል?

ዶ/ር ሚኪያስ፡- አዎን! እንዲያጠናከር አድርጎታል፡፡ ለምሳሌ ያህል የፅኑ ሕሙማን አገልግሎት መስጠት በጣም አስቸጋሪ ነበር፡፡ ኮቪድ-19 ከተከሰተ ወዲህ ግን አገልግሎቱን የማጠናከር ሥራ ተከናውኗል፡፡ ትልቁንና ሚሊኒየም የኮቪድ ሕክምና ማዕከልን ለማቋቋም ችለናል፡፡ የላቦራቶሪ ምርመራ ደቡብ አፍሪካ እየላክን ነበር የምናሠራው፡፡ አሁን ግን እዚሁ በአገራችን እንዲሠራ አድርገናል፡፡ ከዚህም አልፎ ተርፎ የቫይረሱን ዝርያ ለመለየት አስችሎናል፡፡ ይህ እንግዲህ በአዲስ አበባ ብቻ ያለውን ነው ያየነው እንጂ፣ በየክልሉም የተከናወኑ የማጠናከሪያ ሥራዎች መከናወናቸው ልብ ሊባል ይገባል፡፡ ይህም ሆኖ ግን መታየት ያለበት እንደ መልካም አጋጣሚ ሳይሆን፣ ወረርሽኙን በመከላከል ሒደት ውስጥ የተለያዩ የጤና ተቋማት ተገቢውን ድጋፍ ማግኘታቸውን ነው፡፡  እስከሁንም ከወረርሽኙ እንዳልወጣን መረዳት ያስፈልጋል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የግብርናና የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ሻሸመኔ ከተማ ማደጋቸውንና መማራቸውን፣ በአግሮ ሜካኒክስ በዲፕሎማ...

‹‹የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ሥራቸውን በነፃነት ሳይፈሩና ሳይሸማቀቁ እንዲያከናውኑ ዋስትና የሚሰጣቸው ሕግ የለም›› አቶ አመሐ መኮንን፣ የሕግ ባለሙያና የመብት ተሟጋች

ለበርካታ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች በፍርድ ቤት በመሟገት የሚታወቁት የሕግ ባለሙያ፣ ጠበቃና የመብት ተሟጋቹ አቶ አመሐ መኮንን የፈረንሣይና  የጀርመን መንግሥታት በጋራ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር የላቀ...

‹‹የአጎራባች ክልሎች የሰላም ዕጦት በእኛ ላይ ሸክምና ጫና ፈጥሮብናል›› ከአቶ ባበከር ሀሊፋ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የግብርና ቢሮ ኃላፊ

አቶ ባበከር ሀሊፋ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ወንዶ ገነት ኮሌጅ በፎረስትሪ ሠርተዋል። ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተምረው አጠናቀዋል። ከ2002 ዓ.ም. እስከ 2003 ዓ.ም....