Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየመማር ማስተማሩና የኮቪድ-19 መከላከል ሥራዎች እንዲቀናጁ ጥሪ ቀረበ

የመማር ማስተማሩና የኮቪድ-19 መከላከል ሥራዎች እንዲቀናጁ ጥሪ ቀረበ

ቀን:

  • በኮቪድ-19 የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከስድስት ሺሕ በላይ ሆኗል

በኮቪድ-19 ወረርሽኝና በክረምቱ ወራት ምክንያት ለወራት ተዘግተው የቆዩ ትምህርት ቤቶች፣ ከጥቅምት 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ተከፍተው የመማር ማስተማሩን ሥራ በማከናወን ላይ ናቸው፡፡ ይህ ዓይነቱ አካሄድ እንደተጠበቀ ሆኖ ወረርሽኙን በተመለከተ ዓምና ይደረጉ የነበሩት ዝግጅቶችና ጥንቃቄዎች ዘንድሮም ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የጤና ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ፡፡

የጤና ሚኒስትር ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) ባለፈው ቅዳሜ በጠሩት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳመለከቱት፣ ከሚፈለጉት ዝግጅቶችና ጥንቃቄዎች መካከል የመከላከሉ ሥራ ሳይስተጓጎል ከመማር ማስተማሩ ሥራ ጎን ለጎን አብሮ እንዲሄድ፣ መምህራን ክትባት እንዲወስዱ፣ ወላጆችም ልጆቻቸውን በሥነ ልቦና ዝግጁ እንዲሆኑና መከላከያ ዘዴዎችንም እንዲያውቁት ማድረግ ይገኝበታል፡፡

በየትምህርት ቤቱ የመማርና የማስተማር ሒደቱና የኮቪድ-19 የመከላከያ ዘዴዎችን የመጠቀምና ክትባቱንም የመውሰድ እንቅስቃሴ እንዳያስተጓጉሉ ለማድረግ የሚያስችል ሥራ፣ ትምህርት ሚኒስቴርና ጤና ሚኒስቴር በጋራ ማከናወናቸውንና ለተግባራዊነቱም አቅጣጫ ማስቀመጣቸውን ነው ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) የተናገሩት፡፡

መምህራንም ሆኑ ተማሪዎች ሁሉም ወደ ትምህርት ቤት ሲሄዱና በክፍል ውስጥም እያሉ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ማስክ ማድረግ የሚኖርባቸው ሲሆን፣ በክፍሉ ውስጥ ያለውም ሁኔታ እንደ የትምህርት ቤቱና እንደየክልሉ ሁኔታ እንዲሆን ለማድረግ የሚያስችል አቅጣጫ ተሰጥቷል፡፡ ይህም ማለት የተማሪዎች ቁጥር ትንሽ በሆኑባቸው ትምህርት ቤቶች በመደበኛ፣ ርቀታቸውን መጠበቅ የሚያስችል ቁጥር የሚያስተናግዱ ትምህርት ቤቶች በግማሽ ቀን ፈቃድ ማስተማር እንደሚችሉ ገልጸው፣ ይህንኑ አቅጣጫ የመቆጣጠርና የመከታተል ሥልጣን ለትምህርት ቤቶችና ለትምህርት ቢሮዎች መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡

እንደ ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) ማብራሪያ፣ የዓለም ጤና ድርጅት በወረርሽኝ ዙሪያ ላሉት ዓለም አቀፍ ሥርጭት ዋነኛ ያላቸው ሦስት ዓበይት ችግሮችን አውጥቷል፡፡ አንደኛው የዴልታ ዝርያ መስፋፋት ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ክትባቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ በበቂ ሁኔታ አለመዳረሱ ነው፡፡ በየአገሩ የሚወጡ መመርያዎች አለመተግበርና በቫይረሱም ሆነ በክትባቱ ዙሪያ ያሉ የተዛቡ መረጃዎች ለሥርጭቱ መባባስ ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው፡፡

እነዚህ የተገለጹት ችግሮችም እንደ አንዱ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ሲታይ ሁሉም ችግሮች በስፋት የሚገኙ ናቸው፡፡ የዴልታ ዝርያም በስፋት ከመሠራጨቱ አኳያ በቅርቡ በየቀኑ በሞት የሚታጡት ወገኖች ቁጥር እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለው መሆኑን መገንዘብ እንደሚያስፈልግ ነው ሚኒስትሯ የገለጹት፡፡  

እስከ ጥቅምት 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ የሞት ቁጥር 6,026 ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል፡፡ ባለፈው ሳምንት ብቻ 308 ወገኖች በበሽታው አጥተናል ያሉት ሚኒስትሯ ይህ እንግዲህ ባለፉት አራት ሳምንታት የተመዘገበው የሞት ቁጥር መሆናቸው ሲታይ 946 ሰዎች የሞት ምጣኔው በየቀኑ በአማካይ 44 ሰዎች እንደሞቱ ያሳያል ብለዋል፡፡

የዴልታ ኮሮና ቫይረስ እየተዛመተ ባለባት ኢትዮጵያ የሚሞቱት ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ ሲሆን፣ ሟቾቹ ሁሉም በሚባልበት ደረጃ አለመከተባቸውን ሚኒስትሯ ገልጸዋል፡፡

ካለፈው ሰኔ እስከ ነሐሴ አጋማሽ ሕይወታቸውን ካጡት መካከል አንዱ ብቻ ክትባት መውሰዱ ሌሎቹ ግን አለመከተባቸውን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል፡፡

ክትባትን እንደ መከላከያ

‹‹ክትባቱ ትልቁና አንዱ የመከላከያ ዘዴ ነው›› ያሉት ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) ያልተከተቡ ሰዎች ለበሽታው በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ እንደሆኑ፣ ከተያዙም የመታመምና በፅኑ ታመው ወደ ሞት የመሄዳቸው ዕድል እጅግ ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ሚኒስትሯ ሲዲሲ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያካሄደውን የዳሰሳ ጥናት ዋቢ አድርገው እንዳብራሩት፣ ያልተከተቡ ሰዎች በቫይረሱ የመያዝን ዕድላቸው ከ4.5 እጥፍ በላይ፣ ሆስፒታል የመግባት ዕድላቸው ከ10 እጥፍ በላይ ይጨምራል፡፡ ታሞ የመሞት ዕድላቸው ከ11 እጥፍ በላይ ይሆናል፡፡

ከተለያዩ ዓለም አቀፍና አኅጉራዊ ጥምረቶች ጋር በጋራ በመሥራት የክትባት ምጣኔው ወይም የሚገኘው የክትባት ቁጥር እንዲጨምር ለማድረግ የሚያስችል ብዙ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ አሁንም በርካታ ክትባቶች በየተቋማቱ እየተሰጡ እንደሚገኙ፣ በቀጣይ ወራትም ሰፊ ቁጥር ያላቸው የክትባት ዶዞች እንደሚገኙ ሚኒስትሯ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ተተኳሪ ጉዳዮች

ኮቪድ-19 በወረርሽነት ዓለምን ካካለለ ከሁለት ዓመት እልፍ ብሏል፡፡ በእነዚህ ወራት  የዓለም ሕዝብ ከኮሮና ቫይረስ እንዲጠበቅ፣ ‹‹በደዌ ዳኛ በአልጋ ቁራኛ›› እንዳይያዝ የጤና ባለሙያዎችና ዓለም አቀፋዊም ሆነ አገራዊ ተቋማት ማስገንዘቢያዎችን ከመስጠት ችላ ያሉበት ጊዜ አልነበረም፡፡

ኮቪድ -19 ከቀላል እስከ ከባድ የመተንፈሻ አካል ሕመም የሚያስከትል የቫይረስ ዝርያ ሲሆን በበሽታው የተያዙ ሰዎች ትኩሳት፣ ሳል፣ የትንፋሽ መቆራረጥና የመተንፈስ ችግር ምልክቶች ይታይባቸዋል፡፡

ኅብረተሰቡ በሽታው በቀላሉ የሚተላለፍ በመሆኑ ሳይዘናጋ ለተለያዩ ጉዳዮች በአንድ ቦታ መሰባሰብን በማስወገድ፣ እጅን አዘውትሮ በመታጠብ፣ ሰዎች በሚሰበሰቡበት ቦታዎች ላይ የአፍንና የአፍንጫ መሸፈኛ በማድረግ፣ በአካል ንክኪ የሚደረግ ሰላምታን በመተውና አካላዊ መራራቅን በመተግበር የበሽታውን ሥርጭት እንዲከላከል ኢንስቲትዩቱ ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡

ለዚህም የኮሮና ቫይረስ መከላከያን አራቱን ‹‹›› ሕጎች በመተግበር የበሽታውን ሥርጭት ሁሉም እንዲከላከልም ጥሪ አቅርቧል፡፡

አራቱ ‹‹›› ሕጎች

  • መራራቅ አካላዊ ርቀት መጠበቅ፣
  • መታጠብ እጅን በተደጋጋሚ በውኃና በሳሙና መታጠብ፣
  • መቆየት አስገዳጅ ካልሆነ ቤት ውስጥ መቆየት፣
  • መሸፈን ከቤታችን ወጥተን ስንንቀሳቀስ የአፍንና የአፍንጫ መሸፈኛ (የፊት ማስክ) መጠቀም፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...