Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናተመድ በኢትዮጵያ ላይ የፖለቲካ አጀንዳ የለኝም አለ

ተመድ በኢትዮጵያ ላይ የፖለቲካ አጀንዳ የለኝም አለ

ቀን:

“ኢትዮጵያ መቼም ቢሆን ሉዓላዊነቷን አታስደፍርም” በተመድ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬስ ድርጅታቸው በኢትዮጵያ ላይ ምንም ዓይነት የፖለቲካ አጀንዳ እንደሌለው አስታወቁ፡፡

ዋና ጸሐፊው ዓርብ መስከረም 28 ቀን 2014 ዓ.ም. በትዊተር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፣ ተመድ በኢትዮጵያ ላይ የፖለቲካ አጀንዳ እንደሌለው አስታውቀው፣ “አጀንዳችን ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰበት ያለውን የኢትዮጵያ ሕዝብ መደገፍ ነው፤” ብለዋል፡፡

“ግጭቱን ለማስቆም ማንኛውንም ዕርምጃ መውሰድ አለብን፤” ያሉት ጉተሬስ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ በማንኛውም ሥፍራ ለማንኛውም ሰው ሰብዓዊ ዕርዳታ መድረሱን ማረጋገጥ ይኖርብናል ሲሉም ገልጸዋል፡፡

የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት አጋማሽ በኢትዮጵያ ጉዳይ ባደረገው ስብሰባ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ሰባት የተመድ ሠራተኞችን ከአገር ያስወጣበትን ምክንያት እንደማያውቁ ጉተሬስ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ቀደም ሲልም የመንግሥት ውሳኔ “አስደንግጦኛል” ማለታቸውም አይዘነጋም፡፡

በፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የመንግሥት ውሳኔ ከዓለም አቀፍ ሕግ የሚጣረስ እንደሆነም በመግለጽ፣ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ጠይቀው ነበር፡፡ ለዚህም የሰጡት ምክንያት ‹‹ከኢትዮጵያ መንግሥት ምንም ዓይነት መረጃ በጽሑፍ አልቀረበልኝም›› የሚል ነበር፡፡ ከዚህም አልፈው ተርፈው ገለልተኛ አይደለህም ተብለው ዘለፋ እንደ ደረሰባቸው በምሬት ተናግረዋል፡፡

የተመድ ዋና ጸሐፊን መልዕክት በትዊተር የተከታተሉ በርካቶች ግን፣ ተመድ በኢትዮጵያ ላይ ፖለቲካዊ አጀንዳ እንዳለው በመግለጽ ዋና ጸሐፊውን ወቅሰዋል፡፡ ከተሰጡት አስተያየቶች መካከል የፀጥታው ምክር ቤት በአንዲት ሉዓላዊት አገር ውስጣዊ ጉዳይ ለመፈትፈት በተደጋጋሚ ስብሰባ መጥራቱ፣ የፖለቲካ አጀንዳ ከመባል ውጪ ሌላ ትርጉም የለውም ሲሉ የጉተሬስን ሐሳብ ውድቅ አድርገዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የሕወሓት ታጣቂዎች የተመድ ዓርማ ባላቸው በርካታ ከባድ ተሽከርካሪዎች ተጭነው ሲንቀሳቀሱ የሚያሳዩ የቪዲዮ ምሥሎችን እንደ ማስረጃ በማቅረብ፣ ይህም ተመድ በሰብዓዊ ድጋፍ ስም በሽብርተኝነት ለተፈረጀው ሕወሓት መወገኑን ያሳያል ሲሉም ዋና ጸሐፊውን ሞግተዋቸዋል፡፡ ተመድ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ከመጠን በላይ ጣልቃ መግባቱ፣ የፖለቲካ አጀንዳ እንዳለው ማረጋገጫ ነው ሲሉም የዋና ጸሐፊው አስተያየት ተቀባይነት የለውም ብለዋል፡፡

በተመድ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ታዬ አፅቀ ሥላሴ (አምባሳደር) በፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ባደረጉት ንግግር፣ ምክር ቤቱ አሁንም ለስብሰባ መጠራቱ ከፍተኛ ገረሜታ እንደፈጠረባቸው ለመደበቅ እንደማይፈልጉ አስታውቀው፣ “ይህ የተከበረ አካል አንድ ሉዓላዊ አገር በዓለም አቀፍ ሕግ ላይ ተመሥርቶ በወሰደው ትክክለኛ ዕርምጃ ላይ መነጋገሩም ያልተለመደ ነው፤” ሲሉም ተችተዋል፡፡

በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ አገሮች የተመድ ሠራተኞችንና ዲፕሎማቶችን በተገለጹና ባልተገለጹ ምክንያቶች ከአገራቸው እንዲወጡ ማድረጋቸው የሚታወቅ መሆኑን በማስታወስ፣ ‹‹እንዲህ ዓይነት ውሳኔዎችን በተመለከተ ተመድ ተሰብስቦ ያውቃል ወይ?›› በማለት ጠይቀው፣ “እኛ ግን መቼም ቢሆን አናስታውስም፤” ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ታዬ (አምባሳደር) የፀጥታው ምክር ቤት አባላት ይህንን ጉዳይ በመረዳት ለኢትዮጵያ መንግሥትና ለተመድ እንደሚተው ተስፋ እንዳላቸው ገልጸው፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ግን ውሳኔውን በተመለከተ ምክንያቱንም ሆነ ማብራሪያ ለመስጠት በምንም ዓይነት ሁኔታ ሕጋዊ ግዴታ እንደሌለበት አስታውቀዋል፡፡

ነገር ግን የተመድ ሠራተኞች በተጨባጭ ማስረጃ ከአገር እንዲወጡ መደረጉን አክለው፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ከአገር እንዲወጡ የወሰነባቸውም የገቡትን ቃለ መሃላ፣ ሙያዊ ሥነ ምግባርና የሰብዓዊ ድጋፍ መርህ በመጣሳቸው እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ በትግራይ ክልል በረሃብ ያልሞቱ ሰዎችን ሞተዋል በማለት የተረጂዎችን ቁጥር በሚሊዮን መጨመራቸውን፣ በቅርቡ 12 ሰዎች በረሃብ ሳቢያ ሞተዋል ብለው ሪፖርት ማድረጋቸውን፣ በተደጋጋሚ ሐሰተኛ መረጃዎችን በማስተላለፍ፣ የጦር መሣሪያዎች በማቀበልና በሌሎች አፍራሽ እንቅስቃሴዎች ተሳታፊ በመሆን በሽብር ለተፈረጀው ቡድን ወገንተኝነታቸውን አረጋግጠዋል ሲሉም አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም በሳዑዲ ዓረቢያ ማንነትን በመለየት ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ ተመላሽ እንዲደረጉ በማመቻቸት፣ በተለይ የትግራይ ተወላጆችን ስሙ ያልተጠቀሰ ሦስተኛ አገር በመውሰድና በወታደራዊ ሥልጠና ተሳታፊ በማድረግ ለውጊያ በማዘጋጀትም ሚና እንደነበራቸው አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ የሙያ ሥነ ምግባራቸውን አክብረው ኃላፊነታቸውን ለሚወጡ የተመድ ሠራተኞችና ኃላፊዎች አክብሮት እንዳላት፣ እንዲሁም በክብርና በእኩልነት መርህ ከሚመለከቷት ወዳጆቿ ጋር ተባብራ ለመሥራት ሁሌም ቁርጠኛ መሆኗን አስረድተው፣ ከዚህ ውጪ ግን ኢትዮጵያም መቼም ቢሆን ሉዓላዊነቷን አታስደፍርም ብለዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ፣ ከአገር እንዲወጡ የተወሰነባቸው የተመድ ሠራተኞች የፈጸሙዋቸውን አምስት ዋና ዋና ጉዳዮች ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡ እነሱም ሰብዓዊ ዕርዳታን ለሕወሓት አሳልፎ መስጠት፣ ስምምነት የተደረገበትን የፀጥታ ሥራ መጣስ፣ የግንኙነት መሣሪያዎችን ለሕወሓት ማቅረብ፣ ሰብዓዊ ዕርዳታ ለማድረስ የተላኩ ከ400 በላይ ተሽከርካሪዎች በሕወሓት ለወታደራዊ ዓላማ ሲውሉ ለማስመለስ ጥረት አለማድረግና በተደጋጋሚ ቸልተኛ መሆን፣ እንዲሁም የተሳሳቱ መረጃዎችን ማስተላለፍና ሰብዓዊ ድጋፎችን ፖለቲካዊ ማድረግ ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...