Monday, July 22, 2024

ልጓም የሌለው ፈረስና ተጠያቂነት የሌለበት ሥልጣን አንድ ናቸው!

በኢትዮጵያ አዲስ መንግሥት ሲደራጅ የመጀመርያው ጊዜ ባይሆንም፣ ዘወትር የሚጠየቅ ነገር ግን ሁሌም ምላሽ የሌለው የሚደራጀው መንግሥት ካለፉት የተሻለ መሆኑን በተግባር ማሳየት ለምን ይቸግረዋል የሚለው ነው፡፡ ለምሳሌ ከእነ ችግሮቹም ቢሆን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት በግልጽ ያስቀመጠው አንድ እውነት አለ፡፡ ይህም የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ፣ ተጠያቂነትና ኃላፊነት እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ ሕግ አውጪው ፓርላማም አስፈጻሚውን መንግሥት እንዲቆጣጠር ሥልጣን ሰጥቶታል፡፡ የፓርላማ አባላትም እያንዳንዳቸው 100 ሺሕ ሕዝብ በመወከል የተመረጡ ስለሆነ ኃላፊነታቸውን የሚወጡት ለሕገ መንግሥቱ፣ ለወከላቸው ሕዝብና ለህሊናቸው እንደሆነም ይታወቃል፡፡ የምክር ቤቱ አባላት ከወከላቸው ሕዝብ በተጨማሪ በአንድነት የሚያገለግሉት የኢትዮጵያን ሕዝብ ይሆናል ማለት ነው፡፡ በዚህ መሠረት ቃለ መሃላ ፈጽመው ሥራቸውን ሲጀምሩ፣ የአስፈጻሚው መንግሥት ሥልጣን ከፍተኛ ቁጥጥር እንዲደረግበት ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በምርጫው ውጤት መሠረት መንግሥት የሚያደራጀው ገዥው ፓርቲ ጣልቃ ገብነት በመንግሥት መደበኛ ሥራ ውስጥ እንዳይታይ፣ የመንግሥት ሹማምንት ሥልጣን በሕግ እንዲገራ፣ መንግሥትም በሕጉ መሠረት በቅደም ተከተል ሥራውን በግልጽነትና በተጠያቂነት እንዲያከናውን፣ ለተቋማት ግንባታና በአጠቃላይ አገሪቱ ከገባችበት ዘርፈ ብዙ ችግሮች ውስጥ ለማውጣት ተግቶ እንዲሠራ ብርቱ ቁጥጥር ማድረግ ይኖርበታል፡፡

 

የሚደራጀው መንግሥት ከፊቱ በርካታ ችግሮች እንዳሉ የታወቀ ነው፡፡ እነዚህ ችግሮች በቀላሉ የሚቀረፉ እንዳልሆኑም ግልጽ ነው፡፡ የመንግሥት አሠራር ግልጽና ተጠያቂነት ሲኖርበት ግን፣ ችግሮቹን በቅደም ተከተል ለመቅረፍ የሚያስችሉ በርካታ አማራጮች ይኖራሉ፡፡ መንግሥት ሥራውን ሲጀምር ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ ጦርነቱን በፍጥነት በመቋጨት ሰላም ማረጋገጥ ነው፡፡ ንፁኃን እያለቁ፣ እየተፈናቀሉ፣ ንብረታቸው እየወደመና በአጠቃላይ የአገሪቱ ማኅበረ ኢኮኖሚያዊ መዋቅር እየፈራረሰ መቀጠል አይቻልም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዚህ ቀደም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ባስከተለው ከፍተኛ ችግር ምክንያት ያደቀቀው የኑሮ ውድነት አልበቃ ብሎ፣ በጦርነቱ ምክንያት ሊቋቋመው የማይችል ከባድ ፈተና ገጥሞታል፡፡ ጦርነቱ እየተራዘመ ሰላም ሲጠፋ ከኢኮኖሚና ከማኅበራዊ ዘርፈ ብዙ ችግሮች በተጨማሪ፣ በአገር ህልውና ላይ አደጋ ስለተደቀነ ይህ ጉዳይ ከምንም ነገር በላይ መፍትሔ ይሻል፡፡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላም ዋነኛው የህልውና መሠረት በመሆኑ፣ ሰላም ከማስፈን በፊት የሚቀድም ምንም ጉዳይ የለም፡፡ የተራዘመ ጦርነት ክቡር በሆነው የሰው ልጅ ላይ ከሚያደርሰው አስከፊ ጉዳት በተጨማሪ፣ በአገር ህልውና ላይ የሚያስከትለው አደጋ ከባድ ነው፡፡ አዲሱ መንግሥት ይህንን ኃላፊነቱን በሚገባ መወጣት የሚችለው ሥራውን በግልጽነት፣ በኃላፊነትና በተጠያቂነት መርህ ለማከናወን ዝግጁ ሲሆን ብቻ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በዚህ ዘመን ከምትጋፈጣቸው በርካታ ችግሮች መካከል የሚጠቀሰው ከዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ጋር ያላት ግንኙነት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለዲፕሎማሲ አዲስ አይደለችም፡፡ በቀድሞው የመንግሥታቱ ማኅበርም (ሊግ ኦፍ ኔሽንስ) ሆነ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማግሥት በተመሠረተው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) አባልና መሥራች የሆነች፣ እንዲሁም የቀድሞውን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁኑን የአፍሪካ ኅብረት ለመመሥረት ግንባር ቀደም የነበረች አገር ናት፡፡ ለአፍሪካዊያን ነፃነት ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክታለች፡፡ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሕጎችና ድንጋጌዎች ሲፀድቁ ዋነኛ ተሳታፊ ከመሆኗም በላይ፣ ለዓለም ሰላም መጠበቅ በተለያዩ ሰላም የማስከበር ዘመቻዎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከት ስሟ ገዝፎ የሚታወቅ ነው፡፡ በዓለም ታላላቅ መድረኮች ተሰሚነቷንና ነፃነቷን ለማስከበር ከፍተኛ ተጋድሎ ያደረጉ ታላላቅ ዲፕሎማቶች አገር ናት፡፡ ምንም እንኳ በዲፕሎማሲው መስክ በጣም ውስብስብና አስቸጋሪ ግንኙነቶችና ፍላጎቶች ጫናቸው ቢበረታም፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላት ተቀባይነት መጓደል የለበትም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያን አስመልክቶ የሚስተዋሉ የተበላሹ ግንኙነቶችን ፈር ማስያዝ ይገባል፡፡ ከዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ጋር ተኳርፎ መዝለቅ አይቻልም፡፡ ለዚህ ደግሞ በመስኩ የዳበረ ዕውቀት፣ ልምድና ክህሎት ያላቸው ዜጎች በወረንጦ መፈለግ አለባቸው፡፡ ይህንን ተግባራዊ ማድረግ የሚቻለው ግን የመንግሥት አሠራር ግልጽነትና ተጠያቂነት ሲኖርበት ብቻ ነው፡፡

የመንግሥት ሥልጣን ግልጽነት፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት እንዲኖርበት ግፊት መደረግ ያለበት ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ የመንግሥት አመራርን ከጨበጡ ግለሰቦች ውስጥ ብዙዎቹ በአገር ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሱት፣ የያዙት ሥልጣን እንደ ርስት እየተቆጠረ ብልሹ አሠራሮች በመስፈናቸው ነው፡፡ ‹‹ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል›› የሚባለው ፊውዳላዊ አስተሳሰብ እስካሁን ድረስ የተሿሚዎች መርህ ሊሆን የቻለው፣ ሥልጣን ቁጥጥር ስለማይደረግበትና ስለሚባለግበት ነው፡፡ እዚህ ላይ አንድ ምሳሌ ማንሳት በርካታ ጉዳዮችን ለማጠቃለል ይረዳል፡፡ እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ መሠረት የሆነው መሬት የብሔር ሰሌዳ እየተለጠፈለት በግላጭ እየተወረረ የድጋፍ መግዣ የሆነው፣ ተጠያቂነት የሌለበት ሥልጣን የግለሰቦችና የቡድኖች መፈንጫ በመሆኑ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝብ ማገልገል ያለባቸው የሕዝብ ተመራጮችም ሆኑ ተሿሚዎች በፅንፈኛ ብሔርተኝነት አስተሳሰብ ተመርዘው፣ ዜጎችን እያበላለጡ ለሁከትና ለትርምስ በር የሚከፍቱ ነውረኛ ድርጊቶች ውስጥ በመሰማራታቸው ምክንያት ሕዝብና አገር መከራቸውን እያዩ ነው፡፡ ከእንዲህ ዓይነቱ የዘቀጠ ድርጊት ውስጥ መውጣት የሚቻለው፣ የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽና ተጠያቂነት ሲኖርበት ነው፡፡

በስድስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለመጪዎቹ አምስት ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስትርነት እንዲያገለግሉ የተሰየሙት ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ለሕዝብ በገቡት ቃል መሠረት ኃላፊነታቸውን መወጣት የሚችሉት የተናገሩትን ተግባራዊ ለማድረግ ሲችሉ ነው፡፡ አዲሱ መንግሥታቸው የጥበብ ሁሉ መጀመርያ ማድረግ ያለበት በብዙኃኑ ሕዝብ ተዓማኒነትን እንዴት ማግኘት እንደሚቻል በማወቅ ነው፡፡ ድጋፍና ጭብጨባ ብቻ ሳይሆን ተቃውሞንም ማስተናገድ መቻል አለበት፡፡ የትኛው ሥራው ከየትኛው መቅደም እንደሚገባው በግልጽ ማሳየት ይኖርበታል፡፡ በጦርነቱ ምክንያት ከደሃ ጎጇቸው ተፈናቅለው በረሃብ እየተቆሉ ያሉ ኢትዮጵያዊያን ጉዳይ እንቅልፍ ሊነሳው ይገባል፡፡ እነዚህ ወገኖች ከወደቁበት ተነስተው በሰላም የሚኖሩበት መፍትሔ ላይ ማተኮርና ለተግባራዊነቱም በአጭር ታጥቆ መነሳት አለበት፡፡ የአገሪቱ ችግሮች እንደ አንድ ግዙፍ ተራራ የተቆለሉ በመሆናቸው፣ በቅደም ተከተል በጠንካራ አመራሮችና ክህሎት ባላቸው ባለሙያዎች በመታገዝ በሕዝባዊ ተሳትፎ መፍትሔ ለመፈለግ ዝግጁ መሆን የግድ ሊሆን ይገባል፡፡ መንግሥታቸው የአጨብጫቢዎች፣ የአስመሳዮችና  የአድርባዮች መሰባሰቢያ ከሆነ እንኳንስ ችግር ሊፈታ ኢትዮጵያን አዘቅት ውስጥ ነው የሚከታት፡፡ ዓምደ መንግሥቱ ለግለሰቦች ተክለ ሰብዕና ሳይሆን ለብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅም ሲባል መሠረቱን ያጠናክር፡፡

አዲሱ መንግሥት ለሕግ የበላይነት መከበር፣ ለማኅበራዊ ፍትሕ መስፈን፣ ለሁሉም መብቶች መረጋገጥ፣ ለብሔራዊ መግባባት መጀመር፣ ለሕገወጥ አሠራሮችና ለሥርዓተ አልበኝነት መክሰም፣ ለግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት መከበርና ለመሳሰሉት ታላላቅ አገራዊ ክንውኖች ስኬት እንዲሠራ የኢትዮጵያ ሕዝብ ድጋፍ ያስፈልገዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የተለየ ሐሳብ ያላቸው የሰላማዊ ፖለቲካ ተፎካካሪዎች በምክንያታዊ አስተሳሰብ በመመራት የሰላ ሂስ ማቅረብ ሲጠበቅባቸው፣ ጎን ለጎንም ራሳቸውን እያዘጋጁ የተሻሉ አማራጮችን ሕዝብ ፊት ይዞ ለመቅረብ ይዘጋጁ፡፡ ጭፍን ድጋፍና ጭፍን ተቃውሞ ለአገር እንደማይበጁ ከበቂ በላይ ታይቷል፡፡ ኢትዮጵያ በሕግ እንድትመራ፣ ኢፍትሐዊ አሠራሮች ከሥራቸው ተነቅለው እንዲጣሉ፣ ጽንፈኝነትና ጋጠወጥነት እንዲወገዱና በአጠቃላይ አገርን ቀውስ ውስጥ የሚከቱ ብልሹ አሠራሮች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከኢትዮጵያ ምድር ተነቅለው እንዲጣሉ በጋራ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ውጪ ግን መንግሥት ምንጊዜም ቢሆን በሕዝብ ድምፅ እንዲመሠረት፣ የጉልበተኞች ጊዜ እንዲያበቃና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ፍላጎት መሠረት እንዲይዝ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት መታገል አለባቸው፡፡ በዚህ መሠረት የሚመሠረት መንግሥት ደግሞ አሠራሩ ለሕዝብ ግልጽነት ያለው፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት የሚኖርበት እንዲሆን ቀይ መስመር ሊኖር ይገባል፡፡ ይህንን ማድረግ ካልተቻለ ግን ልጓም የሌለው ፈረስና ተጠያቂነት የሌለበት ሥልጣን አንድ መሆናቸውን መረዳት ተገቢ ነው!    

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከፍተኛ ትርፍ ቢያገኝም የውጭ ምንዛሪ ገቢው ቅናሽ ማሳየቱ ተጠቆመ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2016 የሒሳብ ዓመት ያሰባሰበው የውጭ ምንዛሪ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለልዩነት ዕውቅና የማይሰጥ ፖለቲካ ፋይዳ ቢስ ነው!

በፍርኃትና በሥጋት የተኮማተረ አገር ለመለወጥም ሆነ ለማደግ ዝግጁ መሆን አይችልም፡፡ አጉል ድፍረትና ምግባረ ብልሹነት በተንሰራፋበት ስለነፃነት መነጋገር አይቻልም፡፡ ፍርኃት እንደ ወረርሽኝ አገር ምድሩን አዳርሶ...

ለሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎቶች ልዩ ትኩረት ይሰጥ!

በዚህ ዘመን ለሰው ልጅ የሚያስፈልጉ ነገሮች ብዛታቸው እየጨመረ ቢመጣም፣ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን መሠረታዊ የሚባሉ ፍላጎቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ሊቸራቸው ይገባል፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ...

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተገኙበት የሚዲያ ሽልማት ሥነ ሥርዓት መካሄዱ ይታወሳል፡፡ ‹‹ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ለሠሩ የአገር ውስጥና የውጭ...