Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ይነጋል!

እነሆ ጉዞ ከመድኃኔዓለም ወደ ፒያሳ፡፡ የመንገደኛው ግርግር ማለቂያ ያለውም አይመስልም። አንዳንዱ እግሩ እየመራው የሚራመድ እንጂ ቀልብ ያለው አይመስልም፡፡ ወዲያ ደርሶ ወዲህ መመለስ፣ ወዲህ ተስቦ ወዲያ መሽቀንጠር ወስዶ የሚመልሰው መንገድ ባህሪ ቢሆንም፣ የአንዳንዱ ነፍስያ ግን ደመ ነፍሳዊነት የተጣባው ይመስላል። በዚህ ላይ ደግሞ ጨለምተኛው ከተስፈኛው፣ ቀልደኛው ከኮስታራው፣ ከበርቴው ከምስኪኑ፣ ጨካኙ ከሩኅሩኁ የተቀላቀሉበት ጎዳና ድንቅ ይላል። ወትሮም ጎዳናው ምክንያትና ረቂቅ ዕሳቤ ብሎ ነገር ሳይጎበኘው ነው ዘመናት የተሸኙት። እንዲሁ በደመነፍስ በሚሰጥ ስያሜና ቅጥያ በመደናበር የተሞላ ሕይወት፣ የዚህች ምስኪን አገር ጎዳና ልዩ መለያ ነው። ይህንን በቀላሉ ለመረዳት ከሕዝቡ ቁጥር እጥፍ የሆነውን ችግር ማሰብ ብቻ በቂ ነው። በድህነት እየራበው እንደሚግደረደር ምስኪን፣ ልባችንን በአጉል ኩራትና ለራስ የሚሰጥ ባዶ ግምት ደጋግሞ የተጫወተብን እኛ ላይ ብቻ ሳይሆን ይቀራል? ከዚህ ሁሉ አሰልቺ ሀቅ በስተጀርባ የሆነው ሁሉ ቢሆንም ዛሬም የመኖር ጉጉት አለብን። ዛሬም ትግል ሜዳው ላይ እንደ ሙጃ በበቀለ ሥውር ተስፋ ታጅቦ ፍጥረቱን ያተራምሰዋል። እጅ መስጠት የረገጡትን ተሸክመው በሚመለሱበት የሕይወት ጎዳና፣ በጭራሽ የሚታሰብ ነገር አይመስልም። የሰው ልጅ እንደ ሸክላ ተሰባሪ የሆነ ባህሪ ያለውን ያህል፣ እንደ ብረት ጠንካራ መንፈስ ባለቤት ጭምር መሆኑን በግልጽ እያስመሰከረ ይራመዳል። ወደፊት!

 

ታክሲያችን ከረዥሙ ሠልፍ መሀል እየቆነጠረ ከሰበሰበን ውስጥ ከወደ ጋቢና ሁለት ወጣቶች፣ ከሾፌሩ መቀመጫ ጀርባ አንድ የአትክልት ነጋዴና ወጣት ሊስትሮ፣ ከእነሱ ጀርባ ታክሲው ተበላሽታበት ተራውን ተሳፋሪ የሆነ የታክሲ ሾፌርና ለግላጋ ቆንጅዬ ልጅ ተቀምጠዋል። እንደ ኖኅ መርከብ ሁለት ሁለት ተጣምደን ከተሳፈርነው የመጨረሻዎቹ ተሳፋሪዎች እኔና በትኩረት መጽሐፍ የምታነብ ነጭ ሦስተኛው መቀመጫ ላይ ተሰይመናል። ቀሪዎቹ አራቱ የመጨረሻ ወንበር ታዳሚዎች የኮሌጅ ተማሪዎች ሲሆኑ፣ ሁካታቸውና የሚያወሩት ወሬ ፍሬ ፈርስኪነት አገር ያስለቅቃል። ወያላችን ታክሲው እንደ ሞላለት ዘሎ በሩን ከርችሞታል። ሾፌሩ በአንዳች መላና ቀመር ካልሆነ የማይነሳውን ታክሲ አመል ጠንቅቆ ስለሚያውቅ፣ ወደ ታች አጎንብሶ የሆነ ነገር ይጎረጉራል። ሁሉም በግል ስሜቱና ምልከታው የተለያየ ነገር ላይ ዓይኑን ቢተክልም፣ ጆሮው የሚያዳምጠው የተማሪዎቹን የማይጨበጥ የወሬ ክምር ነው። ወሬ ብቻ አሉ!

“አንቺ ትናንት ያ ልጅ እንደንስ ሲልሽ እንደዚያ ታዋርጂዋለሽ?” ስሙልኝ ይመስላል ድምጿ። “እባክሽ እሱ እኮ የማን ባል የነበረ መሰለሽ?” ስትል ወዲያኛዋ ለጆሮ የሚጥም የሴት ልጅ ስም ትጠቅሳለች። ከጓደኝነት በታች ባልነት ተቃሎ ያለ ቦታው ሲጠቀስ የሚሰሙ ፊታቸው ሲለዋወጥ ይታወቃል። አንዴም ተሳስተው ስለትምህርታቸው ወይም ፍሬ ስለሚጨበጥበት ነገር ሲነጋገሩ የማይሰሙት እነዚህ ‘የኮሌጅ ተማሪ’ ተብዬዎች፣ የአስረሽ ምቺው የምሽት ታሪካቸውን በአደባባይ ይዘከዝኩታል፡፡ “ይገርማል እናንተ የዘንድሮ ሰው ለትችት እንኳ አልመች አለ እኮ?” ሲል ነጋዴው ጎልማሳ፣ የተማሪዎቹ ቅጥ ያጣ ሳቅና ረብሻ ስለዋጠው በቅጡ አልተሰማም። ‘ያን ጊዜ ነው የአገር ሞት፣ ስለምድሩ ደንታ አጥቶ ዜጋዋ ዳር የቆመ ዕለት’ ያለው ገጣሚ ትውስ ቢለኝ፣ አዲስ ነገር ማየት የተጠማው ዓይኔ ዕንባ ያቀር ጀመር። “ዕንባዎቻችን ቢገደቡ ከህዳሴው ግድብ ባልተናነሰ የኃይል እጥረት ችግራችንን ባቃለሉ ነበር!” ያለው ወያላ እንዴት ተዘነጋኝ? ምነው መርሳትና መረሳሳት እንዲህ ጠነከረ!

ታክሲያችን ተነስቶ ተንቀሳቅሰናል። ወያላው ሒሳብ እየሰበሰበ ቆየና ልክ መጽሐፍ ላይ ተተክላ ቢጠሯት የማትሰማዋ ፈረንጅ ዘንድ ሲደርስ፣ “ኧረ ጎበዝ እርዱኝ፣ የእንግሊዝኛ ፎዚያ (ፎቢያ ለማለት ነው በእሱ ቤት) ተነሳ እኮ?” አለ። ተሳፋሪዎቹ ሳቅ እያሉ በወያላው ሁኔታ ይዝናናሉ። ይቅርታ ጠይቄ ፈረንጇን ከንባብ ተመስጦዋ ቀሰቀስኩለትና ታሪፉን ነገርኳት። “ወንድሜ እንደ ጀመርከው እዚያው ጨርሰው እሺ፣ አደራ እኔ ‘ኔትወርኩ’ ውስጥ የለሁም። እንዲያውም ከቻልክ ‘የሚፈልጓቸውን ወያላ አሁን ማግኘት አይችሉም’ በልልኝ…” እያለ ፉገራውን አጧጧፈው። ፈረንጇ ሳቅ ተበራክቶ ግራ ገብቷት ብትታይም፣ በራስ መተማመኗ ከመጠን ያለፈ ስለነበር ፈጥና ወደ መጽሐፏ ተመለሰች። መቻል ነው!

“ኧረ ተፎገርን፣ መሀላችን አንድ ፈረንጅ ብትገኝ እሷም አጫዋቿና ጓደኛዋ መጽሐፍ ይሁን? ቆይ እኛ እስከ መቼ ነው ጓደኞቻችን ጎድን ጥብስና ጥሬ ሥጋ፣ መጠጥ ቤቶችና ምሽት ቤቶች ሆነው የሚቀሩት?” እያሉ ከወደ ጋቢና ወጣቶቹ ሲጨዋወቱ ይሰማሉ። እነሱን ተቀብሎ ጎልማሳው ነጋዴ፣ “ወይ እናንተ፣ እሱስ ቢሆን በቀላሉ መቼ ተገኘ ብላችሁ ነው? እዬዬም ሲደላ ብሏል የአገሬ ሰው…” ብሎ ተናገረ። “እሱም ብቻ ሳይሆን ምናልባት በመንግሥት ምሥረታ ወቅት ተዘንግቶስ ቢሆን?” ሲል የታክሲው ሾፌር፣ “እንዴ፣ እንዴት ነው ነገሩ? ሁሉንም ነገር በመንግሥት አላከን እንችለዋለን እንዴ? ‘የቄሳርን ለቄሳር የእኛን ለእኛ’ እንደ ሥልጣን ክፍፍሉ ሁሉ የሥራ ክፍፍልም ግድ ነው…” ብላ አጠገቡ ያለቸው ቆንጅዬ በግለ ሂስ ሒሳብ በነገር ወጋጋችው። ለነገር ቀንዱ የሾለ ብቻ በዛ እኮ!

ለጥቂት ጊዜ ዝምታ በታክሲያችን ውስጥ ነግሦ ቆይቶ ወሬ የሰማነው ከሾፌሩ መቀመጫ ኋላ የተሳፈሩት ነጋዴና ሊስትሮ ሲጨዋወቱ ነው። “እኔ ምለው፣ እኛ የምናውቀው ሊስትሮ በእግሩ እያዘገመ ሲሸቅል ነው። ምናልባት አንተ በሊስትሮዎች ታሪክ ከእነ ዕቃህ የተሳፈርክ የመጀመርያው ሊስትሮ ሳትሆን አትቀርም። ነው ወይስ የታክሲ ውስጥ አገልግሎትም ጀመራችሁ? መቼም እኮ የዘመኑ ሥራ ፈጠራ ድንጋይ ከሚፈልጠው ‘ሞል’ እስከሚገነባው ‘ኮሜዲያዊ ትራጀዲ’ ሆኗል። ዜጋ ከሚያነቃው የሚያደንዘው በዝቷል…” ሲል እያሳሳቀ ይጠይቀዋል። ሊስትሮው፣ “ኧረ እኔስ ታክሲ ናፍቆኝ ነው…” ብሎ መለሰ። “ማለት?” ይጠይቀዋል ነጋዴው። “በቃ፣ ሰው ማታና ጠዋት እየተሠለፈ የትራንስፖርት ችግር ቀልቡን ሲያሳጣው፣ እንደ ወትሮው ዘና ብሎ ጫማ ማስጠረጉን እየረሳው መጥቷል። ሐሳቡ ሁሉ ‘ታክሲ መጣ? ሄደ?’ ላይ ሆነና ገበያችን ቀዘቀዘ…” አለው ትክዝ ብሎ፡፡ እኔን ያሰኛል!

“እና ሥራችን በቀዘቀዘ መጠን ታክሲ ለዓይናችን የሚያምረን ከመንገደኛው ይልቅ እኛ ሆነናል…” ሲል የማይመስል ነገር አመሳስሎ ብሶቱን ያሰማል። የታክሲው ሾፌር፣ “አሁን እኮ የትራንስፖርት ችግሩ ለይቶለታል። ምንም ዓይነት መጓጓዣ በየዓይነቱ ቢታጎርባት አዲስ አበባ የምትችል አይመስለኝም። ምን ነካችሁ? እኔን የሚገርመኝ ስንትና ስንት የተማረ በሞላበት አገር ዘመናዊ የትራንስፖርት ሲስተም መዘርጋት ያቅታል…” ሲል፣ “ወዳጄ ችግሩ የተማረ መብዛቱ አይደለም፣ ጭንቅላትን በአግባቡ ማሠራት አለመቻል ነው። መማር የሚጠቅመው የዕውቀት ሽግግር ለማድረግ መሆን ሲገባው፣ ወረቀቱን ከያዙ በኋላ አንብበው የማያውቁ ስለበዙ ነው ማሰብ ያልተቻለው፡፡ አዲሱ መንግሥት ሲደራጅ በአሮጌ አቁማዳ አዲስ ወይን እንዳይሆን ነገሩ፣ ለዕውቀትና ለክህሎት ባለቤቶች ዕድሉ እንዲሰጥ በሕግ አምላክ ማለት አለብን…” ሲል አንድ ወጣት ሁላችንም በአድናቆት አንገታችንን ወዘወዝን፡፡ ልክ ነዋ!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ጥቂት ቀደም ብሎ ፈረንጇ ወርዳ ዕድሜ የተጫናቸው አዛውንት አሳፍረናል። ዓይን ሥራ የማይፈታባት ፒያሳ በቅርብ ርቀት እየታየችን ነው። ከማየት ባለፈ ትዝታ ያለበት በተመስጦ ከራሱ ጋር የትም ደርሶ ሲመለስ መታዘብ ይቻላል። “አሁን ቆይ አዲሱ መንግሥታችን እንዲህ ያለውን ታሪካዊና ጥንታዊ ሥፍራ እንዴት ይመለከተዋል?” ስትል ቆንጂት ጠየቀች። ሁኔታዋ እንጂ አስተሳሰቧ ‘ደንታ ቢስነት’ የሚባል የዘመኑ ፋሺን ያልተበረዘባት መሆኗ ለማንም ግልጽ ነው። “የአሁኑን አላወቅንም እንጂ የበፊቱ ከማፍረስ በስተቀር ቅርስና ታሪክ መጠበቅ መቼ ያውቃል ብለሽ ነው?” ሲሉ አዛውንቱ የመጀመርያ አስተያየታቸውን ሰጡ። እንዲህ ነው እንጂ!

“ምን እሱ ብቻ? ውሳኔው ‘ሥልጣን’ ባለው እንጂ ‘ሙያ’ ባለው አካል መቼ ይሰጣል? የተሠራው ይፈርሳል፣ ከተማው ገና አሁን አይደል እንዴ አረንጓዴ መናፈሻ ማየት የጀመረው። ከተማችን መኪኖች በሚለቁት የተቃጠለ ጭስ ከሰል ቤት እንዳይመስል፣ ሁላችንም ለአካባቢ ጥበቃና ለጤናማ አኗኗር መለመድ የበኩላችንን እናድርግ…” ስትል ቆንጂት ደግማ ተነፈሰች። ንግግሩ ቀጥሏል። “ምን ይኼ ብቻ፣ መብታችንን ብቻ ሳይሆን ግዴታችንንም እንወቅ፡፡ እርስ በርስ እየተባላን ከምንደኸይ፣ ፈጣሪ የሰጠንን ፀጋ አልምተን እንክበር፡፡ የሚሠሩትን እናክብር፣ እናወድስ፣ እናበረታታ፡፡ አጥፊዎችን ደግሞ እንገስፅ፡፡ ይህንን ማድረግ ስንችል ድቅድቅ ጨለማው በንጋት ብርሃን ይተካል…” እያለን ፒያሳ ደርሰን ተለያየን፡፡ እውነትም ይነጋል!  መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት