Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበኮቪድ-19 ምክንያት በአንድ ሳምንት ውስጥ 326 ሰዎች ሞቱ

በኮቪድ-19 ምክንያት በአንድ ሳምንት ውስጥ 326 ሰዎች ሞቱ

ቀን:

  • በኢትዮጵያ የተከተቡት ከሕዝቧ ከ3 በመቶ በታች ነው

በኢትዮጵያ አዲሱ የኮቪድ-19 ዝርያ የሆነው ዴልታ ቫይረስ በከፍተኛ ደረጃ እየተሠራጨ በመሆኑ የበርካታ ሰዎች ሕይወት እያለፈ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አሁናዊ መረጃ እንደሚያሳየው ከመስከረም 18 እስከ 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ በአገር አቀፍ ደረጃ በኮቪድ-19 ምክንያት ባጠቃላይ 326 ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል፡፡ ይህም ባለፈው ሳምንት (ከመስከረም 10-16) ከተመዘገበው የ271 ሰዎች ሞት የ55 ብልጫ አሳይቷል፡፡ ኮቪድ-19 በኢትዮጵያ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ ከፍተኛ የሞት መጠን የተመዘገበበት ሳምንት መሆኑን መረጃው ያሳያል፡፡

ከተለያዩ የአስተዳደር አካባቢዎች በተለይ በአዲስ አበባ እየተመዘገበ ያለው የሞት መጠን ከሌሎቹ ሲነፃፀር እስከ 65 በመቶ ይደርሳል፡፡

 በዚህ ሳምንት ከ771 በላይ የሚሆኑ ታካሚዎች ወደ ፅኑ ሕክምና ክፍል ገብተው የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው እንደሚገኝ፣ በአዲስ አበባና በአንዳንድ ከተሞች የታካሚዎች ብዛት ከመጨመሩ ጋር ተያይዞ የፅኑ ሕሙማን ክፍል ሞልቶ ታካሚዎች ለከፍተኛ ችግር እየተጋለጡ መሆናቸውን ከኢንስቲትዩቱ ለማወቅ ተችሏል፡፡ እስከ መስከረም 25 ቀን ድረስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 348,669 ሲደርስ ያገገሙት ደግሞ 315,177 ናቸው፡፡ ሕይወታቸው ያለፈው 5,722  ሆኗል፡፡

የተከታቢ ቁጥር ያነሰባት ኢትዮጵያ

የዓለም ጤና ድርጅት ሁሉም አገሮች ከሕዝቦቻቸው መካከል አሥር በመቶ ያህሉን እስከ መስከረም 2014 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ የኮቪድ ክትባት እንዲያስከትቡ ግብ አስቀምጧል፡፡

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ግቡን ማሳካት ቀርቶ ከግቡ ግማሽ ያህሉን እንኳ አላሳካችም፡፡ ዓለም አቀፉ ተቋም ያወጣው መረጃ እንዳብራራው፣ አፍሪካ ውስጥ ከሚገኙት 54 አገሮች መካከል ዓለም አቀፉ ጤና ያወጣውን ግብ ያሳኩት 15 ብቻ ሲሆን በአኅጉሩ ካሉት አገሮች ውስጥ ግማሾቹ ብቻ ከሁለት ከመቶ ያነሰ ሕዝባቸው ክትባቱን እንዲያገኝ አድርገዋል፡፡ ብዙ ሕዝብ ያላቸው አገሮች ከግቡ ላይ ለመድረስ እንዳልቻሉ፣ ከነዚህም አንዷ ኢትዮጵያ ከሦስት በመቶ ያነሰ ሕዝቧን መከተብ እንዳልቻለች አመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መስከረም 24 ቀን ባወጣው አሁናዊ መረጃው በኢትዮጵያ የተከተቡ ሰዎች ቁጥር 2,890,113 ብቻ ነው፡፡

ከከፍተኛ መዘናጋት ማን ይታደግ?

በአገር አቀፍ ደረጃ በተመረጡ 14 ከተሞች ላይ የኮቪድ-19 መከላከያ መንገዶችን (የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማድረግ፣ የእጅ መታጠብና ርቀትን መጠበቅ) በተመለከተ በተሠራው የምልከታ ዳሰሳ ውጤት መሠረት በአብዛኛው ከተሞች ላይ የኮቪድ-19 መከላከያ መንገዶች ትግበራ ዝቅተኛ መሆኑና በኅብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ የሆነ መዘናጋት እንዳለ ተረጋግጧል፡፡

በማኅበረሰቡ ዘንድ የኮቪድ-19 መከላከያ መንገዶችን ተግባራዊ ያለመደረጋቸው ምክንያቶች፣ ኅብረተሰቡ የኮቪድ-19 ቫይረስ እንዲሁም መከላከያ መንገዶችን የፖለቲካ አንድምታ መስጠት፣ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች በኮቪድ-19 መከላከያ መንገዶች ትግበራ ላይ ለኅብረተሰቡ አርዓያ ሆኖ አለመገኘት፣ መመርያ 803/2013 አፈጻጸም ላይ በየደረጃው በሚገኝ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት በኩል ትኩረት አለመስጠት፣ መመርያ 803/2013 ለማስፈጸም ኃላፊነት ያላቸው በየደረጃው የተዋቀሩ ግብረ ኃይሎች መመርያ ለማስፈጸም ያላቸው ተሳትፎ አነስተኛ መሆኑን፣ ለኅብረተሰቡ ወቅታዊ መረጃዎችን ተደራሽ ለማድረግ የሚዲያ ትኩረት አነስተኛ መሆን፣ ኮቪድ-19 የሚያስከትለውን ሰብዓዊ፣ ኢኮኖሚዊና ማኅበራዊ ጉዳቶች አቅልሎ ማየት ዋና ዋናዎቹ መሆናቸው ተመልክቷል፡፡

የኮቪድ-19 የመከላከያ መንገዶችን ተግባራዊ ለማድረግ በኅብረተሰቡ ዘንድ መሰላቸት መፈጠሩ፣ የመከላከያ መንገዶችን ከመተግበር አንፃር አፈጻጸማቸውን የሚለካ የክትትልና የግምገማ ሥርዓት አለመኖሩ፣ በመሆኑም የኮቪድ-19 ሥርጭትን ለመከላከልና የሚያስከትለውን ሞት ለማስቆም የሚከተሉትን የመከላከያ ዘዴዎችን አጠናክሮ መተግበር አስፈላጊ ይላል ኢንስቲትዩቱ፡፡

  1. መመርያ 803/2013 ዓ.ም. ተግባራዊነት ላይ በየደረጃው የሚገኝ ኃላፊነት የተጣለበት ግብረ ኃይል (አመራርሮች፣ የፀጥታ አካላትና ማኅበረሰቡ) ትኩረት በመስጠት፣
  2. በየደረጃው የሚገኝ አመራር በኮቪድ-19 መከላከያ መንገዶች ትግበራ ላይ ለማኅበረሰቡ አርዓያ መሆን፣
  3. ሚዲያዎች ተገቢውን የአየር ሰዓት በመስጠት ለኅብረተሰቡ ወቅታዊ መረጃዎችን ማድረስ፣
  4. በሕዝባዊና ሃይማኖታዊ በዓላት የሚፈጠሩ መሰባሰቦችን ማስቀረት፣
  5. የመንግሥት፣ የሕዝብና የግል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የኮቪድ-19 መከላከያ መንገዶችን እንዲተገብሩ ማድረግ፣
  6. የኮቪድ-19 ምልክቶች ሲታዩ ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ አፋጣኝ ምርመራ ማካሄድ፣
  7. ሁሉም ዕድሜው ከ18 ዓመት በላይ የሆነው የማኅበረሰብ ክፍል የኮቪድ-19 ክትባትን በመንግሥት ጤና ተቋማት በመሄድ መውሰድ፣
  8. ኮቪድ-19ን በጋራ እንከላከል!
spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...