Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሚኒስሮች ምክር ቤት በገቢ ግብር ደንብ ላይ ያደረጋቸው ማሻሻያዎች ምንድናቸው?

ተዛማጅ ፅሁፎች

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት ሐሙስ መስከረም 13 ቀን 2014 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባው ከተመለከታቸው ጉዳዮች መካከል በሥራ ላይ የሚገኘው የገቢ ግብር ደንብ ይገኝበታል፡፡

የገቢ ግብር ደንብ ቁጥር 410/2009 ከነሐሴ ወር 2009 ዓ.ም. ጀምሮ በሥራ ላይ የዋለ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ የገቢ ግብር ሥርዓትን ዘመናዊና ቀልጣፋ ለማድረግ፣ የአገሪቱን ኢኮኖሚ በተገቢው መንገድ በመምራት ተገቢውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ማስገኘት ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡

ይሁን እንጂ የገቢ ግብር ደንቡ አንዳንድ አንቀጾች ግልጽነት የጎደላቸውና በተወሰኑ የኢኮኖሚ ዘርፎች እንቅስቃሴ ላይ ጫናን እያሳደሩ መሆኑ በመታወቁ፣ በተለዩት በእነዚህ ደንቦች ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ ተጠይቋል፡፡

የቀረበውን ማሻሻያ የተለከተው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ማሻሻያውን ተቀብሎ ያፀደቀ ሲሆን፣ የተደረጉት ማሻሻያዎችን በተመለከተ ሪፖርተር በሚከተለው ሁኔታ አቅርቦታል፡፡

በገቢ ሰብሳቢው ተቋምና በግብር ከፋዮች መካከል የውዝግብ ምንጭ እንዲሁም በኢንቨስትመንት ላይ ጫና በማሳደራቸው ማሻሻያ እንዲደረግባቸው የተወሰነባቸው አንቀጾችና ማሻሻያዎቹ እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡

የካፒታል ዕቃዎች የኪራይ ውል (አንቀጽ 34)

በካፒታል ዕቃ ንግድ ሥራ አዋጅ ቁጥር 103/1990 እንደተደነገገው ሦስት ዓይነት የካፒታል ዕቃዎች የኪራይ ውል ያለ ሲሆን፣ እነዚህም የፋይናንስ ኪራይ፣ የአጭር ጊዜ የመጠቀሚያ ኪራይና የዱቤ ግዥ ናቸው፡፡

በፋይናንስ ኪራይና በአጭር ጊዜ የመጠቀሚያ ኪራይ የንብረቱ ባለቤት አከራይ ሲሆን፣ በተዋዋይ ወገኖች ስምምነት መሠረት በውሉ ዘመን መጨረሻ የንብረቱ ባለቤትነት ወደ ተከራዩ ሊተላለፍ ይችላል፡፡ በዱቤ ግዥ ውል ግን ገዥው በከፈለው ገንዘብ መጠን የንብረቱ ባለቤት የሚሆን ሲሆን ዕዳውን ከፍሎ ሲያጠናቅቅ ያለምንም ቅድመሁኔታ ሙሉ በሙሉ የንብረቱ ባለቤት ይሆናል፡፡

ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት በካፒታል ዕቃ ኪራይ ንግድ ሥራ አዋጅ ቁጥር 103/1990 አንቀጽ 16 የዱቤ ግዥ ስምምነትን በሚመለከት የእርጅና ቅናሽ የሚታሰበው ለተከራዩ መሆኑ በግልፅ ተደንግጓል፡፡

ይሁን እንጂ በገቢ ግብር ደንብ አንቀጽ 34(1) በሦስቱም ዓይነት የካፒታል ዕቃዎች ኪራይ ውል ተከራዩ የከፈለው የኪራይ ክፍያ ከጠቅላላ የንግድ ሥራ ገቢ ላይ ተቀናሽ የሚደረግና ለተከራዩ የእርጅና ቅናሽ የማይታሰብ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

በዚህም ምክንያት የካፒታል ዕቃዎችን በዱቤ ግዥ ውል በመከራየት ሥራቸውን የሚያከናውኑ አነስተኛና ጥቃቅን ድርጅቶች ለንብረቱ ዋጋ ያወጡት ወጪ በአጭር ጊዜ ውስጥ በወጪ ተቀናሽ እንዲሆንላቸው የሚያስችለው የእርጅና ቅናሽ ተጠቃሚ ባለመሆናቸው ሥራ በጀመሩባቸው ዓመታት ከፍተኛ ግብር እንዲከፍሉ ይጠየቃሉ፡፡

ይህንን ችግር ለማቃለል የገቢ ግብር ደንቡ ከካፒታል ዕቃ ኪራይ ንግድ ሥራ አዋጅ ጋር በተጣጣመ መልኩ እንዲቀረፅ ተደርጓል፡፡ በከፊል ለንግድ ሥራ በዋለ ሕንፃ ላይ የሚታሰብ የእርጅና ቅናሽ (አንቀጽ 40)  በሕንፃ ሥራ አዋጅ የተደነገገውን በመከተል እንዲሁም ለታክስ አስተዳደር ያለውን አመቺነት ከግምት ውስጥ በማስገባት ለሕንፃ የእርጅና ቅናሽ የሚፈቀደው የሕንፃው ግንባታ ከተጠናቀቀ በኋላ እንደሚሆን ተደንግጓል፡፡

ይሁን እንጂ ከተጠናቀቀ በኋላ በከፊል ለንግድ ሥራ በከፊል ደግሞ ለሌላ አገልግሎት ስለሚውልንፃ የሚደነግገውን የደንቡን አንቀጽ 40 ሙሉ በሙሉ ሳይጠናቀቅ ለኪራይ የዋለ ሕንፃ ላይ የእርጅና ቅናሽ እንዲሰላ የሚፈቅድ አንቀጽ እንደሆነ በመቁጠር ያለመግባባት ይፈጠራል፡፡

ይህንን ውዥንብር ለማጥራት አንቀጹ የሚመለከተው ሙሉ በሙሉ ግንባታው ከተጠናቀቀ በኋላ በከፊል ለንግድ ሥራ የዋለን ሕንፃ መሆኑ በግልፅ እንዲመለከት ተደርጓል፡፡

ኪሣራን ስለማሸጋገር (አንቀጽ 42(1))

አንድ ግብር ከፋይ በንግድ ሥራ እንቅስቃሴ ውስጥ ባለበት ጊዜ ሊካካስለት የሚችለው ሁለት ጊዜ ያጋጠመ ኪሳራ እንደሆነና ይህም ኪሳራ የሚሸጋገረው ቢበዛ አምስት ዓመታት ጊዜ እንደሆነ በገቢ ግብር አዋጁ ተደንግጓል፡፡

ይሁን እንጂ ግብር ከፋዩ ኪሳራውን ለማካካስ የሚችለው ግብር የሚከፈልበት ገቢ ሲኖረው በመሆኑ በአምስቱ ዓመት ጊዜ ውስጥ ያጋጠመውን ኪሳራ ማካካስ የሚያስችል ግብር የሚከፈልበት ገቢ ከሌለው ኪሳራው ከአምስት ዓመት በላይ ሊሸጋገር ይገባል የሚል ክርክር ይነሳል፡፡

በንግድ ሥራ ውስጥ ያለ ግብር ከፋይ ላልተወሰነ ጊዜ ኪሳራ እያጋጠመው በሥራው ሊቀጥል የሚችልበት ሁኔታ ሊኖር ስለማይችል አዋጁ ሊካካስ የሚችለው ሁለት ጊዜ ያጋጠመ ኪሳራ ሆኖ በአምስት ዓመት ውስጥ መሆኑን በግልፅ የደነገገ ሆኖ ሳለ ለአንቀጹ የሚሰጠው ትርጉም የተሳሳተ ነው፡፡

ይህንን ግልጽ ለማድረግ በአምስቱ ዓመት ውስጥ ግብር ከፋዩ ቀድሞ ካጋጠመው የሁለት ጊዜ ኪሳራ በላይ ተጨማሪ ኪሳራ አጋጥሞኛል የሚል የገቢ ማስታወቂያ የሚያቀርብ ከሆነ ኪሳራው ከተጠቀሰው ጊዜ በኋላ ሊሸጋገር የማይችል መሆኑ ግልፅ ተደርጓል፡፡

የውጭ አገር ገንዘብ ምንዛሪ ኪሳራ

          በገቢ ግብር ደንቡ አፈጻጸም ረገድ አስቸጋሪ ከነበሩት ድንጋገዎች አንዱ የውጭ አገር ገንዘብ ምንዛሪ ኪሳራን የሚመለከተው ድንጋጌ ነው፡፡ ከባንኮች ውጪ ያሉ ሌሎች የንግድ ሥራ ድርጅቶች ለካፒታል ንብረት ማፍሪያ የወሰዱትን ብድር በሚከፍሉበት ወይም በውጭ ምንዛሪ ሌሎች የንግድ ሥራ እንቅስቃሴዎችን በሚያከናውኑበት ጊዜ የውጭ ምንዛሪ ኪሳራ ያጋጥማቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ የገቢ ግብር ደንቡ በውጭ ምንዛሪ ግብይት የደረሰ ኪሳራ ሊካካስ የሚችለው በውጭ ምንዛሪ ግብይት ከተገኘ ጥቅም ጋር ብቻ እንደሆነ ስለሚደነግግና እነዚህ ድርጅቶች የውጭ ምንዛሪ የማይዙ በመሆኑ ከግብይቱ የሚያገኙት ጥቅም ስለሌለ ለከፍተኛ ችግር ሲዳረጉ ቀይተዋል፡፡

ይህንን ችግር ለማቃለል በውጭ ምንዛሪ ግብይት ያጋጠመ ኪሳራ ለሁለት ተከፍሎ፣ ማሻሻያ እንዲደረግበት ተወስኗል፡፡

በዚህም መሠረት አንደኛ፣

  • የውጭ ምንዛሪ ግብይቱ የተፈጸመው ከካፒታል ንብረት ግዥ ጋር በተያያዘ ከሆነ ኪሳራው የካፒታል ንብረቱ የተገዛበት ዋጋ ላይ ተደምሮ ለእርጅና ቅናሽ መሠረት እንዲሆን፣
  • የውጭ ምንዛሪ ግብይቱ የተፈጸመው ከካፒታል ንብረቱ ግዥ ጋር ባልተያያዘ ሁኔታ ከሆነ ኪሳራው በግብር ዘመኑ እንደ ወጪ እንዲያዝ፣  በሚያስችል አኳኋን አንቀጹ ተሻሽሏል፡፡ 

የካፒታል ዋጋ ዕድገት ጥቅም ግብር (አንቀጽ 56(1))

የካፒታል ዋጋ ዕድገት ጥቅም ግብር የሚከፈለው ለንግድ ሥራ የተያዘንንፃ ወይም አክሲዮንን በማስተላለፍ በሚገኝ የዋጋ ዕድገት ጥቅም ላይ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የገንዘብን የመግዛት አቅም መቀነስ ተከትሎ የዋጋ ግሽበት ማስተካከያ እንዲደረግ የገቢ ግብር ደንቡ የሚፈቅደው ለህንፃ ብቻ በመሆኑ፣ አክሲዮን የሚሸጡ ግብር ከፋዮች የዋጋ ግሽበት ማስተካከያ ሳይደረግ የአክሲዮን ሰነዱ ላይ በተፃፈው ዋጋ (Par Value) እና በተሸጠበት ዋጋ መካከል ያለው ልዩነት ጥቅም እንደሆነ ተቆጥሮ ግብር እንዲከፍሉ ይጠየቃሉ፡፡

ይሁን አንጂ በገቢ ግብር አዋጁ እንደተመለከተው ግብር ከፋዩ በትክክል አግኝቷል ሊባል የሚችለው ጥቅም በአክሲዮኑ የወቅቱ ዋጋና በተሸጠበት ገንዘብ መካከል ያለው ልዩነት ስለሆነ ከአክሲዮን ሽያጭ ለሚገኝ የዋጋ ዕድገት ጥቅምም የዋጋ ግሽበት ማስተካከያ እንዲፈቀድ በሚያስችል አኳኋን አንቀጹ ተሻሽሏል፡፡ 

ተካክሶ ያልተጠናቀቀ ኪሳራ (አንቀጽ 68) 

    ግብር ከፋዮች ቀደም ሲል በሥራ ላይ በነበረው አዋጅ ሁለት ኪሳራ የተካካሰላቸው ቢሆንም በአዲሱ አዋጅ መሠረት ተጨማሪ ሁለት ኪሳራ ሊካካስላቸው እንደሚገባ ይጠይቃሉ፡፡ 

     በመሆኑም ለዚህ ጥያቄ መሠረት የሆነው ግልፅነት የጎደለው አንቀጽ እንዲሻርና ሊካካስ የሚችለው ከሁለት ዓመት ኪሳራ ውስጥ ያልተካካሰው ቀሪ መጠን ብቻ መሆኑ ግልፅ እንዲሆን ተደርጓል፡፡

የደንቡ ተፈፃሚነት

ከዚህ በላይ ከተጠቀሱት የደንቡ ድንጋጌዎች ጋር በተያያዘ በተፈጠረ ያለመግባባት በርካታ ጉዳዮች ውሳኔ ሳያገኙ በእንጥልጥል ላይ ይገኛሉ፡፡ በመሆኑም ችግሩን ወጥ በሆነ መልኩ ለመፍታት ክፍያ ያልተፈጸመባቸው ከተዘረዘሩት ጉዳዮች ጋር የተያያዙ የግብር ጉዳዮች በዚህ ደንብ መሠረት ፍጻሜ የሚያገኙ መሆኑን የሚገልፅ ድንጋጌ እንዲካተት ተደርጓል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች