Wednesday, July 24, 2024

ሕዝብ ከአዲሱ መንግሥት ብዙ ነገሮች ይጠብቃል!

ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. በተደረገው ምርጫ ውጤት መሠረት፣ ብልፅግና ፓርቲ ሰኞ መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም. አዲስ መንግሥት ያደራጃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የአዲሱ መንግሥት አደረጃጀት በርካታ አዳዲስ ጉዳዮች ይዞ ይመጣል ተብሎ ስለሚታሰብ፣ ለአዲሱ ፓርላማም ሆነ ለአስፈጻሚው መንግሥት ከብዙ በጥቂቱ ምክረ ሐሳብ ማቅረብ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ አዲሱ ፓርላማ የሕግ አውጭነት ሚናውን በአግባቡ እንዲወጣ በሕግ የተሰጠውን ሥልጣን መጠቀም ሲኖርበት፣ እንደ ከዚህ ቀደሞቹ አምስት የፓርላማ ዘመኖች የአስፈጻሚው ጉዳይ አስፈጻሚና የማኅተም መርገጫ (Rubber Stamp) ከመሆን ራሱን መከላከል መቻል ይጠበቅበታል፡፡ የፓርላማ አባላትም ለሕግ የበላይነት፣ ለወከላቸው ሕዝብና ለህሊናቸው ታማኝ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ በምክር ቤት አባልነት ቆይታቸውም ከፓርቲ ወገናዊነት በመላቀቅ ለአገር ክብርና ህልውና ሲሉ፣ የሚፈለግባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ቃል መግባትና በተግባር ማሳየት አለባቸው፡፡ አስፈጻሚው የመንግሥት አካል መንግሥታዊ ተቋማት በነፃነትና በገለልተኝነት እንዲሠሩ ማደራጀት ሲኖርበት፣ ተቋማቱን የሚመሩ ተሿሚዎች ሆኑ ባለሙያዎች በዕውቀትና በሥነ ምግባር የተመሰከረላቸው ሊሆኑ ይገባል፡፡ የፓርቲ አባልነትንና የብሔር መሥፈርትን ብቻ በመከተል ተቋማቱን ማሽመድመድ ይብቃ፡፡ ለተቋማት ግንባታና ለብቁ የሰው ኃይል ሥምሪት ትልቅ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል፡፡  የመንግሥት ሥልጣን ተጠያቂነትና ኃላፊነት ያለበት መሆኑ በተግባር መረጋገጥ አለበት፡፡ በሥልጣን መባለግም ሆነ በሕዝብ ላይ መቀለድ ማብቃት አለበት፡፡ በሁሉም መንግሥታዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት መሠረታዊ ለውጥ በግልጽ መታየት አለበት፡፡

የመንግሥታዊ ተቋማት ጉዳይ ሲነሳ እጅግ በጣም ጥቂት ቢሆኑም ተስፋ ሰጪ ለውጥ የታየባቸው አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ካሉበት ዘርፈ ብዙ ችግሮች አኳያ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡ በተቻለ መጠን የአስፈጻሚውን ጫና ተቋቁሞ በነፃነት ለመሥራት የሚያስችል ጭላንጭል እንዳለ እያመላከተ ነው፡፡ አዲሱ መንግሥት በተደራጀ ማግሥት በተሻለ ነፃነት የበለጠ ሥራ እንደሚያከናውን ተስፋ አለ፡፡ በፍትሕ ተቋማት በኩል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተስፋ ሰጪ ጅምሮች ቢታዩም፣ አሁንም ረዥም መንገድ መጓዝ እንደሚኖርባቸው ግልጽ ነው፡፡ ፍትሕ እንደ ሸቀጥ በሚቸረቸርበት አገር ውስጥ ሕግ ተርጓሚው አካል፣ በነፃነትና በገለልተኝነት የሚሠራበት ምኅዳር እንዲፈጠር ብርቱ ትግል ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ባለሙያዎች ግንባር ቀደም ታጋዮች መሆን አለባቸው፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱ መልክ መያዝ ካልቻለ ለሕዝባችንም ሆነ ለአገራችን የሚያተርፈው መከራ ብቻ ነው፡፡ የፋይናንስ ተቋማትን የሚቆጣጠረው ብሔራዊ ባንክ በዓለም ላይ ያሉ ምርጥ ተሞክሮዎች ተወስደው በአዲስ አደረጃጀት ገጽታውን መቀየር ብቻ ሳይሆን፣ ተጠሪነቱ ከአስፈጻሚው እጅ ወጥቶ ለፓርላማው መሆን ይኖርበታል፡፡ የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ ጤንነት መረጋገጥ ያለበት በባንኮቹ ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን፣ ብሔራዊ ባንክ ጤናማ አደረጃጀትና ተጠሪነት ጭምር መሆን አለበት፡፡ በዘርፉ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ የሚነሳ ጉዳይ በመሆኑ፣ የአዲሱ ፓርላማና የመንግሥት አንዱ የቤት ሥራ ይኸው መሆን ይኖርበታል፡፡ ከዚህ በተረፈ የመከላከያን፣ የፖሊስን፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትንና  የሌሎች የፀጥታ አካላትን ገለልተኝነት በተግባር በማረጋገጥ፣ አገርን ብቻ እንዲያገለግሉ ማድረግ የፓርላማውም የመንግሥትም ኃላፊነት ነው፡፡ በተለያዩ መንግሥታዊ ሹማምንትና በጥቅም ተጋሪዎቻቸው የሚፈጸሙ ዝርፊያዎችንና ሌብነቶችን ማስወገድ የሚቻለው የመንግሥት አሠራር ግልጽነት፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ሲኖርበት መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ በሥልጣን መባለግ በሕግ የሚያስጠይቅ ወንጀል መሆን አለበት፡፡

በአሁኑ ጊዜ ለሕዝብና ለአገር እየከበደ ያለው የኢኮኖሚ ቀውስ በጣም አንገብጋቢ እየሆነ ነው፡፡ ይህ ቀውስ መፍትሔ ካልተገኘለት ከዚህ ቀደም ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ አደጋ ያስከትላል፡፡ ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በአንፃራዊነትም ቢሆን እያስመዘገበችው  የነበረው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት መቀጠል አለበት፡፡ ዕድገቱ ተገቶ ወደ ኋላ መንሸራተቱ ከቀጠለ ከጦርነቱ ጋር ተዳምሮ የሚያስከትለውን ጥፋት ለመተንበይ ያስቸግራል፡፡ ሁሉም ክፍላተ ኢኮኖሚዎችና ዘርፎች በአስደንጋጭ ሁኔታ እየተቀዛቀዙ ስለሆነ፣ አገሪቱ አሉኝ የምትላቸው የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ምክረ ሐሳብ አቅርበው ተቀባይነት ያላቸው የፖሊሲ መፍትሔዎች በፍጥነት ሥራ ላይ ሊውሉ ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለመግለጽ ከሚያስቸግር የኑሮ ውድነት ጋር መጋፈጥ እያቃተው ነው፡፡ አዲሱ መንግሥት ለአገራቸው በነፃ ጭምር አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ የሚችሉ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ባለሙያዎች ሊያግዙት ስለሚችሉ፣ በሩን በሰፊው ከፍቶ አዳዲስ የፖሊሲ አማራጮች ላይ ማተኮር አለበት፡፡ ጦርነት ከሚያስከትላቸው ችግሮች መካከል አንዱ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ማድረቅ ሲሆን፣ የአገር ውስጥ ኢንቨስትመንቱም በዚያው መጠን ይቀዛቀዛል፡፡ በዚህም ምክንያት በተለይ በከተሞች ከፍተኛ የሆነ ሥራ አጥነት ይፈጠራል፡፡ ወትሮም በሥራ አጥነት የሚሰቃዩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወጣቶች ባሉባት አገር ውስጥ፣ ለሥራ ፈጠራ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ መፍትሔ ማቅረብ ካልተቻለ ጊዜውን ጠብቆ እንደሚፈነዳ ቦምብ የሚያስከትለው  መዘዝ ከባድ ነው፡፡ ሥራ አጥነትን ለመቅረፍ የሚያስችሉ መፍትሔዎች የሚገኙት በፖለቲካ ተሿሚዎች ሳይሆን፣ በዘርፉ የዳበረ ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች እንደሆነ መገንዘብ ይገባል፡፡

የዋጋ ንረትን በተመለከተ በመንግሥት በኩል ያለው አረዳድና ውሳኔ አሰጣጥ መንታ ባህሪያት ይታዩበታል፡፡ በአንድ በኩል በባለሙያዎች የሚታገዙ ተቋማት ዕርምጃዎች ጅምራቸው መልካም ቢሆንም፣ በሌላ በኩል ደግሞ ለዋጋ ንረት መባባስ የተወሰኑ አካላትን ተጠያቂ በማድረግ ከእውነታው የሚሸሹ ሹማምንትና ተቋማት መኖራቸው በራሱ ችግር ነው፡፡ የዋጋ ንረቱን ለመግታት ለፋይናንስ ዘርፉ የወጡ የተለያዩ መመርያዎች በተለይ ብድር ለተወሰነ ጊዜ ማገድ፣ የባንኮችን ተቀማጭ ብድር መጠባበቂያ መጨመር፣ የቦንድ ግዥ፣ የገንዘብ ዝውውር እንቅስቃሴን መቆጣጠርና የመሳሰሉት ለጊዜው አዋጭ ቢመስሉም፣ በፋይናንስ ዘርፉ ላይ የሚያስከትሉት መዘዝም ሊታሰብበት ይገባል፡፡ የማሻሻያ መመርያዎቹ ትንፋሽ ለመስጠት ያግዛሉ ቢባልም፣ በተለይ የባንክ ብድሮች ታግደው ሲቆዩ በባንኮቹ ላይም ሆነ በኢኮኖሚው ላይ የሚፈጠረው ጫና ከባድ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ የዋጋ ንረቱ ጉዳይ አቅርቦትና ፍላጎትን ለማመጣጠን የሚያግዙ ሥራዎች ላይ ማተኮር የግድ መሆን አለበት፡፡ የወጪና የገቢ ንግዱን ሰፊ ክፍተት ለማጥበብ የኢምፖርት ዕቃዎችን በአገር ውስጥ መተካትና መሠረታዊ የፍጆታ ምርቶችን በብዛት ማምረት፣ የግብርናውንና የአገልግሎት ዘርፎችን ለከፍተኛ ዕድገት የሚያነሳሱ የፖሊሲ ለውጦች ያስፈልጋሉ፡፡ በጊዜያዊነት የዋጋ ንረቱን ለመከላከል ሲታሰብ የስግብግቦችና የአሻጥረኞች ችግር ይታወቃል፡፡ ለዚህም ዋነኛ ምክንያቱ የሰላም ዕጦት በመሆኑ አስተማማኝ ሰላም ማስፈን ያስፈልጋል፡፡

በሰሜን የአገሪቱ ክፍል እየፈሰሰ ያለው ደምና የንብረት ውድመት በፍጥነት ካልቆመ፣ የሕዝብ ደኅንነትና የአገር ህልውና ከባድ ቀውስ ያጋጥመዋል፡፡ ከዚህም አልፎ ተርፎ ማዕቀብ ለመጣል እያስፈራራች ያለችው አሜሪካና ማዕቀቡን የምትቃወመው ቻይና፣ በኢትዮጵያ ምክንያት ፍጥጫ ውስጥ ሊገቡ እንደሚችሉ ምልክቶች እየታዩ ነው፡፡ ሁለቱ ልዕለ ኃያላን የኢትዮጵያን ቀውስ ምክንያት አድርገው የቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን ዓይነት ፍጥጫ ሲጀምሩ፣ ኢትዮጵያ የውክልና ጦርነት አውድማ ልትሆን እንደምትችል መገንዘብ ይገባል፡፡ ይህ ጦርነት ይዞት የመጣው ጦስ ውጤቱ የንፁኃንን ደም በማፍሰስ፣ በማፈናቀልና የአገር ሀብት በማውደም ብቻ ሳይሆን የሚለካው፣ ኢትዮጵያን ከዚህ ቀደም ዓይታው የማታውቀው አዘቅት ውስጥ ሊከታት ስለሚችል የተጠኑ የመፍትሔ አማራጮች ላይ ማተኮር ያስፈልጋል፡፡ ሁለት ኃያላን ጥቅማቸውን አስልተው ሲነሱ የሚያስተባብሯቸው ሌሎች አካላትም የራሳቸውን ፍላጎት ይዘው ስለሚንቀሳቀሱ፣ ኢትዮጵያውያን ይህንን ከባድ ጊዜ ለመሻገር የሚያስችል አንድነት ከማጠናከር ጎን ለጎን መፍትሔውም ላይ በጋራ መምከር ይጠበቅባቸዋል፡፡ የሚደራጀው አዲሱ መንግሥትም ይህንን ሥጋት በመገንዘብ ከወዲሁ ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ዝግጅቱም ‹‹ሲሮጡ የታጠቁት ሲሮጡ ይፈታል›› እንዳይሆን፣ ለባለሙያዎች ምክረ ሐሳቦች ጆሮውን ማዋስ አለበት፡፡ ኢትዮጵያ ከገባችበት አደገኛ ምስቅልቅል ውስጥ መውጣት አለባት፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብም ከአዲሱ የመንግሥት አስተዳደር ብዙ ነገሮች እየጠበቀ ነው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የፖለቲካ ፓርቲዎች ከእንቆቅልሽ ጨዋታ ውስጥ ውጡ!

በወርኃ ሚያዝያ ተካሂዶ የነበረው ውይይት ቀጣይ ነው የተባለው መድረክ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩንና የተፎካካሪ ፓርቲዎችን እንደገና ሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም. አገናኝቶ ነበር፡፡ መንግሥትን የሚመራው...

ለልዩነት ዕውቅና የማይሰጥ ፖለቲካ ፋይዳ ቢስ ነው!

በፍርኃትና በሥጋት የተኮማተረ አገር ለመለወጥም ሆነ ለማደግ ዝግጁ መሆን አይችልም፡፡ አጉል ድፍረትና ምግባረ ብልሹነት በተንሰራፋበት ስለነፃነት መነጋገር አይቻልም፡፡ ፍርኃት እንደ ወረርሽኝ አገር ምድሩን አዳርሶ...

ለሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎቶች ልዩ ትኩረት ይሰጥ!

በዚህ ዘመን ለሰው ልጅ የሚያስፈልጉ ነገሮች ብዛታቸው እየጨመረ ቢመጣም፣ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን መሠረታዊ የሚባሉ ፍላጎቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ሊቸራቸው ይገባል፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ...