Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ስንት ጉድ ይሰማ?

በጎዳናው ላይ ዓይናችንን ተክለን በቅጽበት የተሰወሩትን ታክሲዎች እንጠብቃለን። የዛሬው ጉዟችን ከፒያሳ ወደ ቦሌ ነው። ከአሁን አሁን እንደ መና ዱብ ሲሉ ለመያዝ ሰው በንቃትና በአንክሮ ሁኔታዎችን ያጠናል። አጠገቡ ያለውን ሰው አቅምም በዓይኖቹ ሚዛን ይሰፍራል። መቼም የዘንድሮ ሰው ስለ ክብደቱ ባያነሱበት ደስ ባለው። የመንገድ ዳር ሚዛኖች መብዛታቸው ሰው በየዕለቱ የሚደርስበትን ማነስ እየተመዘነ እንዲረዳው ይመስላል። የሚገርመው ምን መሰላችሁ? እነዚህ ሚዛኖች እንደ ሥጋ ቤት ወይም እንደ አትክልት ተራ ሚዛን ኪሎ ይሰርቃሉ መባሉ ነው። ከሌላውስ ይሁን እንበልና እንተወው፡፡ ከሰው ላይ ኪሎ ሰርቀው ምን ሊረባቸው? ለሚለው ጥያቄ መልሱ ሰውዬው እንደገና ሌላ ሚዛን ወይም እዚያው ሚዛን ላይ ከፍሎ እንዲመዘን ለማድረግ ነው ሲባል ሰማሁ። አሁን ይኼን የሥራ ፈጠራ ወይስ ፈለጣ ትሉታላችሁ? ምንም ሊባል ይችላል!

ቀና ብዬ ወደ ተሰበሰቡት ሰዎች ሳይ የትራንስፖርት ችግር ምን ያህል እየተባባሰ እንደመጣ ተገነዘብኩ። አጠገቤ የቆመው አንዱ በምሬት፣ ‹‹ስንቱን እናስብ ይሆን? ወጥተን መግባታችን እኮ ራሱ አብስትራክ ነው…›› እያለ ከራሱ ጋር ያወራል። አብዶ ሳያሳብደኝ ብዬ ስሸሸው አንዱ ደግሞ፣ ‹‹ወይ ታክሲና ጊዜ? ተለምነን እንዳልተሳፈርን እንዲህ ህልም ይሁንብን?›› እያለ ብቻውን ይለፈልፋል። የባሰ አታምጣ እኮ ነው፡፡ ብዙ ከመቆሙ የተነሳ እዚያው ፊኛውን የሚያቀለውን የሰው ብዛት ሳይ የከተማዋ ፅዳት አሳሰበኝ፡፡  አያድርስ ነው እንጂ የሚባለው እንደ እኔ ሐሳብ ከሆነማ፣ ሰው ፊቱን አዙሮ የሚለቀው ነዳጅ ነው ተብሎ እንዳይቀላቀል ያስፈራል። ምን ታደርጉታላችሁ? ቀላቃይና ቀልቃላ በበዛበት ጎዳና!

ይኼኔ አንድ ባዶ ታክሲ ሲከንፍ ወደ እኛ መጣ። ሁላችንም ሠልፉን ትተን ግር ብለን ወደ ታክሲው ተጠጋን። መጠጋጋታችን ሲጨምር ፍትጊያውና አቅም መፈታተሹ ተጀመረ። መሀል በመግባት ሳንዱች የሆነ ተጋፊ፣ ‹‹ዘንድሮ እኮ በኅብረት ካልሆነ ግለሰብ ምን በልቶ ብቻውን ይችለዋል? ጎበዝ እስኪ ሆበሉና እነዚህኛዎቹን ወደዚያ እናባር…›› እያለ ክንድ ያስተባብራል። ሌሎች ግን የሰሙትም አይመስልም። የኩራተኛው ወያላ እጆች በሩን አንሸራተው እስኪከፍቱት ይቁነጠነጣሉ። ከመክፈቱ በፊት ከመካከላችን አንዱ፣ ‹‹ሞባይሌን… ኪሴን…››  እያለ መጮህ ጀመረ። ግርግሩ ቆመና ሁላችንም ወደ ሰውዬው ዞርን፡፡ ሰውዬው ሌባ የተባለውን ሰው እጅ ይዞ ከእነ ሞባይሉ እያሳየን፣ ጩኸቱ ከንቱ እንዳልነበር ያረጋግጥልናል። ሌባው እየተቁለጨለጨ፣ ‹‹በቃ ከነቃህ ይቀራል ልቀቀኝ…›› ይለው ጀመር። ‹‹አለቅም ሌባ፣ ደግሞ አፍ አለኝ ብለህ ታወራለህ?›› ይለዋል መልሶ። ‹‹አፍማ ኖሮኝ መብላት አቅቶኝ ነው የሰረቅኩህ፣ በቃ ልቀቀኝ አሁን…›› እንደ መቆጣት እያለ ተናገረ። ‹‹ሌባ ተይዞ ዱላ ጥየቃ… አትለውም እንዴ?›› እያለ አንዱ ሊያጋድል ይተጋል። ግርግሩ ሲቀዘቅዝ መቀመጫችንን ያዝን። ሰው እንዲህ ነገር ማወሳሰብ ብሶበት አረፈው? ኧረ ያስፈራል አሁንስ!

ታክሲያችን ጉዞውን ጀምሮ ግስጋሴውን ቀጥሏል። ወያላችን ሒሳቡን በፍጥነት እየሰበሰበ አሥር ጊዜ ወደ መስኮቱ ይሳባል። ትርፍ ለመጫን እንቋመጠ የተረዳው ሾፌር ደግሞ፣ በማስጠንቀቂያ መልክ በዓይኑ እየደጋገመ ያስተውለዋል። ታክሲያችን በዋናው የቦሌ አውራ መንገድ እየፈሰሰ ነው። ‹‹ከፊት ከፊት የቆመው ሕንፃ ስንቱን ጉድ ሸፍኖ ይዞልናል እባካችሁ?›› አለ አንድ ጎልማሳ። አጠገቡ የተቀመጠች ወጣት ደግሞ፣ ‹‹ምን ዋጋ አለው የተቀደደ የውስጥ ልብስ እየለበሱ ውዱን ከላይ ቢደርቡበት? ከሠራን አይቀር ከውስጡ ጀምረን ነበር ጥሩ የሚሆነው…›› ብላ ቆዘመች። እንዴት አትቆዝም? እዚህ አገር አስቦ መሥራትና አስቦ አለመጨረስ እኩል አድካሚ ነው። ‹‹ዓለም ዘጠኝ ናት ሲባል አፍሪካ አንድ መሆኗንም እንጃ?›› ያለኝ ወያላ ትዝ አለኝ። ስንቱ ይታወሳል!

ወዲያው አንድ እናት ዘንቢላቸውን አንጠልጥለው ተሳፈሩ። ገና ከመቀመጣቸው፣ ‹‹ተመሥገን፣ ተመሥገን ጌታዬ፣ ለቀሪው ዘመኔ ደግሞ አንተ ታውቃለህ…”›› እያሉ ምሥጋናውን ያዥጎደጉዱት ጀመር። ምሥጋናቸው ለምን እንደሆነ ያልገባው ወያላ፣ ‹‹እማማ ምነው ምን ተገኘ?›› አላቸው። ‹‹ከዚህ በላይ ዓለም የት አለ? ድሮ ከዚህ ከጉልቱ አንዳንዱን ነገር ሸማምቼ ታክሲ ለመሳፈር መከራ ነበር። አሁን ይኼው ገና ብቅ ከማለቴ መንደር ውስጥ አግኝቼው ተሳፈርኩበታ…›› አሉት። ‹‹ይገርማል እኮ፣ እኛ ስንት ሰዓት ሙሉ የጠበቅነው ታክሲ ለእሳቸው በሰከንድ ይድረስላቸው? አጀብ አያሰኝም?›› ይለዋል ከኋላዬ የተቀመጠው ሰው አብሮት ላለው ጓደኛው። አሁን ይኼ የአርባ ቀን ዕድል ይባል ይሆን? እንጃ!

ሾፌሩ በትንሹ ከከፈተው ሙዚቃ እኩል እያቀነቀነ ‹‹አይ ቦሌ?! ሃ…ሃ..ሃ.. ቦሌና ምቾቷ… ምን ይሻላት ይሆን ቦሌ…›› እያለ ያሾፋል። እኛም እናዳምጠው ጀመርን። ወያላው፣ ‹‹ምን ታደርገዋለህ? ትዳር ጫናው ሲበዛ ያስለፈልፋል ሲባል አልሰማህም? ወይስ አታውቀውም? ለነገሩ አንተን አጋቡህ እንጂ ገና ምኑ ገብቶህ…›› ብሎ አሾፈበት። ወሬው ከሾፌሩ መነሻ ሐሳብ ጋር  ባይጣጣምልንም፣ ወያላው የሾፌሩን በግድ መዳር ሲዳስስልን ዘና እንደ ማለት አልን። ሾፌሩ ተናዶ፣ ‹‹አሁን ይኼን ከቦሌ ጋር ምን አገናኘው? ወገኛ ነገር ነህ…›› ቢለው፣ ‹‹ቦሌና ወዳጆቿ እንዲህ ባለው ምቾት እንደተጎዱ ማን ተጎዳ?›› ብሎ ተያያዥነቱን ሲያስረዳው አንዱ ተሳፋሪ፣ ‹‹አሁን ይኼ ዘመን ያለፈበት ወሬ ምን ይረባል ብለህ ነው›› እያለ ሲማረር አዛውንቷ ሰሙት፡፡ ሰምተውትም፣ ‹‹አይዞህ ልጄ፣ ዘመናት የነጎዱት በከንቱ ወሬዎች ስንታሽ ነው። መጪው ጊዜ ግን ከወሬ ተላቀን ካልሠራንበት አይታገሰንም። ስለዚህ ከዘመኑ እኩል ለመራመድ ዘመናዊ አስተሳሰብ ተላበሱ…›› ሲሉን እየተገረምን ሰማናቸው። የግድ ነው!

ታክሲያችን ወደ ቦሌ እየተቃረበ ሲመጣ ከጨዋታው ተገልሎ የነበረው ወያላ አንገቱን ቀና አድርጎ ወደፊት እያየ ለሾፌሩ፣ ‹‹አየኸው? አየኸው?›› እያለ መናገር ጀመረ፡፡ ሾፌሩ ዓይኖቱን መንገዱ ላይ ሰክቶ፣ ‹‹ምኑን ነው የማየው?›› አለው፡፡ ወያላው ዓይኖቹ እንደፈጠጡ፣ ‹‹ትራፊኩን ነዋ…›› እያለ ወደ ታች መደበቅ ጀመረ፡፡ ሾፌሩ መሪውን በቡጢ እየጠለዘ፣ ‹‹ትርፍ አትጫን ስልህ ጉድ ትሠራኝ?›› እያለ ሲጮህ ታክሲው በፀጥታ ተሞላ፡፡ እንዳጋጣሚ ትራፊክ ፖሊሱ ለመንገዱ ጀርባውን ሰጥቶ ስለነበር በሾፌሩና በወያላው ላይ የመጣው መዓት ለጊዜውም ቢሆን በረድ አለ፡፡ እኚያ እናት ግን ሁኔታውን ገምግመው ሰላም መውረዱን ካረጋገጡ በኋላ፣ ‹‹ምናልባት እንደ ኳስ ተጫዋቾቹ እየተናበባችሁ ብታጠቁና ብትከላከሉ?›› ሲሉ ፀጥታው ደፍርሶ ሳቅ በሳቅ ሆንን፡፡ ‹‹እውነቴን እኮ ነው እነዚህ እነ ማን ናቸው…›› ብለው ቆም ሲሉ፣ አንዱ ጣልቃ ገብቶ፣ ‹‹ቡናና ጊዮርጊስ?›› አላቸው፡፡ አዛውንቷ እየተቆጡ፣ ‹‹ኧረ ወዲያልኝ እኔ ያልኩት ኳሷን በደንብ እየተጫወቱ ስለሚያዝናኑን ስለሜሲና ስለሮናልዶ ነው እንጂ፣  በኳስ ስለሚራገጡት አይደለም…›› ሲሉት ሳቅን፡፡ አንዱ ነገረኛ፣ “እዚህም ኳስ እዚያም ኳስ፣ እዚህም ተጫዋች እዚያም ተጫዋች…” እያለ ሲያላዝንባቸው፣ ‹‹ተናግረህ ሞተሃል እባክህ? እንቁራሪት በሬ አክላለሁ ብላ ተነፋፍታ ሞተች ሲባል አልሰማህም? ድንቄም…›› አሉ፡፡ ወያላው፣ ‹‹ማዘር ምን መሰለዎት እዚህም ከእነ ሜሲና ከእነ ሮናልዶ የሚያስንቁ ሊኖሩ ይችላሉ ማለቱ ነው እኮ…›› እያለ ሲስቅ፣ የማይበገሩት እናት፣ ‹‹መጀመርያ አቅምንና ልክን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ አለበለዚያ አማረብን ብለን እንዳናስጠላ…›› አሉ፡፡ እውነት ነው!

የአዛውንቷን ንግግር በንቃት ሲከታተል የነበረ ሌላ ተሳፋሪ፣ ‹‹ዕድሜ ለዴሞክራሲ የፈለገንን እየተናገርን እንደፈለግን እንኖራለን…›› ሲል ሌላው ከአፉ ተቀብሎ፣ ‹‹ዴሞክራሲ ስትል አንድ ነገር ትዝ አለኝ፣ አንድ ጓደኛዬ የነገረኝ ነው…›› ብሎ ዞር ዞር እያለ ሲያየን ጆሮዎቻችንን አዋስነው፡፡ ‹‹እንዲህ እንዳሁኑ ስንጨዋወት የዴሞክራሲ ነገር ተነሳ፡፡ ከዚያ ያ ያልኩዋችሁ ሰው የእኛ ዴሞክራሲ ግራ ጎኑ ከቻይና ሲሆን፣ የቀኝ ጎኑ ደግሞ ከአሜሪካ ነው አለን፡፡ ፊትና ጀርባውስ ብለን ስንጠይቀው፣ ከፊት በኩል ከፈረንሣይ ከኋላው ደግሞ ከእንግሊዝ ነው አለን…›› ብሎ ሲስቅ፣ አዛውንቷ ደግሞ፣ ‹‹ቆይ… ቆይ…›› አሉትና ሳቁን አቋረጡት፡፡ እኚህ አዛውንት መቼም ጨዋታውን ይችሉበታል፡፡ ‹‹ሌላውን በሙሉ ከነገረህ የዴሞክራሲያችን ጭንቅላት ከየት ነው አለህ?›› ብለው ሲጠይቁት፣ ‹‹አይ እማማ ይህንንስ አልነገረንም…›› አላቸው፡፡ አዛውንቷ ሳቅ እያሉ፣ ‹‹ቀጣፊ በለው፣ ዴሞክራሲያችን እንደ ዘመኑ መኪና እንዴትና ከየት እንደተገጣጠመ ከነገረህ ጭንቅላቱ አፍሪካዊ መሆኑን እንዴት አጣው?›› ሲሉት ታክሲው በሳቅ ጎርፍ ተጥለቀለቀ፡፡ በዚህ መሀል ወያላው፣ ‹‹መጨረሻ…›› ባይለን ኖሮ ስንት ጉድ ይሰማ ነበር? መልካም ጉዞ!

 

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት