Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

​​​​​​​‹‹የከተሞች መስፋፋት ጎርፍን ያስከትላል›› ሰለሞን ገብረዮሐንስ (ዶ/ር)፣ የዋተር ኤንድ ላንድ ሪሶርስ ሴንተር የሪች ግሎባል ሪሰርች ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ

በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኘውን ማኅበረሰብ ያማከለና በተለያዩ ሦስት የምርምር ርዕሶች ላይ ትኩረት ያደረገ ፕሮጀክት ቀርፆ፣ ለተግባራዊነቱ ዕውን መሆን ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ የሚያደርገው ሪች ግሎባል ሪሰርች ፕሮግራም ነው፡፡ ፕሮግራሙ በኢትዮጵያ፣ ኬንያና ባንግላዴሽ የሚከናወን ሲሆን፣ ትግበራውም በየአገሮቹ ካሉት አጋሮቹ ጋር በመቀናጀት ይከናወናል፡፡ የኢትዮጵያ አጋሩና ፕሮጀክቱን የሚያከናውንለት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ‹‹የወተር ኤንድ ላንድ ሪሶርስ ሴንተር›› ሲሆን፣ የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ደግሞ ሰለሞን ገብረዮሐንስ (ፒኤችዲ) ናቸው፡፡ በፕሮጀክቱ አተገባበር፣ አፈጻጸምና ተዛማጅ በሆኑ ጉዳዮችን አስመልክቶ ሥራ አስኪያጁን ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የሪች ግሎባል ሪሰርች ፕሮግራም አመሠራረትና የሥራ ድርሻ ቢያብራሩልን?

ዶ/ር ሰለሞን፡- ሪች ግሎባል ሪሰርች ፕሮግራም ዋና መሥሪያ ቤቱ በእንግሊዝ ሲሆን፣ የተቋቋመውና በሦስት አገሮች የኢትዮጵያ፣ ኬንያና ባንግላዴሽ የምርምር ሥራ የጀመረው በ2007 ዓ.ም. ነው፡፡ ፕሮግራሙን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚመራው ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ሆኖ፣ በፋይናንስ የሚደግፈው ደግሞ ዲኤፍአይዲ ዩኬ (የእንግሊዝ ዓለም አቀፍ የልማት ተቋም) ነው፡፡ ሦስቱም የምርምር ሥራዎች እየተከናወኑ ያሉት በአዋሽ ተፋሰስ ላይ ነው፡፡ ከእነዚህም መካከል አንደኛው የውኃ ጤንነት/ጥራቱን የተመለከተ ነው፡፡ ሁለተኛው ርዕስ የአየር ጠባይ ለውጥ (ክላይሜት ሪዘሊያንስ) የሚያመጣውን ተፅዕኖ ተቋቁሞ ማለፍ የሚቻልበትን ያለመ ነው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ማኅበራዊ ሳይንስ ይህም ማለት በቤተሰብና በማኅበረሰብ መካከል በሚታየው ልዩነት ላይ ያተኮረ ነው፡፡ በተጠቀሱት የምርምር ርዕሶች ላይ ያለመ ጥናት፣ ምርምርና ትንተና ከተሠራ በኋላ ግኝቱ በሳይንቲፊክ ጆርናል ወጥቷል፡፡ ምርምሩ የተከናወነው በአዋሽ ተፋሰስ ላይ ነው፡፡ ምርምሩን ለማከናወንና ዳር ለማድረስ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት፣ የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ የውኃና ፍሳሽ አገልግሎትና ሌሎች በውኃ ዙሪያ የሚሠሩ ተቋማት የማይናቅ ዕገዛና ትብብር አድርገዋል፡፡ 

ሪፖርተር፡- በውኃ ጤንነትና በአየር ጠባይ ለውጥ ላይ የተከናወኑ ምርምሮችንና በዚህም የተደረሱባቸውን ግኝቶች ቢያብራሩልን?

ዶ/ር ሰለሞን፡- አንድ መታወቅ ያለበት ነገር ቢኖር የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለው ተፅዕኖ ወይም እንቅፋት ድርቅና ኃይለኛ ጎርፍ ማስከተሉ ነው፡፡ ድርቅ ደግሞ የምንጭና የጉድጓድ ውኃ መጠን እንዲቀንስ ያደርጋል፡፡ የውኃ መጠን የመቀነሱ ሁኔታ እየበዛና እየሰፋ ሲሄድ የኬሚካልና ባዮሎጂካል ሰብስታንስ ከበፊቱ በእጥፍ ወይም በባሰ መልኩ ውኃ ውስጥ የመገኘት ሁኔታ ይታይባቸዋል፡፡ በዚህ መልኩ ያለውን ውኃ መጠቀም ደግሞ ለጤንነት መታወክ ይዳርጋል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የወቅቶች መለዋወጥ ከድርቅና ከጎርፍ በበለጠ ቤተሰብ ውኃ ተደራሸነት ላይ እንቅፋት ይፈጥራል፡፡ በሴቶች ላይ የሚያደርሰውም ጫና ኃይለኛ ነው፡፡ በእርሻ ላይም ችግር መፍጠሩ አያጠያይቅም፡፡ ምክንያቱም የሚጠበቀውና የሚፈለገው ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ መጣል ሲገባው፣ ወይም ቀድሞ ወይም ዘግይቶ ሊመጣ ይችላል፡፡ የመስፋት፣ የመጥበብ ሁኔታም ይታይበታል፡፡ ይህ ዓይነቱም ሁኔታ ከመጠጥ ውኃ ላይ ከሚያሳድረው ተፅዕኖ ባሻገር ለእርሻም ተስማሚ እንዳልሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡   

ሪፖርተር፡- የምንጭና የጉድጓድ ውኃ በዚህ መልኩ ከተበከሉ የተጠቃሚዎች ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል? የሚለውን በምርምሩ ታይቷል?

ዶ/ር ሰለሞን፡- የምንጭና የጉድጓድ ውኃ በአብዛኛው የሚጠቀሙ በገጠር የሚገኙ ቤተሰቦችና አንዳንድ ኢንዱስትሪዎች ናቸው፡፡ የውኃዎቹ መበከል ደግሞ ተጠቃሚ የሆኑ ቤተሰቦችን ለከፋ የጤንነት ጉዳት እንደሚዳርጋቸው አያጠያይቅም፡፡ በተለይም ሴቶች ለከፋ እንግልት ይዳረጋሉ፡፡ ይህም የሚሆነው ውኃ ፍለጋ ብዙ ኪሎ ሜትር በእግራቸው ስለሚጓዙ ነው፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ከተበከለው የምንጭና የጉድጓድ ውኃ በስተቀር ሌላ አማራጭ ስለሌላቸው ነው፡፡ ይህንን ለማስተካከል ወይም ሌላ የውኃ አገልግሎት ለመፍጠር የሚያስችላቸው የፋይናንስ ምንጭ ከሌላቸው ችግሩ ይወሳሰብባቸዋል፡፡ ለከፋ አደጋም ይጋለጣሉ፡፡ ኢንዱስትሪዎች ግን በቂ የሆነ የፋይናንስ ምንጭ ስላላቸው ሌላ የጉድጓድ ውኃ አስቆፍረው ሊጠቀሙና የተለያዩ የተደራሽነትን ሁኔታ ሊያመቻቹ ይችላሉ፡፡   

ሪፖርተር፡- ጎርፍ የሚያስከትለው ጉዳት በምርምሩ ወቅት እንዴት ነው የተገመገመው?

ዶ/ር ሰለሞን፡- ጎርፍ በተከሰተ ቁጥር ከመኖሪያ ቤትና ከተለያዩ ፋብሪካዎች የሚወጣው ፍሳስ ቆሻሻ ጠራርጎ ይወስድና ወደ መኖሪያ አካባቢና እርሻ ላይ እንዲንጣለል ያደርጋል፡፡ ወንዞችንም ይበክላል፡፡ ጨዋማ የሆኑ ትንንሽ ሐይቆችም በተለይ በዚሁ ጎርፍ አማካይነት በየእርሻ ውስጥ እየፈሰሱ ቦታው ለእርሻ ተስማሚ እንዳይሆን ያደርጉታል፡፡ በምርምሩ ሥራ ላይ የታየው አንድ ትልቁ ነገር ቢኖር የአየር ንብረት ለውጥ ሕዝብ ላይ ከሚያሳደረው ተፅዕኖ ባላነሰ የከፋ እንቅፋት የሚፈጥረው የከተሞች መስፋፋት መሆኑ ነው፡፡ ይህም ማለት ከተሜነት ወይም የከተሞች መስፋፋት ለጎርፍ መከሰት መንስዔ መሆኑ ነው፡፡ በተለይ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ከተያያዘ አደጋውን በእጥፍ ያባብሰዋል፡፡ የከተሞች መስፋፋት ማለት መሠረተ ልማቶችን ማስቀመጥ ብቻ ሳይሆን ተፈጥሯዊ ነገሮችን ሁሉ እንደሚቀንስ ወይም እንደሚያጎሳቁል መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ዝናብ ድንገት ጠብ ቢል የሚገባበትን ያጣና መሬት ላይ ጎርፍ ሆኖ ይፈሳል፡፡  

ሪፖርተር፡- ጥናቶች የተከናወኑት በአዋሽ ተፋሰስ ላይ እንጂ በከተማ ላይ አይደለም፡፡ ይህ እስከሆነ ድረስ የከተሞች መስፋፋት ለጎርፍ መንስዔ መሆናቸው እንዴት ሊታወቅ ቻለ?

ዶ/ር ሰለሞን፡- የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም በተመለከተ በአዋሽ ተፋሰስ ላይ የተከናወነው ምርምር የደረሰባቸው ግኝቶች ወይም ውጤቶች እንደ ክልል ወይም አንድ አገር አቀፍ የሚታዩበት ሁኔታ አለ፡፡    

ሪፖርተር፡- በምርምር የተደረሰባቸውን ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ምን መደረግ አለበት የሚለው ታይቷል?

ዶ/ር ሰለሞን፡- አዎ! ታይቷል፡፡ ለተጠቀሱት ችግር አንድ መፍትሔ ተደርጎ የታየው የተቀናጀ አስተዳደራዊ ሁኔታ መፍጠርን ነው፡፡ ሌላው የመፍትሔ አቅጣጫ ደግሞ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ ወይም ጉዳት የሚጠቁም መረጃን ለተለያዩ ማኅበረሰቦችና አካላት ማድረስ፣ የአየር ንብረት ለውጥን ሊያመጡ የሚችሉ የተለያዩ ግብዓቶችን ማሳየት የሚሉና ሌሎች ይገኙባቸዋል፡፡  

 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

አደራውን ለመጠበቅ ዕድል ያላገኘው ቅርስ ባለአደራ

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማኅበር ከተመሠረተ ሦስት አሥርት አስቆጥሯል፡፡ ማኅበሩ በእንጦጦ ተራራማ ቦታዎች በአደራ በመንግሥት በተረከበው 1,300 ሔክታር መሬት ላይ የተለያዩ አገር በቀል ዛፎችን በመትከል...

ብዝኃ ትምህርቱን ‹ስቴም› ለማስረፅ

ስሜነው ቀስቅስ (ዶ/ር) የስቴም (Stem) ፓውር ግብረ ሰናይ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተርና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የቴክኖሎጂ አማካሪ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የማስተርስና የፒኤችዲ...

‹‹እውነታውን ያማከለ የሥነ ተዋልዶ ጤና ግንዛቤን ማጠናከር ያስፈልጋል›› ደመቀ ደስታ (ዶ/ር)፣ በአይፓስ የኢትዮጵያ ተወካይ

በሥነ ተዋልዶ ጤና ጉዳዮች ላይ በመሥራት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሰው አይፓስ፣ የኢትዮጵያን ሕግ መሠረት አድርጎ በሴቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና ከጤና ሚኒስቴርና ከክልል ጤና ቢሮዎች...