Wednesday, July 24, 2024

ኢትዮጵያ ከገባችበት አረንቋ ውስጥ በፍጥነት ትውጣ!

ከሰሜን የተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እየተሰሙ ያሉ ሰቆቃዎች ይረብሻሉ፡፡ ንፁኃን በየቀኑ እየተገደሉ፣ እየተፈናቀሉና ጥሪታቸው እየወደመ ነው፡፡ የሕፃናትና የእናቶች፣ የአረጋውያንና የአቅመ ደካሞች ጩኸት ከመቼውም ጊዜ በላይ አድማሱን እያሰፋ ነው፡፡ ከትግራይ ጀምሮ እስከ አማራና አፋር ክልሎች ድረስ በሕዝባችን ላይ እየደረሰ ያለው መከራ በጊዜ መፍትሔ ካልተፈለገለት፣ የአገር ህልውና ሥጋቱ እየጨመረ ቀውሱ ከቁጥጥር ውጪ ሊሆን ይችላል፡፡ ኢትዮጵያ ያለችበት አስጨናቂ ውጥረት የሚያሳስባቸው ባዕዳን ሳይቀሩ፣ ይህ ከባድ ጊዜ አገር ሊያፈርስ እንደሚችል እያስጠነቀቁ ነው፡፡ በጦርነቱ ቀጣና ውስጥ ያሉ ወገኖች ይህ ሁሉ መከራና ውርጅብኝ ውስጥ ሆነው መፍትሔ አለማፈላለግ የታሪክ ተጠያቂነት ያስከትላል፡፡ የአሜሪካ ባለሥልጣናትም ሆኑ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የተለያዩ ሹማምንት በተደጋጋሚ፣ ወታደራዊ ፍልሚያው አዋጭ እንዳልሆነና ድርድር እንዲጀመር እያሳሰቡ ነው፡፡ የመንግሥት ተቀዳሚ ኃላፊነት የአገርን ሰላምና የሕዝብን ደኅንነት መጠበቅ በመሆኑ፣ ይህ ጦርነት በፍጥነት የሚጠናቀቅበትንና ሰላምና መረጋጋት የሚፈጠርበትን መፍትሔ ማምጣት ይጠበቅበታል፡፡ ጦርነቱ እየተስፋፋ፣ ዕልቂቱና ውድመቱ እየተባባሰ የሚቀጥል ከሆነ ግን መጪው ጊዜ ተስፋ አይኖረውም፡፡ ለአገር ይበጃል የሚባል መፍትሔ እንዲመጣ ከሃይማኖት መሪዎች፣ ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከልሂቃን፣ ከንግዱ ማኅበረሰብ አባላት፣ ከሲቪል ማኅበራት ተወካዮችና ከሌሎችም የኅብረተሰብ ክፍሎች ወኪሎች ጋር በመምከር አገር በቀል መፍትሔ ማፈላለግ ይገባል፡፡

ኢትዮጵያ የገጠማት ፈተና እንዲወገድ ከእልህና ከስሜታዊነት በላይ ምክንያታዊ አማራጮች ላይ ማተኮር ያስፈልጋል፡፡ የፖለቲካ አለመረጋጋት ግጭት ጋብዞ ከፍተኛ ዕልቂትና ውድመት ሲደርስ፣ መፍትሔ የሚገኝባቸው አማራጮችን መዘንጋት የሚያስከትለው መዘዝ ከፍተኛ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን በተለያዩ ማንነቶችና ባህሎች ውስጥ የራሳቸው የሆኑ በርካታ አገር በቀል የግጭት አፈታት ዘዴዎች አሉዋቸው፡፡ በእልህና በግትርነት ምክንያት ካልሆነ በስተቀር እነዚህን ውጤታማ ዘዴዎች በመናቅ፣ የባዕዳንን ገላጋይነትና ጣልቃ ገብነት መጠበቅ ሞኝነት ነው፡፡ ማንም ይሁን ማን በዕርቅና በግልግል ስም ይዞ የሚመጣው የተጠና ጥቅሙን ነው፡፡ ጥቅምን ለማስከበር ሲባልም በቀላሉ ሊፈታ የሚችል ችግርን በማወሳሰብ ለትውልድ የሚተላለፍ ጠባሳ ይተዋሉ፡፡ ኢትዮጵያዊያን አገራቸው ከገባችበት አደገኛ ማጥ ውስጥ ለማውጣት የሚበጀውን ነገር ከማድረግ ወደኋላ ማለት የለባቸውም፡፡ መንግሥትም ቢሆን ግራና ቀኙን አማትሮ ውሳኔ ላይ መድረስ የሚችለው፣ በኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎት ላይ መሆን ስለሚገባው ከማኅበረሰቦች ተወካዮች ጋር ምክክር ያድርግ፡፡ ምክክሩም በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ላይ ያተኮረና እውነተኛ መፍትሔ የሚፈልግ ይሁን፡፡ የጦርነቱ የመከራ ገፈት ቀማሽ የሆኑ ወገኖች ለማሰብ የሚከብድ መከራ ውስጥ ሆነው ዘና ማለት አይቻልም፡፡ ከጦርነቱ ወላፈን በተጨማሪ ረሃብና ጠኔ እያሰቃያቸው ጊዜ መስጠት አያስፈልግም፡፡

አሁን አጣዳፊው ጉዳይ ኢትዮጵያን ከገባችበት አረንቋ ውስጥ መንጭቆ ማውጣት ነው፡፡ ከዚህ አጣዳፊ ጉዳይ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ሌሎች ነገሮች ስለማይኖሩ፣ መላ ኢትዮጵያዊያንም ሆኑ መንግሥት የመፍትሔውን መንገድ ለማመላከት መረባረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ በልማትና በዕድገት ወደፊት መገስገስ የምትችለው ሰላምና መረጋጋት ሲሰፍን ነው፡፡ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ደግሞ ሁለገብ የሆነ ጥረት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ጥረት ለግጭትና ለውድመት መንስዔ ሊሆኑ የሚችሉ የፖለቲካ አለመግባባቶችን ወደ ውይይትና ድርድር ጠረጴዛ መውሰድ፣ በቅራኔ የተወጠሩ ግንኙነቶችን ማርገብ፣ ደም መፋሰስ ውስጥ የሚከቱ ተቃርኖዎችን ማለዘብ፣ በማኅበራዊ የትስስር ገጾች የሚደረጉ የቃላት ጦርነቶችን መቀነስ፣ በሁሉም ችግሮች ላይ መግባባት ቢያስቸግርም ተቀራርቦ ለመነጋገር የሚያስችሉ ጉዳዮችን መለየትና በአገር በቀል የችግር መፍቻ ሥልቶች አማካይነት መፍትሔ ለመፈለግ መስማማት የግድ መሆን አለበት፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ከጦርነቱ በላይ ከፍተኛ ዕልቂት ሊያስከትል የሚችለው ረሃብ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወገኖቻችንን ሕይወት ሊነጥቅ እንደሚችል ማሰብ ይገባል፡፡ በአራቱም ማዕዘናት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ይህንን አደጋ የደቀነ ጊዜ ለመሻገር የሚያስችሉ አዋጭ ምክረ ሐሳቦችን እንዲያቀርቡ ዕድሉ ይሰጣቸው፡፡

ኢትዮጵያ የገባችበት ውስብስብ ፈተና እንዲህ በቀላሉ መፍትሔ ይገኝለታል ተብሎ ባይታሰብም፣ ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው ሲሉ በአንድነት መቆም ከቻሉ በርካታ አማራጮች እንደሚኖሩ መዘንጋት ተገቢ አይደለም፡፡ ጦርነት የማይፈታውን ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መሞከር አዳጋችና አታካች መሆኑ ቢታወቅም፣ እያንዣበበ ያለው አደጋ ከአገርና ከሕዝብ ስለማይበልጥ ማንኛውም ዓይነት መስዋዕትነት ተከፍሎ ሰላም መስፈን ይኖርበታል፡፡ ጥንታዊትና ታሪካዊት የሆነችው ኢትዮጵያ የጦርነት አውድማ መሆን ስለሌለባት፣ ለአገራቸው የሚጨነቁና የሚያስቡ ልጆቿ ይህ የመከራ ጊዜ በፍጥነት እንዲቋጭ የሚፈለግባቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት ይጠበቅባቸዋል፡፡ አገር በመድፍና በሮኬት እየታረሰችና ንፁኃን ያለ ጥፋታቸው እየተጨፈጨፉ ስለነገ ብሩህ ተስፋ ማለም አይቻልም፡፡ ሕይወታቸው በተዓምር የተረፉት ከድህነት ጎጆዋቸው ተፈናቅለው በረሃብ አለንጋ እየተገረፉ የተሻለ ቀን ይመጣል ብሎ መጠበቅ አይታሰብም፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ አገራቸውን የሚወዱ ዜጎችና ሌሎችም ማኅበረሰባዊ ኃላፊነት ያለባቸው ወገኖች በሙሉ፣ ይህንን ከባድ ጊዜ ለመለወጥ የሚያስችል መፍትሔ ላይ ትኩረት ማድረግ አለባቸው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ መቀጠል አይቻልም፡፡ በመላ ኢትዮጵያዊያን ትብብርና በአገር በቀል የችግር መፍቻ ዘዴዎች ከዚህ ፈተና ውስጥ መውጣት ተገቢ ነው፡፡

 ሕዝብ ራሱን በራሱ ማስተዳደር የሚችለውና የሚዳኘው፣ በገዛ ቋንቋው የሚጠቀመው፣ ባህሉንና ወጉን በነፃነት ማከናወን የሚችለውና የተለያዩ መብቶቹን የሚያስከብረው በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እንጂ፣ ጀብደኞችና ሥርዓተ አልበኞች በሚቆሰቁሱት ጦርነት አይደለም፡፡ አለመግባባት ሲኖር ጠመንጃ ከማንሳት በፊት በሰላም መነጋገር መቅደም ሲኖርበት፣ ለግለሰቦችና ለስብስቦች ፍላጎት ሲባል አገር ትመሰቃቀላለች፡፡ ኢትዮጵያዊያን ሲተባበሩ ግን ማኅበራዊ ፍትሕ ማስፈን ይቻላል፡፡ ይህም ታሪካዊ ጠላቶችን አንገት ያስደፋል፡፡ ኢትዮጵያ ሰላሟ ሲቃወስ ግን ታሪካዊ ጠላቶች ይፈነጥዛሉ፡፡ ለኢትዮጵያ ያዘጋጁት የክፋት ወጥመዳቸው ስለሠራላቸው ይቦርቃሉ፡፡ ኢትዮጵያዊያን በጠላቶቻቸው ፊት እርስ በርስ ከሚተናነቁ በአንድነት ቢሠለፉ ነው ዓለም የሚያከብራቸው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ፀፀቱ ለትውልድ ጭምር ይተርፋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጣዊ ሰላሟ እንዲታወክና ከጀመረችው ጉዞ እንድትገታ ከፍተኛ የሆነ ሴራ አለ፡፡ ኢትዮጵያዊያንም በዚህ ሴራ ተጠልፈው እርስ በርስ እንዲተላለቁ ይፈለጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ከውጭ ኃይሎች ጋር የሚተባበሩ የውስጥ ኃይሎች እንዳሉ በድርጊታቸው ተረጋግጧል፡፡ እነዚህ የውስጥ ኃይሎች የተሰጣቸውን ተልዕኮ ለማስፈጸም ማንኛውንም ሰይጣናዊ ድርጊት ከመፈጸም አይመለሱም፡፡ ኢትዮጵያ ያለችበት መከራ የዚህ ውጤት ለመሆኑ መጠራጠር አያስፈልግም፡፡ ኢትዮጵያዊያን ይህንን ሴራ ማክሸፍ የሚችሉት አገራቸውን ከማጥ ውስጥ ጎትተው በማውጣት ነው፡፡

ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያን እንደ ቅርጫ በመከፋፈል ትንንሽ አገር ለመፍጠር የሞከሩ ቅኝ ገዥዎችን ፈለግ የተከተሉ ሳይሳካላቸው ቀርተው ከመድረኩ ሲገለሉ፣ የእነሱ ወራሽ ለመሆን የሚጣጣሩ ያንኑ የማይረባ አጀንዳ እያራገቡ ሕዝብ ለማጫረስ ሴራ ጎንጉነዋል፡፡ ለዓላማቸው ስኬትም የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል፡፡ ከእነዚህ ሙከራዎቻቸው መካከል የሚጠቀሰው ከልዩነቱ ይልቅ፣ አንድነቱን አፅንቶ የኖረውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ማኅበራዊ እሴቶች ማፈራረስ ነው፡፡ እርስ በርሱ በማጋጨትና በማጋደል በጋራ የገነባቸውን ትውልድ ተሻጋሪ እሴቶቹን ለመናድ ጥረት ተደርጓል፡፡ ሕዝቡ ውስጥ እንዲህ ያለ በደል ሲፈጸም ተስፋ መቁረጥ፣ ራስን መጥላትና እንዳሻው ይሁን የሚባሉ ግዴለሽነቶች እየተፈጠሩ፣ አገር የማያባራ ግጭት ውስጥ እንድትገባ ነው ፍላጎቱ፡፡ ዕብሪትና አጉል ጀብደኝነትን ስንቅ አድርገው የተነሱ ጀብደኞች፣ ለዘመናት የተገነቡ የጋራ ማኅበራዊ እሴቶችን እየናዱ አገርን መቀመቅ የሚከቱ ድርጊቶች ሲፈጽሙ በግልጽ እየታየ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከአገር የሚቀድም የለም በማለት ለአገራቸው ህልውና የተነሱ ዜጎችን ማየት ያፅናናል፡፡ እነሱን መደገፍና ማበረታታት የመላ ኢትዮጵያዊያን ተግባር መሆን አለበት፡፡ ለአገር ብሔራዊ አንድነትና ደኅንነት ሲባል ሰላማዊ ጥረቶችን ማገዝ የግድ መሆን አለበት፡፡ ይህንን ማድረግ ካልተቻለ ግን በሚፈጠረው ችግር የጋራ ተጠያቂነት እንደሚኖር መዘንጋት አይገባም፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያን ከገባችበት አረንቋ ውስጥ ጎትቶ ማውጣት ያስፈልጋል!

 

 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የፖለቲካ ፓርቲዎች ከእንቆቅልሽ ጨዋታ ውስጥ ውጡ!

በወርኃ ሚያዝያ ተካሂዶ የነበረው ውይይት ቀጣይ ነው የተባለው መድረክ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩንና የተፎካካሪ ፓርቲዎችን እንደገና ሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም. አገናኝቶ ነበር፡፡ መንግሥትን የሚመራው...

ለልዩነት ዕውቅና የማይሰጥ ፖለቲካ ፋይዳ ቢስ ነው!

በፍርኃትና በሥጋት የተኮማተረ አገር ለመለወጥም ሆነ ለማደግ ዝግጁ መሆን አይችልም፡፡ አጉል ድፍረትና ምግባረ ብልሹነት በተንሰራፋበት ስለነፃነት መነጋገር አይቻልም፡፡ ፍርኃት እንደ ወረርሽኝ አገር ምድሩን አዳርሶ...

ለሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎቶች ልዩ ትኩረት ይሰጥ!

በዚህ ዘመን ለሰው ልጅ የሚያስፈልጉ ነገሮች ብዛታቸው እየጨመረ ቢመጣም፣ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን መሠረታዊ የሚባሉ ፍላጎቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ሊቸራቸው ይገባል፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ...