Monday, July 22, 2024

ኢትዮጵያ ከጥገኝነትና ከተመፅዋችነት ትላቀቅ!

ኢትዮጵያ ከማንኛውም ዓይነት የውጭ ተፅዕኖ መገላገል የምትችለው፣ ኢትዮጵያዊያን አገራቸው ሰላም እንድትሆን ተመሳሳይ አቋም ሲኖራቸው ነው፡፡ የውጭ ኃይሎች ጣልቃ የሚገቡትም ሆነ በተለያዩ መንገዶች የሚያስፈራሩት፣ ሰላምና መረጋጋት ጠፍቶ ዕልቂትና ውድመት በመበርከቱ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ የሚበጃት የሕዝቧ ሰላምና አንድነት ነው፡፡ ሰላምና አንድነት በመፈላለግ፣ በመከባበር፣ በመፈቃቀርና በመተሳሰብ ላይ እንዲመሠረት ከአውዳሚ ድርጊቶች መታቀብ ያስፈልጋል፡፡ ሰላምና መረጋጋት በሌለበት ዕድገት አይታሰብም፡፡ የሰላም መንገድ ተዘግቶ ጦርነቱ አድማሱን የሚያሰፋ ከሆነ፣ የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት እየተጠናከረ በራስ መወሰን ያቅታል፡፡ ኢኮኖሚው ደቆ ረሃብና እርዛት ይከተላሉ፡፡ እንኳንስ የማዕቀብ ማስፈራሪያ እየመጣ ይቅርና እንዲሁም እንደ ነገሩ የሆነው ኢኮኖሚ፣ ብዙኃኑን ሕዝብ መታደግ አቅቶት አስመራሪው ድህነት በስፋት ተንሰራፍቷል፡፡ በጦርነት ጊዜ ኢኮኖሚው እንዴት ይመራ? የዋጋ ግሽበቱን ለመቆጣጠር ምን ይደረግ? ሥራ አጥነትን ለመቅረፍ የትኞቹ ዘርፎች ላይ በስፋት ይሠራ? ለተቸገሩ ወገኖች መደረግ ካለበት ዕርዳታ በተጨማሪ ለዘለቄታዊ መፍትሔው ምን ይደረግ? የሚሉና ሌሎች መሠረታዊ ጉዳዮች ትኩረት ይፈልጋሉ፡፡  ማንም እየተነሳ ማዕቀብ ሲጥል ወይም የሚያዳክም ድርጊት ሲፈጽም ሸብረክ ማለት የማይቻለው፣ ኢትዮጵያዊያን አገራቸው የሥራ ምድር እንድትሆን ቁርጠኝነት ሲኖራቸው ነው፡፡ ሰላምና መረጋጋት የሚሰፍነው አገራዊ ጥንካሬ ሲኖር ነው፡፡ ይህ ጥንካሬ ደግሞ ከጥገኝነትና ከተመፅዋችነት ያላቅቃል፡፡

ሰፊ ለም መሬት፣ ከፍተኛ የሆነ የውኃ ሀብት፣ በጋ ከክረምት የሚያሠሩ የአየር ፀባዮች፣ ተዝቀው የማያልቁ የማዕድን ሀብቶች፣ በአፍሪካ ተወዳዳሪ የሌላቸው በርካታ የቱሪዝም መስህቦች፣ ጠንካራና ታታሪ የሰው ኃይልና የመሳሰሉት ፀጋዎች ያሏት ኢትዮጵያ ለምን የረሃብና የልመናምሳሌት ተደረገች? በምፅዋት ጠያቂነት መዝገብ ውስጥ ለምን ስሟ ጎልቶ ሠፈረ? ዘይት፣ ስኳር፣ ስንዴና የመሳሰሉትን የፍጆታ ምርቶች አገር ውስጥ ማምረት እየተቻለ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከውጭ ለምን ታስገባለች? በምግብ ምርት ተትረፍርፋ ለዓለም ገበያ አቅራቢ መሆን ሲገባት በምን ምክንያት ነው ጥገኛና ተመፅዋች የሆነችው? የውጭ ብድር ዕዳ ለምን ተቆለለባት? በተፈጥሮ ፀጋዎቿ ያልተጠቀመች አገር ለማዕቀብ የምትንበረከከው፣ ከድህነት መንጥቆ የሚያወጣት ብርቱ ፖሊሲ ሳይኖራት ሲቀር ነው፡፡ ሕዝቡን የኑሮ ውድነት የሚያሰቃየው ኢኮኖሚው በአግባቡ ስለማይመራ ነው፡፡ ብር እያተሙ ገበያው ውስጥ በስፋት እየረጩ የኑሮ ውድነቱን በነጋዴዎች ላይ ብቻ ማሳበብ ደካማነት ነው፡፡ የውጭ ኃይሎች ማዕቀብ ቢጥሉ ኢኮኖሚውን እንዴት መታደግ እንደሚቻል በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ዝግጅት ያስፈልጋል፡፡ ነባራዊውን ሁኔታ ያገናዘበ የባለሙያዎች ትክክለኛ ምክክር መደረግ አለበት፡፡ኢትዮጵያ የዘመናት ችግሮች የሚቀረፉት ኢትዮጵያውያን በጋራ ለሥራ ታጥቀው ሲነሱና በባለሙያዎች ሲታገዙ ነው፡፡

ለኢትዮጵያ የሚበጀው በዕውቀት የታገዘ የሥራ ባህል ነው፡፡ በዕውቀት የታገዘ የሥራ ባህል እንዲኖር ግን ጥራት ያለው ትምህርት ያስፈልጋል፡፡ ጥራት ያለው ትምህርት ሲኖር ጥራዝ ነጠቅነት ሥፍራ አያገኝም፡፡ በአስተማማኝ ዕውቀት የተገነባ ማኅበረሰብን ለሥራ ማዘጋጀት በጣም ቀላል ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ማኅበረሰብ በሥርዓት መኖር የሚችል፣ ኃላፊነት የሚሰማው፣ ከስሜታዊነት ይልቅ ለምክንያታዊነት የሚያደላ፣ ባልተረጋገጠ መረጃ የማይተራመስ፣ አጥብቆ የሚጠይቅና የሚሞግት፣ እንዲሁም ለሞራልና ለሥነ ምግባር እሴቶች ከፍ ያለ ቦታ የሚሰጥ ነው፡፡ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ሕይወቱ በከፍተኛ ዲሲፕሊን የታነፀ ነው፡፡ ከግላዊና ከቡድናዊ ጥቅም ይልቅ ለብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅም ቅድሚያ ከመስጠቱም በላይ፣ ለጀብደኝነትና ለሥርዓተ አልበኝነት ቦታ አይኖረውም፡፡ በመርህ መመራትና በሥርዓት መኖርን የለመደ ማኅበረሰብ ለሥራ ትልቅ ክብር አለው፡፡ ሠርተው የሚያሠሩ መሪዎችን ይፈልጋል፡፡ ሁሌም የሚተጋው ለዕድገት ነው፡፡ ዕድገት የሚገኘው በትምህርት በመሆኑ ትውልዱን ጥራት ባለው ትምህርት ለማነፅ ይተጋል፡፡ ለነገዎቹ በርካታ ተመራማሪዎችና ሳይንቲስቶች የምትመች አገር ያዘጋጃል እንጂ፣ በማይረቡ ምክንያቶች እየተጋጨ አገር ለማፍረስ አይሯሯጥም፡፡ የነገውን ባለሙሉ ሰብዕና ትውልድ ያፈራል እንጂ፣ አገር የሚያዋርድና የሚያተራምስ ትውልድ አይፈጥርም፡፡ ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ከጥገኝነትና ከተመፅዋችነት የሚያላቅቃት ትውልድ ነውና፡፡

ኢትዮጵያ ከተሠራባት ተስፋ እንዳላት በርካታ ማመላከቻዎች አሉ፡፡ በረሃብ፣ በጦርነት፣ በኋላቀርነትና በተለያዩ መከራዎች ስሟ ይነሳ የነበረ አገር ገጽታዋ መቀየር አለበት፡፡ እዚህና እዚያ የሚነሱ ግጭቶችንና ውድመቶችን በፍጥነት ማስቆም ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ የነፃነት፣ የፍትሕ፣ የልማትና የእኩልነት አገር እንድትሆን በአንድ ላይ መነሳት ይገባል፡፡ ኢትዮጵያዊያን እየተፋቀሩ፣ እየተሳሰቡ፣ እየተከባበሩና በኅብረት እየሠሩ መጪውን ጊዜ ብሩህ ማድረግ ይችላሉ፡፡ ለዚህም ኢትዮጵያን ከወራሪዎችና ከተስፋፊዎች ለመከላከል የተደረጉ ተጋድሎዎች ህያው ምስክር ናቸው፡፡ ለዓለም ጥቁር ሕዝቦችና በጭቆና ቀንበር ለነበሩ ሁሉ ታላቅ ተምሳሌት የነበረችው ኢትዮጵያ ከተሠራባት፣ እንኳን በአፍሪካ በዓለም ደማቅ ሆና መታየት ትችላለች፡፡ ከሴራ፣ ከጥላቻ፣ ከቂም በቀልና በአጠቃላይ ለዕድገት ከማይጠቅሙ አላስፈላጊ ድርጊቶች በመራቅ የሥራን ክቡርነት ማንገሥ ተገቢ ነው፡፡ ዕብሪትና ጀብደኝነት አይጠቅሙም፡፡ ከድህነትና ከኋላቀርነት ለመላቀቅ ዋነኛው ቁልፍ ሰላም ነው፡፡ በአፍሪካም ሆነ በዓለም ብርቱ ተፎካካሪ ለመሆን ሰላምና መረጋጋት ያስፈልጋል፡፡ በሞራልና በሥነ ምግባር በመታነፅ ነገን ማቀድ የብልሆች ተግባር ነው፡፡ ይህንን ለማድረግ በአንድነት መነሳት ሲቻል ደግሞ፣ የሚገኘው ውጤት አስደማሚ እንደሚሆን መጠራጠር አይገባም፡፡

 በተለያዩ መስኮች የተሰማሩ ኢትዮጵያዊያንም አኩሪ ተግባር በመፈጸም አስተዋጽኦ ማበርከት አለባቸው፡፡ ፖለቲከኞች የፓርቲ ፖለቲካ ሥራቸውን በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ እያከናወኑ፣ የነገዋ ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲያዊት አገር እንድትሆን ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡ ዘመኑ የሥልጣኔ ነው እየተባለ ከዘመነ የዕድገት መሥፈርት በታች መገኘት የለባቸውም፡፡ ከመሰሪነት፣ ከጥላቻ፣ ከቂም በቀልና ከኋላቀር ድርጊቶች መላቀቅ አለባቸው፡፡ ካላስፈላጊ ግጭቶችና ትርምሶች በመውጣት ለውይይት፣ ለክርክርና ለድርድር ራሳቸውን ማዘጋጀት አለባቸው፡፡ ለሰላማዊና ለዴሞክራሲያዊ ፉክክሮች ብቁ ለመሆን ዝግጅት ቢያደርጉ ይበጃቸዋል፡፡ በተቃርኖ የተሞሉ የታሪክ ስንክሳሮችን እያገላበጡ ስላልነበሩበት ዘመን ከመወዛገብ፣ ዛሬ ከእነሱ የሚፈለገውን ለመወጣት ቢተጉ ያስከብራቸዋል፡፡ ሕዝብ ዳኝነቱን የሚሰጠው ዛሬ ለሚከናወን ምሥጉን ተግባር እንጂ፣ ለትናንቱ ጥፋት ውግዘት አይደለም፡፡ ዛሬ ሳይሠሩ ትናንትን መወንጀል ስንፍና ነው፡፡ ዘመኑ ደግሞ ሰነፎችን አይታገስም፡፡ ስለዚህ ሁሉም ፖለቲከኞች ወደ ቀልባቸው ተመልሰው ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የበኩላቸውን ይወጡ፡፡ ኢትዮጵያንም ከሚያንዣብባት የውጭ ኃይሎች ማዕቀብና ጫና ይከላከሉ፡፡ ኢትዮጵያን ከጥገኝነትና ከተመፅዋችነት ማላቀቅ የግድ ነው፡፡

ከእያንዳንዱ ግለሰብ ጀምሮ መንግሥትን እስከሚመሩ ሰዎች ድረስ ሥርዓት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ የሚሠራን መኮርኮም፣ ማበሳጨትና ተስፋ ማስቆረጥ ተገቢ አይደለም፡፡ የሚሠራ ሰው መከበር አለበት፡፡ አገር የሚዘርፉ ሰዎች በጠራራ ፀሐይ እንደ ልባቸው እየሆኑ፣ ንፁኃንን በተለያዩ መንገዶች ማስመረር መቅረት አለበት፡፡ የአገሪቱን መሬት በግላጭ እየወረሩ የሚሸጡ፣ የመንግሥት ካዝና የሚያራቁቱ፣ ፕሮጀክቶችን ከጥራት ደረጃቸው በታች በመሥራት የሚዘርፉ፣ በቡድን በመደራጀት የአገር ሀብት የሚያግዙ፣ ግብር የሚሰውሩ፣ ጥራት የሌላቸው ዕቃዎችን በገፍ ከውጭ የሚያስገቡ፣ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው መድኃኒቶችንና ምግቦችን የሚሸጡ፣ ሚዛን የሚያጭበረብሩ፣ ተሽከርካሪዎችንና የተለያዩ ንብረቶችን ተደራጅተው የሚዘርፉና በአጠቃላይ በአቋራጭ ለመክበር ከሰማይ በታች ያሉ ኃጢያቶችን የሚፈጽሙ በሕግ ይባሉ፡፡ ሕግ ባለበት አገር ውስጥ ከሕግ በላይ የሆኑ ጉልበተኞችን መንግሥት ሥርዓት ማስያዝ አለበት፡፡ የሕግ የበላይነት በሕገወጥነት ላይ የበላይ መሆን ካልቻለ ሥርዓተ አልበኝነት ይነግሣል፡፡ ሕገወጥነት ለቅራኔ፣ ለግጭት፣ ለዕልቂትና ለውድመት መንስዔ ስለሆነ ከኢትዮጵያ ምድር መወገድ አለበት፡፡ ኢትዮጵያ ለማንኛውም ዓይነት ማዕቀብ የማትንበረከከው፣ ለግጭት የሚያነሳሱ ድርጊቶች ሲወገዱ  ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከጥገኝነትና ከተመፅዋችነት መላቀቅ አለባት!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከፍተኛ ትርፍ ቢያገኝም የውጭ ምንዛሪ ገቢው ቅናሽ ማሳየቱ ተጠቆመ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2016 የሒሳብ ዓመት ያሰባሰበው የውጭ ምንዛሪ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለልዩነት ዕውቅና የማይሰጥ ፖለቲካ ፋይዳ ቢስ ነው!

በፍርኃትና በሥጋት የተኮማተረ አገር ለመለወጥም ሆነ ለማደግ ዝግጁ መሆን አይችልም፡፡ አጉል ድፍረትና ምግባረ ብልሹነት በተንሰራፋበት ስለነፃነት መነጋገር አይቻልም፡፡ ፍርኃት እንደ ወረርሽኝ አገር ምድሩን አዳርሶ...

ለሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎቶች ልዩ ትኩረት ይሰጥ!

በዚህ ዘመን ለሰው ልጅ የሚያስፈልጉ ነገሮች ብዛታቸው እየጨመረ ቢመጣም፣ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን መሠረታዊ የሚባሉ ፍላጎቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ሊቸራቸው ይገባል፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ...

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተገኙበት የሚዲያ ሽልማት ሥነ ሥርዓት መካሄዱ ይታወሳል፡፡ ‹‹ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ለሠሩ የአገር ውስጥና የውጭ...