Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊአገራዊው የዲጂታል የጤና መረጃ ሥርዓት ዝርጋታ በጤና ተቋማት

አገራዊው የዲጂታል የጤና መረጃ ሥርዓት ዝርጋታ በጤና ተቋማት

ቀን:

አሁን ያለንበት አራተኛው የቴክኖሎጂ አብዮት ዘመን ዓይነተኛው መገለጫው ዲጂታል አብዮት ሲሆን፣ ይህም በፍጥነቱ፣ በተደራሽነቱና በተፅዕኖ ፈጣሪነቱም ወደር የለሽ መሆኑ ይነገርለታል፡፡ ዲጂታል ቴክኖሎጂ ዛሬ ያልደረሰበት የዓለም ጫፍ፣ ተፅዕኖ ያልፈጠረበትም የሥራ መስክ የለም፡፡ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ውስጥ መጠነ ሰፊ ሥራዎች ከሚታዩባቸውና ለውጥ እያስመዘገቡ ከመጡ ሴክተሮች መካከል የጤናው ሥርዓት  ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ነው፡፡

የጤና ሚኒስቴር ባዘጋጀው የዲጂታል ጤና ‹‹ዓብይ ስብሰባ›› (ኮንፈረንስ) እና ዓውደ ርዕይ ሲከፈት የተገኙት ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ዓለም ፀሐይ ጳውሎስ እንደተናገሩት፣ በዲጂታል ጤና ሥርዓት ግንባታ ውስጥ የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መረጃ ሥርዓት በሁሉም የጤና ዘርፍ ዕርከኖች መረጃዎችን ለመተንተን፣ ለመሰብሰብና ለውሳኔ ሰጪነት ለማብቃት እየተጠቀምንበት ነው፡፡ ወረዳዎች ከጤና ጣቢያ ጋር በበይነ መረብ እንዲተሳሰሩ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎችም በመከናወን ላይ ናቸው፡፡

‹‹የጤና አቅርቦት ሥርዓትን ለማዘመን የተለያዩ ሶፍትዌሮች ሥራ ላይ ውለዋል፡፡ የደም አቅርቦትን በኢንፎርሜሽን ሲስተም እንዲከናወን ተደርጓል፣ እንዲሁም ከወረቀት ሥራ ሙሉ ለሙሉ ወደ ዲጂታል ሥራ ከጥቅል መረጃ ወደ ግለሰቦች መረጃ ትንተና አቅንተናል፤›› ብለዋል፡፡ 

‹‹የዲጂታል ጤና ለሁሉ አቀፍ የጤና ሽፋን›› በሚል መሪ ቃል ለሁለት ቀናት የተካሄደው ምክክር መስከረም 5 ቀን 2014 ዓ.ም. በተጀመረበት ሥነ ሥርዓት ላይ ሚኒስትር ዴኤታዋ እንዳብራሩት፣ ከተበታተነና ከተበጣጠሰ የጤና መረጃ ሥርዓት ወደ እርስ በርስ የሚናበብ ወይም ደግሞ ዘላቂነት ወዳለው ሥርዓት ለመሻገር ከመቼውም በላይ በጋራና በቅንጅት መሥራት አስፈላጊ ነው፡፡

እስካሁንም በተከናወነው እንቅስቃሴ ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ድረስ፣ እንዲሁም በአስተዳደሩ መዋቅርም ጭምር ከሪፈራል ሆስፒታል እስከ ጤና ኬላ ድረስ ማለትም ከ20,000 በላይ በሚሆኑ ጤና ተቋማት ውስጥ የዲጂታል ጤና ሥርዓት እንደተዘረጋ፣ ከ300,000 በላይ የሚሆኑ የጤናው ዘርፍ ሠራተኞች አቅማቸውን በመገንባት የዲጂታል ጤና ሥርዓትን እንዲለማመዱ ለማድረግ የሚያስችል ተግባር ተከናውኗል፡፡

የጤና ሚኒስቴር በመጀመርያውም ሆነ በሁለተኛው የጤናው ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለጤና መረጃ አብዮት ትኩረት በመስጠት የዲጂታል የጤና ሥርዓትን ለማስፋፋትና አሠራሮችን በቴክኖሎጂ ለማዘመን በየዘርፉ እየሠራ እንደሚገኝም / ዓለም ፀሐይ አስታውሰዋል፡፡

የጤና ሚኒስትር ሊያ ታደሰ (ዶ/ር)፣ በጤናው ዘርፍ የሚፈለገውን ትራንስፎርሜሽን ለማምጣት፣ የጤና አገልግሎት ሽፋን ፍትሐዊነትና ጥራትን እንዲሁም የታካሚውን ደኅንነት ለማረጋገጥ፣ የጤና ሥርዓት ምሰሶዎች ላይ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍና የጤና ሥርዓቱን ለማጠናከር እየተሄደ ባለው እንቅስቃሴ ላይ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ያለው ፋይዳ እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡

እንደ ሚኒስትሯ አባባል፣ የኤሌክትሮኒክ ሔልዝ ሲስተም ከ5,500 በላይ በሚሆኑ የጤና ኬላዎች ላይ የተጀመረ ሲሆን፣ በዚህም ከአምስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ አባወራዎችና እማወራዎች ከእነ ሙሉ የቤተሰብ አባላት ጋር የጤና ሁኔታቸው ሊመዘገብ ተችሏል፡፡ ከዚህም ሌላ የሰው ሀብት አስተዳደርንና አመራርን ለማሻሻል፣ የጤና ግብዓት አቅርቦትን የመረጃ አያያዝና ሥርጭትን ለማዘመን የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት እንደተከናወኑ አስረድተዋል፡፡

የመረጃ አብዮት አተገባበር የመረጃ አያያዝን ከጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች እስከ ሆስፒታሎች ድረስ በተዘረጋ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም በማዘመን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩትን ቤተሰቦች ሁኔታ በመረጃ ቋት በማደራጀት ጤናቸውን በቀላሉ ለመከታተል ማስቻሉ ለቀጣዩ ሥራ ተስፋ ሰጪ መሆኑንም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

የኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ (አይሲቲ) መሠረተ ልማትን ለማስፋፋት፣ ውጤታማና ችግር ፈቺ የሆኑ ዲጂታል ቴክኖሎጂዎችንና አገልግሎቶችን ለማበልፀግና ለመለየት፣ እንዲሁም የጤና ባለሙያዎችን የዲጂታል ቴክኖሎጂ አጠቃቀም በማሳደግ፣ የጤና መረጃ በቀላሉ ተደራሽ እንዲሆን፣ የተሻለ መረጃ ትንተናና አጠቃቀም እንዲኖር ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች ከሰባት የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በጋራና በቅንጅት እየተከናወነ መሆኑንም ነው ሚኒስትሯ ያመለከቱት፡፡

የኢትዮጵያ የመረጃ መረብ ደኅንነት (ኢንሳ) ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ሹመት ግዛው (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ አስደናቂ ወደሆነው ዲጂታል ሥነ ምኅዳር የመግባት ቁርጠኝነት ጤናንና ተያያዥነት ያላቸውን የአገልግሎት ሽፋን ለማሳደግ ያለው ጥቅም እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ጤናንና በርካታ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አገልግሎቶቻቸውን በሒደት ወደ ዲጂታል ሥነ ምኅዳር እንዲወስዱት ማድረግ፣ ኢትዮጵያ በ2017 ዓ.ም. ካለመችው የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ጋር ለማጣጣም የበርካታ አገሮችንም መልካም ተሞክሮ እንድትከተል ከማድረግ አንፃር ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ከኢትዮጵያ መልክዓ ምድራዊ ዳርቻነት ወደ ምናባዊ ማዕከል (ቨርቹዋል ሴንተር ስሩ አፕሊኬሽን ቴክኖሎጂ) እንዲሸጋገር ለማድረግ፣ የዲጂታል የሳይበር መስክ ሥራዎችን በአግባቡ ወደ መሬት ማውረድ ለነገ የማይባልና ሁሉም ሊረባረብበት የሚገባ ተቀዳሚ ሥራ መሆን እንደሚኖርበትም ነው ዋና ዳይሬክተሩ የጠቆሙት፡፡

የዲጂታል ጤና ትግበራ ጉዳይ በዘላቂነት ከተያዘና ወደ ብዙ ተግባር እንዲገባ ከተደረገ፣ የሌሎች ጤናን የሚደግፉ ዘርፎች የአገልግሎታቸውን ደረጃ ከፍ ማድረግ ከተቻለ፣ እንደ ኮቪድ-19 የመሳሰሉ ወረርሽኞች በሚከሰቱበት ወቅት የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ለመቋቋም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

‹‹የዲጂታል ጤና ሥርዓት ተግባራዊ ሲደረግ የመረጃ ጥሰትን ወይም የሳይበር ጥቃትን የመከላከል ተግባር አብሮ ታሳቢ ሊደረግ ይገባል፡፡ የሳይበር ጥቃት ቀጣይ የዓለም ወረርሽኝ ሊሆን ይችላል ተብሎም ይገመታል፡፡ በሳይበር ጥቃት ምክንያት ከሚደርሱ ጉዳዮች አገርን፣ ተቋማትንና ራስን፣ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብን ጭምር የመጠበቅ ኃላፊነት አለብን፤›› ብለዋል፡፡  

በተለይ የጤና ዘርፍ ምን ያህል የሳይበር ጥቃት ተጋላጭ እንደሆነ ለማወቅ፣ በ2012 ብቻ የዓለም ጤና ድርጅት የተሰነዘረበት የሳይበር ጥቃት በእጥፍ እንደጨመረበት ይፋ ማድረጉን ማስታወስ እንደሚገባ፣ የጤና ክብካቤ መስኩም (የሔልዝ ኬር ኢንዱስትሪውም) ከ2012  እስከ 2017  ድረስ ለሳይበር ሴኩዩሪቲ ብቻ እስከ 125 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ማድረጉን ከዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በኢትዮጵያም ባለፈው ዓመት ብቻ ከ28,000 በላይ አደገኛ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች እንደተሰነዘሩ፣ ጥቃቶቹ ዒላማ ያደረጉትም በመጀመርያ ፋይናንስ፣ ከዚያ ቀጥሎ የጤና ተቋማትን እንደሆነ የመገናኛ ብዙኃን፣ እንዲሁም የግል ተቋማትና ሌሎች በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ወሳኝ መሠረተ ልማቶችን እንደነበር ነው ዋና ዳይሬክተሩ ያመለከቱት፡፡

‹‹አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅቶች፣ ቁጥጥርና ተገቢ ዕርምጃ ባይወስድና እነዚህ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች ቢደርሱ ኖሮ፣ በተቋማትና በአገር ደረጃ ሊደርሱ የሚችሉ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የዲፕሎማሲና የሥነ ልቦና ጫናና ኪሳራ እጅግ በጣም ከፍተኛ ይሆን ነበር፤›› ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ከዚህ አኳያ ከማንኛውም የዲጂታል ሥራዎች ጎን ለጎን የሳይበር ደኅንነትን የማረጋገጥ ሥራ እኩል ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

‹‹ሦስት የሳይበር ደኅንነት ምሰሶዎችን ሁልጊዜ በእኛ ዘንድ ቅድሚያ ሊጣቸው ይገባል፤›› የሚሉት ሹመት ግዛው (ዶ/ር)፣ ከምሰሶዎቹም መካከል አንደኛው በትክክለኛ መንገድ የሠለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት ሲሆን፣ ሁለተኛውና ሦስተኛው ቴክኖሎጂና መሠረተ ልማትን ማስፋፋት፣ እንዲሁም የሳይበር ፖሊሲዎች፣ ሥልቶችና ደረጃዎች አስፈላጊነት እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡  

የዲጂታል ጤና አገልግሎት የኢትዮጵያን አጠቃላይ የጤና ሥርዓት የአቅም ደረጃ በማሳደግና ዘመኑን የዋጀ የጤና አገልግሎት በመስጠት ረገድ የሚኖረው ሚና ከፍተኛ እንደሆነ የተናገሩት፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

የዲጂታል ኢትዮጵያ 2012 እስከ 2017 ዓ.ም. አገራዊ ስትራቴጂ ትኩረት ካደረጋቸው አንዳንድ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን በመጠቀም የሚሰጡ የአገልግሎቶችን ሽፋን በፍጥነት ማስፋፋትን የሚያመላክት መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

በስካይ ላይት ሆቴል የስብሰባ አዳራሽ በተከናወነው በዚሁ ሥነ ሥርዓት ላይ ጤና ሚኒስቴር ያዘጋጀውና የጤና ሥርዓቱን ወደፊት ሊያራምዱ ይችላሉ ተብለው የታመኑባቸው ሁለት ሰነዶች ይፋ ሆነዋል፡፡

የጤና ሚኒስቴር የተለያዩ አጋር አካላትና ባለሙያዎችን በማሳተፍ ያዘጋጃቸው ሁለት መሪ ሰነዶች፣ ዲጂታል የጤና ንድፍ (Digital Health Blue Print) እና ኤሌክትሮኒክ የጤና ማህደር (Electronic Health Record Standard) ለታዳሚዎቹ የተዋወቁ ሲሆን፣ሚኒስቴሮች፣ኤጀንሲዎች፣ተጠሪ ተቋማት፣ የዩኒቨርሲቲዎችና የአጋር ድርጀቶች ኃላፊዎች ሰነዶቹን መነሻ በማድረግ ከጤና ሚኒስቴር ጋር ተባብረው ለመሥራት ፊርማቸውን አስቀምጠዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...