Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ዕቅድና ድርጊት እንዳይፋለሱ!

ሰላም! ሰላም! አዲሱ ዓመት ከባተ ሳምንት ሞላውም አይደል፡፡ አንዱ ጥልቅ አሳቢ መሳይ፣ ‹‹ዓመቱ ቢቀያየር እኛ ካልተለወጥን ምን ይፈይዳል…›› ሲለኝ፣ የምመልስለት የረባ መልስ ስላልነበረኝ አንገቴን ነቅንቄ አለፍኩት፡፡ ሰውየው እውነቱን እንደሆነ የገባኝ ብሆንም፣ ለመልስ መስነፌ አናዶኝ ነው መሰል ብሽቅ አልኩኝ። በአዲስ ዓመት በዓል ማግሥት ንዴቴን ዋጥ አድርጌ ስራመድ አንድ ወፈፍ ያደረገው የሚመስል፣ ‹‹በአሮጌ አቁማዳ አዲስ ወይን አይቀመጥም፡፡ ለምን ቢባል አዲሱ ወይን ሲፈላ አሮጌው አቁማዳ ከአቅሙ በላይ ስለሚሆንበት ይቦተረፍና ወይኑ ይባክናል፡፡ አሮጌ አስተሳሰብ ላይ የተቸከሉም ለአዲሱ ትውልድ ስለማይመጥኑ መግባባት አይቻልም፡፡ አንድ የአሮጌው ዘመን ትራፊ የሆነ ሰው በአዲሱ ዘመን ሰው ጉዳይ ውስጥ ዘው ብዬ እገባለሁ ሲል መሳቂያ ይሆናል፡፡ ለምን ቢባል የዘመኑን ነገር ለዘመኑ ሰው ተውለት የሚል መርህ ስላለ ነው፡፡ የአሮጌው ዘመን ሰዎች ከአዲሱ ዘመን አስተሳሰብ ተጣልተው በጦርነት አገር ለማውደም መነሳታቸው የሚያሳየን፣ የአዲሱን ወይንና የአሮጌውን አቁማዳ ታሪክ ነው…›› እያለ በጉልህ ድምፅ ሲናገር ቆሜ አንገቴን በአድናቆት እያወዛወዝኩ አዳመጥኩት፡፡ ዞር ዞር እያልኩ ሳይ ብዙዎች ግራ የተጋቡ ይመስላሉ፡፡ አንዳንዴ እኮ የእኛ ሰው ይገርመኛል፡፡ በአግቦና በአሽሙር የተካነ ሆኖ ሳለ እንዲህ መሰሉ የተዋጣላት ሐሳብ አይገባውም፡፡ አጃኢብ ነው!

በቀደም አንድ ወዳጄ መጣና ሰላም ሳይለኝ፣ቆይ ግን አንተ እስከ መቼ ነው ያን እከሌ የሚባል ደላላ የማትጠቁመው? ከአንተ በላይ የሚያውቀው የለም። ከአንተ በላይ በእሱ ደባና የሌብነት ቅሌት የተደፈቀ የለም። ለእንጀራህም ለእኛም ብለህ በዚህ ሞቅ ያለ ጊዜ አግለህ ብትተኩሰው?” አይለኝ መሰላችሁ።ስለማን ነው የምታወራው?” ስለው ስሙን ጠራውናቄስ ይጥራውብሎ ተንገሸገሸ።ለምን አንተ አትጠቁመውም?” አልኩት። «እኔ እንዳንተ አላውቀው። አንተ ግን ተነካክተሃል…ብሎኝ አረፈዋ። የዘንድሮ ነገርና ነገረኛ ልጥፍ ሲያደርግባችሁ እንዲህ ነው ይኸውላችሁ። ዕድሜ ለፌስቡክና ለዩቲዩብ አይባል ነገር። በላይክና በኮሜንት ያበደው የሦስተኛው ዓለም ሰው፣ ከሳሽና ተከሳሽ ስለሚምታቱበት ነው መሰለኝ ለወፍ የሰደደው ወንጭፍ ፍሬውን ማርገፍ ይቀናዋል። እና ዙሪያ ጥምጥም የምዞረው ምን ልላችሁ ፈልጌ ነው? በሰው ጥቆማ ጣልቃ የሚገባ ሰው በዝቷልና ጠንቀቅ እያላችሁ። አጥብቃችሁ ማሰራችሁን ሳታረጋግጡ ዘቅዝቃችሁ ለመሸከም አትቸኩሉ ነው በአጭሩ። በአገራችን ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት እጃቸውን ያስረዘሙ ኃይሎች ባሉበት በዚህ ጊዜ፣ ጣልቃ ገብነትን መቃወም የጋራ አጀንዳ ብናደርገው ምን ይመስላችኋል ለማለት ያህል ነው፡፡ ማሳሰቢያ በሉት!

እናላችሁ ዛሬ በአጭር ባጭሩ የማጫውታችሁ ጉዳዮች አሉ። በረዥሙ መጫወት እንኳን ለእኛ ለነገረኞችም አልሠራ ብሏል። ካላመናችሁኝ ጦር ሰባቂዎችን ጠይቋቸው። የአገር ጉዳይን ግን ከእኔ የበለጠ የሚነግራችሁ የለም። በአጭሩ ብያለሁና ስጀምር በአጭሩ ሳስቀምጠው ዘመናችን የከተፋ ሆኗል። ሐሳብ ይከተፋል፣ ሙዚቃ ይከተፋል፣ የመንግሥት ድምፅ ይከተፋል፣ የሕዝብ ልሳን ይከተፋል፣ ኧረ ምኑ ቅጡ። ለምን ይሆን ብዬ ከምሁሩ የባሻዬ ልጅ ጋር ሳወራ፣ ‹‹ከሥጋ ጋር ባለን ለየት ያለ ቁርኝት የመጣ ዘይቤ ሳይሆን አይቀርም…ነበር ያለኝ።ጥብስና ክትፎ የአምሮቱ ማሳረጊያ ለሆነ ኅብረተሰብ፣ ከሐሳብ እስከ እሴት ከታትፎ ቢያላምጥ ለውጡ አይታየውም….›› የሚለውን የጨመረበት ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ነው።በዘመነ ኢንተርኔት ለምሁር ቅጥያ ብቻ ቢቀረውም…የሚለው ግን የእኔ ነው። የምሁራን ነገር ከተነሳም የብዙዎቹ ዕውቀት ከሙዚቃ ከታፊዎች አይሻልም፡፡ ይህንን ለማረጋገጥ ቴሌቪዥናችሁን ከፍታችሁ የተንታኞቻችንን ሁኔታ ማየት በቂ ነው፡፡ ከበቂም በላይ!

ስለዘመንና ከተፋው እያወራሁ ጨዋታችንን መከታተፋችንን ትተን ለአፍታ ተቃራኒውን እናስብ። ታክሲ ላይ ተለጥፎ ካያችሁት ጠቁሙኝ ኮሚሽን እቀበልበታለሁ። የከተፋ ወይም በአጭር በአጭሩ የመመተር ተቃራኒ ዘንድ ስትሄዱ በቀላሉ ረዥም የሚባል ቃል አለ። እንደ እኛ ላለ አራት ጎማ አምላኪዎች በቀላሉ ለማስረዳት በረዥሙ ማብራት የሚለውን ሐረግ መጠቀም ነው። እናም መንገዱ በሙሉ በረዥሙ የሚያበሩ መኪኖች ሰበብ እያደር እንደወጣ በሚቀረው ሰው ደም ታጥቦ አርቆ ማሰብ ሲከብደን ስታዩ ምን ትላላችሁ? አዛውንቱ ባሻዬ፣ ‹‹ሰው ሲያወራ የሚውለው በልቡ የሞላውን ነው…›› ይላሉ። ለወትሮው ሲባል እንሰማ የነበረው ልብ ሩቅ አዳሪ መሆኑን ነበር። የዘንድሮ ልብና ሐሳብ ምን አዚም እንደያዘው በጥናት ባይረጋገጥም፣ በአጭር በአጭሩ በተሸራረፉ ነገሮች ተሞልቶ አገር እንደ መካን እዬዬዋ በአራቱም ማዕዘን ደምቆ አረፈው። ታዲያስ? ትንተናችን ይኼን ይኼን ቢጎበኘው የሚል ሐሳብ አልጫርኩባችሁም? አይዟችሁ ስለአጫጫሩ አትጨነቁ ዋናው መንደዱ ነው፡፡ ሐሳቡ ማለቴ ነው!

ስናወራ ደህይተን እንደቀረነው ነገር ስለቃቅም ጎጆዬን እንዳላፈርስ ስለሠጋሁ የሆነለጌስት ሐውስነትየተዘጋጀ ግቢ ቤት ለማከራየት ወዲያ ወዲህ ማለት ጀመርኩ። ይቅርታ አድርጉልኝና ስንቱን የእግዜርቢዝነስእንደዘጋነው ስታስቡ ግርም አይላችሁም? እንግዳ ባረፈበት አገር ሁሉ የእግዜር እንጂ የሰው አይደለምና በነፃ ሲስተናገድ እንዳልኖረ፣ ዛሬ ለእንግዳ ማረፊያ ቤቶች የሚጠየቀውን ዋጋ ሳይ እኮ ነው ይኼን የምለው።በስንቱ እንጠየቅ ይሆን?” ይላሉ ባሻዬ ነገሩ እያስገረማቸው። እንዳልኳችሁ የሚከራይ ምርጥ የእንግዳ ማረፊያ ቤት እንዳለ እየለፈፍኩ ስዘዋወር፣ ሁለት ጥንድ በአዛውንትነት ዕድሜ ላይ የሚገኙ ሰዎች አገኘሁ። ቤቱን አሳይቻቸው ሳበቃ ለአንድ ወር በጥሬው ከፍለው ወዲያው ገቡት። የእኛ አገር አዛውንቶች ዘመድ እንደሌለው እንዴት ይሆናል? እያልኩ ከራሴ ጋር ስሟገት ቆየሁና ኮሚሽኔ እጄ እንደገባ (መጀመርያ የመቀመጫዬን ነዋ) ልጠይቃቸው ወሰንኩ። ቀልጠፍ ነዋ!

‹‹ይኼን ያህል ገንዘብ ከፍሎጌስት ሐውስከመከራየት ዘመድ ወዳጅ ጠፋ እንዴ?›› አልኳቸው እያሳሳቅኩ። እንዳይሆን ሆኖ እንዳንሆን ያደረገን አብዮት ከመፈንዳቱ አንድ ወር በፊት (ተማሪ ነበሩ ያኔ) እንደተዋወቁ፣ ኋላም መረጋጋት ሲርቅ ከአገር እንደተሰደዱ፣ ዛሬ 47 ዓመታቸው ተመልሰው የመጡት እነዚህ የተሳኩ የፍቅር ዓመታት እያሰቡ አገራቸው ላይ ኬክ ለመቁረስ እንደሆነ አጫወቱኝ። ያደለውና  ብልጡ ፍቅርን ሙጥኝ ብሎ ድንበር ተሻግሮ በሰው አገር መሬት ለሚነገር ታሪክ ይበቃል። ያላደለው ደግሞ አገሩንና ወገኑን በጦርነት እያተራመሰ የደም ታሪክ ጽፎ ለማስታወስ የሚከብድ ታሪክ ያሳልፋል። የሕይወት ተቃራኒ ጎዳና እያስደነቀኝ ፈዝዤ ቀረሁ። የዛሬ 47 ዓመት ለአንድ አገር ብሩህ ተስፋ አንድ መሆን ተስኖን ወደ ጀርባና ሆድነት መለወጣችን ሳይበቃ፣ ችግራችንን ወደ እዚህ ዘመን አስተላልፈን እንፋጃለን አልኩ ለራሴ። የጥላቻም ታሪክ ዕድሜው ይወሳል ለካ እናንተ? ይገርማል እኮ! ላይሳካላን መስሎን ባዶ እጅ አጨብጭበን መቅረታችንን እያሰብኩ ራሴን አመመኝ። ጥያቄው ግን ዛሬስ ነው? ዛሬስ እዚያው ነን? ወይስ ተሽሎናል? መልሱን ለእናንተው ልተወው!

ታዲያ እንደምታውቁት በጥቂቱ ዘርቶ በብዙ የሚያጭደው ዘራፊ ብቻ በመሆኑ፣ ሌላው ቢዝነስ አይጠፋም እያልኩ መባከኔን ቀጠልኩ። አንዴ እዚያ ስል አንዴ እዚህ ስል ዓይኔ የሚገባው ነገር ሁሉ ነገር ይፈልገኛል። ወዲያ ማዶ ታክሲ ጥበቃ የተሠለፈው ሕዝብ፣ ከተማውን በዘንዶ የተወረረ አስመስሎት ይታያል። እዚህ ማዶበኔትወርክ’ መቆራረጥ ሊያብድ የደረሰው ብቻውን እንደ ዕብድ እያወራ ያመለጠውን ሒሳብ እያወራረደ ይጣደፋል። ውኃ የመሰለ ሊያዩት የሚያሳሳ አውቶሞቢል በአጠገቤ ሲያልፍ እያየሁአወይ ኑሮብዬ ሳልጨርስስለመድኃኔዓለም?” ብሎ ምፅዋት የሚጠይቀኝ አንድ የእኔ ብጤ (ብቻውን እንዳይመስላችሁመላው ቤተሰቦቹ ጭምር ይዞ ነው) ይታከከኛል። ቀዬውን ጥሎ የተፈናቀለ ቤተሰብ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ልቤ ሲንሰፈሰፍ ይታወቀኛል፡፡ ወይ ነዶ!

አንዱ ለእረፍትቫኬሽንብሎ አገር ይለቃል፣ ሌላው ከመኖሪያው ተፈናቅሎ ቤተሰቡን ሰብስቦ ቀዬውን ይለቃል። ይኼን ውጥንቅጥ ሳይ ምንም ሥራ መሥራት አቃተኝ። ያለፍንበት መንገድ ወስዶ ወስዶ የት እንዳደረሰን እያየሁማን ይሆን ተጠያቂው?’ ስል ራሴን ጠየቅኩት። እንኳን የተወለደው ገና ያልታሰበውም ከተጠያቂነት እንደማያመልጥ የባሻዬ ልጅ አንዴ ያጫወተኝ ትዝ ሲለኝ፣ ነገሩን ችላ ብሎ ማለፍ ከብዶኝ እነሆ እንዲህ እላችሁ ጀመር። የመደብ ልዩነቱ እያደር መስፋቱ፣ ግንዛቤና ገንዘብ በጥቂቶች ዘንድ መገኘቱ፣ ብዙኃን በችጋር ለበቅ እየተጠበጠቡ ዘመናት መሸምጠጣቸው፣ ለውጥ ፉከራ ብቻ ሆኖ መቆየቱና ጦርነት ውስጥ መኖር መለመዱ እንደ እኔ አደባባይ ላይ ሆናችሁ ስታስቡት ደም ያፈላል። የረሱትን እያስተወሱ የማሩትን ያስረግማል። ‹‹ማርና ወተት›› የምታፈሰው ኢትዮጵያችን ሁሌ እያጓጓችን በማይጨበጥ የተስፋ ህልም ላይ ተንጠልጥለን መኖራችን ማክተሚያው መቼ ይሆን? ኧረ እኔስ ናፈቀኝ ጎበዝ!

በሉ እንሰነባበት። ቀን አያወጣው አያወርደው የለም። የሚወጣው ለእናንተ አይነገርም። ይልቅ እየወረደ ያስቸገረንን ነገር ልጠቁማችሁ። በስም ሽፋን እየተድበሰበሰ እንጂ ሰሞኑን የብዙዎች እንጥል መውረዱን ልብ ብላችኋል? የምሬን እኮ ነው። ትናንትና ዓይኔን ስገልጥ ጉሮሮዬ ደህና ነበር። ማንጠግቦሽን፣ ‹‹ደህና አድረሻል?›› ካልኳት በኋላ እንጥሌ በቦታዋ የለችም። ደርሶ ጉሮሮዬ ከረከረኝ። ቁርጥማት ወረረኝ። ማንጠግቦሽ እዚያው በዚያው ሲያንዘፈዝፈኝ ስታይ ልግመት ነው ብላ እንደማኩረፍ አሰኛት። ድምፄ ሲዘጋ ግን የሚያደርጋትን አሳጣት። ወዲያው ለባሻዬ ልጅ ደወልኩ። መድኃኒት አያጣም ብዬ ነዋ።ሃሎስል ባሻዬ ስልኩን አንስተው፣ ‹‹እንጥሉ ወርዳ ድምፁ ተዘግቷል…›› አሉኝ። ‹‹መቼ አመመው?›› ስላቸው፣ ‹‹ኧረ አሁን ከእንቅልፉ ሲነሳ በደንብ አናግሮኛል። ማር በነጭ ሽንቁርት ላስልሰው ነው…›› ብለው ስልኩ ተዘጋ። ይኼ ነገር አዲሱ የቫይረስ ዝርያ ይሆን እንዴ፡፡ ወገኖቼ ተጠንቀቁ!

ማንጠግቦሽም የዋዛ አደለችም ምናምኑን እየደባለቀች ስትግተኝ ውላ ከቀትር በኋላ አቅሜ መለስ ሲል ባሻዬ ዘንድ ደወልኩ። ጥርጣሬ ስላለኝ መሄድ የለብኝማ፡፡ ‹‹አይገርምዎትም ተነጋግረን አገር ማቅናት ያልቻልን ሰዎች እንደ ተመካከረ ሰው በሽታ እኩል ሲጥለን?›› ስላቸው፣ ‹‹መድኃኒተኛ አይጥፋ እንጂ ደግሞ በሽታ ምንድነው አንበርብር? የዛሬ ልጆች እንደሆነ በትንሽ በትልቁ እንደ አራስ ልጅ ፍንግል ፍንግል ነው። ይልቅ ካነሳኸውስ የሚያሳስበኝ እያደር እየቀዘቀዘብን የመጣው የፍቅር ጉዳይ ነው። ፍቅር በማር አይለሰልስ። በወጌሻ አይታሽ። ምን ታደርገዋለህ?›› ብለውኝ ተሰነባበትን፡፡ የትኩሳቴና የእንጥሌ ጉዳይ ከአዲሱ ኮሮና ቫይረስ ጋር ያለው ግንኙነት ቢያሳስበኝም፣ ቆይቶ በደንብ ሲሻለኝ ሥጋቴ ቀነሰ፡፡ ሄጄ ምርመራ እስካደርግ ድረስ ቤቴ አርፌ ተቀምጫለሁ፡፡ ለማንኛውም የአዲሱን ዓመት ጅማሬ አኳኋን እያሰላሰልኩ አንድ ሐሳብ ውልብ አለብኝ፡፡ ድርጊታችን በዕቅድ ላይ ካልተመሠረተ ቅዠት እንደሚሆን፣ ዕቅዳችን ደግሞ በድርጊት ካልታገዘ ከንቱ መሆኑ ነው የታሰበኝ፡፡ መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት