Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበኢትዮጵያ በኮቪድ-19 የሞቱት ከአምስት ሺሕ በላይ ሆኑ

በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 የሞቱት ከአምስት ሺሕ በላይ ሆኑ

ቀን:

  • አገልግሎት ሰጪ ሠራተኞች በመከተብ አርዓያ እንዲሆኑ ጥሪ ቀርቧል

በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ወረርሽን ከተከሰተበት ወዲህ 5,059 ሰዎች መሞታቸውን የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በአሁናዊው መረጃው አስታውቋል፡፡

የቫይረሹ ዝርያ በሆነው ዴልታ በሦስት ቀናት ብቻ ማለትም ከመስከረም 4 እስከ 6፣ 2014 ዓ.ም. 92 ግለሰቦች ለሕልፈተ ሕይወት ተዳርገዋል፡፡

እስከ መስከረም 6 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ 328,735 ሰዎች ቫይረሱ የተገኘባቸው ሲሆን 5,059 ሰዎች ደግሞ በወረርሽኙ ሳቢያ ሕይወታቸው አልፏል። በኮቪድ ወረርሽኝ የመያዝ ምጣኔውም ወደ 20 በመቶ ማሻቀቡ ተገልጿል፡፡

በሆስፒታሎች የአስተኝቶ ማከሚያ ክፍሎች፣ አጋዥ የመተንፈሻ መሣሪያ እጥረት እያጋጠመ፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከዕለት ወደ ዕለት በከፍተኛ ደረጃ ከመሠራጨቱም በላይ ሰብዓዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮችን እያስከተለ እንደሚገኝም ተገልጿል፡፡

በዚህም የተነሳ የኮቪድ-19 ሥርጭትን ለመከላከልና የሚያስከትለውን ሞት ለማስቆም የሚከተሉትን የመከላከያ ዘዴዎችን መተግበር አስፈላጊ መሆኑን የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡

 ከመከላከያ ዘዴዎቹም መካከል ለመጪው የአዲስ ዓመትና ሌሎች ሕዝባዊና ሃይማኖታዊ በዓላት የሚፈጠሩ መሰባሰቦችን ማስቀረት፣ ሁሉም ተቋማት ደንበኞቻቸውን የኮቪድ-19 መከላከያ መንገዶችን እንዲተገብሩ ማድረግ፣ የኮቪድ-19 ምልክቶች ሲታዩ ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ ምርመራ ማካሄድና የኮቪድ-19 ክትባትን መከተብ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ከዚህም ሌላ በበዓል ወቅት ለዕርድ አገልግሎት የሚውሉ ማንኛውንም ቁሳቁሶች ንፅህናቸውን እንዲጠበቁ ማድረግና ንክኪዎችን መቀነስ፣ ለግብይት ከቤት ውጪ በሚደረግ መንቀሳቀስ ማስክ ማድረግ፣ የእጅ ማፅጃ ሳኒታይዘር መያዝ ያስፈልጋል፡፡

 በበዓል ወቅት ከሌሎች ሰዎች ጋር የሚኖር ማኅበራዊ ግንኙነት መቀነስ፣ ያልበሰሉ የምግብ ተዋጽኦዎችን እንደ ጥሬ ሥጋ፣ ያልተፈላ ወተትና ሌሎችን ከመመገብ መቆጠብ፣ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በመመርያ 803/2013 ዓ.ም. ላይ የተቀመጡ ድንጋጌዎችን ተግባራዊ ማድረግ ከመከላከያ ዘዴዎች ተጠቃሾች መሆናቸውን ኢንስቲትዩት አስታውሷል፡፡ 

በተያያዘ ዜና፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ለሕዝብ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት፣ የኮቪድ ክትባትን በመከተብ ለሌሎች አርዓያ መሆን እንዳለባቸው ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡

ቢሮው ማሳሰቢያ የሰጠው፣ በኮቪድ-19 ክትባት አወሳሰድ ላይ የሚታዩ ተግዳሮቶችን ከሚመለከታቸው የመንግሥትና የግል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር መስከረም 6 ቀን ባካሄደው የምክክርና የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ላይ ነው፡፡

ቢሮው በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንደገለጸው፣ በውይይቱ የሁሉም ባንኮች ኃላፊዎችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የግልና የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ተሳታፊ የሆኑ ሲሆን፣  የኮቪድ 19 ክትባት እንደ ከተማ ያለው አፈጻጸምና ተግዳሮቶቹ ለውይይት ቀርበዋል፡፡

በውይይቱም ክትባቱ መሰጠት ከተጀመረ ወራት ቢቂጠሩም በኅብረተሰቡ ያሉ መሠረት የሌላቸው አሉባልታና ትክክለኛነት በጎደላቸው ወሬዎች ምክንያት በሚፈለገው መጠን እየተሰጠ እንዳልሆነም ተጠቁሟል፡፡

አሁን ላይ በከተማዪቱ ጆንሰን፣ አስትራ ዜኒካና ሲኖፋርም የተሰኙ የክትባት ዓይነቶች በሁሉም የመንግሥት የሕክምና ተቋማት በነፃ እየተሰጡ እንደሚገኙ የገለጹት የቢሮው ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ ሀንጋቱ መሃመድ፣ እነዚህ የክትባት ዓይነቶች እንደማንኛውም የመድኃኒት ዓይነት ቀላል የጎንዮሽ ሕመም እንደ ራስ ምታት፣ ማቅለሽለሽ ውጭ ሌላ የከፋ ችግር እንደማያስከትሉና ሌሎች አገሮችም እየተጠቀሙበትና ውጤት ያመጡበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኃላፊዋ፣ ክትባቱ ማንኛውም ዕድሜው 18 ዓመት በላይ የሆነው ሁሉ በነፃ በመከተብ፣ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የመጣውን በኮቪድ ሞትና የፅኑ ሕሙማን ቁጥር ከመቀነስ አንፃር ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን አሳስበዋል፡፡

በተለይም ከሥራ ባህሪያቸውከፍተኛ ደረጃ ለኅብረተሰቡ አገልግሎት የሚሰጡ እንደ ባንክ፣ ትራንስፖርትና መሰል ተቋማት ሠራተኞቻቸውን በማስከተብ ያለውን ተጋላጭነት መቀነስ እንደሚገባም በውይይቱ መድረክ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...