Tuesday, July 23, 2024

ከረሃብ ጋር ለተፋጠጡ ወገኖች ሕይወት አድን ምላሽ ያስፈልጋል!

በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ከተለያዩ አካባቢዎች በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖች ከረሃብ ጋር ተፋጠዋል፡፡ ሕፃናት፣ አራሶች፣ ነፍሰ ጡሮች፣ አቅመ ደካማ አዛውንቶች፣ አካል ጉዳተኞችና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች በከባዱ የክረምት ወቅት ከደሳሳ ጎጆዋቸው ተፈናቅለው ሜዳ ላይ ወድቀዋል፡፡ የቤተሰብ አባሎቻቸውን በጦርነቱ ምክንያት ያጡ በርካታ ወገኖች፣ ጎጆዎቻቸው ተቃጥለውባቸውና ንብረቶቻቸው ወድመውባቸው ባዶ እጃቸውን በመቅረታቸው የሚላስ የሚቀመስ አጥተዋል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ረሃቡ በመፅናቱ ሳቢያ የሕፃናትና የአቅመ ደካሞች ሁኔታ ያስደነግጣል፡፡ ብዙዎቹ በጦርነት ቀጣና ውስጥ የሚገኙ ተጎጂዎች በከፍተኛ ሥቃይ ውስጥ ስለሆኑ፣ በተቻለ መጠን ጦርነቱ በፍጥነት እንዲያበቃ ካልተደረገ ቀውሱ ከሚታሰበው በላይ ነው የሚሆነው፡፡ በረሃብ የተጎዱ ሕፃናትና አቅመ ደካማ አዛውንቶች የምግብም ሆነ የሕክምና ዕርዳታ ካላገኙ ዕጣ ፈንታቸው ያሳስባል፡፡ የአገር ውስጥም ሆኑ ዓለም አቀፍ የረድዔት ድርጅቶች ሰብዓዊ ዕርዳታዎችን በፍጥነት እንዲያቀርቡ ምቹ ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡ የረሃቡ አድማስ እየሰፋ ከሄደ ከቁጥጥር ውጪ ሆኖ መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ ቀውስ ሊከሰት ይችላል፡፡ ይህ አስከፊ ቀውስ ከመድረሱ በፊት ግን ለሕይወት አድን ምላሽ መረባረብ የግድ ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ የአገር ህልውና ከምንም ነገር በላይ አሳሳቢ እየሆነ ነው፡፡ በሰሜን የአገሪቱ ክፍል እየተካሄደ ባለው ጦርነት እየተስተዋለ ያለው ዕልቂትና ውድመት ረሃብ እያስከተለ ነው፡፡ የሕዝባችን ደኅንነትና የአገራችን ህልውና አሳሳቢ ሲሆን፣ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት በመቆም የጋራ አቋም ሊኖረን ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ ከወዲሁ ከፍተኛ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ዝግጅቱን ለማድረግ ደግሞ ሁሉም ወገኖች ያለውን አሳዛኝ ሁኔታ በአንክሮ መረዳት ይገባቸዋል፡፡ የአገር ህልውና ከዕለት ወደ ዕለት አደጋ ውስጥ እየገባና ወገኖቻችን ከእሳት ወላፈኑ በተጨማሪ ለረሃብ ሲጋለጡ፣ ቆም ብሎ በማሰብ የተለያዩ አማራጮችን ማማተር ተገቢ ነው፡፡ ከዕልቂት የተረፉ ወገኖቻችን ተፈናቅለው በረሃብ አለንጋ እየተገረፉ ስለሆነ አማራጮች ይታዩ፡፡ ካለፉት ተደጋጋሚ ስህተቶች በመማር በዚህ አሳሳቢ ጉዳይ መነሻ ምን ይደረግ ብሎ መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ በቅርብ ርቀት የሚገኙ አገሮች በእርስ በርስ ፉክክር ሳቢያ የማያባራ ጦርነት ውስጥ ገብተው ሕዝባቸውን ለዕልቂትና ለአካል ጉዳት፣ ለስደትና እጅግ ከፍተኛ መጠን ላለው የንብረት ውድመት ዳርገዋል፡፡ በኢትዮጵያም ዕልቂትና ውድመት የሚያበቃበት ዘዴ ይፈለግ፡፡ ኢትዮጵያዊያን በረሃብ እየተቆሉ ያሉ ወገኖቻቸውን ሕይወት የመታደግ ኃላፊነት አለባቸው፡፡

ኢትዮጵያ ያለችበት አጣብቂኝ ሁኔታ ከመፍትሔ ይልቅ ሌላ ችግር ለማስተናገድ ይከብደዋል፡፡ የመፍትሔ ሐሳቦችን ሳይሆን የጥፋት መንገዶችን ለማስተናገድ መሞከር ኢትዮጵያንም ሆነ መላ ሕዝቧን የማይወጡበት አረንቋ ውስጥ ይከታል፡፡ ኢትዮጵያን ከገባችበት ቀውስ ውስጥ ለመታደግ የሚያስፈልገው ብሔራዊ ውይይት ብቻ ነው፡፡ ለግማሽ ክፍል ዘመን ያህል የዘለቀው የተበላሸ የፖለቲካ ፍጥጫ፣ ከድጡ ወደ ማጡ እየሆነ ኢትዮጵያን የማትወጣው አደጋ ውስጥ እየከተተ ነው፡፡ ለቡድኖች ፍላጎት ሲባል ብቻ የኢትዮጵያ ህልውና አደጋ ውስጥ ሲገባ፣ ነዳጅ እያርከፈከፉ የበለጠ ለማባባስ መሞከር የእነ ሶሪያን ዓይነት ዕልቂት፣ ስደትና ውድመት መጋበዝ ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባው በሠለጠነ መንገድ መነጋገር ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ከቡድናዊ ፍላጎት በላይ ለአገርና ለሕዝብ ሲታሰብ ብቻ ነው፡፡ ከማናቸውም ዓይነት የኃይል ተግባር በመቆጠብ በብሔራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባትና መፍትሔ በማፍለቅ ብቻ ነው፡፡ ሕዝባችን በየቦታው ተፈናቅሎ በረሃብ እየተጠበሰ ስለሆነ፣ በመረባረብ ሰላም ማስፈንና ሕይወት መታደግ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ነው ኢትዮጵያን ጠፍንጎ ከያዛትጥፋት ደዌ መታደግ የወቅቱ ጥያቄ የሚሆነው፡፡

አሁን ወቅቱ የተግባር መሆን አለበት፡፡ ዓለም በፍጥነት እየተለወጠ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣት በማንኛውም መስክ የሚታዩ ድክመቶችን ማረም፣ የተበላሹትን ማስተካከል፣ ለሕዝብ ፍላጎት መገዛት፣ የሕዝብ ተሳትፎን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ፣ ከሕዝብ ጋር በግልጽ መነጋገር፣ በአገሪቱ በሰላም ተቻችሎ ለመኖር የሚረዱ የፖሊሲና የስትራቴጂ ለውጦችን ማከናወን፣ የሕዝብን የልብ ትርታ እያዳመጡ ለለውጥ የሚረዱ ማናቸውንም ዕርምጃዎች ለመውሰድ መዘጋጀት፣ ለወጣቶች የአገር ፍቅር መንፈሳቸውን የሚያሳድጉ ሥራዎችን ማከናወን፣ ማሳተፍና የመሳሰሉት ጠቃሚ ሐሳቦች ያስፈልጋሉ፡፡ የመንግሥት ዕርምጃ ኢትዮጵያን ከገባበት አጣብቂኝ ውስጥ ከማውጣት በላይ ሕዝቡን የሚጠቅምና የሚያረካ ይሁን፡፡ ጊዜን በሚገባ ለመጠቀም፣ ኢትዮጵያውያንን በሙሉ ለማንቀሳቀስና ውጤትማስመዝገብ መትጋት አስፈላጊ ነው፡፡ ያለንበት ዘመን ጊዜ ባለፈባቸው አስተሳሰቦች እንደማይመራ የዓለም በርካታ ክስተቶች እያሳዩ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ከሕዝቡ ንቃተ ህሊና ጋር የሚመጣጠን ምላሽ ይጠበቃል፡፡ የተፈናቀሉ ወገኖች ተርበው ከንፈር መምጠጥ ፋይዳ የለውም፡፡ የተራቡ ወገኖችን ሕይወት ለመታደግ ተግባራዊ ምላሽ የግድ ነው፡፡ ኢትዮጵያም ከቀሰፋት ደዌ መገላገል አለባት፡፡

ዘመናዊነት ለማኅበራዊ ዕድገት ትልቅ ፋይዳ አለው፡፡ የለውጥ አንቀሳቃሽ በመሆኑም በሕዝቡ ባህል፣ ልማድ፣ አኗኗር፣ አስተሳሰብ፣ መስተጋብርና በመሳሰሉት ዕመርታ እንዲኖር ይረዳል፡፡ የረቀቁ ቴክኖሎጂዎችን ለማወቅና ለመላመድ ያግዛል፡፡ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገውን ሽግግር ያፋጥናል፡፡ ከግብርና ኢኮኖሚ የበላይነት በማላቀቅ የኢንዱስትሪ ሽግግርን ያቀላጥፋል፡፡ በኅብረተሰቡ ውስጥ ለግጭት የሚዳርጉ አላስፈላጊ ሽኩቻዎችን በውይይትና በድርድር ያለዝባል፡፡ ጭፍን ጥላቻዎችና በመረጃ ያልተደገፉ ጥርጣሬዎችን ከማስወገዱም በላይ፣ በግልጽ የሚታዩ መረጃዎችንና ማስረጃዎችን በማቅረብ ሥልጡን ግንኙነቶችን ያዳብራል፡፡ በተትረፈረፈ ሀብታቸው፣ በምርት ዕድገታቸውም ሆነ በጥራታቸው፣ የረቀቁ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀማቸው፣ የተንደላቀቀ ኑሮ ለዜጎቻቸው በማመቻቸታቸው፣ በሕዝባቸው ውስጥ ተመጣጣኝ ዕድገት በመፍጠራቸውና ተሰሚነት በማግኘታቸው በዓለም ገዝፈው የሚታወቁ በሥልጣኔ ወደፊት የገፉ አገሮች ብቻ ናቸው፡፡ የኋላቀርነት ትርፉ ድህነትና በሽታ ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያም ፅኑ ደዌ የለከፋት ከሥልጣኔ ጋር ተለያይታ፣ የግጭትና የትርምስ መናኸሪያ በመሆኗ ነው፡፡ ልጆቿ ከቀዬአቸው ተፈናቅለው እየተራቡ ያሉትም በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ሕይወታቸውን ለመታደግ ርብርቡ ይጠናከር፡፡

አገር የምትለማው፣ የምታድገው፣ የምትበለፅገውና በዴሞክራሲያዊ ጎዳና ላይ በኩራት መረማመድ የምትችለው ከዘመናት ችግሮች በመላቀቅ ለዜጎቿ ምቹ ስትሆን ብቻ ነው፡፡ አስተማማኙና ዘለቄታዊው መንገድ ይኼ ብቻ ነው፡፡ አንድ ሕመምተኛ ከሚያሰቃየው ፅኑ ደዌ የሚድነው በሚገባ ተመርምሮ ፈውስ የሚሆነው መድኃኒት ሲታዘዝለትና በአግባቡ ሲወስደው ነው፡፡ አገርም የሚያስፈልጋት እንዲህ ዓይነቱ ፍቱን አሠራር ነው፡፡ ከምንም ነገር በላይ ኢትዮጵያ ለምትባል ትልቅ አገር ህልውና ልዩ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል፡፡ በተሳሳተ መንገድ ህልውናዋን በማሳነስ ጠባብ ቡድናዊ ጉዳዮች ላይ ብቻ ማተኮር የሚጎዳው መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፡፡ የአሁኑ ትውልድ ለመጪው ትውልድ ማስረከብ ያለበት ምን እንደሆነ ማወቅ ይኖርበታል፡፡ አሁን የሚታዩ ችግሮች ከአገር ፍቅርና ከመጪው ትውልድ ፍላጎት አንፃር ዘለቄታዊ መፍትሔ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡ ይህንን አለማድረግ በታሪክ ያስጠይቃል፡፡ ትርፉም መቆጨት ይሆናል፡፡ አገርን የምታህል ትልቅ የጋራ ቤትና ይህንን ጀግናና ኩሩ ሕዝብ ይዞ ዕልቂትና ውድመት ውስጥ መዘፈቅ በፍጥነት ማብቃት አለበት፡፡ ኢትዮጵያ የገጠማት ችግር ስለሚታወቅ መፍትሔውም አስተማማኝ መሆን አለበት፡፡ መሸፋፈንና ማደባበስ ይብቃ፡፡ ሕዝባችን ለከፋ ረሃብ እየተጋለጠ በመሆኑ ትኩረት ሕይወት ለመታደግ ይሁን፡፡ ለዓይን ሕመም ማሸት  እንደማይታዘዘው ሁሉ፣ ኢትዮጵያን ቀስፎ የያዛት ፅኑ ደዌም መድኃኒቱ ዕልቂትና ውድመት መሆን የለበትም፡፡ ሌላው ጉዳይ በሒደት እንደሚደረስበት ተስፋ በማድረግ፣ ለጊዜው ግን ከረሃብ ጋር ለተፋጠጡ ወገኖች ሕይወት አድን ምላሽ ያስፈልጋል!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከፍተኛ ትርፍ ቢያገኝም የውጭ ምንዛሪ ገቢው ቅናሽ ማሳየቱ ተጠቆመ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2016 የሒሳብ ዓመት ያሰባሰበው የውጭ ምንዛሪ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለልዩነት ዕውቅና የማይሰጥ ፖለቲካ ፋይዳ ቢስ ነው!

በፍርኃትና በሥጋት የተኮማተረ አገር ለመለወጥም ሆነ ለማደግ ዝግጁ መሆን አይችልም፡፡ አጉል ድፍረትና ምግባረ ብልሹነት በተንሰራፋበት ስለነፃነት መነጋገር አይቻልም፡፡ ፍርኃት እንደ ወረርሽኝ አገር ምድሩን አዳርሶ...

ለሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎቶች ልዩ ትኩረት ይሰጥ!

በዚህ ዘመን ለሰው ልጅ የሚያስፈልጉ ነገሮች ብዛታቸው እየጨመረ ቢመጣም፣ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን መሠረታዊ የሚባሉ ፍላጎቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ሊቸራቸው ይገባል፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ...

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተገኙበት የሚዲያ ሽልማት ሥነ ሥርዓት መካሄዱ ይታወሳል፡፡ ‹‹ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ለሠሩ የአገር ውስጥና የውጭ...