Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ተጀመረ!

በአዲስ ዓመት መንፈስ ተሞልተን እነሆ መንገድ ጀምረናል። አዲስ ዓመትን በተስፋና በጥንካሬ የጀመረ ካሰበበት መድረሱ አይቀርም ይባል ነበር ድሮ፡፡ ድሮን አትናቁ፡፡ ድሮን ያስታወሰ የወደፊቱ አይከብደውምና፡፡ ከፒያሳ ወደ አዲሱ ገበያ ልንጓዝ ነው። መንገድ ጅማሬ እንጂ መቋጫ የለውም ይላሉ ጎዳናውያን ተራማጆች። የአረማመድ ቄንጥ ከእነ ጫማ ቁጥራችን ተብጠርጥሮ በሚበረበርበት በዚህ ጎዳና፣ ተጓዥና አጓጓዥ ብዙ ይባባላሉ። ‹‹ታያታለህ እንዴት እንደ ለበሰች? አሁን ቢጫ ኮት በጥቁር ሱሪ ይደረጋል?›› ይላል ከተሠለፍነው መሀል አንዱ። በሩቅ አውቶሞቢሏን በንቃት እየዘወረች ውበት የለቀቀባትን ቀዘባ እየጠቆመ። ‹‹ኮቱንስ ይሁን፣ ሱሪዋን እንዴት ከዚህ ሆነህ ልታየው ቻልክ?‹‹ ይላል ወዳጁ። ‹‹ቀላል ነው፣ እንደ እኔ ተደራጅተህ ቡቲክ ስትከፍት ይገልጽልሃል…›› ይላል ያኛው። ‹‹ለዚህም ተደራጁ ተባለ እንዴ?›› ቦርሳ ያንጠለጠለ ጎልማሳ ጠየቀ። ‹‹እነሱ ደግሞ ማን ናቸው?›› ዓይኑ ከዚያች ባለቢጫ ኮት ወጣት አልነቀል ያለው ጠየቀ። ጎልማሳው በኮባ እንደተጠቀለለ ያልበሰለ ሊጥ መልሱ በጥያቄ ተሸፍኖ ተመለሰለት መሰል ዝም አለ። ‹‹ሰው በቃ በተውላጠ ስም እነሱ እኛ እያለ ማነካካቱንሙድአደረገው አይደል?›› ይለኛል ከኋላዬ የተሠለፈ ቀጭን ጎልተው የሚንከባለሉ ዓይኖች ያሉት ወጣት። ወሬው ሊደራ ነው!

 ትከሻዬን ሰብቄ በአልገባኝም ስመልስለት ደግሞ፣ ‹‹ቆይ ለምን አንደኛውን መሀል ገብቶ አስቁሟትሊፍትአይጠይቃትም?›› ይለኛል። የቅርብ ሩቅ አዳሪው ሰምቶት ኖሮ፣ ‹‹ማን በሠራው መንገድ ነው ማን መሀል ገብቶ የሚገጨው?›› ብሎ ዞረበት። ከጀርባዬ የቆመው ደፋር ‹‹አየህ? ወይ ማጥመድ አይችሉ ወይ መጥለፍ አይሳካላቸው፣ ዝም ብለው ዳር ቆመው ቄንጥ ሲያወጡ ሰው ይመስላሉ…›› ብሎ ጎሸመኝ።እኮ እነ ማን?” ብሎ ያኛው ሲያፈጥ፣ ‹‹ስለማን ነው የምናወራው? ስለእኛና ስለእነሱ ነዋ…›› ብሎት ደረቱን ነፋ። ባለቦርሳው ጎልማሳ ዘወር ብሎ፣ ‹‹አቤት! አቤት! ተናግሮ ሞቷል እባክህ። የማይረባ ቅኔ ዘረፍን እያሉ ሰላማችንን የሚያደፈርሱብንን ምናለበት ቢያጣሩልን…›› አለ። ሁላችንም እንዳሻን የማይገጥመውን ሳይቀር ገጣጥማችሁ ትርጉም ካልሰጣችሁ በምንልበት ጊዜ፣ አጣሪኮሚሽንቢቋቋም ማን ሊተርፍ ነው? እንጃ!

አሁን ታክሲ ተሳፍረናል። ከጀርባዬ ተሠልፎ ጆሮዬ ሥር ሲተነፍስብኝ የነበረው ደፋር መሀል መቀመጫ ላይ ከአንዲት ወይዘሮ ጋር ተሰይሟል። ወይዘሮዋ ደርባባነታቸው ልዩ፣ አለባበሳቸው ደግሞ ማራኪና ጥንቅቅ ያሉቸው። ‹‹እማማ እባክዎ ይኼን ግርማ ሰው ሁሉ እንዲያየው ይዘውት እንዳይወርዱ አደራ…›› ይላል ወጣቱ። ‹‹ምን ላድርገው ታዲያ? ልስቀልልህ?›› ይሉታል እያሾፉ። ተጫዋች ናቸው። ‹‹የለም ይፍቀዱልኝና ፎቶ ላንሳው…›› ዓይን አውጣው ፊት ሲሰጠው ያቀረበው ጥያቄ ነው። ‹‹እንዴ? እናንተ ልጆች የፎቶ አብዮት ነው የያዛችሁት የዕድገት? ጊዜው ሥሩብኝ ይላል እናንተ ደግሞ ቴክኖሎጂ አገዘን ብላችሁቀጭ! !› ያለችውን ሁሉ እንደ ፓፓራዚ በፎቶ ምች ስታሳድዱ መዋል ሆኗል ሥራችሁ። እንዲያው ምን ይሻላችኋል?›› ከናፍራቸውን አጣመው ጥርሳቸውን ብልጭ እያደረጉ ያዩታል። ጨዋታ ይችላሉ!

ጉዟችን ቀጥሏል። ከሾፌሩ ጀርባ የተቀመጡ ሁለት ሴቶች ሲያወሩ ቀሪዎቻችን አዳማጮች ነን። ‹‹ገና ለገና አሜሪካ ቪዛ ተመታልኝ ብላ እንዲህ ፀባዩዋ ይቀየር?›› ትላለች ወደ መስኮቱ ጥግ የተቀመጠችው። ‹‹አትገርምሽም? ብርቅ ነው እንዴ አሜሪካ መሄድ? ባንሄድም ዕድሜ ለሆሊውድና ለሲኤንኤን የማናውቀው ነገር የለም…›› ትላለች ጫፍ ላይ የተቀመጠችው። ‹‹ውይ ሰው! ሰው ግን…››  ስታማትብ ቆይታ፣ ‹‹ሳገኝ ከምከዳ አምላኬ ሆይ መጀመርያውኑም አትስጠኝ…›› ብላ አጉል ቃል ገባች። ይኼን ጊዜ ጎልማሳው ወደ ጆሮዬ ጠጋ ብሎ፣ ‹‹ምንድነው የምትለው ልጅቷ? ቪዛ አግኝቶ ይቅርና በባዶ መስሎኝ ሰው የይሁዳን መንገድ የተናነቀው። አይደለም እንዴ?›› ይለኛል። ‹‹አምና ሳይሆን አይቀርም የአዲሱን ዓመት እንጃ…›› የሚለው ከጀርባችን የተቀመጠ ጎልማሳ ነው፡፡ እውነትም እንጃ!

‹‹ሳር ያለ ሐሳብ እየለመለመ፣ የሜዳ አበባ ያለአትክልተኛ እያበበ፣ አዕዋፍ ያለጭንቅ አየርና ባህር እየቀዘፉ የሰው ልጅ ለአንገት ማስገቢያ፣ ለዕለት ጉርሱ ሲታመስ. . . ሳቅ ሳቅም ይላል፣ እንባ እንባም ይላል። ፍልስፍናችን ያው የድግግሞሹ ሕይወታችን ውልድ ነውና ተደጋገመ ብሎስ ማን በምን ጥበቡ ይጠይቀናል? በዛ፣ አነሰ የማን የተፈቀዱ ቃላት ናቸው? ዝምታስ ማን ያፀዳው ሕገ መንግሥት ነው? የመሬት ነው የሰማይ? ስንጠይቅ ውለን ስንጠይቅ ብናድር ቋቱ አይሞላም። የድካማችን ደመወዝም የሰቀል ሽርፍራፊ ያህል አይሰፈርም። እንዲሁ ድካም፣ እንዲሁ ዋይታ፣ እንዲሁ ነገር፣ እንዲሁ ሁካታ እንደ ቀንና ሌት፣ ወራትና ዘመናት ይፈራረቃሉ። መቆም የሚባል ነገር አይታሰብም። እንኳ ለመቆም እየተፍጨረጨርን ተኝተንም ካልተገላበጥን አይሆንም። ምናልባት የዘመኑ መርህ መገላበጥ የሆነው ለዚያ ይሆን?›› የሚለው በሐሳብ የሚዋልለው ጎልማሳ ነው፡፡ ወይ ሐሳብ!

‹‹ሲዘሉ መሰበር የመንገዱ ህልውና መሠረት ቢሆንም ቅሉ፣ በዚህ በአገራችን የአረማመድ ዘዬ ሳንዘል በተቀመጥንበት የተሰበርን ጥቂት አይደለንም። የዚህ ጎዳና ትርክት ብዙ ነው። መውጣትና መውረድ አክርማና ስንደዶ ሆነው ያልቀየሱት ጎዳና የትም አገር ታሪክ አይኖርም። ነፃ ብሎ መንገድ፣ እንደ ጨርቅ የሚጠቀለል አልጋ በአልጋ ጎዳና ለሰው ልጅ አይገባውም የተባለ የተፈጥሮ ሕግ ነው። በዚህ ግጭቱ፣ ተንኮሉ፣ ተግዳሮቱ፣ ሸሩ በማያልቅ የሰው ልጅ ሕይወት ሁሉም እንደ ራሱ አረማመድ እየተጓዘ፣ እንደ ሕዝብ ደግሞ በጋራ መጓጓዣ ሆኖ የደቦ ታሪኩን ይፈትላል። ዓመት ይመጣል ዓመት ይሄዳል። በፈተለው ልክ ሁሉም የድርሻውን ሕይወት እየሸመነና እየለበሰ፣ ለታሪክ ደግሞም ለታዛቢ በሩን ይከፍታል። መንገድ ሁሉን ይዳኛል። ዘመን ሁሉን ያስተዛዝባል። የፍትሕ ያለህ ባዩ ወዮታ ግን አድሮ ይባባሳል። መልካሙና በጎው ነገር የሚዘልቅበት ዘመን ይሁን አዲሱ ዓመት…›› የሚሉት ደግሞ ወይዘሮዋ ናቸው፡፡ መልካም ምኞት!    

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ወይዘሮዋ በተናገሩት እየተብሰለሰሉ፣ ቆስቁሶ ያናገራቸው ጎልማሳ ድምፁን አጥፍቶ፣ አንዱ ከቀበሌ እስከ ፓርላማ የሚታዘበውን እያወራ፣ እነዚያ ወጣት ጓደኛማቾች መግዛት ስለሚፈልጉት የመኪና ሞዴል እየተወያዩ፣ ካጠገባቸው ደግሞ በዝምታ የተዋጡት ባልና ሚስት እንዳቀረቀሩ መጨረሻችን ቀረበ። ጋቢና ከተቀመጡት አንዱ የአውሮፓ ቡድን ደጋፊ ነኝ እያለ አጠገቡ ከተቀመጠው ሌላ ደጋፊ ጋር ደርቢ ገጥሟል። ‹‹እናንተ ምን አለባችሁ? እኛ እዚህ በጠራራ ፀሐይ በረባ ባረባው እንጋጣለን፣ እናንተ ህልውናችሁን እንኳ ዕውቅና ለማይቸሩ ተራጋጮች ታሸበሽባላችሁ…›› አሉ ወይዘሮዋ። ‹‹ምን እናድርግ? ‘ለራሳችሁ አልቅሱተብሎ ተጽፏል…›› ይላቸዋል ከጎናቸው የተቀመጠው። ‹‹ታዲያ ማርገጃ መሬት ጠፋ? ምን ሩቅ ያስኬዳችኋል?›› ወይዘሮዋ ከፍቷቸዋል። ‹‹ስለመሬት ነክ ጉዳይ ባይወራ ደስ ይለኛል…›› ይለኛል ጎልማሳው። ‹‹ዳይፐርአልቆበታል እኮ ማሙሽ…›› ትላለች ደግሞ ከኋላ ሚስት ለባሏ። ባል ደግሞ፣ ‹‹ምናለበት ብትገዥለት? ከትናንት ወዲያ የሰጠሁሽን ገንዘብ ምን አደረግሽው?›› ብሎ ያፈጣል። ‹‹ይኼ መፋጠጥ በአዲስ ዓመት ከቤት ከጀመረ ደግ አይደለም…›› የሚለኝ አጠገቤ የተቀመጠው ነው፡፡ ምን ያድርግ!

 ‹‹አይደብረውም እንዴ ሰውዬው? በሰው መሀልሼምያስይዛታል እንዴ?›› ይባባላሉ ከሾፌሩ ጀርባ የተሰየሙት ሴቶች። የባልና ሚስቱን ንግግር ከወይዘሮዋ ጎን የተቀመጠው ሲያዳምቅ፣ ‹‹ኳስ እኮ ነጋ ጠባ የሚደጋገም ፕሮፓጋንዳ የለው፣ ፖለቲካ ተኮር ዘገባ አያውቅ፣ የራሱን ድምፅ ለማሰማት ሲል የሰው ድምፅ አያፍን፣ በቃ ምን ልበልዎ ኳስ ኳስ ነው። ደግሞ የአውሮፓ ኳስ? ልዩ…›› ሳይጨርስ ወይዘሮዋ፣የአገርህስ?” ብለው ዞሩበት። ይኼኔ ወያላውመጨረሻ!” ብሎ በሩን በረገደው። ‹‹የአገርህስ ነው እኮ የምልህ?›› ወይዘሮዋ አጥብቀው ይጠይቃሉ።ነገርኩዎ እኮ!” ወጣቱ ተወዛገበ። ተሳፋሪዎች አንድ በአንድ መውረድ ጀመሩ። ኑሮው ፖለቲካ፣ መዝናኛው ፖለቲካ፣ ማስተዛዘኛው ፖለቲካ፣ ኳሱ ፖለቲካ በሆነባት ምድር እግር እርሙን በልቶ መርገጡን ቀጠለ። ችግሩን መዘርዘር ቢቀጥል ማቆሚያ ያለው አይመስልም ነበር፡፡ ገና አዲስ ዓመት ከመግባቱ ስንቱ ችግር ተነግሮ ይዘለቃል? ይልቁንስ  ለበረታ መንገዱ እንደማይከብድ ይታወቃልና፡፡ ለማንኛውም አዲስ ዓመት ተጀምሯል! መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት