Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየፈተና ዓመት

የፈተና ዓመት

ቀን:

ዓርብ ጳጉሜን 5 ቀን የተሰናበተው 2013 .. በውድም ይሁን በግድ ከሰላም ይልቅ ጦርነት ተመርጦ ኢትዮጵያ የደማችበት፣ ዜጎቿ የተሰቃዩበትና የሞቱበት ክፉ ዓመት ሆኖ አልፏል፡፡ ከጦርነቱ ባልተናነሰ ዓለም አቀፉ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እስከ 2013 .. የመጨረሻ ሳምንት ድረስ 4,857 ኢትዮጵያዊያንን የቀጠፈበት፣ በዚህ ውስጥም ትጉህ የማኅበረሰብ አገልጋዮቿ የነበሩትን የኪነ ጥበብ፣ የበጎ አድራጎትና የፖለቲካ ልሂቃን ጭምር ያጣችበት ዓመት ነበር፡፡ ይህ የጦርነትና የፈተና ዓመት ቢጠናቀቅም፣ በኢትዮጵያ ላይ ይዟቸው የመጣቸው መከራዎች አላበቁም፡፡ ያለፈው ዓመት መከራና ችግር በአጭር ይወገድ ዘንድ የአገሪቱ ልሂቃን 2013 .. የታለፈውን በትዝብት እያስታወሱ፣ ከችግሩ መውጫ መንገድ ያሏቸውን ለመንግሥትም ሆነ ለማኅበረሰቡ ያስተላልፉ ዘንድ ሪፖርተር አነጋግሯቸዋል፡፡ የተለያዩ ዘርፎችንና የማኅበረሰብ ክፍሎችን የሚወክሉት ልሂቃን የሰጡትን አስተያየት ይመልከቱ፡፡


 

‹‹ሽምግልና የሚኖረው ተሸምጋዮች ሲኖሩ ነው››

መስፍን አርዓያ (ፕሮፌሰር)፣ የአገር ሽማግሌዎች መድረክ ሰብሳቢ

መስፍን አርዓያ (ፕሮፌሰር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአዕምሮ ሕክምና መምህር፣ የአገር ሽማግሌዎች መድረክ ሰብሳቢና የማንነትና የአስተዳደር ወሰን ኮሚሽን አባል ናቸው፡፡ በ2013 ዓ.ም. ባጋጠሙ ቀውሶችና በቀጣይ መደረግ ስለሚገባቸው ጉዳዮች የሰጡት አስተያየት እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

tender

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ውስጥ በ2013 ዓ.ም. የተለያዩ ችግሮች ተከስተዋል፡፡ እነዚህ ችግሮች በማኅበረሰቡ ላይ ያሳደሩትን ተፅዕኖ እንዴት ይገመግሙታል?

ፕሮፌሰር መስፍን፡- እንግዲህ 2013 ዓ.ም. ከባድ ዓመት ነበር፡፡ ወሳኝ ድርጊቶች የተፈጸሙበትም ነው፡፡ ከእነዚህም መካከል ታላቁ የህዳሴ ግድብ በታሰበው ደረጃ የሞላበትና ሌሎችም የልማት ሥራዎች ይጠቀሳሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በአገሪቱ የደረሱ የተፈጥሮ አደጋዎች ከተጋረጡ ችግሮች መሀል ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ይህም ሆኖ ግን ከሁሉም በላይ በኅብረተሰቡ ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ አንዱ ሰው ሠራሽ ችግር በተለይ ጦርነቱ ነው፡፡ ጦርነቶችና ግጭቶች በየቦታው ነው የተካሄዱት፡፡ ግጭቶቹ በብሔረሰቦችና በአካባቢዎች መካከል ነበር፡፡ እኔ የአገር ሽማግሌዎች መድረክ ሰብሳቢ እንደ መሆኔ መጠን ብዙ ነገሮችን ለማስተዋል ችያለሁ፡፡ የአካባቢ ሽማግሌዎች የአካባቢያቸውን ችግር መፍታታቸው እንደ ታላቅ ድል ይቆጠራል፡፡ ከዚህ አንፃር በሶማሊና በኦሮሚያ፣ በሶማሊና በአፋር ክልሎች፣ እንዲሁም በአንዳንድ ሥፍራዎች ተከስተው የነበሩት ችግሮች በተወሰነ ደረጃ ተፈትተዋል፡፡ ነገር ግን በትግራይና በአማራ፣ እንዲሁም በትግራይና በፌዴራል መንግሥት መካከል የተከሰተውና አሁን መጨረሻ ላይ ደግሞ እስከ አፋር የዘለቀው ችግር በኅብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ማሳደሩ አይካድም፡፡ ተፅዕኖውም ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ሥነ ልቦናዊ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ተፅዕኖዎች ዘርዝር አድርገው ሊያብራሩልን ይችላሉ?

ፕሮፌሰር መስፍን፡- ኢኮኖሚያዊው ተፅዕኖን ወደፊት ነው የምናየው፡፡ የኑሮ ውድነትን እያስተዋልን ነው፡፡ ሰሜን አሁን እያረሰ አይደለም፡፡ በዚህም የተነሳ በ2014 ዓ.ም. ብዙ ችግሮች ሉያጋጥሙ ይችላሉ፡፡ ከትግራይና ከአማራ ክልሎች ውጪ ያሉ በሚገባ ካላረሱና በሚገባ የሚያስፈልገውን ነገር ካላገኙ ከፍተኛ ጫና ማስከተሉ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ጦርነቱ የሚፈጀው ገንዘብና የሚወድመው ንብረት ብቻ ሳይሆን በሰው ሕይወት ላይ የሚደርሰው ውድመት፣ በቀጣዩ ዓመት ሊታዩ የሚችሉ የአካል ጉዳቶችና የአዕምሮ ስብራቶች ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳድሩብናል ብዬ አስባለሁ፡፡ አንድ መታወቅ ያለበት ነገር ቢኖር ችግሩ የሁላችንም መሆኑ ነው፡፡ በትግራይ፣ በምዕራብ ኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በአማራና በአፋር እየደረሰ ያለው ችግር ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚነካ ነው፡፡ በሕዝባችን ላይ ከፍተኛ የሆነ የሥነ ልቦና፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ይፈጥራል ብዬ አስባለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- የአገር ሽማግሌዎች መድረክ በተጠቀሱት ችግሮች ላይ ምን እያደረገ ነው? በዚህስ ያጋጠመው ተግዳሮት ይኖር ይሆን?

ፕሮፌሰር መስፍን፡- የአገር ሽማግሌዎች መድረክ የአካባቢ ችግር በአካባቢ የአገር ሽማግሌዎች ይፈታል ብሎ ያምናል፡፡ በዚህም ምክንያት ነው በሶማሊ፣ በኦሮሚያና በአፋር የተከሰቱት ችግሮች በአካባቢ ሽማግሌዎች ሲፈቱ የነበረ ነው፡፡ እኔ የምመራው መድረክ የሚሠራው ነገር ቢኖር ይህንን ማመቻቸት ነው፡፡ ችግሩ አሁን የደረሰበት ደረጃ ላይ እንዳይደርስ የሃይማኖት አባቶችን ጨምሮ በየጊዜው ወደ አማራ፣ ትግራይና ኦሮሚያ ከዚያም ባለፈ ወደ ተለያዩ ቦታዎች በመመላለስ ጦርነቱ እንዳይጀመር፣ በወንድማማቾች መካከል ዕልቂት ስለሚያመጣ ጥንቃቄ ሊደረግለት እንደሚገባ፣ ፖለቲከኞችም ወደ ክብ ጠረጴዛ ዙሪያ እንዲመጡ እስከ መጨረሻው ሰዓት ወይም ጦርነቱ እስከ ተጀመረበት ድረስ ጥረት ስናደርግ ቆይተናል፡፡ እንዲያውም በመጨረሻ የፌዴራልና የትግራይ ክልል ኃላፊዎች በአዲስ አበባ ከተማ ስብሰባ እንዲቀመጡ ሁኔታዎችን ካመቻቸን በኋላ ነው በስተመጨረሻ የፈረሰው፡፡ እስከዚህ ድረስ መሄዳችንንም መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ጦርነቱም ከተጀመረ በኋላ መቀሌ ሄደን ተኩስ እንዲያቆሙ፣ ተኩስ አቁሙም በሁሉም እንዲተገበር መክረናል፡፡ ተኩስ ከቆመ በኋላ ጥያቄዎች በክብ ጠረጴዛ ዙሪያ መፈታት እንደሚችሉ ከማሳወቅ፣ ከመጎትጎትና ከመሥራት የቦዘንበት ጊዜ የለም፡፡ እነዚህ ጥረቶች ሁሉ በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት ተግባራዊ አልሆኑም፡፡ ሽምግልና የሚኖረው ተሸምጋዮች ሲኖሩ ነው፡፡ ይህ በጣም ወሳኝ ነገር ነው፡፡ አሁንም  ቢሆን ሁሉም ወገኖች ተኩስ አቁመው ወደ ድርድር እንዲመጡ የአገር ሽማግሌዎች መድረክ ምኞትና ፍላጎት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚታየው ችግር በውይይትና በንግግር ይፈታል የሚል እምነት አለዎት?

ፕሮፌሰር መስፍን፡- ከመጀመርያው ቢሆን ኖሮ ይፈታል የሚል እምነት ነበረኝ፣ ሁላችንም ነበረን፡፡ እኛ በጣም ተግተን የሠራነው መጀመርያውኑ ይፈታል ከሚል እምነት ነበር፡፡ በአማራና በትግራይ መካከል የነበረው አለመረጋጋት እንዲወገድ ተንቀሳቅሰን ነበር፡፡ ይህም ማለት የሁለቱንም ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮችን አቶ ገዱና ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ሕዝብ ቃል እንዲገቡ አድርገን እንደነበር አይዘነም፡፡ በዚህም የተነሳ ለአንድ ዓመት ያህል በሁለቱም በኩል ፀጥታ የሰፈነበት ሁኔታ ነበር፡፡ ሁልጊዜ ሕዝቡን፣ ፖለቲከኞችን፣ መሪዎችን በየቦታው ሄደን ስናነጋግር ሕዝቡ የሚለን በሕዝቦች መካከል ምንም ችግር የለም፡፡ ይህም ማለት በአማራ፣ በኦሮሞ፣ በትግራይ ሕዝብ መካከል ችግር የለብንም፣ አሁን ችግር የሚፈጥሩብን ፖለቲከኞቻችን ናቸው የሚል ነው፡፡ እኛም እንዳየነውና እንደተረዳነው ከሆነ በሕዝብ ላይ ጫናና ግፊት ሊኖር ይችላል፡፡ ነገር ልዩነት አለ ብለን አናምንም፡፡ አሁን የሚወሰነው ፖለቲካዊ ውሳኔ ነው፡፡ ይህን ውሳኔ ለመወሰን ሁሉም እስከደፈረ ድረስ ጦርነቱ የማይቆምበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ አሁን የምናየው አዝማሚያ ግን ያንን አስተማማኝ የሚያደርግ አይደለም፡፡ ጦርነቱ ዞሮ ዞሮ መቆሙ አይቀርም፡፡ ነገር ግን በሕዝብ መሀል ጥሎት የሚያልፈው አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ስብራት ለብዙ ጊዜ ይቀጥላል፣ የሚያሳስበንም ይኸው ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- ከዚህ አኳያ ችግሩ በንግግርና በውይይት እንደማይፈታ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል ማለት ነው?

ፕሮፌሰር መስፍን፡- መፍትሔ አያገኝም የምንለው ነገር የለም፡፡ የናይጄሪያ ጉዳይ በአንድ ሽምግልና ላይ በቅርቡ ተነስቶ ናይጄሪያ ውስጥ በደረሰው ጦርነት በተለይ በባያፍራና በፌዴራል መንግሥቱ መካከል በተካሄደው ጦርነት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ያለቁት፡፡ ያ ሁሉ ሕዝብ ካለቀ በኋላ ግን ዕርቅ ወርዷል፡፡ ነገሮችም ያለቁት በክብ ጠረጴዛ ዙሪያ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ልቦና ከሰጣቸው በተለይ፣ በተለይ ጦርነቱን ለማቆም ፍላጎት ካለ ወደ ሰላም የማይመጣበት ምክንያት ይኖራል ብለን አናስብም፡፡

ሪፖርተር፡- ውይይትና ድርድር ለማካሄድ ቅድመ ሁኔታን እንደ መደራደርያ አድርገው የሚያስቀምጡ አካላት አሉ፡፡ በዚህ ዓይነት አካሄድ ችግሮች እንዴት ሊፈቱ ይችላሉ?

ፕሮፌሰር መስፍን፡- እኛ ሽማግሌዎች መጀመርያውንም የተናገርነው ነገር ቢኖር፣ ‹‹ለሰላም ምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ አይሰጥም›› የሚል ነው፡፡ መጀመርያ ሰላምን ትፈጥራለህ፡፡ ይህም ማለት ተኩስ አቁም ከሆነ መጀመርያ ተኩስ ታቆማለህ፡፡ ከዚያ ወደ ክብ ጠረጴዛ ዙሪያ ለመምጣት ትሰማራለህ፡፡ ለዚህም ነው እንግዲህ በሁኔታዎች ላይ ተወያይቶ መፍታት የሚቻለው፡፡ በጉልበት የሚሆን ነገር አይኖርም፡፡ ይህም ጥፋትና ውድመት እንጂ ሌላ የሚያመጣው ነገር የለም፡፡ በነገራችን ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተጠያቂነትም ሊኖር ይችላል፡፡ ስለዚህ ይህ እንዳይሆን ቅድመ ሁኔታ ሳይሆን ጥያቄው በአስቸኳይ ተኩስ ለማቆም ተስማምቶ ወደ ነበረው ስንመለስ መነጋገር ነው የሚያዋጣው፡፡ ሽማግሌ ሁልጊዜ ስለሰላም ነው መናገር የሚችለው፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ ላይ የሚያክሉት ካለ ዕድሉን ልስጥዎት?

ፕሮፌሰር መስፍን፡- በቅድሚያ ለመላው የኢትዮጵየ ሕዝብ ለአዲሱ ዓመት በሰላምና በጤና እንኳን አደረሳችሁ እላለሁ፡፡ በ2013 ዓ.ም. በችግር ብናሳልፍም በታላቁ ህዳሴ ግድብና ባስመዘገብናቸው ልማቶች ድል ተቀዳጅተናል፡፡ ከምንጊዜም በላይ ኢትዮጵያዊነትን እያሳየን መጥተናል፡፡ ለሁላችንም የሚያዋጣን  ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡ ስለሆነም  ባህሎቻችን፣ መብቶቻችንንና ቋንቋዎቻችን በሚገባ እያስከበርን ወደ ብልፅግና ጉዞ መረባረብ ይገባናል፡፡


 

 

‹‹መሸነፍን ማወቅ ትልቅ ነገር ነው››

አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ፣ የኅብረት ባንክ ቦርድ ሊቀመንበርና የኢትዮጵያ የባንክ ዳይሬክተሮች የምክክር ማኅበር ሰብሳቢ

tender

የኅብረት ባንክ የቦርድ ሊቀመንበርና የኢትዮጵያ የባንክ ዳይሬክተሮች ምክክር ሰብሳቢ የሆኑት ጎምቱው ኢንሹራንስ ባለሙያ አቶ ኢየሲስ ወርቅ ዛፉ በተጠናቀቀው 2013 ዓ.ም. ቀውሶችና መፍትሔዎችን በተመለከተ የሰጡት አስተያየት እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡- በ2013 ዓ.ም. እንደ ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ችግሮች ተከስተዋል፡፡ እነዚህን ችግሮች እንዴት ይገልጿቸዋል? በተለይ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የተከሰተው ችግርስ በውይይት ይፈታል ብለው ያምናሉ?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- አንዳንድ ጊዜ ይህን ብዬ ነበር ማለት ሲበዛ ጥሩ አይደለም፡፡ ለብዙ የአገሬ ሕዝብ በሰሜን ኢትዮጵያ የደረሰው ነገርና ዛሬ ያለንበት ሁኔታ ሊመጣ እንደሚችል የታወቀው ዛሬ አይደለም፡፡ እ.ኤ.አ. በ1992 የዛሬ 30 ዓመት ማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያን በዘጠኝ ክልሎች በሁለት ከተሞች ተከልለው አዲስ ካርታ በሽግግር መንግሥቱ በተመሠረተበት ወቅት፣ ነፍሳቸውን ይማረውና የሽግግር መንግሥቱ ሸንጎ አባል የነበሩት ዶ/ር ኃይሌ ወልደ ሚካኤል፣ ወ/ሮ ገነት ዘውዴና ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ አንድ የት እንዳሉ የማላውቃቸው አንድ የሶማሌ ተወላጅ ናይጄሪያ ሌጎስ በሚገኘው ኢትዮጵያ ኤምባሲ ውስጥ ኢሕአዴግ ስላመጣው ለውጥ መረጃ እንሰጥኃለንና ለብቻህ ና ተብዬ ሄጄ ነበር፡፡ እነዚህ ሰዎች ሲያወያዩኝ በዚያች ምሸት ከተነሱ ነገሮች ውስጥ አንዱ በኢትዮጵያ ውስጥ ቀደም ብለን የፊውዳልን ሥርዓት ነበር ስንታገል የነበረው፣ በደርግ ጊዜ ደግሞ በድሆችና በባለፀጎች መካከል ቅራኔ በመኖሩ ይህ የሚፈታው በማርክሲዝምና በሌኒኒዝም ነው የሚፈታው ተብሎ ተሞክሯል፡፡ በእኛ አገር ሁኔታ ግን እኛ የተረዳነው በብሔር ብሔረሰብ ባለው ልዩነትና ጭቆና ነው፡፡ እሱን መልስ ካገኘንለት ኢትዮጵያ ከዚህ በኋላ ችግር አይገጥማትም ብለን ነው የምናምነው አሉኝ፡፡ እኔ ደግሞ የሽግግር ጊዜ ነው ብላችኋል፣ ያለውም የሽግግር መንግሥት ነው፡፡ እናንተም የሽግግር ሸንጎና መንግሥት አባላት ነን ብላችሁኛል፡፡ እንደ ሽግግር ሸንጎና መንግሥት ሥር ነቀል ለውጥ እናደርግም ብላችሁኛል፡፡ ታዲያ የኢትዮጵያን ካርታ እንደገና ለምን ሠራችሁት? በዘርና በሃይማኖት ላይ የተመሠረተ ፌዴራሊዝም የተዳፈነ እሳት ነው፡፡ ነገ ከነገ ወዲያ ያቃጥለናል፡፡ ይልቁንስ በንጉሡ ጊዜ ብዙ የጎደሉ ነገሮች ቢኖሩም፣ እውነተኛ የኢትዮጵያዊነት ስሜት እያቆጠቆጠ መምጣት ጀምሯል፡፡ በተለይ በአዳሪ ትምህርት ቤቶች ውስጥ፡፡ ተማሪ ሆኜ፣ የተማሪ መሪ ሆኜ ጃንሆይ ፊት ቀርቤ፣ የጮህኩበት አድኃሪነት በዚህ ሰዓት መቅረብ የለበትም፡፡ ጊዜውን ጠብቆ እንጂ ወደፊት ብዬ ነበር፡፡ በዘር ላይ የተመሠረተ ፌዴራሊዝም በምንም መንገድ አይሆንም፡፡ ኢትዮጵያ ስዊዘርላንድ አይደለችም፡፡ አንድ ቀን ያቃጥለናል ብዬ ተናግሬ ነበር፡፡

ምናልባት ትዝ ካለህ ከሦስት ዓመት በፊት በሒልተን ሆቴል በተዘጋጀ አንድ መድረክ ላይ እንዲሁ ይህንን ደግሜ ተናግሬያለሁ፡፡ እዚህ መድረክ ላይ አቶ ዓባይ ፀሐዬ፣ አቶ ስብሃት ነጋ፣ እንዲሁም ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳም ነበሩ፡፡ በዚሁ መድረክ ላይ ያቀረብኩት ሌላም ጉዳይ ነበር፡፡ ይህም አንቀጽ 39 እስከ መገንጠል በሚል የተቀመጠው፣ ማርክሲስቶች እንዲሁ ስላሉ እነሱ በሕገ መንግሥታቸው ውስጥ ስላስቀመጡት ነው? ወይስ ያን ጊዜ የኤርትራ ነፃ አውጪ ግፊት ስለነበር እነሱን ለማስደሰት ስትሉ ነው? ወይስ ለምንድነው ይህንን ያደረጋችሁት? ይህ እኮ እንደገና የተዳፈነ እሳት ነው ብዬ ነበር፡፡ ዛሬ በዓይኔ በገሃድ የማየው የአጥፍቶ ጠፊ ሥራ (ጠመንጃ ይዘው የሚዋደቁትንና የሚወድቁትን ትተን) ንፁኃን ኢትዮጵያውያን ከወዲህም ከወዲያ፣ በመነኮሳትና በሕፃናት ላይ ሳይቀር እንዲህ ያለውን ዓይነት ጥፋት ያስከተለው ጉዳይ ሊመጣ እንደሚችል ይታወቅ ነበር፡፡ አድማጭ ባለመኖሩ፣ መወያየት በጣም እያነሰ በመሄዱ፣ ምንም ሳንዘጋጅ ዱብ ዕዳ ነው የመጣብን፡፡ በአሁኑ ጊዜ እንደ ሕግ ነገሮችን በውይይት መፍታት የሥልጣኔ ምልክት ነው፡፡ እኔም መሠረታዊ እምነቴ ይኼ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አጠቃላይ እንዲህ ያለውን አገራዊ ቀውስ ለመፍታት መፍትሔው ምን መሆን አለበት?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- አሁን ባለንበት ሁኔታ ከሆነ እንጃ መለኮታዊ መፍትሔ ካልሆነ በስተቀር፣ በምን ሁኔታ በሰላም ልንፈታው እንደምንችል ለማመልከትና ለማሰብ ያስቸግረኛል፡፡ የግድ አንዱ ወገን ሸብረክ ካላለ እንዴት ሊሆን ነው? አሁን ባለንበት ሁኔታ በተለይ ያለፉትን ሁለት ሳምንታት ያየሁት ነገር፣ ሁላችንም እንደ እምነታችን መለኮታዊ መፍትሔ ያስፈልገናል፡፡ መፍትሔው ላልከው አንዳንድ ጊዜ መሸነፍን ማወቅ ትልቅ ነገር ነው፡፡ በበኩሌ በመጨረሻ ለአንድ ወገን ወገንተኛ ነን፡፡ ይህም ወገንተኝነቴ ኢትዮጵያ አትከፋፈልም፣ ኢትዮጵያውያን መከፋፈል የለባቸውም የሚል ነው፡፡ ሚስተር ታቦ ኢምቤኪ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን የመጡ ሰሞን እዚህ አዲስ አበባ በተዘጋጀ መድረክ ላይ ንግግር አድርገው ነበር፡፡ አስተማሪ ንግግር ነበር፡፡ ሚስተር ማንዴላ ታስረው እስር ቤት በነበሩበት ጊዜ የነጮቹ መንግሥት ከኒልሰን ማንዴላ ጋር ድርድር አካሄደ፡፡ ከጊዜ በኋላ ከሁሉም በኩል ሊያደርጉት የተስማሙት ምንድነው ብለን ብንጠይቅ፣ ጥቁሮቹ ነጮቹን አላሸነፉም፣ ነጮቹም ጥቁሮቹን አላሸነፉም፡፡፡ ስለዚህ ምንም እንኳን ነጮቹ የበላይነት ቢኖራቸውም ተሸነፉ፡፡ ይህም ሲሆን ያሉት አንድ ነገር፣ ‹‹ደቡብ አፍሪካ የምትባል አገር አለችን፤›› የሚል ነበር፡፡ ይህች አገር የሁላችንም ነች፡፡ የነጮቹም የጥቁሮቹም አገር ነች፡፡ ይህችን አገር ሁላችንም ልንኖርባት ስለሚገባ እንሰብሰብና እንዴት ሁላችንም አብረን ልንኖርባት እንደምንችል እንወያይ፡፡ በዚህ ውይይት ውስጥ ስንገባ ግን ስምምነት ላይ እስከምንደርስ ማንኛውም ወገን ጠመንጃ አያነሳም፡፡ ይህንን ቃል ኪዳን ሁለቱ ወገኖች ፈጽመው ነው ስብሰባ የጀመሩት፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ካለው የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር ግን የደቡብ አፍሪካው ገጠመኝ ለእኛ እንደ ምሳሌ ሊሆን ይችላል? ምክንያቱም በሽብርተኝነት የተፈረጀ አካል ተዋናይ በሆነበትና ኢትዮጵያ ትጥፋ የሚል መፈክር የያዙ ጭምር የሚሳተፉበት ከመሆኑ አንፃር መነጋገር ይችላል ወይ? ወደ አንድ ስምምነት የሚያመጣ ነው ወይ?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- እሱን እኮ ነው ያልኩህ፡፡ መሸነፍን ማወቅ ብልህነት ነው፡፡ ኢትዮጵያን አጠፋለሁ ማለት አይቻልም፡፡ ኢትዮጵያ አትጠፋምና ይህንን ማለት አይቻልም፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ እንደማትጠፋ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ደቡብ አፍሪካ እኮ አርበኞች ሲነሱ ነጮቹን ባህር ውስጥ አስገብተን እኛ አሸንፈን ይህችን አገር እንወስዳለን፣ ነጮቹም ደግሞ እነዚህ ጥቁሮች ምንም ዓይነት ነገር አንሰጣቸውም፣ እናጠፋቸዋለን ብለው ነው የተነሱት፡፡ በመጨረሻ ላይ ግን ከጊዜ በኋላ የደረሱበት ደቡብ አፍሪካ አንድ አገር ነች፣ ነጮችም ጥቁሮችም በዚህች አገር መኖር አለባቸው የሚል ነው፡፡ እንዴት አብረን እንደምንኖር ቁጭ ብለን እንወያያለን፣ ቁጭ ብለን ስምምነት ላይ እስከምንደርስ ድረስ ግን ማንኛውንም የጦር መሣሪያ አናነሳም ብለው ቃል ገብተው ነው፡፡ እስሁንም ድረስ በጥቁሮችና በነጮች መካከል ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ብዙ ያልተፈቱ ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ ስለዚህ የሚቀጥል ውይይት ነው፡፡ ኑሮ ራሱ ውይይት ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያ ትጥፋ ብለው መነሳታቸው አይሆንም፡፡ እኛም ደግሞ ኢትዮጵያን እናፈራርሳለን ስላሉ እነሱን ጨርሰን ከምድረ ገጽ ካላጠፋናቸው አናርፍም ማለት አያስፈልግም፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ መቋጫው ምን ይሁን ታዲያ?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- ከሁለቱም በኩል ልክ እንደ ደቡብ አፍሪካ ኢትዮጵያ አገራችን ነች፣ ኢትዮጵያ አትፈራርስም፡፡ ይህች አገር የሁላችንም እንደ መሆንዋ መጠን ሁላችንም አብረን መኖር ስላለብን እንወያይ፣ እንነጋገር፣ እስክንስማማ ድረስ ግን አንገዳደልም ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ባለው ሁኔታ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል የሚለውን ጥያቄ ደጋግመን እንድናነሳ የምንገደድባቸው ሁኔታዎች አይኖሩም?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- ይህንን እንግዲህ ማድረግ በሁለቱም በኩል ትልቅ ተራራ እንደ መውጣት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ያለው ቀውስ ውስጥ ከመገባቱ በፊት ችግሮችን በውይይት ለመፍታት በፌዴራል መንግሥቱ በኩል ብዙ ነገሮች ተሞክረው ነበር እኮ? አሁንስ እንዴት ማስኬድ ይቻላል? ብዙዎች ሊሆን የሚቻል አይሆንም ይላሉ፡፡

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- አውቃለሁ፣ ግን ተስፋ አይቆረጥም፡፡ እነዚህ መርዝ የሚተፉ መሪዎችን ብቻ አይደለም ማሰብ ያለብህ፣ የአገሩን ሕዝብ አስብ፡፡ መሬቱን ብቻ ነው የምንፈልገው? የፈለገው ሰው የፈለገውን ይበል፡፡ ትግራዋዮችም ኢትዮጵያዊያን ናቸው፡፡ ስለዚህ ባሉበት ሁኔታ አይቀጥልም፡፡ ዞሮ ዞሮ ኢትዮጵያ አትፈርስም፣ ከዚያ የሚሰማውን ተወው፡፡ ኢትዮጵያን በምንም ሁኔታ እንደማትጠፋ ሊገነዘቡ ይገባል፡፡ ይህንን ግንዛቤ መውሰድ ካልቻሉ እነዚህ ሰዎች መጀመርያውኑ ታሪካዊ አደጋ ናቸው እንጂ፣ መሪዎች አይደሉም ብዬ ነው የምወስደው፡፡


 

‹‹ጦርነቱ ቢደመደም እንኳን ጠባሳው ለትውልድ የሚሻገር ነው››

አቶ ክቡር ገና፣ የኢኮኖሚ ባለሙያ

አቶ ክቡር ገና፣ የኢኮኖሚ ባለሙያ

          የኢትዮጵያና የአዲስ አበባ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን በመምራት የሚታወቁትና በቅርቡም ኢዜማን (የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕን) በመወከል ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምርጫ በዕጩነት ቀርበው የተወዳደሩት የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ክቡር ገና፣ በተጠናቀቀው 2013 ዓ.ም. የተከሰተው ጦርነትና ውጤቶቹን አስመልክቶ የሰጡት አስተያየት እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ በተጠናቀቀው 2013 ዓ.ም. በጣም የተፈተነችበት ነው፡፡ ጦርነትና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች ዋነኞቹ ናቸው፡፡ በዓመቱ የተፈጠሩትን ችግሮችና በማኅበረሰቡ ላይ ያሳደሩትን ተፅዕኖ እንዴት ይገልጹታል?

አቶ ክቡር፡- ወደ ጦርነት የገባንበት የመጀመርያው ጥይት ከመተኮሱ አስቀድሞ፣ ለወራት የታቀደና ዝግጅት የተደረገበት ራሳችንን ያቆሰልንበት ጦርነት ነው፡፡ በፌዴራል መንግሥት ሥልጣን ላይ ሆኖ አገር ማስተዳደርና የማያቋርጥ ቋሚ ውይይትና መግባባትን የሚጠይቅ ውስብስብ ሒደት መሆኑን ሁላችንም እንገነዘባለን፡፡ ከዚህ በመነሳት ጦርነትን በቀላሉ መቀበልና ማስተናገድ አይገባንም ነበር፡፡ ምክንያቱም ጦርነት አንዴ ከተጀመረ እንደ ስፖርት በቀላሉና በፈለግነው ጊዜ ልናቆመው የምንችለው አይደለም፡፡ ጦርነት ጥሎት የሚያልፈው ጠባሳ ለትውልድ የሚሻገር ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ጦርነት ቢቆም እንኳ ጦርነቱ አልቋል ማለት ላይሆን ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- የተለያዩ ወገኖች በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ያለውን ጦርነት ለመግታት ውይይትን በመፍትሔነት ያቀርባሉ፡፡ ይህ ጦርነት በፖለቲካ ውይይት ይፈታል ብለው ያምናሉ?

አቶ ክቡር፡- በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ያለው ጦርነት ድልን በመጎናፀፍ ወይም አንዱ አንዱን ስላሸነፈ እንደማይቆም ሁሉም የሚረዳው እውነታ ነው ብዬ እገምታለሁ፡፡ የፌዴራል መንግሥት ጦርነቱን በበላይነት ቢያሸንፍና ከዚያ በኋላ የሰላም ስምምነት ተደርጎ ጦርነቱ ቢደመደም እንኳን፣ ከእንዲህ ዓይነቱ ሰፊ ግጭትና ጦርነት ወደ ሰላም ለመሸጋገር የጠራ የሽግግር ሥርዓት የለም፡፡ ቢሆንም ችግሩን ለመፍታት ቀጥተኛም ሆነ ቀጥተኛ ያልሆነ የፖለቲካ ውይይት እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ ምንም እንኳ ሰላም መፍጠር አስቸጋሪ ቢሆንም፣ ሁለቱም ወገኖች ማለቂያና መውጫ ወደ ሌለው ሁኔታ ከመግባታቸው በፊት ውይይት ያስፈልጋል ብዬ አምናለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- አገሪቱ አሁን ከገጠማት ቀውስ ለመውጣት ምን መደረግ አለበት ይላሉ?

አቶ ክቡር፡- ወደ ሰላም ለመምጣት የፖለቲካ ውይይት መፍትሔ ሊያመጣ እንደሚችል በመገመት፣ ሁለቱም ወገኖች ወደ ውይይት ጠረጴዛው ለመምጣት ፈቃደኛ መሆንና ለዚህ የሚከፈለውን መክፈል አለባቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ ከተቻለም ከሁለቱ ውጪ ሁሉም የክልል መንግሥታት አመራሮችን በውይይቱ በማሳተፍና ሁሉንም የፖለቲካ የልዩነት ነጥቦች ጠረጴዛ ላይ አኑረው፣ አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመፍጠር የሠለጠነ ውይይት ማድረግ አለባቸው እላለሁ፡፡


 

‹‹መንግሥት ኃላፊነቱን እንዲወጣ በአጽንኦት እንጠይቃለን››

ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ፣ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጠቅላይ ጸሐፊ

tender

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ፣ አገሪቱ በ2013 ዓ.ም. የገጠማተን ፈተና በተመለከተና በአዲሱ ዓመት ከዚህ ፈተና ለመውጣት መንግሥትና ማኅበረሰቡ ምን ማድረግ እንደሚገባቸው የሃይማኖት ተቋማትን በመወከል አስተያየታቸውን ለሪፖርተር ሰጥተዋል፡፡ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ጥያቄ፡- በ2013 ዓ.ም የተከሰቱት የተለያዩ ችግሮች በማኅበረሰቡ ላይ ያሳደሩት ተፅዕኖ ምንድነው?

መልስ፡- የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ የአንበጣ መንጋ የጎርፍ መጥለቅለቅ ጉዳቶች፣ ብሔርንና ሃይማኖትን ሽፋን ያደረጉ ግጭቶችና ሁከቶች፣ ወታደራዊ የሕግ ማስከበር ዘመቻንና ጦርነትን ተከትሎ በንፁኃን ላይ የሕይወትና የንብረት ጉዳት መድረስና መፈናቀል አሉታዊና ፈታኝ ክስተቶች እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ በሌላ በኩል ገደብ የለሽ ሆኖ እየቀጠለ ያለው የኑሮ ውድነትም ለበርካታ ዜጎች፣ በተለይም በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደረው ኢትዮጵያዊ ኑሮውን እንዳከበደው እንረዳለን፡፡

ጥያቄ፡- የተፈጠረውን አገራዊ ቀውስ ለማስተካከል መወሰድ ያለበት መፍትሔ ምንድነው?

መልስ፡- ጦርነት ሰውን የሚበላና የአገርን ውስን ሀብት የሚያወድም መጥፎ ክስተት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከዚህ አንፃር መንግሥት ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም. በትግራይ ክልል የነበረው ጦርነት እንዲያበቃ የተናጠል የተኩስ አቁም በማወጅ፣ ለሰላም ያለውን ፍላጎትና ዝግጁነት በተግባር ያሳየበት መሆኑንና እንደ መንግሥትም ኃላፊነቱን ለመወጣት የወሰደው አቋም የሚደነቅ ነው፡፡ ስለሆነም ዛሬም መንግሥት ሰላምን የማስቀደም መርህና ሕጋዊ አሠራር በከፍተኛ ዲሲፕሊን እንዲረጋገጥ፣ ፍትሕ ሳይጓደል ሕግና ሥርዓት እንዲጠበቅ መንግሥታዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ በአጽንኦት እንጠይቃለን፡፡ አገራዊ መግባባትን በማጎልበት የሁሉንም ወገን ሐሳብና አመለካከት ያለ ምንም አድልኦ የሚያስተናግዱ ነፃና ግልጽ የውይይት መድረኮችን በማመቻቸት፣ በመካከላችሁ ፍፁም መከባበር፣ ይቅርታና እውነተኛ ዕርቅ በማድረግ ኢትዮጵያን እንድታሻግሩ ከልብ እናሳስባለን፣ እኛም ፈጣሪ ይረዳችሁ ዘንድ እንጸልያለን፡፡

የአገራችን ወቅታዊ ፈተና በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ተለዋዋጩ የፖለቲካ ዕሳቤ ከሕዝብ ማንነት ስለማይበልጥ ስሜታዊ በሆኑ ኃላፊነት በጎደላቸው ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች የሚደረጉ ንግግሮችንና ቅስቃሴዎችን በምክንያታዊነት ኢትዮጵያውያን እንዲመዝኑ፣ የሁሉንም ወገን ሐሳብ እንዲያከብሩ፣ አላስፈላጊ ፍረጃን እንዳይቀበሉ አደራ እላለሁ፡፡ ከማንኛውም ፓርቲና የፖለቲካ ማኅበር ይልቅ የአገርን ዘላቂ ጥቅም በማስቀደም የዜግነት ኃላፊነታችሁን ትጠብቁ ዘንድ አደራ እንላለን፡፡ ልባችሁን ለይቅርታና ዕርቅ ክፍት በማድረግ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱና ትከባበሩ ዘንድ አደራ እንላለን፡፡


 

‹‹በእያንዳንዱ ጥይት ውስጥ እየሄደ ያለው ዶላርና ብር ነው››

ዳኪቶ ዓለሙ (ዶ/ር)፣ በአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ የንግድ ሥራ ኮሌጅ የአካውንቲንግና ፋይናንስ ትምህርት ክፍል ኃላፊ

tender

ዳኪቶ ዓለሙ (ዶ/ር) የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በአካውንቲንግ ከሃረማያ ዩኒቨርሲቲ፣ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን በአካውንቲንግና ፋይናንስ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያገኙ ሲሆን፣ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ህንድ አገር ከሚገኘው አንድራ ዩኒቨርሲቲ በኮርፖሬት ፋይናንስ ተቀብለዋል፡፡ በሃረማያ ዩኒቨርሲት በመምህርነትና የትምህርት ክፍል ኃላፊነት ያገለገሉ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የንግድ ሥራ ትምህርት ቤት ከመምህርነት ባሻገር ያለፉትን ሁለት ዓመታት የአካውንቲንግና ፋይናንስ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ሆነው እያገለገዩ የሚገኙ ዕድሜያቸው ከሰላሳዎቹ አጋማሽ ትንሽ ከፍ ያለ ምሁር ናቸው፡፡ ከመምህርነታቸው ባሻገር ከፋይናንስ ጋር በተያያዘ ከአሥር በላይ የመንግሥት የልማትና የግል ድርጅቶችን የማማከር ሥራዎችን ሠርተዋል፡፡ ከማማከር ሥራቸው ባሻገር የተለያዩ ከፋይናንስ ተቋማት ጋር የተገናኙ ጥናቶችን፣ የፕሮጀክት ጥናቶችን ያደረጉ ሲሆን፣ ገሚሶቹ የታተሙ ሲሆን ቀሪዎቹ በሒደት ላይ ናቸው፡፡  በ2013 ዓ.ም. ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶች ላይ የሰጡት አስተያየት እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡- 2013 .ም. ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በእርስዎ ሙያዊ ምልከታ እንዴት ይገለጻል?

ዳኪቶ (ዶ/ር)፡- የ2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ በሁለት የተለያዩ መልኮች ማንሳት ይቻላል፡፡ አንድም መልካም የሆኑ እንቅስቃሴዎች የተስተዋሉበት ሲሆን፣ በሌላም በኩል ደግሞ ችግሮችና ፈተናዎች የተስተዋሉበት ነው፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ተደምረው ያመጡት ውጤት ምንድነው የሚለውን ማየት ያስፈልጋል፡፡ ምንም እንኳን እንዲህ ዓይነት ጉዳዮች በጥናት ላይ ተመሥርተው መተንትን ቢገባቸውም፣ ሆኖም ግላዊ ዕይታን መሠረት አድርገው የሚገለጹት ጉዳዮች የሚከተሉት ናቸው፡፡ በተጠናቀቀው የ2013 ዓ.ም. በኢኮኖሚ ረገድ መንግሥት ከወሰዳቸው ዕርምጃዎች ውስጥ የብር ኖት ለውጡ አንዱ ጉዳይ ነው፡፡ ከሌሎች  አገሮች ተሞክሮ ለማየት እንደሚቻለው አገሮች የገንዘብ ኖቶቻቸውን ሲለውጡ የተለያዩ ችግሮች ያጋጥሟቸዋል፡፡ በተለይ ታዳጊ የሚባሉት አገሮች፡፡ ከዚህ አንፃር በኢትዮጵያ የተደረገው የብር ኖት ለውጥ ውጤታማ ነው ለማለት ይቻላል፡፡ አገሪቱ የብር ኖቷን ባትለውጥ ኖሮ አሁን ያለው የዋጋ ግሽበት ከሚባለው በላይ ይባባስ ነበር፡፡ አንድ አገር የገንዘብ ለውጥ እንድታደርግ ከሚያደርጓት ነገሮች መካከል ህብዕ ኢኮኖሚ ወይም ከሕግ ውጪ የሚደረጉ የንግድ እንቅስቃሴዎች ሲበዙ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ግሽበት፣ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርና ኅትመቶች እንዲስፋፉ በር ይከፍታል፡፡

ሌላው በዓመቱ ከታዩ መልካም የሆኑ ጉዳዮች መካካል የፋይናንስ ዘርፉን ለማሻሻል መሞከሩ ነው፡፡ በሌሎች አገሮችም የፋይናንስ ዘርፉ ሲሻሻል ኢኮኖሚያዊ ዕድገቶች መመዝገባቸው የሚጠበቅ ነው፡፡ የኢኮኖሚ ዕድገት በቀላሉ ከሚገለጽባቸው ጉዳዮች አንዱ የፋይናንስ እንቅስቃሴ ስለሆነ፡፡ ይህም ብር ካለበት አንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ማንቀሳቀስ መቻልን ይመለከታል፡፡ በተለይ በበጀት ዓመቱ የወጣው የካፒታል ገበያ አዋጅ ትልቅ አስተዋፅኦ አለው ተብሎ ይታመናል፡፡ ይህም በዋናነት ባንኮችን ጠንካራ ከማድረጉ ጋር ይያዛል፡፡ የሚያመጣው ለውጥ ወደ ፊት የሚታይ ቢሆንም፣ የተደረገው እንቅስቃሴ በጥሩ ጎኑ ይጠቀሳል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የንግድ አዋጁ የተሻሻለበት ሒደትም በበጎ ጎኑ የሚነሳ ጉዳይ ነው፡፡ ከወለድ ነፃ የሆኑ የፋይናንስ እንቅስቃሴዎች  በስፋት ባለፈው ዓመት ውስጥ ወደ ተግባር ተቀይረዋል፡፡ ሰዎች በፍልስፍናቸውና በሚያስቡት ነገር የመጠቀም ጉዳዮችን በግሌ በጥሩ እወስደዋለሁ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ዋናው ተፈላጊ ነገር ሀብት መንቀሳቀሱ እስከሆነ ድረስ፡፡ ሌላውና ትልቅ ጉዳይ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን በወቅቱ የማገባደድና የመጨረስ እንቅስቃሴ ተጠቃሹ ነው፡፡ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ በከተማዋ ተግባራዊ የተደረጉት ፕሮጀክቶች አለማንሳት አይቻልም፡፡

የውጭ ዕዳን በመቀነስ ረገድ የተሠራው ሌላው ተጠቃሽ ጉዳይ ነው፡፡ ውጤታማ ያልሆነን ፕሮጀክት ማቆም ተገቢ ውሳኔ ነው፡፡ ኢንቨስትመንትን የሚያስገባ ብቻም ሳይሆን የሚያስወጣ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ያስፈልጋታል ይቺ አገር፡፡ ለዚህ ማሳያ ከሆኑ ዘርፎች መካካል የኮንስትራክሽን ዘርፉን ማንሳት ይቻላል፡፡ ቁጥሩን በትክክል ለማስቀመጥ ብቸገርም፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚ 30 በመቶ የሚንቀሳቀሰው በኮንስትራክሽ ዘርፉ ነው፡፡ ያ ማለት ብሮች የሚንቀሳቀሱት በኮንትራክተሩ ነው፡፡ ሆኖም በዚያው መጠን ገንዘብ በበቂ ሁኔታ የለኝም የሚለው አካልም ኮንትራክተሩ ነው፡፡ ውጤታማ ያልሆነን ፕሮጀክት ይዞ ውጤታማ ካልሆነ ራሱንም አይጠቅምም፣ አገርንም አይጠቅምም፡፡ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ፈታኝ ከሆኑ ጉዳዮች ውስጥ ደግሞ የአገሪቱ ፖለቲካዊ ሁኔታ የተረበሸ መሆኑ ክፍተቶችን የፈጠረ ጉዳይ ነው፡፡ ፖለቲካና ኢኮኖሚ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው፡፡ ሁለቱን ነጣጥሎ ማየት አይቻልም፡፡ የአገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ የፈጠረው ተፅዕኖ በግልፅ የሚታይ ነው፡፡ ኮቪድንም ሳንረሳ፡፡

የግብርና ምርታማነት መቀነስ ሌላው ችግር ነው በአንድ አገር ላይ በተለይም በክረምት ወቅት፣ እዚህም እዚያም ጦርነት እስካለ ድረስ ማምረት ፈታኝ ነው፡፡ ተፅዕኖውም ቀጣይነት ያለው ይሆናል፡፡ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴው ላይ ያሳደረው ተፅዕኖም ጉልህ ነው፡፡ ከጥር 2013 ዓ.ም. በፊት የነበረውን የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ብንመለከት በ20 በመቶ መቀነሱን ያሳየናል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ከውጭ የሚላከው የሃዋላ እንቅስቃሴ ቀንሷል፡፡ እነዚህ ሁሉ ብዙ ተፅዕኖዎች አላቸው፡፡ ከላይ ለተጠቀሱት ኢኮኖሚ መዋዠቆች ሁሉ መሠረት የሆነው ጉዳይ ሰላም ነው፡፡ ሰላም እንዲመጣ የሕግ የበላይነት መከበር አለበት፡፡ የሕግ የበላይነት ካልተከበረ ተረጋግቶ የሚከናወን እንቅስቃሴ አይኖርም፡፡ የበረሃ አንበጣ በራሱ ኢኮኖሚው ላይ ምን ያህል ጫና እንደፈጠረ መረዳት ይቻላል፡፡ የተመረተውንም ምርት ምን ያህል እንዲቀንስ እንዳደረገው የሚታወቅ ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ክስተቶች ምን ዓይነት ተፅዕኖዎች ፈጠሩ የሚለውን ስናይ፣ በዋናነት ኢኮኖሚው እንዳያድግ ነው ያደረጉት፣ ድህነትን ነው ያባባሱት፣ የዋጋ ግሽበትን ነው የጨመሩት፡፡

በንድፈ ሐሳብ ደረጃ የዋጋ ግሽበት በምንድነው የሚመጣው የሚለውን ስናይ፣ የብር ኢኮኖሚ ውስጥ መብዛት ነው ብለን ልናነሳ እንችላለን፡፡ ይኼ አንዱ ምከንያት ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ብቸኛው ምክንያት አይደለም፡፡ ብር ኢኮኖሚ ውስጥ ባይኖርም የዋጋ ግሽበት ሊፈጠር ይችላል፡፡ የምርት አቅርቦት እስከሌለ ድረስ ግሽበትን ማስተካከል አይቻልም፡፡ በመሆኑም አቅርቦት ላይ ሊሠራ ይገባል፡፡ ምርታማነት ላይ ተፅዕኖ ከሚፈጥሩ ነገሮች መካከል አንዱ ጦርነት ነው፡፡ በጦርነት በዋነኛነት የሚሳተፈውና ሕይወቱ የሚያልፈው ወጣቱ እንደ መሆኑ መጠን፣ ከጦርነት ውጪ ባለው ሒደት የሚቀሩት ሕፃናትና አዛውንቶች ናቸው፡፡ ይህም ምርታማነት እንዲቀንስ ምክንያት ይሆናል፡፡ ጦርነት ለአጭር ጊዜ ተካሄደ ለረዥም ጊዜ የሚፈጥረው ተፅዕኖ ትልቅ ነው፡፡ በእርግጥ አንድ አካል ወደ ጦርነት የሚገባው በብዙ ገፊ ምክንያቶች ሊሆን ይችላል፡፡ በእርግጥ ፖለቲካውን ተከትለው የተፈጠሩት ቀውሶች በአጭር ጊዜ ተፈተው የሚቀረፉ ናቸው ለማለት አንችልም፡፡ ሆኖም ፖለቲካዊ ጉዳዮች የሚፈቱት በፖለቲካ እንደሆነ ግን መዘንጋት የለበትም፡፡

ሪፖርተር፡- አገሪቱ የገጠማትን ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመፍታት ምን ዓይነት መፍትሔዎች ያስፈልጋሉ?

ዳኪቶ (ዶ/ር)፡- ከዋጋ ግሽበት ጋር ተያይዞ በቀላል አቀራረብ ለማስቀመጥ ያህል የሚሆነው ምንድነው? አሁንም ቢሆን መሠራት ያለበት ምርታማነት ላይ ነው፡፡ የገንዘብ አቅርቦት ችግር ባይኖርም ምርት እስኬለ ድረስ፣ ምርታማነት ካላደገ ያለው ምርት ተመናምኖ ሌሎች ቀውሶችን ይፈጥራል፡፡ በአገሪቱ ያለው የምርት አቅርቦት አነስተኛ ስለሆነ መንግሥት ማድረግ ያለበት የሞኒተሪና የፊስካል ፖሊሲ ሥራ እንዳለ ሆኖ፣ በተጓዳኝ ምርታማነት ላይ ብዙ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ በተለይም የመሠረታዊ የምግብ ፍጆታ አቅርቦቶች በዋናነት በአገር ውስጥ መመረት የሚችሉት ላይ ብዙ ሊሠራ ይገባል፡፡ በዚህ ሁሉ ሒደት ውስጥ የግሉን ዘርፍ ማበረታት ያስፈልጋል፡፡ ምንም እንኳን ያስኬዳል አያስኬድም የሚለው እንዳለ ሆኖ በአገልግሎት ዘርፍ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በግብርናው ዘርፍም መንግሥታዊ የሆኑ ኢንተርፕራይዞች ሊኖሩ ይገባል፡፡ ይህን የምለው ለምንድነው? አገር በቀል ባለሀብቶችን ብንወስድ አደጋ ተጋፍጠው ወደ አንድ ዘርፍ መግባት አይፈልጉም፡፡ በመሆኑም በሰፋፊ የእርሻ ሥራ መንግሥት ቀድሞ ገብቶ በመሥራት፣ በዘርፉ ለውጥ አምጪ ሥራዎችን በማከናወን፣ በግሉ ዘርፍ እንዲከናወን ቀስ ብሎ ጥሎ መውጣት ይጠበቅበታል፡፡ እንደዚያ ካልሆነ ከዚህ ቀደም ለሰፋፊ እርሻ መሬት ልማት በሚል ስም ከባንኮች ብር ወስደው 40 በመቶውን በበሬ አስተራረስ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የተፈጠረው ችግር ነው የሚደገመው፡፡ ከገበሬው የተለየ አሠራርን ተግባራዊ አላደረጉም፡፡ ለምን ቢባል? አደጋ መጋፈጥ ስላልፈለጉ፡፡ በመሆኑም መንግሥት የግሉን ዘርፍ በሰፋፊ እርሻ ልማት ሊገባ ከሚችልባቸው ጉዳዮች መካከል፣ በዘርፉ ውስጥ ገብቶ መሥራት ይቻላል የሚለውን በማሳየት ነው፡፡ በዚህም ሳቢያ አቅርቦትን ማሻሻል ይቻላል፣ የምርት አቅርቦት ማዕከላት ቁጥር የተሻሻለ ይሆናል፣ የዋጋ ግሽበትንም በአጭር ጊዜም ባይሆን በዓመታት ውስጥ በተቻለ መጠን የሚስተካከልበት ሁኔታ ይኖራል፡፡

ሌላው ትልቁ ጉዳይ መንግሥት ተዓማኒነት ያላቸውን መንግሥታዊ ተቋማትን መፍጠር ይገባዋል፡፡ አዲስ የሚቋቋመው መንግሥት በዚህ ረገድ ብዙ የቤት ሥራ ይጠብቀዋል፡፡ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች በደመነፍስና ለሚዲያ ፍጆታ ሲሉ መሥራት የለባቸውም፡፡ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ እንዲህ ሆነ ብለው መልዕክቶችን በማኅበራዊ ትስስር ገጽ ከማጋራት ባለፈ የሚታይ ነገር ሊሠሩ ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- ቀጣዩ ጊዜ  ከአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች አንፃር እንዴት ይሆናል ብለው ይጠብቃሉ? ምንስ መልዕክት ያስተላልፋሉ?

ዳኪቶ (ዶ/ር)፡- ከላይ ስንዘረዝራቸው የመጡ ጉዳዮች ከፖለቲካና ከዲፕሎማሲ ጋር የሚያያዙ ናቸው፡፡ መንግሥት እንደ መንግሥት ራሱን ዓይቶ ምን ማድረግ አለበት የሚለውን አንስተናል፡፡ ነገር ግን አንድ ያልተነሳ ጉዳይ ቢኖር የአርቴፊሻል የዋጋ ግሽበት ጉዳይ ነው፡፡ ለምሳሌ የዚምባቡዌን ጉዳይ እዚህ ላይ ማንሳት ይቻላል፡፡ አገሪቱን ጠፍሮ የያዛት አርቴፊሻል ግሽበት ነው፡፡ ምዕራባውያን አገሮች እጃቸው ረዥም ነው፡፡ ኢትዮጵያን ከምትጠቀማቸው ባለ ወደብ አገሮች ጋር በመመሳጠር በእጅ አዙር ነገሮችን ለማባባስ እንቅስቃሴ አያደርጉም ማለት አንችልም፡፡ ስለሆነም በአካባቢው ያሉ አገሮችንና አልፎ ተርፎም የምዕራቡ ዓለም አገሮችን በስልት መያዝ አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ያ ካልሆነ አርቴፊሻል የምንለው የዋጋ ግሽበት በአገሪቱ ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ ቀላል አይሆንም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ አገሮች የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የቱ ጋ ስስ ነው የሚለውን ጠንቅቀው የሚያውቁ በመሆናቸው፣ ይህን ጉዳይ ታሳቢ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የአገሪቱ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ መሆን አለበት፡፡ ምርታማነትን ማጠናከርና የግሉ ሴክተርን መደገፍ እንዲሁ ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም፡፡ በተጨማሪም እዚህና እዚያ ያሉ አለመረጋጋቶችን በዘዴ መያዝ ያስፈልጋል፡፡ ያላለቁ ፕሮጀክቶችን ወደ ሥራ ማስገባት መንግሥትን የሚያጠናክሩት ናቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶችን በውይይትና በተለያዩ ሥልቶች ማርገብ ያስፈልጋል፡፡ ያ ካልሆነ በእያንዳንዱ ጥይት ውስጥ እየሄደ ያለው ዶላርና ብር ነው፡፡ አገር ውስጥ ተተኳሽ መሣሪያ ቢመረትም ጥሬ ዕቃው የሚመጣው ከውጭ ነው፡፡ በአጠቃላይ ቀጣዩ የአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ስንመለከት ሁለት ዓይነት ጉዳዮችን መጠበቅ ይቻላል፡፡ በአዎንታዊ ጎኑም ሆነ እንዲሁም በፈታኝ ሒደት ውስጥ፡፡


‹‹አዲሱ ዓመት መረጋጋት የሚሰፍንበት የለቅሶና የሞት ዜናዎች ቀርተው በሰላም የምንኖርበት ዘመን ይሁንልን››

አቶ ውበቱ አባተ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ

tender

የተጠናቀቀውን 2013 ዓ.ም. አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ጋር የተደረገው አጭር ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡- በተናጠቀቀው ዓመት በእግር ኳስ ስፖርት ዘርፍ የገጠሙ ፈተናዎችና ዕድሎች ምንድናቸው?

አቶ ውበቱ፡- በ2012 ዓ.ም መጠናቀቂያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ መንግሥት ማንኛውም ሰው በቡድን እንቅስቃሴ ማድረግ እንደማይችል ክልከላ ማድረጉን ተከትሎ፣ እግር ኳስም የችግሩ ሰለባ ነበር፡፡ ክለቦችም ከተጫዋቾች ጋር የነበራቸው እንቅስቃሴ የተገደበ በመሆኑ ምክንያት፣ ተጫዋቾች ለሰባት ወራት ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ሳያደርጉ በመቆየታቸው፣ ተጫዋቾችን ለማዘጋጀት ከ2012 ዓ.ም. መጠናቀቂያ እስከ 2013 ዓ.ም ድረስ ጊዜ ወስዶብናል፡፡

በሽግግር ወቀት ከስድስት ሳምንት  ያላነሰ ጊዜ ቢያስፈልግም፣ የመጀመርያ የማጣሪያ ጨዋታ ለማድረግ ከአንድ ወር ያነሰ ጊዜ ውስጥ ኒጀርን ገጥመናል፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ቡድናችን ከጊዜ ወደ ጊዜ፣ ከጨዋታ ወደ ጨዋታ እየገነባንና እያሻሻልን፣ ከስምንት ዓመት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፍ ችለናል፡፡ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፋችን ትልቅ ድል ነበር፡፡ ለዚህም በርካቶች የሚመሠገኑበት ነው፡፡

በ2013 ዓ.ም. ተመልካቾች ስታዲየም ተገኝተው ጨዋታ መመልከት ካለመቻላቸውም በላይ፣ ለእግር ኳስ መልካም ጊዜ ነበር፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የቀጥታ የቴሌቪዥን ሽፋን ማግኘቱና ሊጉ በክለቦች መተዳደር መቻሉ የእግር ኳሱ ስኬታማ ዓመት ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- በ2014 ዓ.ም. ተስፋ የሚያደርጉት ምንድነው? ለመላው ማኅበረሰብ የሚያስተላልፉትስ መልዕክት?

አቶ ውበቱ፡- በ2012 ዓ.ም. ጥር ወር ላይ የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ይካፈላል፡፡ ይኼ ብሔራዊ ቡደን የሁሉም ኢትዮጵያዊ ስለሆነ ቡደኑን ሁሉም ዜጋ፣ እንዲሁም መንግሥትም ባለው አቅም ድጋፍ ሊያደርጉለት ይገባል፡፡ ከዚያ በሻገር 2014 ዓ.ም. ለሁሉም የሰላም፣ የፍቅርና የደስታ ይሁን፡፡ አዲስ ዓመት መረጋጋት የሚሰፍንበት የለቅሶና የሞት ዜናዎች ቀርተው በሰላም የምንኖርበት ዓመት ይሁንልን፡፡


 

‹‹ለዚህ ሁሉ ችግርና ቀውስ የዳረጉን ሕግ ፊት መቅረብ አለባቸው››

ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ

tender

ስመ ጥሩ አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ኢትዮጵያ በ2013 ዓ.ም. ያለፈችበትን ፈተና ለማስቀረት ሲጥሩ ከነበሩ ተሰሚነት ያላቸው ኢትዮጵያዊያን መካከል አንዱ ነው፡፡ ጥረቱ ግን ፍሬ አላፈራም፡፡ ይባስ ብሎ ማኅበረሰቡን ለመርዳት ያስገነባው ትምህርት ቤት የጦርነቱ ሰለባ ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያ የተፈተነችበትን 2013 ዓ.ም. አስመልክቶ የሰጠው አስተያየት እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡- በ2013 ዓ.ም. በአገሪቱ የተከሰቱ የሚገኙ የተለያዩ ችግሮች በማኅበረሰቡ ላይ ያሳደሩትን ተፅዕኖ እንዴት ትገልጻቸዋልህ?

ሻለቃ ኃይሌ፡- 2013 ዓ.ም. በሁለት ወገኖች ማለትም ኢትዮጵያ ትፍረስ በሚሉና ኢትዮጵያ አትፈርስም በሚሉ እጅግ አደገኛ በሆነ ፈተና ውስጥ ነው ወደ 2013 ዓ.ም. ያለፍነው፡፡ በኅብረተሰቡ ዘንድም ከኑሮ ውድነት ጀምሮ ሕይወትና ንብረት እንደ ቀልድ ሲጠፋ ያየንበት ዓመትም ነው፡፡ ኢትዮጵያ አገር እንደ አገር የመቀጠሏ ነገር በራሱ እጅግ አጣብቂኝ ውስጥ የገባበት፣ በአጠቃላይ ትልቅ ፈተና ያሳለፍንበት ዓመት ነው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ 2013 ዓ.ም. ጥሩ ነገሮች ይዞልን መጥቷል፡፡ ዓመቱ ምንም እንኳ ችግርና ችግር ያጋጠመው ቢሆንም፣ እኔ በዕድሜ ካየሁት ሁሉ የበለጠ ነገር ይዞልን መጥቷል፡፡ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ከዳር እስከ ዳር ነግሶ የወጣበት ጥሩ አጋጣሚ ሆኖ ያለፈበትም ዓመት ነው፡፡ በዚህ ረገድ አገር መፍረስ አለበት ብለው በመነሳት ለዚህ ሁሉ ችግርና ችጋር ለዳረጉን ወገኖች በግሌ ምሥጋናዬ ከፍ ያለ ነው፡፡ በጣም በጣም ጠቅመውናል፡፡ ሕዝባችንን ከዳር እስከ ዳር አነቃንቀውታል፡፡ በተለይ የኢትዮጵያዊነት ስሜት ከምንጠብቀው በላይ ከፍ ብሎ የወጣበት ዓመት ነበር፡፡

እንዲህ ዓይነት ኢትዮጵያዊነት በእኔ ዕድሜ አልተመለከትኩም፡፡ ለዚህም ነው ግጭቱ ያስከተለው ጉዳትና ችግር እንደተጠበቀ ሆኖ ጥሩ ነገር ይዞልን መጥቷል ያልኩት፡፡

ሪፖርተር፡- ዓለም አቀፍ ችግር ከሆነው ኮቪድ-19 በተጨማሪ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍልና በተለያዩ አካባቢዎች ያረበበው አደጋ በውይይትና በንግግር ይፈታል የሚል እምነት አለህ?

ሻለቃ ኃይሌ፡- ቀድሞ ቢሠራበት ኖሮ ይህ ሁሉ የሰው ሕይወትና ንብረት ባልጠፋ ነበር፡፡ የሆነ ሆኖ ግን እንደ ሽማግሌ ችግሩን በውይይትና በንግግር ለመፍታታ ዕድሉ አለ ብዬ አምናለሁ፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ችግሩ በውይይት ይፈታል ብሎ ለማሰብ ከባድ ነው፡፡ ምናልባት ጦርነቱ ከተቋጨ በኋላ ውይይትና ንግግር የሚለውን ተስፋ አልቆርጥም፡፡ ይሁንና ለዚህ ሁሉ ሞትና ውድመት ምክንያት የሆኑ ሕግ ፊት ቀርበው መጠየቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ቀጥሎ ነው ውይይትና ድርድር መምጣት ያለበት፡፡ ይህ ሳይሆን የስንት ሰው ቤተሰብ ሕይወትና ንብረት ወድሞ ድርድርና ውይይት እንዴት ሊሆን ይችላል? ይህ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ አሁንም ሆነ ወደፊት መናገር የምፈልገው በአንድ ሉዓላዊ አገር የቱንም ያህል ልዩነት እንኳ ቢኖር፣ ከግጭት በፊት መነጋገርና መወያየት ያስፈልጋል፡፡ በየትኛውም ዓለም ጦርነት ለትውልድ የሚተርፍ ውድመት ካልሆነ ትርፍ አያስገኝም፡፡ የእኛዎቹም ከዚህ ሁሉ በፊት ረጋ ብለው ቢያስቡ ኖሮ ዛሬ የምናወራው ጥፋት ባልተከሰተ ነበር፡፡ ሕዝብ ፍትሕ ይፈልጋል፣ የአንድ አገር ሕዝብ ፍትሕ ካላገኘ በአገሩና በመንግሥቱ እምነት ያጣል፡፡ ለዚህም ነው አሁን ጦርነቱ መቋጫ ሳያገኝ ውይይትና ድርድር ተዓማኒነቱ አናሳ ነው ያልኩት፡፡ ፍትሕ የግድ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም በጦርነቱ ከፍተኛ ሰቆቃና እንግልት የገጠማቸው ወገኖች ያለ ምንም ፍትሕ፣ የጠፋው ሁሉ ጠፍቷል በሚል ነገሮች በውይይትና በድርድር መፍትሔ ያገኛሉ ማለት ለእኔ አግባብነት የለውም፡፡ ምክንያቱም በግለሰቦች ዕብሪትና ማናለብኝነት የጠፋው የሰው ሕይወትና ንብረት ቀላል አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- በአጠቃላይ የተፈጠረውን አገራዊ ቀውስ ለማስተካከል መወሰድ ያለበት መፍትሔ ምንድነው?

ሻለቃ ኃይሌ፡- አሁን በአገራችን የተፈጠረው ቀውስ ቀደም ተብሎ ነገሮች በውይይትና በንግግር እንዲፈቱ ቢደረግ ኖሮ ባልተከሰተ ነበር፡፡ እንደ ሽማግሌነቴ አሁንም ውይይትና ንግግር እንዲኖር እፈልጋለሁ፡፡ ምክንያቱም ቀውሱ ለሁላችንም (ለሁሉም የኅብረሰብ ክፍል) አደጋ አለው፡፡ በመሆኑም ጣት ከመጠቋቆም ወጥተንን መነጋገር አለብን፡፡ ለጠፋው ጥፋት በሕግ መጠየቅ ያለበት እንደተጠበቀ ሆኖ ማለቴ ነው፡፡ ተቀራርቦ መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ የብዙ ሰው ሕይወትና ንብረት ጠፋቷል፣ ወድሟል፡፡ ያንን እያስታወሱ መቆዘም አያስፈልግም፡፡ ተቀራርቦ በመወያየትና በመነጋገር ኢትዮጵያም እንደ አገር ሕዝቡም እንደ ሕዝብ ወደ ቀድሞ እንቅስቃሴ እንዲመለስ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የብዙ ሰው ሕይወትና ንብረት ወድሟል፣ በቃ ሊባል ይገባል፡፡ ይህ ከመሆኑ በፊት ግን አሁንም ደግሜ ደጋግሜ መናገር የምፈልገው ለዚህ ሁሉ ችግርና ቀውስ የዳረጉን ወገኖች ሕግ ፊት መቅረብ አለባቸው፡፡


 

‹‹በዚህ ዘመን ጦርነት ውስጥ መግባታችን ሊያመን ይገባል››

ወ/ሪት ከውሰር ኢድሪስ፣ የኢዜማ የምርጫ ስትራቴጂና ማኔጅመንት ሰብሳቢ

tender

ወ/ሪት ከውሰር ኢድሪስ ዕድሜያቸው በ30ዎቹ የመጀመርያ አካባቢ ሲሆን፣ በሕግ የመጀመርያ ዲግሪ አላቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) የምርጫ ስትራቴጂና ማኔጅመንት ሰብሳቢ ናቸው፡፡ በፓርቲው ውስጥ ግንባር ቀደም ከነበሩ ጥቂት ሴቶች አንዷ በመሆን ይታወቃሉ፡፡ የተጠናቀቀው ዓመት እንዴት እንዳለፈ የሰጡት አስተያየት እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡- 2013 ዓ.ም. ኢትዮጵያ በርካታ ክስተቶች የታዩበት ዓመት ነበር፡፡ እርስዎ ደግሞ በኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ፓርቲ ውስጥ ትልቅ ቦታ ነበረዎት፡፡ ዓመቱ እንዴት አለፈ?

ወ/ሪት ከውሰር፡– 2013 ዓ.ም. የመጀመርያው ነገር በኢትዮጵያ ከለውጡ በኋላ በትክክል ምርጫ ያደረግንበት ዓመት ነው፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ እኔ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዕጩ ነበርኩ፡፡ በተጨማሪም የኢዜማ የምርጫ ስትራቴጂ ማኔጀመንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ነበርኩ፡፡ በዚህ ዓመት ቀጥታ አዲስ ነገር ይዞልን ይመጣል የሚል ተስፋ ባደረግነው ምርጫ ውስጥ በቀጥታ ተሳታፊ ነበርኩ፡፡ በዚህ ምርጫ እኛ ስንንቀሳቀስ የነበረው እንደ ስድስተኛ አገራዊ ምርጫ ሳይሆን አንደኛ አገራዊ ምርጫ እንደሆነ አድርገን በማሳብ ነው፡፡ ይህ ማለት አንዴ እንኳን እንዲህ ዓይነት ሽግግር ይደረግ በሚል ሙሉ ነገራችንን ሰጥተን ያደረግነው ምርጫ ነው፡፡ እንግዲህ ውጤቱም መጥቷል፣ ነገር ግን እኛ ይህን ውጤት በትክክል የምንመዝነው ለ2013 ዓ.ም. ካስቀመጥነው ግብ አንፃር ነው፡፡

የ2013 ዓ.ም. የኢዜማ የምርጫ ግብ የሚለካው ዴሞክራሲያዊ የምርጫ ሒደት የአገርን ህልውናና ቀጣይነት ማረጋገጥ የሚል ነው፡፡ ስለዚህ ከማሸነፍ አኳያ አይደለም ያስቀመጥነው፡፡ በጣም አስፈላጊ የነበረው ሒደት ደግሞ የአገርን ህልውናና ቀጣይነት ማረጋገጥ ነበር፡፡ ኢዜማ በአገር ደረጃ ሁለተኛው ተፎካካሪ ፓርቲ ነበር፡፡ ከብልፅግና ቀጥሎ ይኼንን ምርጫ በዚያ ደረጃ ብዙ ነገሮችን ችለን የምራችንን በማድረጋችን፣ በዚህ አገር ሕጋዊ መንግሥት እንዲፈጠር ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገናል፡፡ ምክንያቱም ለውጡ መጣ፣ ቀጥሎም ምርጫ አልተደረገም፡፡ እንደሚታወቀው በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ምርጫ በሰዓቱ ለምን አይደረግም በማለትና ሚልና እኛ ምርጫ እናደርጋለን በሚል ግብግብ፣ ምንም እንኳ ከጀርባው ብዙ ምክንያቶች ቢኖሩም አንድ ትልቅ ጦርነት ተከስቷል፡፡

እኔ እንደ አንድ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዕጩ ለአገሬ አንድ ነገር እንዳበረከትኩ አውቃለሁ፡፡ ምን አደረግሽ ካልከኝ አገሪቱን በምርጫ ምክንያት ከሚመጣ ቀውስ አድኛታለሁ፡፡ ይህችን አገር ለማዳን እንደ ፓርቲም እንደ ግለሰብም የራሴን ሚና ተጫውቻለሁ፡፡ ኢዜማ ከፍተኛ የሆነ ቁጥር ያለው አገራዊ ተፎካካሪ ባይሆንና ትልቁ ሕዝብ ከኢዜማ ጋር ባይሆን ኖሮ በአገር ደረጃ ሊፈጠር የሚችለውን ነገር ምን እንደሆነ አናውቅም ነበር፡፡ ስለዚህ እንደ ፓርቲም አገሪቱ ያለችበት አገራዊ ውጥንቅጥ ሳይበቃ፣ በምርጫ ምክንያት ሊመጣባት የሚችለውን ቀውስ መቀልበስ ችለናል፡፡

ሪፖርተር፡- በፓርቲው ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጥዎት ሴት የፓርላማ ዕጩ ተወካይ ነበሩ፡፡ ሴት በመሆንዎ በምርጫ ዓመቱ ምን ፈታኝ ሁኔታ ገጥምዎት ነበር?

ወ/ሪት ከውሰር፡– ምንድነው ትልቁ ችግር ልምምድ አለመኖር ነው፡፡ ለወንድም ሆነ ለሴት ፖለቲካ አስቸጋሪ ነገር ነው፡፡ እንደሚታወቀው በቀላሉ እንድትገባበት የሚስብ ነገር አይደለም፡፡ ከማሳሰር፣ ከማስገደልና ከማሰደድ ወጥቶ ፖለቲካ በቃኝ ብለህ የምትወጣበት ጊዜ አይደለም፡፡ ልምምዱ የለም፡፡ ይህ ማለት ጉዳዩ ለማንም አስፈሪ ነው፡፡ ያን ፍርኃት ግን ሰብስበህ ቦታው ላይ ለመገኘት ራሱ የፖለቲካ ባህሉ ነው አስቸጋሪ የሚሆነው፡፡ ስለዚህ የፖለቲካ ባህሉ ከመጠላለፍ አልወጣም፣ ወደ ሰጥቶ መቀበል አልመጣም፣ ወደ ድርድር አልመጣም፡፡ እንዲሁም በፓርቲዎች መካከልና በመንግሥት መካከል ያለው ግንኙነት እንደሚፈለገው ባለመሆኑ በጣም አስቸጋሪ ነገር ነው፡፡

በዚሁ አጋጣሚ ለሴቶች ማስተላለፍ የምፈልገው በኢዜማ የምርጫ ቅስቀሳ መሪ እኔ ነበርኩ፡፡ ይህንን የምርጫ ቅስቀሳ መርቻለሁ፡፡ የኢዜማን በአገር ደረጃ የምርጫ ቅስቀሳ የመራነው አራት ሴቶች ብቻ ነበርን፡፡ እናም ይህን የምርጫ ቅስቀሳ ስመራ የነበረውን ችግር ያለፍኩት የምርጫውን ስትራቴጂ በደንብ ስለማውቅ ነበር፡፡ ስለዚህ ሴቶች እንደ ሴት ያለብንን ድክመት መቀየር ከፈለግን፣ በገባንበት ነገር ላይ ግልጽ የሆነ መንገድ ልንይዝ ይገባል፡፡ ነገር ግን ባልገባን ወይም ግልጽ የሆነ ነገር በሌለበት ሁኔታ የሴትነት ድክመቱ ተጨምሮ ብዙ ዋጋ ያስከፍላል፡፡

ሪፖርተር፡- 2013 ዓ.ም. በአገር ደረጃ እንዴት አለፈ? ከፓርቲ አባልነት ወጣ በማለት ቢነግሩን?

ወ/ሪት ከውሰር፡– ከባድ ጊዜ ነው፡፡ ለመውጣታችን ግን ማረጋገጫ የለንም፡፡ ከምንም ነገር በላይ የዜጎቻችንን ሕይወት እየገበርን ነው፡፡ በተለይም በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በተቀሰቀሰው ጦርነት፣ እንዲሁም በውጭ ኃይሎች ተፅዕኖ ኢኮኖሚያችን አደጋ ውስጥ እየገባ ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ ጦርነት መልስ ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ ውይይት ያስፈልጋል፡፡ ለዚያ ደግሞ ዝግጁ መሆን አለብን፡፡ ከምንም ነገር በላይ ደግሞ ፖለቲከኞች፡፡ ምክንያቱም አገር የፖለቲካ ሥሪት በመሆኗና የኢኮኖሚውም ቀውስ በፖለቲካ ሥሪት የሚመጣ በመሆኑ እየሄድንበት ያለው መንገድ ሊያመን ይገባል፡፡ በዚህ ዘመን ጦርነት ውስጥ መግባታችን ሊያሳዝነን ይገባል፡፡ ምክንያቱም ይህ ልንመካበት ወይም ልንመፃደቅበት የሚገባ ጉዳይ አይደለም፡፡ በዚህ ድህነታችን ላይ ጦርነት ውስጥ ገብተናል፡፡ እናም እንደ አገር ከባድ ነገር ውስጥ ነው የገባነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ ጦርነት መልስ ከልብ የመነጨና ቁጭት የተሞላበት፣ በተለይም እንዴት እዚህ ደረስን የሚል ቁጭት ያለበት የፖለቲካ ድርድርና በሰጥቶ መቀበል መርህ የሚመራ ውይይት ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ስል መንግሥት ትልቁ ባለድርሻ ነው፡፡ ነገር ግን በአሸናፊነት ልቡ ያበጠ ተደራዳሪ አንፈልግም፣ አገሪቱም አያስፈልጋትም፡፡ ይህች አገር በፖለቲካ ደሃ ሆና የፖለቲካ ጦርነት ውስጥ ገብታለች፡፡ ትልቅ አገርና ብዙ ሕዝብ ይዘን እንዲህ ዓይነት የፖለቲካ ቀውስ አይገባንም ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- በ2014 ዓ.ም. ኢትዮጵያ እንዴት እንድትቀጥል ይመኛሉ?

ወ/ሪት ከውሰር፡– በ2014 ዓ.ም. ለፖለቲከኞች መዳንን እመኛለሁ፡፡ ፖለቲካችን ታሟል፡፡ ነገር ግን አሁን ከገባንበት ችግር ስለወጣን ብቻ በቃ ይኼው አለፈ፣ ኢትዮጵያ ብዙ ችግሮች ውስጥ ገብታ ታውቃለች፣ ከዚያ ችግር ውስጥም ገብታ ትወጣለች ብለን እንደተለመደው (Business as Usual) ከቀጠልን፣ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ እንደገና ችግር መፈጠሩ አይቀርም፡፡ ስለዚህ ምንም ዓይነት ችግር ውስጥ ገብተን ብንወጣ ይህ ያለፍንበት ችግር ለወደፊት ትውልድ እንዳይቀጥል ጉዳያችን መዝጋት አለብን እንጂ፣ ለትውልድ ማስተላለፍ የለብንም፡፡ እኔም ለ2014 ዓ.ም. የምመኘው ይኼንን ነው፡፡ በቃ የታሪክን ሒሳብ እንዝጋ የሚል የፖለቲካ ተዋናይ ማየት እፈልጋለሁ፡፡ ይህ ማለት ከራሱ በላይ የሚያስብ አገርን ከሥልጣኑ የሚያስቀድም፣ ሕዝቡን ከራሱ በላይ የሚያስቀድም ፖለቲከኛ መፈጠርን ወይም ያሉት ፖለቲከኞች ተቆጭተው ወደዚህ አስተሳሰብ መጥተው ማየት ነው የምመኘው፡፡


 

‹‹ጦርነቱ የፈጠራቸውን መልካም አጋጣሚዎች ልንጠቀምባቸው ይገባል››

አቶ ፀጋዬ አበበ፣ የአበባ ኢንቨስትመንት ባለሀብት

tender

          በኢትዮጵያ የሆርቲካልቸር ዘርፍ በተለይም የአበባ እርሻዎችን በማስፋፋት ራሳቸውንም ሆነ አገራቸውን ከጠቀሙ ባለሀብቶች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱት ባለሀብት አቶ ፀጋዬ አበበ፣ የተጠናቀቀው 2013 ዓ.ም. ፈተናዎችን በተመለከተ የሰጡት አስተያየት እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡- በ2013 ዓ.ም. በአገሪቱ የተከሰቱት የተለያዩ ችግሮች ኅብረተሰቡ ላይ ያደረሱትን ተፅዕኖ እንዴት ይገልጹታል? በተለይ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የተከሰተው ችግር እንዴትስ ይፈታል?

አቶ ፀጋዬ፡- በአጠቃላይ በ2013 ዓ.ም. በአገራችን የተፈጠሩትን ችግሮች በርካታ ናቸው፡፡ በተለይ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ የተከሰተው ችግር በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው፡፡ የአንበጣ፣ የጎርፍ፣ የኮቪድና የመሳሰሉ ችግሮችም ፈተናዎቻችን ነበሩ፡፡ በሰዎች መገደልና መፈናቀል የተፈጠረውም ቀውስ ቀላል አይደለም፡፡ እንዲህ ያሉ ነገሮች ለኢትዮጵያ ፈተና ነበሩ፡፡ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የተነሳው ግጭት መዘዙ አሁንም ድረስ አብሮን አለ፡፡ በመከላከያ ኃይል ላይ የተሰነዘረው ጥቃትና ይህንን ተከትሎ ሕግ ለማስከበር የተወሰደው ዕርምጃ እንደ አገር ብዙ ዋጋ አስከፍሎናል፡፡ የሱዳን መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ የፈጸመው ወረራም ዓመቱን የምናስታውስበት ነው፡፡ ግብፅና ሱዳን የህዳሴ ግድብ የውኃ ውሌትን ለማደናቀፍ የሸረቡት ሴራም አይዘነጋም፡፡ ምርጫውን ለማደናቀፍ ሲሠራ የነበረው ሌላው ችግር ነበር፡፡ እነዚህ አገራዊ ችግሮች በኅብረሰባችን ላይ ያደረሱት ተፅዕኖ እንዳለ ሆኖ፣ በኢኮኖሚው ዘርፍ ላይም ከባድ ጫና አስከትሏል፡፡ በግንቦት ወር ጠቅላይ ሚኒስትሩን በፓርላማ እንደገለጹት በጥቂት ወራት ብቻ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ወጥቷል፡፡ ይህ ለልማት ቢውል ምንኛ እንደምንጠቀምበት ማሰብ ይቻላል፡፡ ሕይወት ጠፍቷል፣ ንብረት ወድሟል፡፡ እነዚህ ነገሮች በሙሉ እንዳይከሰቱ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የሴቶች ጥምረቶች ሁሉ ያላደረጉት ነገር አልነበረም፡፡ ነገር ግን ማስቀረት አልተቻለም፡፡ በአጠቃላይ የተፈጠረው ግጭት የወለዳቸው ክስተቶች ጎድተውናል፡፡

ሪፖርተር፡- በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጠረውን ግጭትና ጦርነት በውይይት መፍታት ይቻላል ብለው ያምናሉ?

አቶ ፀጋዬ፡- አሁን ውይይት ጊዜው አልፎበታል፡፡ የውይይት ጊዜው በጣም ያለፈበት ይመስለኛል፡፡ ለውይይት የተደረጉት ሙከራዎች በሙሉ በመምከናቸው አሁን በውይይት እንመልከታቸው ማለት አይችልም፡፡ እንደ መፍትሔ የምወስደው የተጀመረውን የሕግ ማስከበር ሥራ በቶሎ ማጠናቀቅ ነው፡፡ እንደ እኔ ግምት አሁን ጫፍ ላይ ደርሷል፡፡ ሁለተኛ የተፈጠረውን መልካም አጋጣሚ ሕዝቡ መጠቀም አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- የትኛውን መልካም አጋጣሚ?

አቶ ፀጋዬ፡- ሕዝቡ በአንድነት የቆመበትን መልካም አጋጣሚ ማለቴ ነው፡፡ አንደኛ በኢኮኖሚ ደረጃ ሁሉም የአገራችን ሕዝብ በተሰማራበት የሥራ መስክ መሥራት አለበት፡፡ ሁለተኛ ውይይት ካላደረጋችሁና ካልተቀበላችሁ እያሉ አውሮፓም ሆነ አሜሪካ የሚያደርጉብን ተፅዕኖ ደሃ ስለሆንን ይጎዳናል፡፡ ከድህነት ለመውጣትና ጉዳቱን ለመቋቋም መሥራት አለብን፡፡ ለምሳሌ አሜሪካ የአጎዋን የገበያ ዕድል አነሳለሁ እያለች የምታስፈራራን ነገር ለማስቆም እኛ መሥራት አለብን፡፡ የኤክስፖርት መዳረሻችንን በአውሮፓና በአሜሪካ ላይ ብቻ ማድረጉን ትተን ሌሎች አገሮችን መመልከት አለብን፡፡ አማራጮቻችንን ማስፋት ይኖርብናል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የመከላከያ ኃይላችን ላይ አሁንም መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ የውስጡን ቀውስ ብንፈታውም፣ ከዚህ ቀውስ ጀርባ ለማትረፍ የተሠለፉትን የውጭ ጠላቶች እንደ ግብፅና ሱዳን የመሳሰሉት ነገም አይተኙልንምና በጠንካራ ሕዝባዊ አንድነት፣ ጠንካራ ኢኮኖሚና ጠንካራ መከላከያ መመከት ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ በእነዚህ ሁሉ አሸንፈን ከተገኘን በሌሎች ኢኮኖሚ ላይ ጥገኛ አንሆንም፡፡ ይህን ካደረግን ማዕቀብ ቢያደርጉ እንኳን እንቋቋማለን፡፡

አሁን የተፈጠረው የሕዝባችን አንድነት እጅግ በጣም ጥሩ አጋጣሚ ነው፡፡ ጦርነቱ መጥፎ ችግሮች እንደፈጠረ ሁሉ መልካም አጋጣሚ ፈጥሮልናልና ይህንን በጥሩ ሁኔታ ልንጠቀምበት ይገባል፡፡ ጠላቶቻችን ምንጊዜም ይተኙልናል ብለን ማሰብ የለብንም፡፡ የውጭ ጠላቶቻችን ለዘመናት የነበሩና አሁን ደግሞ በተደራጀ ሁኔታ የመጡ ስለሆነ፣ አንድነታችንንና ኢኮኖሚያችንን ስናጠናክር ነው የምንቋቋማቸው፡፡ በዚህ ላይ ጠንካራ ሥራ መሥራት አለብን፡፡ ያሉትን ችግሮች ተቋቁሞ መንግሥት ጠንክሮ እየሄደ ነው ብዬም አስባለሁ፡፡ በምርጫ ወቅት ምርጫውን ለማደናቀፍ ያልተደረገ ጥረት አልነበረም እነዚህን ሁሉ ነገሮች ተቋቁመን ነው እንግዲህ እዚህ የደረስነው፡፡ አገራችን ያለችበትን ችግር ተወጥታ ወደ ተሻለ ደረጃ ትራመዳለች ብዬ አምናለሁ፡፡ አሁን ግን መከላከያችንን ማጠናከርና ለእሱ የተሻለ ነገር ማድረግ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ጉዳይ መሆን አለበት፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...