Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናሃያ አራት አገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የሰላም ጥሪ አቀረቡ

ሃያ አራት አገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የሰላም ጥሪ አቀረቡ

ቀን:

ሃያ አራት አገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በኢትዮጵያ በሁሉም አካባቢዎች በግጭቶች ተሳታፊ የሆኑ ወገኖች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ከነውጠኛ ግጭቶች፣ ከግጭት አባባሽነትና ከጦርነት ፕሮፓጋንዳዎች በመቆጠብ፣ ለሰላማዊ ንግግሮች ራሳቸውን እንዲያስገዙና የብዙኃኑን ደኅንነትና አብሮነት፣ የኢትዮጵያን ሰላምና ሉዓላዊነት ከአደጋ እንዲከላከሉ ጥሪ አቀረቡ።

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶቹ ዓርብ ጳጉሜን 5 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጡት የጋራ መግለጫ፣ ‹‹በአሁኑ ወቅት አገራችን ኢትዮጵያ በከባድ ቀውስ ውስጥ ትገኛለች። በትግራይ፣ በአማራ፣ በምዕራብና ደቡብ ኦሮሚያ፣ በሶማሊ፣ በአፋር፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች በሚካሄዱ ግጭቶች ምክንያት በሺሕ የሚቆጠሩ ወገኖቻችን እየሞቱ ነው። በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ከቀያቸው እየተፈናቀሉ ነው። ሚሊዮኖች የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ ላይ ጥገኛ እየሆኑ ነው። ሕፃናት ልጆቻችን፣ በዕድሜ የገፉ ወገኖቻችንና ሴቶቻችን በተለየ ሁኔታ ለመከራ ተጋላጭ እየሆኑ፣ ፆታዊ ጥቃትንና ግድያን ጨምሮ የተለያዩ የሰብዓዊ ጥሰቶች ሰለባ በመሆን ላይ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም፣ ‹‹ኢኮኖሚያችን በከፍተኛ ደረጃ እየተጎዳ፣ መሠረተ ልማቶች እየወደሙ ነው። ግጭቶችን በሰላም ለመፍታት የምንጠቀምባቸው የሽምግልናና የዕርቅ ባሕላዊና ማኅበራዊ አቅሞቻችንን ለመጠቀም እያደረግን ያለነው ሁለገብ ጥረት እስካሁን ሰላምን ሊያረጋጋጥልን አልቻለም።  በመሆኑም ሕዝባችንን ለዘመናት ደግፈው ያቆዩ ማኅበራዊ እሴቶቻችን ሳይቀሩ አደጋ ላይ ሊወድቁ ይችላሉ። በዚህ ሰብዓዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ በመቆየት የምናገኘው ነገር ቢኖር የአሁኑ ማኅበራዊ ግንኙነታችንን የበለጠ ማሻከር ብቻ ሳይሆን፣ ለመጪው ትውልድም ቂምና ቁርሾ ማውረስን ሊሆን ይችላል፤›› ሲሉ በመግለጫው ጠቁመዋል።

ይህንን የአዲስ ዓመት የሰላም ጥሪ ለማስተላለፍ የተሰባሰቡ አገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ ላለፉት በርካታ ወራት በኢትዮጵያ እየተስተዋሉ ያሉ ግጭቶች በአስቸኳይ መቆም እንዳለባቸውና ለሰላም ዕድል ሊሰጠው ይገባል በማለት ግልጽ ጥሪ ለማቅረብ የወሰኑት በአሥር ምክንያቶች እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

ምክንያቶቹም፣ ‹‹ለጦርነቱ መንስዔ የሆኑት የተለያዩ የፖለቲካ ችግሮችን በጦርነት በዘላቂነት ሊፈቱ የማይችሉ በመሆናቸው፣ ይፈታሉ ተብሎ ቢታመን እንኳን መንግሥትንና መላው የኢትዮጵያን ሕዝብ የሚያስክፍለው ዋጋ የከፋ መሆኑን ከግምት በማስገባት፣ ጦርነትና ግጭቶች ባሉባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች ደኅንነት ጉዳይ ጊዜ የማይሰጥ በመሆኑ በተለይም ሕፃናት፣ ሴቶችና አረጋውያን ለከፍተኛ አደጋ እየተጋለጡ በመሆናቸው፣ ጦርነቱ በተለይም በወጣቱ የማኅበረሰብ ክፍል ላይ እያስከተለ ያለውን ዕልቂትና ኢኮኖሚያዊ ውድመት፣ እንዲሁም የከፋ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች በመመልከት ይህም ኢትዮጵያ ከገባቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶችና ራሷም ማክበር ከምትፈልጋቸው መብቶች ጋር የሚጣረስ በመሆኑ፣ የአገራችንን የልማት ጉዞ ወደኋላ የሚመልስና የዘላቂ የዕድገት ግቦችን ለማሳካት ከፍተኛ እንቅፋት የሚፈጥር ሆኖ በማግኘታችን፣  ግጭቶቹ እየተስፋፉ በርካታ አካባቢዎችን እያዳረሱ በመሆናቸውና  አሁን መቆም ካልቻለ እጅግ ወደ ከፋ ቀውስ ከመግባታችን በፊት ተነጋግሮ ለመግባባት እና ችግሮቹን ለመፍታት የሚያስችል ሥራ መሠራት ስላለበት ነው፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

‹‹ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራዎቹ እየተባባሱ ወደ አገር አቀፍና ንዑስ አኅጉራዊ ቀውስ ሊያመሩ የሚችሉ በመሆናቸው፣ በተለይም ጦርነቱ በመሠረተ ልማት አገልግሎቶች ላይ እያደረሰ የመጣውን ጉዳት ከግምት በማስገባት፣ ከከፋ ድህነት ለመውጣት በመጣር ላይ የምትገኘው አገራችንን በሌሎች ዘርፎች ላይ ማዋል ያለባት መዋዕለ ነዋይ በጦርነት ላይ ማዋል መጀመርዋ ያለውን ጉዳት በመረዳት መሆኑን፣ ጦርነቱ በማኅበራዊ ግንኙነቶች ላይ ያስከተለውን ጉዳት በመገንዘብ በተለይም በኅብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ የሕዝብ ለሕዝብ አዳሪ ቂምና ቁርሾ እያፈሩ ሊመጡ የሚችሉ መሆናቸውን በመመልከት፣ ቀውሶቹ በኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ዘላቂ ጥቅም ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እየፈጠሩ፣ ለውጭ ኃይሎች ተፅዕኖ ተጋላጭነታችንን እየጨመሩ በመሆኑና የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ኅልውናን የሚፈታተን አደጋ በመደቀኑ፣ ለግጭቶቹ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት አዳጋችነቱ እያደር እያሻቀበ በመምጣቱ፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ የተለያዩ ማኅበረሰብ ክፍሎች ዘንድ የዳበሩ ከጦርነት ወጪ ግጭቶች የሚፈቱባቸው፣ ከጦርነት በኋላም ዕርቅ፣ ሰላምና ፍትሕ ማምጣት የሚችሉ፣ ረቂቅ ልምዶች ስላሉ ለእነዚህ የሰላም እሴቶችና ተሞክሮዎች የፖለቲካ ልሂቃኑ ዕድል እንዲሰጡ ሰላምን መገንባት የሚያስችል ቅድመ ሁኔታዎችን እንዲያመቻቹ ነው፤›› በማለት በመግለጫቸው ጠቁመዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2020 የተጀመረውን የአፍሪካ ‹‹ነፍጥን  ዝም የማሰኘት ዘመቻ›› (“Silencing The Guns Campaign”) የሰላም ጥሪዎችና መግባባት ሊፈጥሩ የሚችሉ ንግግሮችን ማድረግ የሚጀመር በመሆኑ፣ የጦርነቱ መባባስና እየተስፋፋ መምጣት በተለይም የአገር ውስጥ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን በአግባቡ የመከታተል፣ የመመዝገብና የማጣራት ሥራ ላይ እየፈጠረ ያለው ችግርን በመረዳት፣ ይህም በኢትዮጵያ የተለያዩ አስተዳደር ክፍሎች ካለው የግንኙነት አገልግሎት መቋረጥና ነባራዊ የደኅንነት ተግዳሮቶች ጋር የተያያዘ መሆኑን በመገንዘብ እንደሆነም አክለዋል፡፡

‹‹ስለሆነም ስማችን በመግለጫው የተዘረዘረው አገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እነዚህ ግጭቶች አስቸኳይ መቋጫ ያገኙ ዘንድ ይህንን የአዲስ ዓመት የሰላም ጥሪ እያስተላለፍን፣ በአገራችን የሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችም ግጭቶችን በሰላማዊ መንገዶች ለመፍታት ብሎም ሁለንተናዊ የሰላም ግንባታ ሥራና ሁሉን አቀፍ  ዕርቅ እንዲደረግ  የሚያስችሉ ሥራዎች ላይ እንዲያተኩሩ በአክብሮት  ጥሪያችንን እናቀርባለን። የሰላም ጥሪያችን የተሳካ ይሆን ዘንድ በኢትዮጵያ በሁሉም አካባቢዎች በግጭቶች ተሳታፊ የሆኑ ወገኖች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከነውጠኛ ግጭቶች፣ ከግጭት አባባሽ ሁኔታዎችና ከጦርነት ፕሮፓጋንዳዎች በመቆጠብ ለሰላማዊ ንግግሮች ራሳቸውን እንዲያስገዙና የብዙኃኑን ደኅንነትና አብሮነት፣ የአገራችንን ሰላምና ሉዓላዊነት ከአደጋ እንዲከላከሉ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን። እኛም እንደ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ግጭቶችን በሰላማዊ መንገዶች ለመፍታትና ከዚያም ሁለንተናዊ የሰላም ግንባታ ሥራና ሁሉን አቀፍ ዕርቅ እንዲሰፍን ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎችን ለመሥራት ቃል እንገባለን፤›› ሲሉ ሃያ አራቱ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በመግለጫቸው አስታውቀዋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...