Tuesday, July 23, 2024

አዲሱ ዓመት በአዲስ ተስፋ ይጀመር!

አሮጌው ዓመት ተሸኝቶ አዲሱ ዓመት ተጀምሯል፡፡ በአዲስ ዓመት መልካሙን ነገር ሁሉ መመኘት የነበረና ያለ በመሆኑ፣ አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የጤና፣ የደስታና የዕድገት ይሆን ዘንድ ምኞታችንን እንገልጻለን፡፡ ይህ የአዲስ ዓመት የመልካም ምኞት መግለጫ የሰመረ እንዲሆን ደግሞ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብአዲሱ ዓመት ሰላም ይስፈንለት፡፡ መንግሥት፣ እያንዳንዱ ዜጋ፣ የንግዱ ኅብረተሰብ፣ የትምህርትና የጤና ተቋማት፣ ሲቪል ማኅበረሰቡ፣ የፍትሕ አካላት፣ ፖለቲከኞች፣ ወዘተ አዲሱን ዓመት የሰላምና የዕድገት እንዲያደርጉት ጥሪ ይቀርብላቸዋል፡፡ በዚህ አዲስ ዓመት ከአሮጌው ዓመት የተላለፉ የማይጠቅሙ ድርጊቶች መቀጠል የለባቸውም፡፡ ግጭት ቀስቃሽነትና አባባሽነት ቆመው ሰላም መስፈን አለበት፡፡ ሰላም እንዲሰፍን፣ ፍትሕና ርትዕ እንዲረጋገጥ፣ የአገርና የሕዝብ ጠንቅ የሆነው ሌብነት እንዲጠፋ፣ ፀረ ዴሞክራሲያዊና አምባገነናዊ አስተሳሰቦች ቦታ እንዳይኖራቸው ከእያንዳንዱ ዜጋ እስከ ፖለቲካ መሪዎች ድረስ በአንድነት መነሳት አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ በአዲስ ዓመት ለእንዲህ ዓይነቱ መልካም ተግባር ራሳቸውን ያዘጋጁ፡፡ የአዲሱ ዓመት ተስፋና ስጦታ ሰላም ይሁን፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በእያንዳንዱ ቀን በሀቀኝነት፣ በአገልጋይነትና በአገር ፍቅር ስሜት ለመሥራት መዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል፡፡

በአዲሱ ዓመት ተስፋ መሰነቅ፣ የተሻለ ሠርቶ ስኬታማ ለመሆን ቃል መግባትና ለተግባር መዘጋጀት የተለመደ ነው፡፡ በአሮጌው ዓመት ተጀምረው ያልተጠናቀቁትን በከፍተኛ ሞራል ከዳር ለማድረስና አላስፈላጊ ነገሮችን ላለመድገምም አቋም ይያዛል፡፡ በአገር ደረጃ ደግሞ የሚያጋጥሙ ውጣ ውረዶችንና መሰናክሎችን በብልኃት ተሻግሮ ካሰቡበት ለመድረስ፣ በሕዝቡ ውስጥም ሆነ በልሂቃኑ ዘንድ ከፍተኛ መነቃቃት ያስፈልጋል፡፡ አዲሱ ዓመት በርካታ በረከቶችንና ፀጋዎችን ይዞ ሊመጣ ስለሚችል፣ ግጭትና ውድመትን በፍጥነት ማስቆም የግድ ይላል፡፡ የአገር ጉዳይ ሲነሳ ጠበቅ አድርጎ መነጋገር የሚያስፈልገው፣ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ያሉበት ሁኔታ ከባድ ስለሆነ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከጦር ቀጣናነት በፍጥነት ወጥታ የልማት አምባ መሆን አለባት፡፡ በአዲሱ ዓመት በውጭዎቹ ዘንድ ጭምር እየታየንበት ያለውን የተበላሸ ገጽታ መቀየር ካልቻልን፣ ኢትዮጵያንም ሕዝቡንም ቀውስ ውስጥ እንደምንከት ማወቅ አለብን፡፡ ይህ ሥጋት ከፍተኛ የሆነ ትኩረት ይሻል፡፡ ኢትዮጵያ በአፍሪካ የሚገባትን ታላቅ ሥፍራ ማግኘት አለባት፡፡ ኢትዮጵያዊያን በኩራት አንገታቸውን ቀና አድርገው መሄድ የሚጀምሩበት ዓመት እንዲሆን በጋራ መነሳት የግድ ይላል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሙሉ በአዲሱ ዓመት ለሰላም መስፈን ጠንክረው ይሥሩ፡፡ ከጥላቻና ከጨለምተኝነት አስተሳሰብ ወጥተው በዴሞክራሲያዊ መንገድ ይንቀሳቀሱ፡፡ በብሔራዊ ጉዳዮች ላይ በኃላፊነትና በያገባኛል መንፈስ ይነጋገሩ፡፡ በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆን ስለሌለበት፣ የመነጋገሪያው መድረክ በአስቸኳይ ሥራውን እንዲጀምር ይታገሉ፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ የሚሰፋው ወይም የሚጠበው በሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ባህሪ ምክንያት ስለሆነ፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታው ስምረት ሲባል ሁሉም ለሰጥቶ መቀበል መርህ ራሳቸውን ያዘጋጁ፡፡ በዚህ በሠለጠነ ዘመን በጠላትነት እየተያዩ በአንድ የፖለቲካ ዓውድ ውስጥ ሰላማዊ ትግል ማድረግ ስለማይቻል ራሳቸውን ለመልካም ነገር ያዘጋጁ፡፡ በተለይ ገዥው ፓርቲ ብልፅግና አዲሱን መንግሥት ሲመሠርት፣ተፎካካሪ ፓርቲዎች ተሳትፎ አመቺ ሁኔታ መፍጠር አለበት፡፡ ለብሔራዊ መግባባት የሚረዱ መድረኮችን ያመቻች፡፡ ለእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚረዳ መደላድል ይፍጠር፡፡ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች በአዲሱ ዓመት በዚህ መንፈስ ለመንቀሳቀስ ራሳቸውን ያዘጋጁ፡፡ ለሕዝቡም ይህንን የአዲስ ዓመት ስጦታ በማድረግ አርዓያነታቸውን ያሳዩ፡፡ በአዲሱ ዓመት የሰላም ተስፋ ይፈንጥቁ፡፡ ኢትዮጵያን ዳግም ወደ ግጭትና ወደ ውድመት ጎዳና የሚከቱ ብልሹ አሠራሮችን በጋራ ያስወግዱ፡፡

የፍትሕ አካላት ኢትዮጵያ እውነተኛ የፍትሕና የርትዕ አገር እንድትሆን ኃላፊነታቸውን በመልካም ሥነ ምግባር ይወጡ፡፡ የዳኝነት አካሉ በነፃነት እየሠራ ከምግባረ ብልሹነት ራሱን ያፅዳ፡፡ የፍትሕ ደጃፍን የሚያቆሽሹ ሕገወጥ ድርጊቶች ይወገዱ፡፡ ዓቃቢያነ ሕጎችም ሆኑ ለፍትሕ ሥርዓት ዕገዛ ማድረግ የሚጠበቅባቸው ጠበቆች፣ የፍትሕ ሥርዓቱ እንዳይደፈር የሚፈለግባቸውን ኃላፊነት ይወጡ፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱን ከአላስፈላጊ ጣልቃ ገብነቶች ይከላከሉ፡፡ ፍትሕ እንደ ሸቀጥ እንዳይሸጥ እንዳይለወጥ ይታገሉ፡፡ ገንዘብ ያለው የሌለውን እንዳይፈነጭበት ቃል ይግቡ፡፡ ፖሊስን በተመለከተ ደግሞ ከፍተኛ ኃላፊነትና አደራ እንዳለበት ማስገንዘብ ይገባል፡፡ የፖሊስ ተቀዳሚ ተግባር ወንጀል ከመፈጸሙ በፊት መከላከል ሲሆን፣ ወንጀል በሚፈጸምበት ጊዜ ደግሞ ከማንም በፊት ቀድሞ ተጠርጣሪዎችን ሕግ ፊት ማቅረብ ነው፡፡ ፖሊስ ውስጡን በሚገባ በመፈተሽ ይህንን ኃላፊነቱን በብቃት በመወጣት ሕዝብን ማሳመን አለበት፡፡ የብዙኃኑን ሀቀኛ ፖሊሶች ስም የሚያጎድፉ የወንጀል ተባባሪ የፖሊስ ባልደረቦች በመበርከታቸው ምክንያት፣ የተደራጁ ወንጀለኞች የሰው ሕይወት በጠራራ ፀሐይ ከማጥፋታቸውም በላይ ከባድ ዘረፋ እየፈጸሙ ሕግ ፊት መቅረብ አልቻሉም፡፡ መኪና ከቆመበት ቦታ ተሰርቆ ማግኘት አልተቻለም ሲባል፣ በዚህ ወንጀል ውስጥ የተሰማሩ ኃይሎች እነ ማን እንደሆኑ አልታወቁም ማለት ስለሆነ ያሳፍራል፡፡ በተለይ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የተደራጁ ወንጀለኞችንና አገር ለማፍረስ የተሰማሩ ኃይሎችን በተመለከተ ኅብረተሰቡ ጥቆማ እየሰጠ፣ ዕርምጃ በመውሰድ ወንጀልን ማምከን አለመቻል ያስተዛዝባል፡፡ በአዲሱ ዓመት ይህ ነውረኛ ድርጊት እንዳይቀጥል ኃላፊነትን መወጣት ግዴታ መሆን አለበት፡፡

የንግዱ ማኀበረሰብ ለአገሩ የሚያደርገው አስተዋጽኦ የበለጠ ጎልቶ የሚታየው በሥነ ምግባር ሥራውን ሲያከናውን ነው፡፡ ከሥነ ምግባር አፈንግጠውና የኅብረተሰቡን ባህላዊ እሴቶች ንደው በሕዝብ ላይ አደጋ የደቀኑ ወገኖችን የማረቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ ብዙኃኑ በሕዝብ አገልጋይነት መንፈስ በሚሠሩበት አገር ውስጥ ከመጠን በላይ በሆነ ራስ ወዳድነት ውስጥ ተዘፍቀው፣ የግብይት ሥርዓቱን መላቅጡን የሚያጠፉትንና ጤናማ ውድድር እንዳይኖር የሚያደርጉትን፣ የንግዱ ማኅበረሰብ በንግድ ማኅበራትም ሆነ በንግድ ምክር ቤቶች አማካይነት ሊታገላቸው ይገባል፡፡ ምርት በመደበቅ፣ የግብይት ሰንሰለቱን በማዛባት፣ ሰው ሠራሽ የዋጋ ንረት በመፍጠር፣ ሚዛን በማጭበርበር፣ መርዛማ ባዕድ ነገሮችን የምግብ ምርቶች ውስጥ በመደባለቅና የሕዝቡን ሕይወት በማናጋት ላይ የሚገኙት እነዚህ ኃላፊነት የማይሰማቸው ወገኖች አንድ መባል አለባቸው፡፡ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናትንና በየደረጃው የሚገኙ ሹማምንትን የዘረፋ ተባባሪ በማድረግ የግብይት ሥርዓቱን እያበላሹት ስለሆነ የንግድ ማኅበረሰቡ በፅናት ይታገላቸው፡፡ በዚህም ሀቀኛ አገልጋይነቱን ያሳይ፡፡ ጤናማ ፉክክር ያለበትና ለሁሉም የተመቻቸ የውድድር ሜዳ እንዲፈጠር የበኩሉን ይወጣ፡፡ ከመጠን ያለፈ ራስ ወዳድነት አገርን መግደል ነው፡፡አዲሱ ዓመት ከፍተኛ የሆነ የሥነ ምግባር ያስፈልጋል፡፡

ከታሪካዊው ድህነትና ኋላቀርነት መላቀቅ የሚቻለው ለትምህርት በሚሰጥ ፅኑ እምነት ነው፡፡ ወጣቱ ትውልድ በትምህርት ተቋማት ከሚቀስመው ዕውቀት በተጨማሪ፣ ከኅብረተሰቡ የሚማራቸው በርካታ አገር በቀል ዕውቀቶች አሉ፡፡ ትምህርት ማስተዋል ከሌለበት ከንቱ እንደሚሆነው ሁሉ፣ አገርም በማስተዋል ካልተመራች ከገባችበት ቀውስ ውስጥ መውጣት አትችልም፡፡ መንግሥት ወጣቱ ትውልድ እንዲያስብ፣ እንዲያሰላስልና የተሻሉ ሐሳቦችን እንዲያፈልቅ ዕድሎችን ከማመቻቸት በተጨማሪ መሠረታዊ መብቶቹን ማስከበር አለበት፡፡ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችም ያለ ስስት ወጣቱን ማገዝ ይኖርባቸዋል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ መረዳዳት ሲኖር ለዘመናት የነገሡ ጨለምተኛ አመለካከቶች በብርሃናዊ አስተሳሰቦች ይተካሉ፡፡ ‹‹የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው›› የሚባለው ጊዜ ያለፈበት ጎታች አመለካከት ቦታ አይኖረውም፡፡ በመርህ ላይ የተመሠረቱ ጥያቄዎች ሲነሱ ምክንያታዊ ምላሽ ያገኛሉ፡፡ አዲሱ ትውልድ የራሱን ታሪክ መሥራት አለበት፡፡ ትውልድ በዕውቀት ሲታነፅ ዘረኝነት ሥፍረ አይኖረውም፣ አክራሪነትና ፅንፈኝነት ይመክናሉ፡፡ ዘመናዊና ተራማጅ አስተሳሰቦች በአገር በቀል ዕውቀትና ማስተዋል እየተብላሉ ኢትዮጵያን ከከፍታው ማማ ላይ ያደርሷታል፡፡ ምኞትን ወደ ተግባር ለመለወጥ ግን ቁርጠኝነት ይጠይቃል፡፡ ሌብነትን፣ አምባገነንነትን፣ ክፋትንና ራዕይ አልባነትን የሚታገል ቁርጠኝነት የግድ መሆን አለበት፡፡ አዲሱ ዓመት በአዲስ ተስፋ ይጀመር!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከፍተኛ ትርፍ ቢያገኝም የውጭ ምንዛሪ ገቢው ቅናሽ ማሳየቱ ተጠቆመ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2016 የሒሳብ ዓመት ያሰባሰበው የውጭ ምንዛሪ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለልዩነት ዕውቅና የማይሰጥ ፖለቲካ ፋይዳ ቢስ ነው!

በፍርኃትና በሥጋት የተኮማተረ አገር ለመለወጥም ሆነ ለማደግ ዝግጁ መሆን አይችልም፡፡ አጉል ድፍረትና ምግባረ ብልሹነት በተንሰራፋበት ስለነፃነት መነጋገር አይቻልም፡፡ ፍርኃት እንደ ወረርሽኝ አገር ምድሩን አዳርሶ...

ለሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎቶች ልዩ ትኩረት ይሰጥ!

በዚህ ዘመን ለሰው ልጅ የሚያስፈልጉ ነገሮች ብዛታቸው እየጨመረ ቢመጣም፣ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን መሠረታዊ የሚባሉ ፍላጎቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ሊቸራቸው ይገባል፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ...

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተገኙበት የሚዲያ ሽልማት ሥነ ሥርዓት መካሄዱ ይታወሳል፡፡ ‹‹ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ለሠሩ የአገር ውስጥና የውጭ...