Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየተረጋጋ አወቃቀር የሚሻው የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን

የተረጋጋ አወቃቀር የሚሻው የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን

ቀን:

የኢትዮጵያን የዱር እንስሳትና የመኖሪያ አካባቢዎች የማኅበረሰቡንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፎና ተጠቃሚነት ባማከለና ወቅቱ በዋጀ ዘመናዊ አደረጃጀት ተደራጅተው፣ ለምተውና ተጠብቀው ዘላቂ ሥነ ምኅዳራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጥቅም የሚሰጡበት ደረጃ ለማድረስና ለቀጣይ ትውልድ በቅርስነት ለማስተላለፍ ዘርፈ ብዙ ተግባራት መከናወን እንደሚገባቸው በየጊዜው ይወሳል፡፡

‹‹የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ አሠራር ሥርዓትን ዳግም ማጤን ለዘላቂ ልማትና የማኅበረሰብ ኑሮ መሻሻል ያለው ፋይዳ›› በሚል ርዕስ ጳጉሜን 1 ቀን 2013 ዓ.ም. በተካሄደው የግማሽ ቀን የፓናል ውይይት ላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራን፣ የዋልድ ላይፍ ቲንክ ታንክ ቡድን አባላት፣ በዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ዘርፍ ላይ የሚሠሩ አካላት በየተራ ባንፀባረቁት አስተያየት መከናወን ከሚገባቸው ተግባራት መካከል የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን (ኢዱልጥባ) የተረጋጋ አወቃቀር እንዲኖረው ማድረግ ይገኝበታል፡፡

ኢዱልጥባ የተቋቋመው በዘውዳዊው ሥርዓት ከስድስት አሠርታት በፊት ሲሆን፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከ30 በላይ የማፍረስና እንደገና የማዋቀር ሥራ እንደተከናወነበት፣ ይህም የሚሆነው ኃላፊዎችና ሚኒስትሮች በተቀያየሩ ቁጥር የየራሳቸውን አጀንዳ ይዘው በመምጣትና አጀንዳዎቻቸውንም ከማዋቀሩ ጋር የተጣጣመ እንዲሆን ለማድረግ በማሰብ ነው፡፡ በዚህ ዓይነት አካሄድም ሥራ የሠሩ ይመስላቸዋል፡፡ ነገር ግን የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ እንቅስቃሴን ለከፋ አደጋና ጉዳት መዳረጋቸው እንዳልታያቸው ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ባለሥልጣኑ ሥራውን በተሳለጠ መንገድ ሊያከናውን የሚያስችለውን በቂ በጀት መመደብ፣ በሠለጠነ የሰው ኃይል ማጠናከር፣ እንዲሁም የተፈጥሮ ሀብትን ጥበቃ ቦታዎችን ሊያሳድጉ ይችላሉ ብሎ ያመነባቸውን ባለሙያዎች ለሲቪል ሰርቪስ ሳያሳውቅ በነፃነት የመቅጠር ኃላፊነትና መብት ሊቸረው እንደሚገባ አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል፡፡

ከዚህም ሌላ ለሠራተኞችና ስካውቶች በቂ ደመወዝና ሌሎችም ማበረታቻዎች ሊደረግላቸው፣ ነፃ የሕክምና አገልግሎት ሊያገኙ የሚችሉበት ሁኔታ ሊመቻችላቸው እንደሚገባና በዘርፉ ላይ ትኩረት ያደረገ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ማከናወን እንደሚያስፈልግ ከተንፀባረቀው አስተያየት ለመረዳት ተችሏል፡፡

ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል ሰብስቤ ደምሰው (ፕሮፌሰር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የዕፀዋትና የብዝኃ ሕይወት መምህር ኢትዮጵያ 1.1 ሚሊዮን ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት እንዳላት፣ ይህም ከብዝኃ ሕይወት ጋር እንደተያያዘ፣ ነገር ግን ከተጠቀሰው የቆዳ ስፋት ውስጥ ለኢንዱስትሪ፣ ለእርሻና ለተፈጥሮ ሀብት መዋል ያለበትን አካባቢ የሚያሳይ አገር አቀፍ ካርታ ሊኖራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

እንደ እሳቸው አገላለጽ፣ ግሎባል ባዮ ዳይቨርሲቲ ፍሬምወርክ አራት ግቦችና 21 ዓላማዎች (ታርጌት) አሉት፡፡ ከግቦቹም መካከል አንደኛው ያልተጓደሉና የተሻሻሉ ሥነ ምኅዳሮች እንዲኖር ማድረግ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የባሌ፣ የስሜን ተራሮችና ሌሎችም ጥብቅ ቦታዎች የተሻሻሉ፣ ያልተጓደሉ ሥርዓተ ምኅዳር እንዲኖራቸው ማድረግ ይቻላል፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን የኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት ኢንስቲቲዩት፣ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣንና ሌሎችም የፎርስትሪ ኢንስቲትዩት ሊጠናከሩና አቅም ሊሰጣቸው ይገባል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ 86 ጥብቅ ቦታዎች እንዳሉ፣ እነዚህን ቦታዎች በውጭ ድጋፍና ዕርዳታ ሳይሆን በራስ አቅም ለማበልፀግ ጥረት መደረግ እንዳለበት፣ የውጭ ድጋፍና ዕርዳታ አንድ እክል ቢያጋጥም ሊቋረጥ እንደሚችል ሊታወቅ እንደሚገባ ከሰብስቤ ደምሰው (ፕሮፌሰር) አስተያየት ለመረዳት ተችሏል፡፡

ከኢትዮጵያ የቆዳ ስፋት ውስጥ 14 በመቶ ያህሉን ለሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን ከአጠቃላይ በጀት ውስጥ የሚመደብለት 0.01 በመቶ ብቻ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የሥነ ሕይወት አማካሪው ዘለዓለም ተፈራ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ እንደ አማካሪው አባባል በተጠቀሰው በጀት ባለሥልጣኑ የተሟላና ጠንከር ያለ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ሥራ ያከናውናል ብሎ መጠበቅ ዘበት ነው፡፡

የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝና ባለቤታቸው ወ/ሮ ሮማን ተስፋዬ ባቋቋሙት ፋውንዴሽን፣ የአየር ንብረት ለውጥና የኤኮ ቱሪዝም ዳይሬክተር ዓለማየሁ አሰፋ (ዶ/ር) እንዳሳሰቡት፣ ሕጋዊ የሆነ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ መኖር ለዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ሥራ ውጤታማነት የጎላ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

የብዝኃ ሕይወት ተመራማሪ አቶ ላቀው ብርሃኑ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ እንቅስቃሴ ወደማይሆን አቅጣጫ እየሄደ መሆኑን ገልጸው፣ ለብዙ ዘመናት በችግሩ ዙሪያ ሲወራ እንደቆየ፣ ይህም ሆኖ ግን ምንም ዓይነት መፍትሔ እንዳላመጣ ከዚህ አኳያ ትክክለኛውን አካሄደ መሻትና ስትራቴጂውም መቀየር እንዳለበት አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...