Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

​​​​​​​‹‹ሸማች በቂ መረጃ ኖሮት በገበያ ላይ ዕርካታ የሚያገኝበት መንገድ አነስተኛ ነው›› አቶ አሥራት በጋሻው፣ የተስፋ ለኢትዮጵያ የሸማቾች ማኅበር ፕሬዚዳንት

በተለያየ የዓለም ክፍሎች በተለይም በኢንዱስትሪ በበለፀጉ አገሮች ጠንካራ የሸማቾች ማኅበራት ተቋቁመው የሸማቾችን መብቶች ሲያስከብሩ ይስተዋላል፡፡ በአገራችን በኢትዮጵያ ይህንን ያህል ጠንካራ ነው ባይባልም፣ ተስፋ ለኢትዮጵያ የሸማቾች በሚል መጠሪያ የሚታወቅ ማኅበር በቅርቡ ተመሥርቶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ አቶ አሥራት በጋሻው የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ በማኅበሩ እንቅስቃሴ ዙሪያ ፕሬዚዳንቱን ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ተስፋ ለኢትዮጵያ የሸማቾች ማኅበር መቼ ተቋቋመ? ዋና ተግባሩስ ምንድነው? ሕጋዊ ሥልጣኑ እስከምን ድረስ ነው? ይህም ማለት ሸማቹን ወክሎ የመክሰሱ ሁኔታ እንዴት ይታያል? የሸማቹን መብቶች ለማስከበር ምን ያህል ጥረት ያደርጋል?

አቶ አሥራት፡- ተስፋ ለኢትዮጵያ የሸማቾች ማኅበር ዋና ትግባሩ የሸማቾችን መብቶች ማስከበር፣ በተጠቀሱት መብቶች ላይ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ማከናወን፣ እንዲሁም ሸማቾችን ወክሎ ድምፅ መሆኑ ነው፡፡ ማኅበሩ የተቋቋመው የካቲት 1 ቀን 2013 ዓ.ም. ሲሆን፣ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካል ሕጋዊ ዕውቅና አግኝቷል፡፡ የተቋቋመበትም ምክንያት ቀደም ሲል የነበረው የተናጠል እንቅስቃሴ ብዙም ውጤታማ ስላልነበረ፣ በዚህም የተነሳ በማኅበር በመደራጀትና ሕጋዊ ሆኖ መንቀሳቀሱ አዋጪ ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡ የሸማቾች መብቶች ከተከበሩ መክሰስ ብዙም አያስቸግርም፡፡ ምክንያቱም ከሸማቾች መብቶች ውስጥ አንደኛው ሸማቹ ጉዳት በደረሰበት ጊዜ ካሳ የማግኘት፣ ወይም ዕቃውንና ገንዘቡን የማስመለስ መብቶች ተካትቷል፡፡ ከዚህ አኳያ ሸማቹ በቀጥታ አለበለዚያም ማኅበሩ በውክልና ክስ ሊያቀርቡ ይችላሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የሸማቾች መብቶችን መቀበሏ ይታወቃል፡፡ በዚህ ላይ አስተያየት ቢሰጡበት?

አቶ አሥራት፡- በእርግጥ ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የሸማቾችን መብቶች ተቀብላ አፅድቃለች፡፡ ከሕጎቿም አንዱ አድርጋ እየተጠቀመችበት ትገኛለች፡፡ ለዚህም በአዋጅ ቁጥር 813/2006 የወጣ ሲሆን፣ በዚህም የሸማቾች መብት ጥበቃና የንግድ ውድድር ባለሥልጣን የሚል መንግሥታዊ አካል ተቋቁሟል፡፡ ከዚህ አኳያ የሸማቾች መብት ሙሉ ለሙሉ ተረጋግጧል ተብሎ ባይታሰብም፡፡ አንዳንድ በጎ ጅማሮዎች እየታዩ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱን ጅማሮ አጠናክሮ መቀጠል አስፈላጊና አንገብጋቢ ጉዳይ ነው፡፡    

ሪፖርተር፡- በሸማቾች ላይ እየደረሰ ያለውን የመብት ጥሰት ለመዳኘት ወይም ለማስተካከል ያደረጋችሁት ጥረት አለ? ለሥራችሁ መቃናት ከባለሥልጣኑ ጋር ያደረጋችሁት ትስስር ወይም ቅንጅት ካለ ቢያብራሩልን??

አቶ አሥራት፡- እስካሁን ድረስ ሸማቾች የሚያቀርቧቸውን ጥያቄዎች በቀጥታ እያየ ያለው የሸማቾች ጥበቃና የንግድ ውድድር ባለሥልጣን ነው፡፡ ማኅበሩ ገና ወደ ማኅበረሰብ ውስጥ አልገባም፡፡ ነገር ግን የሸማቾች የተንጠለጠለ ወይም ገና መፍትሔ የሚፈልጉ አንዳንድ ጉዳቶች መኖራቸው አይካድም፡፡ ለዚህም ባለሥልጣኑ አንዳንድ ዕርምጃዎችንም ሲወስድ ይታያል፡፡ ከዚህ ውጪ ማኅበሩ የሠራው ሥራ የለም፡፡ መጀመርያ ያደረግነው ነገር ቢኖር ሕጋዊ ሰውነት ካገኘን በኋላ፣ ወደ ባለሥልጣኑ ጎራ በማለት የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማችን ነው፡፡ ከሌሎችም መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች (ንግድ ሚኒስቴር፣ ደረጃዎች ኤጀንሲ፣ የምግብና መድኃኒት አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን፣ ፖሊስ፣ ሠራዊት፣ ዓቃቤ ሕግ፣  ወዘተ) የመግባቢያና የባለድርሻ ሰነድ ምዝገባ ለማካሄድ የሚያስችል እንቅስቃሴ ላይ ነን፡፡ ይህ እንቅስቃሴ በአጠቃላይ የበጎ ፈቃድ እንቅስቃሴ መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል፡፡

ሪፖርተር፡- በዝርዝር ከተጠቀሱ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ጋር የተጠቀሰውን ግንኙነት መፍጠሩ ምን ፋይዳ ይኖረዋል ተብሎ ነው የሚታሰበው?

አቶ አሥራት፡- ፋይዳው ትልቅና ወሳኝ ነው፡፡ ይህም የሆነው የተዘረዘሩት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሸማቹን በተለያዩ መልኩ ሊያገኙት ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት አስተዳደር ባለሥልጣን የተለያዩ ምግቦችንና መድኃኒቶችን ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡና ገበያ ላይ እንዲውሉ የማድረግ ሥልጣን አለው፡፡ በዚህም ሸማቹ የመጠቀም ዕድሉ የሰፋ ይሆናል፡፡ ባለሥልጣኑ ደግሞ በተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት መሠረት የገቡት ምግቦችና መድኃኒቶች በሸማቹ ላይ እክል እንዳያስከትል የመከታተልና የመቆጣጠር ሥልጣን አለው፡፡ የደረጃዎች ኤጀንሲም አስገዳጅ ምርቶች ላይ ደረጃ የማውጣት ሥልጣን አለው፡፡ ይህም ከሸማቾች ጋር በቀጥታ ይገናኛል፡፡ ፖሊስም ሕገወጦችን በመቆጣጠር አስተዋጽኦ አለው፡፡ ዓቃቤ ሕግም በሸማቾች መብቶች ዙሪያ ጥሰቶች ሲከሰቱ፣ ወይም ክስ ሲቀርብ አጣርቶ ለፍርድ ቤት የሚያቀርብበት ሁኔታ አለ፡፡ ከዚህ አኳያ ከፍ ብሎ የተጠቀሱ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ለሸማቹ ያግዛሉ፡፡ በተጓዳኝ ደግሞ ሸማቹ ለሚያቀርበው ጥያቄ መልስ ይሰጣሉ የሚል የፀና እምነት እንዳለን መታወቅ ይኖርበታል፡፡    

ሪፖርተር፡- የተጠቀሱ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች አገልግሎታቸውና ጠቀሜታቸው የጎላ ከሆነ ለምንድነው ማኅበሩ በቀጥታ ከእነሱ ጋር የመግባቢያ ሰነድ ያልተፈራረመው?

አቶ አሥራት፡- በእርግጥ ከመሥሪያ ቤቶቹ ጋር የመግባቢያ ሰነድ አልተፈራረምንም፡፡ የተፈራረምነው ከባለሥልጣኑ ጋር ነው፡፡ ይህም በዋና መሥሪያ ቤት ደረጃ እንደ አስፈጻሚ ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡ በተረፈ ባለሥልጣኑ መግባቢያ ሰነድ መፈራረማችንን የሚገልጽ ደብዳቤ ለእያንዳንዱ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ጽፎልናል፡፡ በጻፈውም ደብዳቤ ላይ የመግባቢያ ሰነዱን በአባሪነት አያይዞ አቅርቧል፡፡ በዚህም የተነሳ መሥሪያ ቤቶቹም እንደ የመብት ማስጠበቅ ሥራችንን ተቀብለውታል፡፡ ወይም ያለምንም ችግር ባለድርሻነታችንን ተቀብለውታል ለማለት ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- ባለሥልጣኑ የተቋቋመው በአጠቃላይ የሸማቾችን መብት ለማስጠበቅና ጤናማ ውድድር እንዲፈጠር ነው፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን በበጀት፣ በሰው ኃይልና በቁሳቁስ ተደራጅቷል፡፡ ከዚህ አኳያ የማኅበሩ መቋቋም ለምን አስፈለገ? ማኅበሩ የሚሠራውን ሥራ ባለሥልጣኑ ብቻውን አይሠራውም ወይ?

አቶ አሥራት፡- የሸማቾች መብቶች በአንድ ባለሥልጣን፣ የመንግሥት በጀት፣ መደበኛ ደመወዝና አሠራር ተጠቃልሎ መፍትሔ ያገኛል ወይም መብቶቹ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ይሆናሉ ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ለዚህም ምክንያቱ የአቅም ውስንነትና የተደራሽነት ችግር ሊኖር ይችላል፡፡ ከዚህም ሌላ ባለሥልጣኑ በፌዴራል ደረጃ የተቋቋመ ቢሆንም፣ በአብዛኛው የሚንቀሳቀሰው በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተሞች ነው፡፡ በሌሎች ክልሎች ላይ ይህንን ሥራ አይሠራም ወይም ደግሞ በውክልና ለንግድ ሚኒስቴር ቢሰጥም፣ በየአካባቢው ያሉ የሚኒስቴሩ ቅርንጫፎች ባላቸው ጥቂት ሠራተኞች ይህንን ጉዳይ ያከናውናሉ ተብሎ አይታሰብም፡፡ በአንፃሩ ደግሞ የሸማቾች መብቶች እጅግ ሰፊ ከመሆኑ አንፃር ጥሰቶቹ በሚፈጸሙበት ጊዜ ተከታትሎ መፍትሔ ለመስጠት የተደራሽነት አቅማቸው አነስተኛ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ የማኅበሩ ተደራሽነት ግን የተሻለ ነው ከሚል በጎ አመለካከት በመነሳት ነው በበጎ ፈቃደኝነት በማኅበር ልንሰበስበው የቻልነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ መንግሥት በዚህ ዙሪያ ያተኮሩ ፖሊሲዎች፣ ሕጎች፣ መመርያዎችና ደንቦች የሚያወጣው ሸማቹ በተገቢው መንገድ ድምፁን የሚያሰማበት መንገድ ለመፍጠር ሲባል ነው፡፡ በዋናነት መጠቀስ ያለበት ነገር ቢኖር፣ ገበያው ላይ ሦስት ዋና ዋና ተዋናዮች መኖራቸው ነው፡፡ አንደኛው ተዋናይ መንግሥት ሲሆን፣ ሁለተኛው ከምርት እስከ አቅርቦት ድረስ የሚሠራ ነጋዴው ነው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ሸማቹ ነው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ሸማቹ እንደ ነጋዴውም ወይም አንድ መንግሥት ጠንካራ አይደለም፡፡ የአቅም ውስንነት አለበት፡፡ የአቅም ውስንነቱም በኢኮኖሚ ወይም በንቃተ ህሊና፣ አለበለዚያም በቂ መረጃ ባለማግኘት መሆን ይችላል፡፡ በዚህም የተነሳ ሸማቹ አቅሙን አጎልብቶ፣ በቂ መረጃ ኖሮት በገበያ ላይ ዕርካታ የሚያገኝበት መንገድ አነስተኛ ነው ተብሎ ይታሰባል፡፡ ይህም ሁኔታ በአገራችን ብሎም በአፍሪካ ከበድ ይላል፡፡ በሌሎች የአውሮፓ አገሮች ግን ሸማቹና ነጋዴው እኩል ዕውቀት ኖሯቸው የመሸመትና መደራደር አቅማቸው ከፍተኛ ነው፡፡      

ሪፖርተር፡- አንዳንድ ነጋዴዎች ምግብ ነክ የሆኑና ሌሎችንም ሸቀጣ ሸቀጦች እየደበቁ ሰው ሠራሽ እጥረት ለመፍጠር ሲንቀሳቀሱ ይስተዋላል፡፡ ይህንን ተግባር ለማምከን ማኅበሩ እስከ ምን ድረስ ተንቀሳቅሷል?

አቶ አሥራት፡- ይህ ጉዳይ በአሁኑ ወቅት ዋነኛ ችግር ነው፡፡ አሁን ላለው የዋጋ ንረት ምክንያቶች ናቸው ተብለው ከሚጠቀሱት መካከል አንዳንዳንድ ሕገወጥ ነጋዴዎች የዕቃ መደበቅ ወይም ደግሞ መሰወር፣ ከዋናው ገበያ አንስቶ ወደ ሌሎች ገበያዎች ማጓጓዝ ወይም ማዘዋወር፣ ምርትን መያዝና አመቺ ጊዜውን ጠብቆ በናረ ዋጋ የመሸጥ እንቅስቃሴዎች ይገኙበታል፡፡ ይህ እንቅስቃሴ እንዲቆም በመንግሥት በኩል በተደጋጋሚ ጊዜ ማስጠንቀቂያ አዘል መልዕክቶች ሲተላለፉ ቆይተዋል፡፡ ችግሩ በማስጠንቀቂያ ብቻ ሊገታ ባለመቻሉ ዕርምጃ እየተወሰደበት ይገኛል፡፡ በዚህም የተነሳ ባለፉት ጥቂት ቀናት ገበያው የመረጋጋት ሁኔታ እየታየበት መጥቷል፡፡ ስለሆነም መንግሥት ዘግይቶም ቢሆን ዕርምጃ ወስዷል፡፡ በዚህም ደላላውን በማግለል ሸማቹና ነጋዴው ብቻ እየተገናኙ እንዲገበያዩ ተደርጓል፡፡ በሌላ በኩል ነጋዴውን ብቻ እንደ አጥፊ የምናይበት ነገር ሊኖር አይገባም፡፡ የተሳለጠ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲኖር ለማድረግ በመንግሥት በኩል የተሠራ ሥራ አልነበረም፡፡ ይህም ሁኔታ ለዋጋ መናር እንድንጋለጥ አድርጎናል፡፡ አሁን ግን ዘግይቶም ቢሆን ዕርምጃ ተወስዷል፡፡  

ሪፖርተር፡- በዚህ ጉዳይ የማኅበሩ ሚና ምን ይመስላል?

አቶ አሥራት፡- ማኅበሩ አቅሙን አጎልብቶ ወደ ማኅበረሰቡ ውስጥ አልገባም፡፡ ዋጋን የማረጋጋት አቅም ገና አልፈጠርንም፡፡ ነገር ግን የችግሩን አሳሳቢነት በተለያዩ መድረኮች ላይ ለመንግሥት ከማሳወቅ ቸል ያለበት ጊዜ የለም፡፡

ሪፖርተር፡- የጨው ዋጋ በእጅጉ ንሮ ከሸማቾች አቅም በላይ ሆኗል፡፡ በዚህም የተነሳ ሸማቾች ለከፍተኛ ችግር ተዳርገዋል፡፡ በዚህ ላይ የሚሰጡት አስተያየት አለ?

አቶ አሥራት፡- የዋጋ መናርን ምክንያት ከማቅረቤ በፊት የጨው አመራረትና ማጓጓዝን በተመለከተ ትንሽ ለማብራራት እሞክራለሁ፡፡ በአፋር ክልል አፍዴራ ውስጥ ጨው አዘል በሆነው ሐይቅ ወይም መስኖ ላይ የሚንጣለለው ጥሬ ጨው ላይ የሚንቀሳቀሱ ብዙ ተዋናዮች አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል አንደኛው ተዋናይ መስኖው ላይ የተንጣለለውን ጥሬ ጨው የሚያመርት ማኅበር ይገኝበታል፡፡ ሌላው ደግሞ የተመረተውን ጥሬ ጨው በጆንያ እየከተተ፣ እያሠረና መኪና ላይ የሚጭንና የሚያወርድ ማኅበር ይገኛሉ፡፡ በመኪና ላይ የተጫነውን ጥሬ ጨው እየተረከቡ በማጠብና አይዳይዝድ በማድረግ የሚያመርቱ ሁለት ፋብሪካዎች አሉ፡፡ እነዚህ ፋብሪካዎች አዮዳይዝድ አድርገው ያመረቱትን ጨው የሚያከማቹባቸው 15 መጋዘኖች በአዲስ አበባና በየአካባቢው አቋቁመዋል፡፡ ጅምላ ነጋዴዎች ከእነዚህ መጋዘኖች አዮዳይዝድ የሚሆነውን ጨው እያወጡ ለቸርቻሪዎች፣ ቸርቻሪዎች ደግሞ ለሸማቾች ያቀርባሉ፡፡  

ሪፖርተር፡- የዋጋ ንረቱ መንስዔው ከየት ነው የመጣው?

አቶ አሥራት፡- የዋጋ ንረቱ መንስዔ ጥሬ ጨው በሚያመርት እና በጫኝና አውራጅ ማኅበራት መካከል በተፈጠረ አለመግባባት የተከሰተ ነው፡፡ ያለመግባባቱ ምክንያት ደግሞ ጥሬ ጨው የሚያመርተው ማኅበር ለጫኝና አውራጅ ማኅበር በኩንታል 10 ብር እየከፈለ ነበር ሲያስጭንና ሊያጓጉዝ የቆየው፡፡ በመካከሉ የጫኝና አውራጅ ማኅበር በኩንታል 20 ብር እንዲከፍለው ጠየቀ፡፡ ጥሬ ጨው የሚያመርተው ማኅበር ደግሞ ጥያቄውን ሳይቀበለው ቆየ፡፡ በዚህም የተነሳ ጥሬ ጨውን የማጓጓዝ ሥራ ተቋረጠ፡፡ የተጓጓዘውን ጥሬ ጨው ተቀብሎ ካጠበ በኋላ አዮዳይዝድ የሚያደርጉት ፋብሪካዎች የጥሬ ጨው ክምችታቸው እየሳሳና እያለቀ መጣ፡፡ በዚህም የተነሳ ማምረቱን ለማቆም ተገደደ፡፡ ፋብሪካዎቹና ማኅበራቱም ይህንን ሁኔታ በወቅቱ ለአፋር ክልላዊ መንግሥት አላሳወቁም፡፡ ንግድ ሚኒስቴርም መረጃ የለውም፡፡ በአዲስ አበባና በሌሉችም አካባቢዎች ባሉት መጋዘኖች ውስጥ ተከማችቶ የነበረው አዮዳይዝድ ጨው እየወጣና መጋዘኖችም ባዶ ወደ መሆን ደረጃ ተቃረቡ፡፡ ይህንን የተረዳው ነጋዴ ወያኔ በአፋር ክልል ባስከተለው ቀውስ ሳቢያ ‹‹ጨው የማምረቱ ሁኔታ ተቋርጧል›› በሚል የውሸት ወሬ በመጠቀም ለሸማቹ በውድ ዋጋ መሸጡን ተያያዘው፡፡ ሸማቾችም ለከፋ የኢኮኖሚ ጉዳት ተዳረጉ፡፡  

ሪፖርተር፡- ይህ ሁኔታ በምን ተቋጨ?

አቶ አሥራት፡- በተጠቀሱት ማኅበራት መካከል ተፈጥሮ የነበረው አለመግባባት መፍትሔ አገኘ፡፡ መፍትሔ ሊያገኝ የቻለውም በኩንታል አሥር ብር መክፈሉ ቀርቶ ወደ 15 ብር ከፍ እንዲል ሁለቱም ወገኖች በመስማማታቸው ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ጥሬ ጨውን እየጫኑ አዮዳይዝድ ወደሚያደርጉት ፋብሪካዎች የማጓጓዝና የማቅረብ ሁኔታ ቀጠሉ፡፡ ፋብሪካዎቹም አዮዳይዝድ ጨው የማምረቱን ሥራ በስፋት ቀጥሎበት ወደ 40 የሚጠጉ ተሽከርካሪዎቹም የተመረተውን ጨው ወደ የመጋዘኖች መጓጓዝና ማከማቸቱን ተያያዙት፡፡ ለሸማቹም በስፋትና በተመጣጣኝ ዋጋ የማቅረቡ ሁኔታ ቀጠለ፡፡ የንግድ ሚኒስቴርም ቁጥጥሩን በማጥበቅ ሰው ሠራሽ እጥረት ለመፍጠር ሲንቀሳቀሱ በተደረሰባቸው ጨው ነጋዴዎች ላይ ልዩ ልዩ ዓይነት ሕጋዊ ዕርምጃ መውሰድን ቀጠለበት፡፡ ይህ ዓይነቱም ሁኔታ ገበያው እንዲረጋጋና ቀድሞ ወደነበረበት ሁኔታ እንዲመለስ አድርጎታል፡፡

ሪፖርተር፡- ‹ለጨው እጥረት ምክንያት የሆነው የአምራቾችና አከፋፋዮች ውዝግብ ነው› የሚል ምክንያት እየተሰማ ነው፡፡ ይህም ምክንያት እርስዎ ካንፀባረቁት ምክንያት ጋር የሚጣጣም ሆኖ አልታየም፡፡ በዚህ ላይ ያለዎትን አስተያየት ቢያካፍሉን?

አቶ አሥራት፡- የአምራችና የአከፋፋዮች ውዝግብ ነው የሚለው መረጃ የለኝም፡፡   

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

አደራውን ለመጠበቅ ዕድል ያላገኘው ቅርስ ባለአደራ

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማኅበር ከተመሠረተ ሦስት አሥርት አስቆጥሯል፡፡ ማኅበሩ በእንጦጦ ተራራማ ቦታዎች በአደራ በመንግሥት በተረከበው 1,300 ሔክታር መሬት ላይ የተለያዩ አገር በቀል ዛፎችን በመትከል...

ብዝኃ ትምህርቱን ‹ስቴም› ለማስረፅ

ስሜነው ቀስቅስ (ዶ/ር) የስቴም (Stem) ፓውር ግብረ ሰናይ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተርና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የቴክኖሎጂ አማካሪ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የማስተርስና የፒኤችዲ...

‹‹እውነታውን ያማከለ የሥነ ተዋልዶ ጤና ግንዛቤን ማጠናከር ያስፈልጋል›› ደመቀ ደስታ (ዶ/ር)፣ በአይፓስ የኢትዮጵያ ተወካይ

በሥነ ተዋልዶ ጤና ጉዳዮች ላይ በመሥራት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሰው አይፓስ፣ የኢትዮጵያን ሕግ መሠረት አድርጎ በሴቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና ከጤና ሚኒስቴርና ከክልል ጤና ቢሮዎች...