Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊከ900 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የውዳሴ መልቲ ስፔሻሊቲ ማዕከል ሊገነባ ነው

ከ900 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የውዳሴ መልቲ ስፔሻሊቲ ማዕከል ሊገነባ ነው

ቀን:

  • በጳጉሜን ለጤና ለ2,000 ሰዎች ነፃ ምርመራ ይደረጋል

ዘርፈ ብዙ የሕክምና አገልግሎት በስፔሻሊቲ (የላቀ አገልግሎት) ደረጃ የሚሰጥባቸው ባለሁለት ሕንፃዎች ማዕከል በ943 ሚሊዮን ብር ወጪ ሊገነባ ነው፡፡

ውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማዕከል በአዲስ አበባ ከተማ በ2,000 ካሬ ሜትር ይዞታ ላይ የሚያስገነባቸው ሕንፃዎች ባለ 21 እና ባለ 11 ወለል ናቸው፡፡ ከሁለቱም ሕንፃዎች ሥር በ1,640 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈና 130 መኪናዎችን የሚይዝ ባለ 5 ወለል የመኪና ማቆሚያ ይኖረዋል፡፡  

ከማዕከሉ የተገኘው መረጃ እንደሚገልጸው፣ ረዥሙ ሕንፃ ከመሬት እስከ 7ኛ ወለል ለሕክምና አገልግሎት የሚውል ሲሆን፣ ከ8ኛ እስከ 20ኛው ወለል ድረስ በእያንዳንዱ ወለል ለአራት ቤተሰቦች የሚሆን መኖሪያ ቤቶች አሉት፡፡

በስተምሥራቅ የሚገኘው ባለ 11 ወለል ሕንፃ ለሕክምና አገልግሎት ብቻ የሚውል ሲሆን፣ ዘጠኝ የሜዲካል ስፔሻሊቲዎች ይኖሩታል፡፡ እነሱም የካንሰር፣ የነርቭና ኀብለ ሰረሰር፣ መውለድ ላልቻሉ ወይም የመካንነት ችግር ላለባቸው፣ ከአንገት በላይ፣ የአጥንት ቀዶ ሕክምና፣ ከምግብ መፈጨት ጋር የተያያዘ ወይም የጨጓራና የአንጀት ችግር፣ የቆዳ ሕክምና ወይም ፕላስቲክ ሰርጀሪ፣ የምስልና የቤተ ሙከራና የአካል ንቅለ ተከላ ማዕከላት ናቸው፡፡

የውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማዕከል  ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳዊት ኃይሉ፣ የተቋማቱ ግንባታ ከሁለት ዓመት በላይ ተጠናቆ በሙሉ አቅሙ ሥራውን ሲጀምር የጎረቤት አገሮች ሕክምና ፈላጊዎችንም ጭምር በመሳብ በሜዲካል ቱሪዝም አስፈላጊውን ሚና መጫወት እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት በመዲናዋ አማካይ በሆነና ለሜዲካል ቱሪዝም አመቺ በሆነ አካባቢ የሚገኘውን ቦታ ለተቋማቱ ግንባታ እንዲውል መፍቀዱ፣ እንዲሁም ጤና ሚኒስቴር ላበረከተው ሁለንተናዊ ድጋፍ ባለሀብቱ ሳያመሠግኑ አላለፉም፡፡

‹‹ውዳሴ መልቲ ስፔሻሊቲ ሴንተር›› በሚል መጠርያ የሚታወቀው ማዕከል ግንባታን ነሐሴ 20 ቀን 2013 ዓ.ም. በተከናወነው ሥነ ሥርዓት ያስጀመሩት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ደረጀ ድጉማ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው ከሌሎች ባለሥልጣናት ጋር የመሠረት ድንጋይ ካኖሩ በኋላ ባደረጉት ንግግር፣ ውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማዕከል በመንግሥት ጤና ተቋማት ያሉትን ክፍቶች በመሸፈን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን፣ ይሄ ዓይነቱም መተጋገዝ ለሌሎች ጤና ተቋማት በአርዓያነት እንዲታይ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

መንግሥት የጨረር ሕክምናን ለማስፋፋት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሆነ፣ በዚህም የማዕከሉ ዕገዛ ከፍተኛ እንደሆነና እስካሁንም ድረስ በውስጡ የሚሰጣቸውም የምርመራ አገልግሎቶች የጤናውን ዘርፍ በማዘመን ረገድ የጎላ አስተዋጽኦ እንዳለው አስረድተዋል፡፡

በዓመት ከ20,000 ሰዎች በላይ ለሕክምና ወደ ተለያዩ ባዕድ አገሮች በመሄድ ለሕክምና ከፍተኛ ወጪና እንግልት እንደሚዳረጉ ያወሱት ደግሞ የጤና ሚኒስትር አማካሪ ዳንኤል ገብረሚካኤል (ዶ/ር)፣ የማዕከሉ መገንባት ሰዎች ወደ ውጭ ከመሄድ እንዲቆጠቡ የበኩሉን ዕገዛ ያደርጋል የሚል እምነት ተጥሎበታል ብለዋል፡፡

አልትራሳውንድ፣ ኤምአርአይና ሲቲስካን ወዘተ. ለተባሉና ጥቅል መጠሪያቸው ‹‹ኢሜጂንግ›› (ምስለ) ለተባሉት ለእነዚህ አገልግሎቶች መስፋፋት መንግሥት የ15 ዓመት ፍኖተ ካርታ እንዳወጣ፣ ለዚህም ዕውን መንግሥት ከግሉ የጤና ዘርፍ ጋር ተቀናጅቶ መንቀሳቀስ እንዳለበት ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ሙሉጌታ እንዳለ (ዶ/ር) በበኩላቸው የግሉና የመንግሥት ጤና ተቋማት በጋራ አብረው የመሥራታቸውን ሁኔታ ሲዳሰስ ከሃያ በመቶ በላይ መሆኑን፣ ይህም ከሌሎች አገሮች ጋር ሲታይ በጣም አነስተኛ መሆኑን ጠቁመው፣ በግልና በመንግሥት አጋርነት መርህ መሠረት አጋርነታቸው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ማዕከሉ በየዓመቱ የሚያካሂደውን ‹‹ጳጉሜን ለጤና›› መርሐ ግብር ዘንድሮም ለ12ኛ ጊዜ እንደሚያካሂድ አስታውቋል፡፡

በዚህም በዝቅተኛ ኑሮ ላይ ለሚገኙና ከ2,000 ሰዎች በማዕከሉ ውስጥ ነፃ ምርመራን  ከጳጉሜን 1 ቀን እስከ ጳጉሜን 5 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ያከናውናል፡፡

 የነፃ ምርመራ አገልግሎት የሚሰጠው በማዕከሉና በሁሉም የማዕከሉ ቅርንጫፎች ሲሆን፣ ተገልጋዮች ደውለው ሲመዘገቡና ቀጠሮ ሲሰጣቸው በሚገለጽላቸው ቅርንጫፎች በመገኘት የአገልግሎቱ ተቋዳሽ እንደሚሆኑ ተገልጿል፡፡

ከዚህም ሌላ ማዕከሉና የማዕከሉ ቅርንጫፎች በተቋቋሙበት ክፍላተ ከተማ ነዋሪ ለሆኑና የምርመራ አገልግሎት ለሚሹ ታካሚዎች ለአገልግሎቱ ከሚከፍሉት የ20 በመቶ ቅናሽ እንደሚደረግላቸው መግለጫው አመልክቷል፡፡

ለነፃ ምርመራ አገልግሎት ብቁ የሚያደርጉ መሥፈርቶች እንዳሉ፣ ከመሥፈርቶቹ መካከል አንደኛው ከመንግሥት የሕክምና ተቋም በሐኪም የታዘዘ የምርመራ ትዕዛዝ መኖርና አስቀድሞ በስልክ ቁጥር 9888 ወይም በ0940050505፣ 0940040404 መደወልን ያመለክታል፡፡ ከዚህም ሌላ በፌስቡክ ውዳሴ ዲያግኖስቲክ ሴንተር መጠየቅ ይቻላል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...