Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሦስተኛው ማዕበል በአዲስ አበባ የመታየት አዝማሚያ ማሳየቱ ተጠቆመ

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሦስተኛው ማዕበል በአዲስ አበባ የመታየት አዝማሚያ ማሳየቱ ተጠቆመ

ቀን:

ከአራት ሳምንታት ወዲህ ሕይወታቸው የሚልፍና የፅኑ ሕሙማን ቁጥር እያሻቀበ ነው

አዲስ አበባ ውስጥ ካለፉት አራት ሳምንታት ጀምሮ በኮቪድ-19 የሚያዙና በፅኑ የታመሙ ሰዎች ቁጥር፣ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩና ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥርም ከፍተኛ መሆኑ ተጠቆመ፡፡

ይህም በበርካታ የአፍሪካ አገሮች እየታየ ያለውን የወረርሽኙ ሦስተኛው ማዕበል የመታየት አዝማሚያ እንደሚያሳይ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዮሐንስ ጫላ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ የኮቪድ-19 ክትባት መስጠት ወረርሽኙን ለመከላከል ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ በዚህም መሠረት በአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑና ከዚህ ቀደም ክትባቱን ያልወሰዱ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለመከተብ ታቅዶ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

ለዚህም በቂ የሆነ ክትባት በአገር ውስጥ መግባቱንና እስካሁንም ድረስ ከ568,000 ዶዝ በላይ ክትባት ቢሮው እንደረተከበ፣ ይህም ወደ መጠናቀቁ ገደማ ሲቃረብ የቀረውን እንደሚረከብ ኃላፊው አስረድተዋል፡፡

ክትባቱ ከሚሰጣቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል ዕድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ የሆኑ፣ እንዲሁም ዕድሜያቸው ከ55 እስከ 64 ዓመት የሆኑና ተጓዳኝ ችግር ያለባቸው ብቻ ቅድሚያ እንዲያገኙ መደረጉን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ከዚህም ሌላ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ ለሆኑና ተጓዳኝ በሽታ ላለባቸው ሰዎች ክትባቱን ለመስጠት መታሰቡን የጠቆሙት ኃላፊው፣ በተጨማሪም በሥራ ባህሪያቸው ይበልጥ ተጋላጭ ናቸው ተብለው ለተለዩና ከ105 በላይ ለሚሆኑ የመንግሥትና የግል ተቋማት (የትራንስፖርት ሴክተር፣ የግልና የመንግሥት ባንኮች፣ የፌዴራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን) ሠራተኞች ለመስጠት መታቀዱንም ከማብራሪያቸው ለመረዳት ተችሏል፡፡

‹‹በአሁኑ ጊዜ በለጋሽ አገሮች ዕገዛ የተለያዩ ክትባቶች ወደ አገራችን እየገቡ ናቸው፡፡ እስካሁንም አስትራዜኒካ፣ ሲኖፋርምና ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን የሚባሉ ክትባቶች አገልግሎት ላይ እየዋሉ ናቸው፡፡ የክትባቶቹ መጠሪያ የተለያየ ቢሆንም፣ በደኅንነታቸውና በፍቱንነታቸው የወረርሽኙን ሥርጭት ከመቆጣጠርና በወረርሽኙ ሊደርስ የሚችለውን የከፋ ሕመምና ሞት ከመከላከል አንፃር ሁሉም ክትባቶች ተመሳሳይ ውጤት ያላቸው በመሆኑ፣ ማኅበረሰቡ ያለ ምንም ሥጋት ወደ መንግሥት ጤና ጣቢያዎች በመሄድ ክትባቱን በነፃ በመውሰድ ራሱንና ቤተሰቡን ከአስከፊ ወረርሽኝ እንዲጠብቅ እናሳስባን፤›› ብለዋል፡፡

ክትባቱን መውሰድ ወረርሽኙን ለመከላከል አንደኛው ዘዴ መሆኑን የጠቆሙት  ዮሐንስ (ዶ/ር)፣ ከዚህ በፊት ሲደረግ የነበሩትን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ዘዴዎችን እንደ እጅን በውኃና በሳሙና አዘውትሮ መታጠብ፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ በአግባቡ መጠቀምና አካላዊ ርቀትን መጠበቅን መተግበር እንደሚያስፈልግም አስታውሰዋል፡፡

ክትባቱ የሚሰጠው በነፃ መሆኑን፣ ምንም ዓይነት ክፍያ የሚጠይቅ አካል ካለ ለጤና ተቋሙ ኃላፊዎች ወይም በአቅራቢው ለሚገኝ የሕግ አካላት ማኅበረሰቡ ጥቆማ እንዲሰጥና ጉዳዩን መንግሥት ተከታትሎ ዕርምጃ የሚወሰድ መሆኑን ከቢሮው ኃላፊ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

እንደ ዮሐንስ (ዶ/ር) ማብራሪያመ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከመንግሥት ጤና ተቋማት ውጪ የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባትን በእጃቸው ይዘው ሲንቀሳቀሱ ተደርሶባቸዋል የተባሉ ሦስት ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ውለው በምርመራ ላይ ናቸው፡፡ ግለሰቦቹ ሊደረስባቸው የቻለው ከጤና ተቋማት ውጪ ክትባቱን ሲቀባበሉ በጥቆማ መሆኑንም አክለዋል፡፡

የግለሰቦቹ አድራጎት በፖሊስ ምርመራና በመጣራት ላይ መሆኑን ገልጸው፣ ውጤቱ ከተረጋገጠ በኋላ ለኅብረተሰቡ ይፋ እንደሚደረግ አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...