Monday, May 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናኢዜማ የአገር ሉዓላዊነትና የሕዝብ ደኅንነት ማስከበር ዘመቻ ግብረ ኃይል እንዲቋቋም ጠየቀ

ኢዜማ የአገር ሉዓላዊነትና የሕዝብ ደኅንነት ማስከበር ዘመቻ ግብረ ኃይል እንዲቋቋም ጠየቀ

ቀን:

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) አሁን የተደቀነውን አደጋ ለመቀልበስ የሚወሰደው ዕርምጃ የዛሬውንም ሆነ የወደፊቱን ወቀሳም ይሁን የድል ሽሚያ ማስቀረት በሚያስችል መንገድ፣ አንድ ወጥ የዕዝ ሰንሰለት ኖሮት ከመንግሥት መዋቅር ውጪ ያሉ ኢትዮጵያዊያንን ጭምር በማሳተፍ፣ በፌደራል መንግሥትና በመከላከያ ሠራዊት አመራር ሰጪነት ብቻ የሚመራ ‹‹ብሔራዊ የአገር ሉዓላዊነትና የሕዝብ ደኅንነት ማሰከበር ዘመቻ ግብረ ኃይል›› በአስቸኳይ እንዲቋቋምና ወደ ሥራ እንዲገባ ጠየቀ።

ግብረ ኃይሉ የፌደራል መንግሥት ግዴታውን ከምንጊዜውም በላይ በከፍተኛ ውጤታማነት መወጣት እንዲችል የወታደራዊ፣ የዓለም አቀፍ ግንኙነት፣ የፕሮፖጋንዳ፣ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉና ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ዜጎች የማገዝ፣ የሀብት ማሰባሰብና ከኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ መሠራት ያለባቸው ሥራዎችን ስትራቴጂ እየነደፈ እንዲከናወኑ ውሳኔ የሚያስተላልፍ መሆኑንም ጠቁሟል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች የአገር ህልውና ፈተና ላይ መውደቁን በቅጡ በመረዳት፣ ያላቸውን ልዩነቶች ወደ ጎን በማለት አባሎቻቸውም የአማፂያኑን ዕብሪት ለማስተንፈስ በሚደረገው እንቅስቃሴ እንዲሳተፉ ኢዜማ ጠይቋል፡፡

- Advertisement -

ኢዜማ በመግለጫው ነሐሴ 10 ቀን 2013 ዓ.ም. ኢትዮጵያ በሕዝቦቿ ተጋድሎ ሉዓላዊነቷን ከውጭ ወረራ በማስከበር ለጥቁር ሕዝቦች ነፃነት ምሣሌ የሚሆን ታሪክ ያላት ሀገር መሆኗን አስታውሶ፣ ‹‹እንዳለመታደል ሆኖ የአገር ድንበርን ከውጭ ወረራ ተከላክሎ ለማስከበር ባለን ቀናዒነት ልክ የውስጥ ችግሮቻችንን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የምናደርገው ጥረት ይህ ነው የሚባል አይደለም፡፡ በዚህ የተነሳ በየጊዜው በሚነሱ ውስጣዊ አለመግባባቶች መነሻነት የዜጎች ሕይወት ማጣትና ሰብዓዊ ቀውስ ውስጥ መግባት የሰርክ ተግባር ሆኖ ቀጥሏል፡፡ አሁን ባለንበት ወቅት በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በሕወሓት ጦረኝት በተለይ በጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. በመከላከያ ሠራዊታችን ላይ በፈጸመው አስነዋሪ ድርጊት መነሻ የተፈጠረውን የሕግ ማስከበር የመንግሥት ዕርምጃን ተከትሎ የተፈጠረው ሰብዓዊ ቀውስ ሳይበቃ፣ ሕወሓት ወደ ሌሎች የአገራችን ክፍል ለማስፋፋት በግልጽ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ለዚህም በቅርቡ ከኦነግ ሸኔ ጋር ያደረገው ይፋዊ ስምምነት የሚታወቅ ሲሆን፣ ከሌሎች ተመሳሳይ ዕኩይ ተልዕኮ ካላቸው በአገር ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ጋር ቀውሱን ለማስፋት እንደሚሠሩ በይፋ እየገለጹ ይገኛሉ፤›› ብሏል፡፡

በአንድነትና በሰላም ላይ የተጋረጠውን አደጋ ለመቀልበስ የሚወሰደው ዕርምጃ ዘላቂ አብሮነትን በማይጎዳ መንገድ ሕግና ሥርዓትን ተከትሎ መወሰድ እንዳለበት፣ የዜጎች ሁሉ ሰብዓዊ መብት ያለምንም ልዩነት በእኩል እንዲከበርም ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

የመከላከያ ሠራዊት በቁጥጥሩ ሥር ከነበሩ ቦታዎች ለቆ መውጣቱን ተከትሎ ኢዜማ ሰኔ 26 ቀን 2013 ዓ.ም፤ ይፋ ባደረገው የቢሆንስ (Scenario) ትንተና፣ ‹‹ሕወሓት አገራችንን ለማተራመስ ከሌሎች አክራሪ ብሔርተኞች ጋር ጥምረት መመሥረት የሚችልበት ሁኔታ የሚፈጠር ከሆነ፣ ለኢትዮጵያ አንድነትና ሰላም በራሱ ከሚፈጥረው አደጋ በተጨማሪ ለኢትዮጵያ የውጭ ጠላቶች መሣሪያ በመሆን አገሪቱ በምትገኝበት ቀጣና ከፍተኛ አደጋ ሊደቅን ይችላል፤›› በማለት መግለጹን፣ የኢትዮጵያ አንድነትና ሰላም እንዲረጋገጥ የሚፈልጉ ኃይሎች በሙሉ አቅማቸው ተረባርበው አደጋውን እንዲቀለብሱ ጥሪ አስተላልፏል፡፡

ሕወሓትን ደግፋችኋል በሚል በጅምላ የሚወሰዱ ዕርምጃዎች በአስቸኳይ እንዲቆሙና በዚህ ሁኔታ የተወሰዱ ዕርምጃዎች አፋጣኝ ማጣራት ተደርጎባቸው የእርምት ዕርምጃ እንዲወሰድ፣ እንዲሁም አሁን ያለውን ሁኔታ እንደ አጋጣሚ በመጠቀም የግል ጥቅም ለማግኘት በዜጎች ላይ እንግልት የሚፈጹሙ የመንግሥትና የፀጥታ ሠራተኞች ላይ  በአስቸኳይ ማጣራት ተደርጎ የማያዳግም ሕጋዊ ዕርምጃ እንዲወሰድ መጠየቁን አስታውሶ፣ ኢዜማ ችግሮች በኃይል አማራጭ ብቻ በዘለቄታው ይፈታሉ የሚል እምነት እንደሌለው፣ አሁን ያለው ችግር በተለይ ደግሞ በዜጎች ላይ እየተፈጠረ ያለው ሰብዓዊ ቀውስ እንዲቆም ሰላማዊ መፍትሔዎች እንዲያገኙ ጥረት ማድረግ ተገቢ ነው ብሎ እንደሚያምን፣ ነገር  ግን ሕወሓትና አጋሮቹ የውስጥም ሆኑ የውጭ የጥፋት ኃይሎች ኢትዮጵያዊያን ለሰላም ያላቸውን ፅኑ አቋም ተረድተው የጦር እንቅስቃሴያቸውን እንዲያቆሙ ማድረጊያው ጊዜ አሁን መሆኑን አስታውቋል፡፡ ወደ ሰላማዊ መስመር እስከሚመለሱ ድረስ የአገርን ሉዓላዊነትና የሕዝብን ደኅንነት ማስጠበቅ በዋነኛነት የመንግሥት ኃላፊነት ቢሆንም፣ ሁሉም ግዴታ ያለበት መሆኑን አስረድቷል፡፡

ኢትዮጵያ እውነት ይዛ ሳለ በሐሰት ፕሮፓጋንዳ ብዛት የውጭ ኃይሎች ጭምር በተቃራኒ እንዲቆሙ የሆኑበትን ሁኔታ እውነቱን በማጋለጥና ትክክለኛ ዘገባዎችን ወደ ሕዝብ በማድረስ በሕዝባችን ውስጥ የተፈጠረውን ብዠታ እንዲያጠሩና እንዲቀለብሱ፣ በሥራቸውም የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡና ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ከፍ እንዲያደርጉ  ጥሪውን አስተላልፏል፡፡ የንግድ ማኅበረሰብ አባላትም በዚህ ፈታኝ ወቅት በተለያየ መንገድ ሠራዊቱንና የሠራዊቱን ቤተሰቦች መደገፍ እንዲቀጥሉ፣ በተለይ በዚህ ወቅት ሊፈጠሩ በሚችሉ ሰው ሠራሽ የገበያ እጥረቶችና እነሱን ተከትሎ በሚመጣው ከፍተኛ የኑሮ ውድነት ዜጎች እንዳይማረሩ፣ አሁን ኢትዮጵያ የገባችበትን ክፉ ሁኔታ እንደ አጋጣሚ በመውሰድ በሸማች ዜጎች ኪሳራና ችግር ለመክበር ከሚደረግ እንቅስቃሴ እንዲቆጠቡና የዜጎች አለኝታ መሆናችውንና በክፉ ቀን ከአገራቸው ሕዝብ ጎን በመቆም አንድነታቸውን እንዲያረጋግጡ ጥሪ አቅርቧል፡፡

ኢዜማ እንደ አገራዊ ፓርቲ የአገር ህልውናን ለማስከበርና የዜጎች ደኅንነት እንዲጠበቅ የሚቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ ጠቁሞ፣ በቀጣይ ከአባላት ጋር በመመካከር የሚያደርጋቸውን ተጨማሪ ነገሮች እንደተጠበቁ ሆኖ አሁን ሁለት መቶ ሃምሳ ሺሕ ብር ከግጭቱ ጋር በተያያዘ በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች ከመኖሪያቸው ለተፈናቀሉና ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ድጋፍ እንዲውል ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር እንደሚያስረክብ አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...