Monday, May 27, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ብልሹው የግብይት ሥርዓት የኑሮ ውድነቱን እያባባሰው ነው!

መንግሥት በፋይናንስ ዘርፉ ውስጥ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የተለያዩ ዕርምጃዎች እየወሰደ ነው፡፡ ይህ ዕርምጃ በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ በሚታዩ ችግሮችም ላይ መቀጠል አለበት፡፡ ከዘመኑ ጋር እኩል መራመድ ያቃተው በሴራና በአሻጥር የተተበተበው የግብይት ሥርዓት፣ ከሕዝብ አቅም በላይ ሆኗል፡፡ የግብይት ሥርዓቱ ጤናማ መሆን ካልቻለባቸው ዋና ዋና ምክንያቶች መካከል አንዱ፣ በፍጆታ ምርቶችም ሆነ በሌሎች ሸቀጣ ሸቀጦች የአቅርቦት ችግር ሳይኖር ሰው ሠራሽ የዋጋ ግሽበት በመፍጠር የኑሮ ውድነቱ መባባሱ ነው፡፡ ነፃ ገበያ በሚል ፈሊጥ ልቅ የሆነው ይህ የግብይት ሥርዓት ጠንካራ ተቆጣጣሪ አካል ስለሚያስፈልገው፣ መሠረታዊ የሚባሉትን ችግሮች መመርመር ይገባል፡፡ የመጀመሪያው አቅርቦቱን አስተማማኝ ማድረግ ሲሆን፣ ቀጥሎ ደግሞ ግብይቱን ጤናማ ማድረግ ነው፡፡ ጤናማ የግብይት ሥርዓት ዋነኛ ተዋናዮች ሸማች፣ ነጋዴና መንግሥት በንቃት የሚሳተፉበት ነው፡፡ እነዚህ ሦስት አካላት በሚገባ ካልተናበቡ የግብይት ሥርዓቱ ይታወካል፡፡ ኢኮኖሚው በነፃ የገበያ ሥርዓት ይመራበታል በሚባልበት አገር ውስጥ፣ የግብይት ሥርዓቱ ጤና በመታወኩ የኑሮ ውድነቱ እየከፋ ነው፡፡ መንግሥት በተጠና መንገድ ኃላፊነቱን መወጣት ይጠበቅበታል፡፡

በነፃ ገበያ ሥርዓት ውስጥ ነጋዴዎችፍትሐዊ ውድድር መፎካከር አለባቸው ሲባል፣ እንዳሻቸው ለሚጨፍሩበት አልጠግብ ባዮች ሜዳው ይመቻቻል ማለት አይደለም፡፡ በአምራችነት፣ በአስመጪነት፣ በጅምላ አከፋፋይነትና በቸርቻሪነት የተሰማሩ የተወሰኑ የተደራጁ ኃይሎች ጤናማ ውድድር እንዳይኖር እያደረጉ ነው፡፡ የምርትና የአቅርቦት ሰንሰለቶችን በመቆጣጠር ዋጋ እንደፈለጉ ይወስናሉ፡፡ ምርቶችን ከመደበቅ ጀምሮ የአቅርቦትና የሥርጭት መስመሮችን ይዘጋሉ፡፡ ሰው ሠራሽ እጥረት በመፍጠር ዋጋ ይቆልላሉ፡፡ ሰላማዊና ጤናማ መሆን የሚገባውን የውድድር ሜዳ በማጣበብ ሕገወጥነትን ያሰፍናሉ፡፡ ስለዚህም የአቅርቦት መስመሩን በማስተካከል ጠንካራ በሆነ የሕግ ማዕቀፍ ቁጥጥር ሊደረግበት ይገባል፡፡ የግብይት ሥርዓቱ ውስጥ ዘለው የገቡ ኃይሎች በባለሥልጣናት ጭምር በመደገፍ ጤናማ ውድድር እንዳይኖር እያደረጉ ነው፡፡ በተለይ ደላሎች ትልቁን ሚና የሚጫወቱበት ይህ የተበላሸ የንግድ ሥርዓት፣ በህቡዕ የተደራጁ ሥውር ተዋንያንን ጭምር ያሳትፋል፡፡ በዚህም ምክንያት ሕዝብ የኑሮ ውድነቱን መቋቋም አቅቶታል፡፡

ገበያውን የተቆጣጠሩ አካላት ሕግና ደንብ አክብረው በሚሠሩ ታታሪዎች ላይ ከፍተኛ ጫና ከመፍጠራቸውም በላይ፣ የሕዝቡን ኑሮ እያናጉ ነው፡፡ የነፃ ገበያ ሥርዓት ትርጉሙ ተዛብቶ ሥርዓተ አልበኝነት እየነገሠ ነው ማለት ይቻላል፡፡ አልጠግብ ባዮች በምግብ ምርቶች ላይ ምክንያታዊ ያልሆኑ ሰው ሠራሽ ጭማሪዎች ሲያደርጉ፣ መሠረታዊ የሚባሉ የፍጆታ ዕቃዎች ከሸማቾች ማኅበራት ሳይቀር በሕገወጥ መንገድ እያወጡ በተጋነነ ትርፍ ሲሸጡ፣ በኔትወርክ የተሳሰሩ ስግብግቦች ምርቶችን ሲደብቁ፣ ባዕድ ነገሮችን ምርቶች ውስጥ ሲደባልቁና እጅግ በጣም አሳፋሪ የሆነ የሚዛን ማጭበርበር ወንጀል ሲፈጽሙ እንዴት ጤናማ የግብይት ሥርዓት ይኖራል? መንግሥት ፍትሐዊ የሆነ የውድድር ሜዳ በማመቻቸት የግብይት ሥርዓቱን ጤናማነት የመቆጣጠር ኃላፊነት አለበት፡፡ የሚመለከተው መንግሥታዊ አካል ሕግ በማውጣት ይህንን ኃላፊነቱን በመወጣት ላይ መሆኑን ቢገልጽም፣ መረን የተለቀቀው የግብይት ሥርዓት ልጓም ሊበጅለት አልቻለም፡፡ ሕግ ቢኖርም የቁጥጥር ሥርዓቱን የሚያስፈጽሙ አካላት ወይም ግለሰቦች በብቃት ሥራቸውን እያከናወኑ አይደሉም፡፡ ኃላፊነት የማይሰማቸው አልጠግብ ባዮችና የእነሱ ቢጤዎች የመንግሥት ሹማምንት ሕገወጥ ግንኙነት ሚስጥር አይደለም፡፡ ከበድ ያሉ ችግሮች ሲያጋጥሙ በዘመቻ የሚከናወነው ዕርምጃ ምንም መፍትሔ ማምጣት አልቻለም፡፡ ተቆጣጣሪ የሚባለው አካል ኃላፊነቱን እየተወጣ አይደለም፡፡

በቀንድ ከብት ሀብት ከአፍሪካ አንደኛ የሆነች አገር ውስጥ ለአንድ ኪሎ ሥጋ እስከ አንድ ሺሕ ብር ክፍያ ሲጠየቅ፣ የግብይት ሥርዓቱ ምን ያህል እንደተበላሸ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ የልኳንዳ ነጋዴዎች ለዕርድ ቄራ የሚያስገቡትን ከብት በውጭ ምንዛሪ ከውጭ እንደማያስገቡ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን የአገር ውስጥ የቁም እንስሳት ግብይትን በሥርዓት ማከናወን ባለመቻሉ ምክንያት፣ ለኢትዮጵያዊያን ሥጋ የአልማዝ ያህል ውድ ሲሆንባቸው ማየት ያሳፍራል፡፡ ይህም የተበላሸው የግብይት ሥርዓት ውጤት ለመሆኑ አንዱ ማረጋገጫ ነው፡፡ ከሥጋ ውጪ የሌሎች ምርቶች ግብይትም አሳዛኝ ነው፡፡ ለቁጥጥሩ መላላት የመጀመሪያው መንግሥት በግብይት ሥርዓቱ ውስት አለኝ የሚለው የመረጃ ተዓማኒነት ላይ ችግር መኖሩ ነው፡፡ በተለያዩ ዘርፎች ከግብይት ሥርዓቱ ጋር የሚያያዙ ችግሮች ሲፈጠሩ፣ የሚወሰደው ዕርምጃ እሳት እንደ ማጥፋት ጥድፊያ የበዛበት ነው፡፡ መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ከገበያ ውስጥ ሲጠፉ ለቅጣት የሚዳረገው ታች ያለው ቸርቻሪ ነው፡፡ ነገር ግን የአቅርቦት መስመሩን አንቀው የያዙትን የተደራጁ ኃይሎች ማንም አያገኛቸውም፡፡ የግብይት ሥርዓቱ ጤናማ እንዳይሆንና ፍትሐዊ ውድድር እንዳይኖር አሻጥር የሚፈጽሙ ኃይሎች ተፅዕኖ በጣም የበረታ በመሆኑ፣ የማስፈጸም አቅሙም እጅግ  የተዳከመ ነው፡፡ ይኼም ያሳስባል፣ አፋጣኝ መፍትሔም ይፈልጋል፡፡

የግብይት ሥርዓቱ ኋላቀር በመሆኑ መሠረታዊ ለውጥ ያስፈልገዋል፡፡ ለዚሀም በዲሲፕሊን የሚመራ የትርፍ ህዳግ ሕግ ማውጣት ያስፈልጋል፡፡ ከመሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች አንስቶ፣ አልባሳትና መጫሚያዎች፣ የቤትና የቢሮ መገልገያ መሣሪያዎች፣ አገልግሎቶችና የመሳሰሉት ከሚያወጡት ዋጋ በላይ የእጥፍ እጥፍ ይተረፍባቸዋል፡፡ ይኼ ደግሞ ንግድ ሳይሆን ዘረፋ ነው፡፡ ጤናማና ፍትሐዊ የውድድር ሜዳ ቢኖር ኖሮ መንግሥት ፈፅሞ ጣልቃ ሳይገባ፣ በጤናማ የውድድር መርህ መሠረት ትርፍ ገደብ ይኖረው ነበር፡፡ አልጠግብ ባዮች ሌላው ቀርቶ ቀረጥ ያልከፈሉባቸውን ምርቶች ሳይቀር በተጋነነ ዋጋ እየሸጡ ግብይቱን ያተራምሳሉ፡፡ ሕጋዊ ነጋዴዎችን ከገበያ ያስወጣሉ፡፡ በመንግሥት አሠራር ረገድ ደግሞ ቀልጣፋ የሆነ የወጪናገቢ ንግድን በዘመናዊ የጉምሩክ ሥርዓት ማስተናገድ አለመቻል ሌላው ችግር ነው፡፡ በተለይ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች በዓለም ገበያ ያላቸው ወቅታዊ ትክክለኛ ዋጋ አለመታወቅ፣ ከዋጋ በታችና በላይ የሆኑ ደረሰኞች በደፋርና ስግብግብ ነጋዴዎች ሲቀርቡ ችላ ማለት ወይም መመሳጠርና የመሳሰሉት ችግሮችም ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ ችግሮች ተደማምረው በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ የትርፍ ህዳግ እንዳይተዋወቅ ሲደረግ፣ ሥርዓተ አልበኞችና ሕገወጦች እንዳሻቸው ይዘርፋሉ፡፡ ጤናማ ውድድር በሌለበት ጤናማ ትርፍ ስለማይታሰብ ሸማቾች የዘራፊዎች ሲሳይ ይሆናሉ፡፡ ፍትሐዊና ጤናማ የግብይት ሥርዓት በሌለበት ዋናው ተጎጂ ሸማቾች ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ጠንካራ የሸማቾች ማኅበራት ወይም ወኪሎች ስለሌሉ፣ ሸማቾች የአልጠግብ ባዮች ሰለባ ሆነዋል፡፡

በንግድ ማኅበረሰቡ ውስጥ ሕግ አክብረው ሸማቾችን የሚያገለግሉ ያሉትን ያህል፣ በስግብግብነት ለዘረፋ የተሠለፉ ሞልተዋል፡፡ ሸማቾች ገበያው ውስጥ ሲገቡ ለመብቶቻቸው የሚከራከሩ ወኪሎች ስለማይኖሩዋቸው ለዘረፋ የተጋለጡ ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ጥራታቸው ለተጓደሉ ምርቶች የተጋነነ ዋጋ ሲጠየቁ፣ በሚዛን ሲዘረፉና የተለያዩ እንግልቶች ሲደርሱባቸው አቅም ስለሌላቸው እንቢተኛ መሆን አይችሉም፡፡ የተደራጁ ስግብግቦች አቅርቦቱን አንቀው ስለያዙት የተጠየቁትን ሳይወዱ በግድ ይከፍላሉ፡፡ ወቅታዊ የተብራራ መረጃ ስለማያገኙና ገበያውን ውዥንብር ስለሞላው የተጠየቁትን ከመክፈል ውጪ አማራጭ የላቸውም፡፡ በዚህ ምክንያት አቅማቸው የኮሰመነ ነው፡፡ በአጠቃላይ ይኼ ኋላቀርና ከዘመኑ ጋር መራመድ ያቃተው የግብይት ሥርዓት በዚህ ሁኔታ መቀጠል የለበትም፡፡ በተለይ መንግሥት ከዘመኑ ጋር እኩል የሚራመድ የፖሊሲ ማዕቀፍ አውጥቶ፣ የቁጥጥር ሥርዓቱን የሚያግዙለት አሠራሮችን መዘርጋት አለበት፡፡ በሠለጠነ የሰው ኃይልም ሆነ በጠንካራ ተቋማዊ አደረጃጀት በመታገዝ ይኼንን ኋላቀር የግብይት ሥርዓት ማፍረስ አለበት፡፡ ጤናማና ፍትሐዊ የንግድ ውድድር እንዲኖር ሕገወጦችና ሥውር ተዋናዮች ከሜዳው ውስጥ መወገድ ይኖርባቸዋል፡፡ በደላላ የሚመራ የግብይት ሥርዓት አገር ያጠፋል፣ ሕዝቡን ያደኸያል፡፡ ብልሹው የግብይት ሥርዓት የኑሮ ውድነቱን እያባባሰው ስለሆነ የመፍትሔ ያለህ መባል አለበት!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ ያቀረቡት መልቀቂያ ተቀባይነት ማግኘቱ ተሰማ

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው እያገለገሉ የሚገኙት የቀድሞው የውኃ ሀብት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለዘመኑ በማይመጥን ዕሳቤ አገር ማተራመስ ይብቃ!

ዘመኑ እጅግ ድንቅ የሚባሉ የሥልጣኔ ትሩፋቶችን በረቀቁ ቴክኖሎጂዎች እያቋደሰ ነው፡፡ ለልማትና ለዕድገት የሚማስኑ የኑሮን ጫና ቀለል የሚያደርጉ ቴክኖሎጂዎችን በብዛትና በስፋት ሲጠቀሙ፣ ያላደላቸው ደግሞ እርስ...

ፖለቲካውም ሆነ ዲፕሎማሲው ብልኃትና ብልጠት አይጉደለው!

ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የሁለቱን አገሮች የ120 ዓመታት የዲፕሎማቲክ ግንኙነት አስመልክቶ ያደረጉት የፖሊሲ ንግግር፣ በመንግሥት በኩል ቁጣ አዘል ምላሽ ነበር ያገኘው፡፡ እንደሚታወቀው የኢትዮጵያና...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት ብትችል፣ ከበርካታ ታዳጊ አገሮች የተሻለ በዕድገት ጎዳና የመገስገስ እምቅ አቅም እንዳላት የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ይህንን የመሰለ...