Tuesday, May 21, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የመንግሥት የመረጃ ፍሰት ከልማዳዊ አሠራር ይላቀቅ!

በሰሜን የአገሪቱ ክፍል በሚካሄደው ጦርነት የኢትዮጵያ ሕዝብ ትኩስና አስተማማኝ መረጃ ባለማግኘቱ፣ በየዕለቱ ከፍተኛ ግራ መጋባት እየተፈጠረ መሆኑን ማንም የሚገነዘበው ነው፡፡ ኃላፊነት ያለበት መንግሥት ወቅታዊና ተዓማኒነት መረጃ በአንድ የመረጃ ማዕከል አማካይነት ማስተላለፍ ስለተሳነው፣ ምንጫቸውና ማንነታቸው የማይታወቅ አካላት ሕዝቡን ባልተረጋገጡ መረጃዎች እያወዛገቡት ነው፡፡ በመረጃ ፍሰት ረገድ የመንግሥትን አዝጋሚነት እንደ መልካም አጋጣሚ የሚጠቀሙ አካላት፣ በፕሮፓጋንዳ የታጀቡ ውዥንብሮችን እያሠራጩ ከፍተኛ ቀውስ እየፈጠሩ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ከብሔራዊ ደኅንነትና ከአገር ጥቅም አኳያ ሁሉም መረጃዎች መለቀቅ አለባቸው ባይባልም፣ መንግሥት አንድ ጠንካራ የመረጃ ማዕከል በመመሥረት የአገርን ውሎና አዳር ለሕዝብ የማሳወቅ ኃላፊነትም ግዴታም አለበት፡፡ በ1990 ዓ.ም. የኢትዮጵያና የኤርትራ ጦርነት ሲጀመር ከተከናወኑ ሥራዎች መካከል አንዱ፣ የመንግሥት ቃል አቀባይ ቢሮ መክፈት እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ቢሮው በየዕለቱ የ24 ሰዓት ሪፖርቶችን በማደራጀት በተለይ ለሁሉም መገናኛ ብዙኃን ጋዜጣዊ መግለጫ በጽሑፍ በመስጠት፣ በግንባርም ሆነ ከግንባር ጀርባ ያሉ ሁነቶች ለሕዝብ ይደርሱ ነበር፡፡ ቴክኖሎጂ በከፍተኛ ደረጃ በዘመነበት በዚህ ጊዜ እንዲህ ዓይነት ማዕከል በማቋቋም፣ የመረጃ ፍሰቱን ማቀላጠፍ ሲገባ ሕዝቡን ለአደናጋሪዎች አጋልጦ መስጠት ተገቢ አይደለም፡፡

የሕዝብ ግንኙነት ዋና ተልዕኮ በአገልግሎት ሰጪና ተቀባይ መካከል ሊኖር የሚገባውን የመረጃ ፍሰት ማቀላጠፍ ነው፡፡ የመንግሥት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊነትና ተልዕኮ ደግሞ መጠኑና አድማሱ የሰፋ ነው፡፡ በተለይ በዚህ ዘመን የመንግሥት ቃል አቀባይ ከመሆን አልፎ የመንግሥት ዋነኛ የመረጃ ቋት ነው፡፡ የተለያዩ መንግሥታዊ መልዕክቶችን በማዘጋጀትና በማሰራጨት፣ በአገር አቀፍና በዓለም አቀፋዊ ክስተቶች ላይ የመንግሥት አቋም ማሳወቂያ ይፋዊ ተቋም በመሆን ሲያገለግል፣ ለአገር ደግሞ መስታወት ይሆናል ማለት ነው፡፡ በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ሲታይ ግን፣ የመንግሥት የሕዝብ ግንኙነት አገልግሎት ከልማዳዊ አሠራር አልተላቀቀም፡፡ የመንግሥትን የሕዝብ ግንኙነት ሥራ እንዲመራ በአዋጅ የተቋቋመ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት የሚባል የረባ ሥራ ሳያከናውን ቆይቶ ቢፈርስም፣ እሱን ተክቶ የመረጃ ፍሰቱን የሚያቀላጥፍ ተቋም ባለመደራጀቱ ምክንያት የመንግሥት የመረጃ ፍሰት ተስተጓጉሏል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢቋቋምም ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎችን በበቂ መጠን ማግኘት አልተቻለም፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሄደው ጦርነት ጅማሬ ላይ አንድ ግብረ ኃይል ተመሥርቶ የመረጃ ፍሰቱ ይቀላጠፋል ቢባልም፣ በአሁኑ ጊዜ ምን እየሠራ እንደሆነ አይታወቅም፡፡

ከበፊት ጀምሮ የመንግሥታዊ ተቋማት የሕዝብ ግንኙነት ክፍሎች፣ የመረጃ አደረጃጀታቸውና ሥርጭታቸው አቅም ደካማ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ብዙዎቹ መንግሥታዊ የሕዝብ ግንኙነት ተቋማት እንኳን መረጃ አደራጅተው ለሚዲያ ሊሰጡ ቀርቶ፣ የተቋማቱን መረጃዎች ስለማወቃቸው በጣም ያጠራጥራሉ፡፡ በመረጃ ነፃነት ሕግ ላይ በተቀመጠው መሠረት እንኳ መረጃ ለመስጠት የማይፈልጉ ብዙ ከመሆናቸውም በላይ፣ በሥርጭቱ ረገድም አድሎአዊነት ይታይባቸዋል፡፡ በጣም ውስን ከሆኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች ወይም ሠራተኞች ውጪ፣ ብዙዎቹ በተለይ የግል ሚዲያዎችን ለማስተናገድ ያላቸው ፍላጎት እጅግ በጣም ቀዝቃዛ ነው፡፡ በደብዳቤ ሳይቀር ተጠይቀው እንኳ መረጃ ለመስጠት አይፈልጉም፡፡ በልማዳዊ አሠራር የተተበተቡ ናቸው፡፡ የመንግሥት የሕዝብ ግንኙነት ሥራ በጣም ከመሽመድመዱ የተነሳ፣ በአገሪቱ የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ለሚዲያ ፍጆታም ሆነ ለምርምር መረጃ ሲጠየቅ ማግኘት አዳጋች ነው፡፡መረጃ ነፃነት አዋጁ በሚያዘው መሠረት የመረጃ ቋታቸውን ያላደራጁና ከጊዜው ጋር ለመራመድ የተሳናቸው በርካታ መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች አሉ፡፡ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ለአንድ ተቋም እንደ ትልቅ ገጸ በረከት መታየት ሲገባው ተቀጥላ ተደርጎ ሚናው በመንኳሰሱ፣ የመንግሥት የመረጃ ፍሰት በሚፈለገው ደረጃ ሊቀላጠፍ አልቻለም፡፡

ጠንካራ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ አንድን አገር በዓለም አቀፍ ደረጃ ከማስተዋወቁም በላይ፣ ኢንቨስተሮችንና ቱሪስቶችን በብዛት ለመሳብ ጠቃሚ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ያላትን የሰው ኃይል፣ የተፈጥሮ ዕምቅ ሀብት፣ የቱሪዝም መስህቦች፣ የኢንቨስትመንት አማራጮች፣ ባለችበት አኅጉርም ሆነ ክፍለ አኅጉር ሊኖራት የሚገባውን መልካም ገጽታ፣ ወዘተ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማስተዋወቅ የሚቻለው ጠንካራ መንግሥታዊ የሕዝብ ግንኙነት ሲኖር ብቻ ነው፡፡ በደካማ የሕዝብ ግንኙነት ምክንያት ግን በተበላሸው የድሮ ገጽታዋ ነው አሁንም ስሟ የሚነሳው፡፡ መረጃ ኃይል ነው፣ መረጃ ሀብት ነው፡፡ መረጃ የበርካታ አጋጣሚዎችና ዕድሎች መገኛ ነው፡፡ መረጃን በአግባቡ ማሠራጨት ባለመቻል ብቻ አገር እየተጎዳች ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ በተለይ ምዕራባውያን ጫናቸው ሊጠናከር ከቻለባቸው ምክንያቶች አንዱ፣ እውነትን ይዞ መረጃን አደራጅቶ ማሠራጨት አለመቻል መሆኑ ብዙዎችን ያስማማል፡፡ በመረጃ እጥረት ምክንያት እንኳንስ የውጮቹ ኢትዮጵያዊያን ሳይቀሩ የተሳሳተ ግንዛቤ እየያዙ ነው፡፡ በዚህ ሳቢያ በሕዝብና በመንግሥት መካከል ሊኖር የሚገባው ጤናማ ግንኙነት ሊሻክር ይችላል፡፡ ከትክክለኛው ነባራዊ ሁኔታ ይልቅ ሐሰት ገንኖ በመውጣት አደጋ ይፈጠራል፡፡ የመረጃ ፍሰቱንጠናከር የግድ መሆን አለበት፡፡

በመንግሥት ፖሊሲዎችና በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ግንዛቤ መፍጠር የሚያስችሉ ሕዝባዊ ውይይቶች በስፋት ከሌሉ፣ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል መተማመን የሚፈጥሩ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለባቸው አሠራሮች ካልታዩ፣ መንግሥታዊ ተቋማት በራፋቸውን ለሕዝብና ለሚዲያ ክፍት ካላደረጉ፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት ለሕዝብ ወቅታዊ ጥያቄዎች ምላሽ ካልሰጡ፣ የሕዝብ አቤቱታዎችና ቅሬታዎች በግልጽ ቀርበው ካልተሰሙ፣ ወዘተ መንግሥት እንዴት የሕዝብ ግንኙነት አለኝ ብሎ ያምናል? እስካሁን የተመጣበት ጉዞ ተመርምሮ የሕዝብ ግንኙነት ገጽታው ካልተለወጠ በስተቀር፣ አሁን በሚታየው ሁኔታ የትም መድረስ አይቻልም፡፡ በደካማ አሠራር መልካም የአፈጻጸም ሪፖርት እያቀረቡ መኩራራት ጊዜ ያለፈበት እንደሆነ መታወቅ አለበት፡፡ መንግሥት በሩን ገርበብ አድርጎ የአገር ውስጥና የውጭ ሚዲያዎችን በስፋት መጋበዝ አለበት፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ የሚመለከታቸው ባለሥልጣናት ከሚዲያዎች ጋር ጊዜ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ሕዝብ የማወቅ መብት በተግባር ሲረጋገጥ፣ የግልጽነትና የተጠያቂነት መንፈሱም በዚያው ደረጃ ይዳብራል፡፡ በሩ ሲዘጋ ግን ሐሰተኛ ሪፖርቶችና የፕሮፓጋንዳ ወሬዎች ይበዛሉ፡፡ በዚህ ደግሞ ማንም አይጠቀምም፡፡ ይህ ልማዳዊ አሠራር በቃ መባል አለበት፡፡

የሕዝብ ግንኙነት ሥራ በመርህ እንጂ በገጠመኝ የሚከናወን አይደለም፡፡ መንግሥት በሕዝብ ግንኙነት ተቋሙ ተጠቃሚ ካልሆነ ከሕዝብ ጋር እንዴት ነው የሚገናኘው? የመረጃ ፍሰቱ በሁለቱም ወገን በተቀላጠፈ መንገድ እንዲካሄድ ካልተደረገ ሕዝብም መንግሥትም ይጎዳሉ፡፡ መንግሥት እጅ ያለ መረጃ ወደ ሕዝቡ፣ ሕዝቡ ዘንድ ያለ መረጃ ደግሞ ወደ መንግሥት ሥርዓት ባለው መንገድ መተላለፍ አለበት፡፡ አቶ እከሌ ወይም / እከሊት ደስ ሲላቸው ወይም  ሲከፋቸው እየተባለ እንደ አየሩ ፀባይ የሚለዋወጥ ከሆነ፣ ከመርህ ይልቅ ገጠመኝ ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ ለአገር አይጠቅምም፡፡ የመንግሥት የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ተቋማዊ አደረጃጀት ያስፈልገዋል፡፡ ብቃት ባላቸው አመራሮችና ባለሙያዎች እየተመራ በሕዝብና በመንግሥት መካከል ድልድይ መሆን አለበት፡፡ ሁሉንም የሚዲያ ተቋማት በእኩልነት ማስተናገድ ይጠበቅበታል፡፡ ከልማዳዊና ከቀርፋፋ አሠራሮች በመላቀቅ ዘመኑ በሚጠይቀው መሥፈርት መሠረት ተግባርንና ኃላፊነትን መወጣት መለመድ አለበት፡፡ ሕዝብ የማወቅ መብት አለው ሲባል ለይስሙላ መሆን የለበትም፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ መቀጠል አይቻልም፡፡ ወቅታዊና ትኩስ መረጃ ከአንድ መንግሥታዊ ማዕከል መውጣቱ የሚጠቅመው የተቃራኒን የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ለማክሸፍ ብቻ ሳይሆን፣ የአገሩ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ የማይገሰስ መብት በመሆኑ ጭምር ነው፡፡ የመንግሥት የመረጃ ፍሰት ከልማዳዊ አሠራር መላቀቅ ያለበት ለዚህ ነው!

 

 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...

በስድስተኛው ዙር ጠቅላላና ድጋሚ ምርጫ የሚሳተፉ ፓርቲዎች በገዥው ፓርቲ ላይ ተቃውሞ እያቀረቡ ነው

በ2013 ዓ.ም. ስድስተኛው ምርጫ ባልተካሄደባቸው ክልሎች በጠቅላላና በድጋሚ ምርጫ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት ብትችል፣ ከበርካታ ታዳጊ አገሮች የተሻለ በዕድገት ጎዳና የመገስገስ እምቅ አቅም እንዳላት የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ይህንን የመሰለ...

የመግባቢያ አማራጮችን ተባብሮ መፈለግ ከጥፋት ይታደጋል!

በአሁኑ ጊዜ ሕዝብና አገርን ጤና የሚነሱ በርካታ ችግሮች በየቦታው እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ ችግሮቹ ከመጠን በላይ እየተለጠጡ ቅራኔዎች ሲበረክቱ ሰከን ብሎ ከመነጋገር ይልቅ፣ የጉልበት አማራጭ...

አገርን ከቀውስ ውስጥ ማውጣት ብሔራዊ አጀንዳ ይሁን!

የአገራቸው መፃኢ ዕድል የሚያሳስባቸው በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ወገኖች፣ በየቀኑ የሚሰሟቸው ማቆሚያ ያጡ ልብ ሰባሪ የግጭትና የጦርነት ዜናዎች እንቅልፍ ይነሷቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ማንኛውም...