Sunday, May 19, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የውጭ ምንዛሪ ግኝትና አጠቃቀም ጠንካራ ፖሊሲ ያስፈልገዋል!

የአንድ አገር ኢኮኖሚ ጤንነት ከሚለካባቸው በጣም ጠቃሚ ከሆኑ መለኪያዎች ውስጥ የውጭ ምንዛሪ ግኝትና አጠቃቀም አንዱ ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ ግኝት አስተማማኝ የሚሆነው፣ አጠቃቀሙን ጤናማ የሚያደርግ ጠንካራ ፖሊሲ ሲኖር ነው፡፡ ወደ አገሪቱ የሚገባውና የሚወጣው የውጭ ምንዛሪ በጠንካራ ፖሊሲ መታገዝ አለበት፡፡ ሰሞኑን በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ የተስተዋለው መረን የወጣ የጥቁር ገበያ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ከዚህ አኳያ መታየት አለበት፡፡ በባንኮች አካባቢ የሚታየው በደላላ ጣልቃ ገብነት የሚከናወነው የድርድር የውጭ ምንዛሪ ግብይት ተመልካች ያጣ ይመስላል፡፡ የውጭ ምንዛሪ አያያዙና ግብይቱ በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ፣ በሕዝቡ ኑሮ ላይ ሊያስከትለው የሚችለው መዘዝ አደገኛ መሆኑን መጠራጠር አይገባም፡፡ በሕጋዊውና በጥቁር ገበያው መሀል የነበረው መጠነኛ ልዩነት በአንድ ጊዜ ተለጥጦ፣ በጥቁር ገበያው በግላጭ አንድ ዶላር እስከ 70 ብር ድረስ መመንዘሩ ሲሰማ የችግሩን መክፋት ያመላክታል፡፡ በዚህ መነሻ አንዳንድ ጉዳዮችን መመልከት ተገቢ ነው፡፡

ፍራቻ የፈጠረው የውጭ ምንዛሪ ሽሚያ

የውጭ ምንዛሪ ፈላጊዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ ማሻቀብ ገበያው ውስጥ ከፍተኛ ሽሚያ እየፈጠረ ነው፡፡ ከእነዚህ ተዋንያን መካከል በሕገወጥ መንገድ ገንዘብ የሚያገኙ ሰዎች ጥቁር ገበያውን ወረውታል፡፡ የብር አቅም መመናመን የሚያሳስባቸው ሰዎች በውጭ ምንዛሪ ለመያዝ ሲሉ ሽሚያውን ይቀላቀላሉ፡፡ የፖለቲካ ውጥረት እንዲፈጠር የሚፈልጉ ኃይሎችም በዚህ ድርጊት ውስጥ በስፋት ሊሳተፉ ይችላሉ፡፡ አስመጪዎች የውጭ ምንዛሪ በወቅቱ ባለማግኘታቸውና በጥቁር ገበያው ውስጥ በከፍተኛ መጠን የብር የመግዛት አቅም ሲዳከም ከዚህ ቀደም በደህና ጊዜ ያስገቡዋቸው ዕቃዎች ላይ ዋጋ በመቆለል የዋጋ ግሽበቱን እያባባሱት ነው፡፡ አቅርቦትና ፍላጎት ባልተጣጣሙበት አገር ውስጥ የውጭ ምንዛሪ ግብይቱ ሰው ሠራሽ ለውጥ ሲታይበት የብዙዎች ኑሮ ይናጋል፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ሥጋት የሚገባቸው ሰዎች ንብረታቸውን በመሸጥ ወይም ያጠራቀሙትን ገንዘብ ወደ ጥቁር ገበያ በመውሰድ በውጭ ምንዛሪ ሲለውጡ፣ የውጭ ምንዛሪ ግብይቱ ጤንነት ይቃወሳል፡፡ በባንኮች አካባቢ የሚስተዋለው ብልሹ አሠራር የደላሎችን ጣልቃ ገብነትን በመጋበዙ፣ ሕገወጥ የውጭ ምንዛሪ ግብይት እንዲስፋፋ በማድረግ ችግር እየተፈጠረ ነው፡፡ በድለላው ውስጥ የሚሳተፉት የባንክ ኃላፊዎች ጭምር በመሆናቸው፣ ችግሩን ከመቼውም ጊዜ በላይ እንዳገዘፈው በግልጽ እየተነገረ ነው፡፡ ይህንን ችግር ሥርዓት ለማስያዝ ብሔራዊ ባንክ የአጭርና የረዥም ጊዜ መፍትሔ ላይ ማተኮር አለበት፡፡

የውጭ ምንዛሪ ግኝት መመናመን

በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ገበያዎች ውስጥ በሚስተዋሉ ችግሮች ምክንያት፣ ከኤክስፖርት የሚገኝ የውጭ ምንዛሪ ገቢ እየቀነሰ ነው፡፡ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሳቢያ የዓለም ገበያ ከመቀዛቀዙም በላይ፣ በቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት ይገኝ የነበረው የውጭ ምንዛሪ መጠን ዝቅተኛ ሆኗል፡፡ አልፎ አልፎ ከተለያዩ የልማት ድርጅቶች ሽያጭና ከቴሌኮም ፈቃድ አገልግሎት የተወሰነ የውጭ ምንዛሪ ቢገኝም፣ ችግሩ አሁንም በስፋት ስለሚስተዋል ክምችቱ አስተማማኝ አይደለም፡፡ የአገሪቱ አምራች ኢንዱስትሪ በአብዛኛው ጥሬ ዕቃዎችንና መለዋወጫዎችን ከውጭ የሚያስገባ በመሆኑ፣ ነዳጅን ጨምሮ በርካታ ሸቀጣ ሸቀጦች በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከውጭ የሚገቡ ስለሆነና ብዙዎችን በአገር ውስጥ ምርቶች መተካት ባለመቻሉ፣ የውጭ ምንዛሪ አያያዝና አጠቃቀምን በአግባቡ ለመምራት እንዳስቸገረ ይታወቃል፡፡ ይህም ጉዳይ ብርቱ መፍትሔ ይፈልጋል፡፡ ከእነዚህም አንዱ ጥቁር ገበያውን ወደ ሕጋዊ መንገድ ለማምጣት የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ ማውጣት ስለሆነ ቢታሰብበት መልካም ነው፡፡

ሕገወጥ የውጭ ምንዛሪ ፍልሰት

ሕገወጥ የውጭ ምንዛሪ ፍልሰት በተለያዩ መንገዶች የሚከሰት ሲሆን፣ በኢትዮጵያም ይኼ ችግር ለዓመታት መፍትሔ ያልተፈለገለት ችግር ነው፡፡ አገሪቱ በዓመት በርካታ ቢሊዮን ዶላሮች የሚገመት የውጭ ምንዛሪ ከምታጣባቸው መንገዶች መካከል አንዱ፣ በሕገወጥ መንገድ የሚገኝ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ወደ ጥቁር ገበያ መጉረፉ ነው፡፡ በተለያዩ ሥራዎች የተሰማሩ የውጭ ሰዎች ገንዘብ ለማሸሽ ሲሉ ጥቁር ገበያውን ያደሩታል፡፡ በተጨማሪም የገቢ ዕቃዎችን ከዋጋቸው በላይ እንደተገዙ በማስመሰል (Over Invoicing) አገር ውስጥ የሚያስገቡ አስመጪዎች መበራከት ከፍተኛ ተፅዕኖ እየፈጠረ ነው፡፡ ለምሳሌ 200 ዶላር የወጣበትን አንድ ምርት 900 ዶላር እንደወጣበት አድርገው የውጭ ምንዛሪ ያጋብሳሉ፡፡ ይህንን ዓይነቱን የውጭ ምንዛሪ ዝርፊያ በተለያዩ ዘዴዎችም ይጠቀማሉ፡፡ ይህ ብርቱ ቁጥጥር ሊደረግበት የሚያስፈልገው ሕገወጥ ድርጊት ነው፡፡ የኢኮኖሚውን ጤንነትም ያናጋል፡፡ ይህም የመፍትሔ ዕርምጃ ያስፈልገዋል፡፡

የሐዋላ ድርጅቶች አሉታዊ ሚና

በአሁኑ ጊዜ በርካታ የገንዘብ አስተላላፊ (ሐዋላ) ኩባንያዎች በአገሪቱ ውስጥ በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ነገር ግንእነዚህ የሐዋላ ኩባንያዎች መካከል ሕገወጥ ድርጊት ውስጥ የተሰማሩ አሉ፡፡ ብዙዎቹ የሚያስከፍሉት የአገልግሎት ኮሚሽን እየጨመረ በመምጣቱ ምክንያት፣ በርካቶች ወደ ጥቁር ገበያው እንዲሳቡ ተደርገዋል፡፡ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ከሕጋዊው መንገድ ይልቅ በሕገወጥ የሐዋላ አስተላላፊዎች ስለሚጠቀሙ፣ ለውጭ ምንዛሪ ፍልሰት ተባባሪ እየሆኑ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት አገሪቱ ማግኘት የሚገባትን እያጣች ነው፡፡ እንደ አማራጭ የሚታዩት የሐዋላ ኩባንያዎች አሠራር በጠንካራ ፖሊሲ መልክ ካልያዘ በስተቀር፣ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ግኝት የበለጠ ችግር ይገጥመዋል፡፡ ጥቁር ገበያው በተስፋፋ ቁጥር ደግሞ ሕገወጥነቱ ይቀጥላል፡፡ ለዚህም መፍትሔ ይፈለግ፡፡

ጠንካራ ፖሊሲ ካልኖረ ችግሩ ይቀጥላል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከበርካታ ተግባራቱ መካከል የውጭ ምንዛሪ አያያዝና አጠቃቀም ጤንነትን መጠበቅ ተጠቃሽ ነው፡፡ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ አያያዝ የአበዳሪ አገሮችንና የባንኮችን ቀልብ የሚስብ በመሆኑ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚፈለገው ሁኔታ እንዲራመድ የማድረግ ኃላፊነትም አለበት፡፡ ክምችቱ ጤነኛ የሚሆነው አጠቃቀሙ ሕጋዊ መንገድን ሲከተል ብቻ ነው፡፡ የንግድ ባንኮች የውስጥ አሠራሮችን ጤናማነት ከመፈተሽና የዕርምት ዕርምጃ ከመውሰድ ጀምሮ፣ የአጭርና የረጅም ጊዜ መፍትሔዎችን ጭምር ማየት ይኖርበታል፡፡ አገሪቱ ካላት ክምችት ላይ ሚዛናዊ በሆነ መንገድ የውጭ ምንዛሪ ባንኮቹ እንዲሰጡ፣ በባንኮቹ መካከል የሚከናወነው ግብይት ጤናማነት ተጠብቆ እንዲካሄድ ማድረግ የአጭር ጊዜ መፍትሔ ነው፡፡ በተጨማሪም ላኪዎች በዓለም ገበያ ውስጥ የሚያጋጥማቸው የዋጋ ማሽቆልቆል ለኪሳራ እንዳይዳርጋቸው ድጋፍ ማድረግ አለበት፡፡ ሁሉም አሠራሮች ጤናማ ሆነው እንዲቀጥሉ በጠንካራ ፖሊሲ መታገዝ ይገባዋል፡፡

በሌላ በኩል የረዥም ጊዜ ተግባሩ መሆን ያለበት የአገሪቱን ኤክስፖርት በማሳደግ፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን እዚሁ ማምረት ማስጀመር ነው፡፡ ይህ አገሪቱ የያዘችው ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ቢሆንም፣ በጠንካራ አፈጻጸም ተግባራዊ ሊሆን ይገባል፡፡ ኤክስፖርት ተስፋፍቶ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እንዲገኝ ሲፈለግ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ መጠናከር ይኖርበታል፡፡ ከውጭ የሚገቡ መሠረታዊ ሸቀጦች እዚሁ እንዲመረቱ ሲደረግ የውጭ ምንዛሪው ከብክነት ይድናል፡፡ ከሕገወጦችም ጥበቃ ይደረግለታል፡፡ በተለይ በገቢና በወጪ ንግድ መካከል የሚታዩ ክፍተቶች ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ መመናመንና ዝርፊያ ዋነኛዎቹ ምክንያቶች ናቸው፡፡ በአጠቃላይ በውጭ ምንዛሪ ግኝትና አጠቃቀም ላይ ተገቢው ጥበቃና ቁጥጥር ካልተደረገ፣ ኢኮኖሚ ጤንነት ችግር ነው የሚሆነው፡፡ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ አያያዝና አጠቃቀምጠንካራ ፖሊሲ ካልታገዘ፣ ኢኮኖሚውን ጤና አሳጥቶ ቀውስ ያስከትላል፡፡ ለዚህም ነው የውጭ ምንዛሪ ግኝትና አጠቃቀም በጠንካራ ፖሊሲ ይመራ የሚባለው፡፡ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን የሚያሰፋ ፖሊሲ አስፈላጊ ከመሆኑም በላይ ለሕገወጥ አሠራሮች በር የሚከፍቱ ድርጊቶችን የሚያመክን፣ የደላሎችን ሰንሰለት የሚበጣጥስ፣ የባንኮችን የድርድር ግዥ አሠራር ሥርዓት የሚያሲዝ፣ ጥቁር ገበያውን ወደ ሕጋዊነት የሚያስገባ፣ አባካኝነትን የሚከላከልና ዘመናዊ አሠራር የሚያሰፍን እንዲሆን መትጋት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ነው የውጭ ምንዛሪ ግኝትና አጠቃቀም ጠንካራ ፖሊሲ ያስፈልገዋል የሚባለው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...

በስድስተኛው ዙር ጠቅላላና ድጋሚ ምርጫ የሚሳተፉ ፓርቲዎች በገዥው ፓርቲ ላይ ተቃውሞ እያቀረቡ ነው

በ2013 ዓ.ም. ስድስተኛው ምርጫ ባልተካሄደባቸው ክልሎች በጠቅላላና በድጋሚ ምርጫ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት ብትችል፣ ከበርካታ ታዳጊ አገሮች የተሻለ በዕድገት ጎዳና የመገስገስ እምቅ አቅም እንዳላት የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ይህንን የመሰለ...

የመግባቢያ አማራጮችን ተባብሮ መፈለግ ከጥፋት ይታደጋል!

በአሁኑ ጊዜ ሕዝብና አገርን ጤና የሚነሱ በርካታ ችግሮች በየቦታው እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ ችግሮቹ ከመጠን በላይ እየተለጠጡ ቅራኔዎች ሲበረክቱ ሰከን ብሎ ከመነጋገር ይልቅ፣ የጉልበት አማራጭ...

አገርን ከቀውስ ውስጥ ማውጣት ብሔራዊ አጀንዳ ይሁን!

የአገራቸው መፃኢ ዕድል የሚያሳስባቸው በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ወገኖች፣ በየቀኑ የሚሰሟቸው ማቆሚያ ያጡ ልብ ሰባሪ የግጭትና የጦርነት ዜናዎች እንቅልፍ ይነሷቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ማንኛውም...