Tuesday, May 21, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

​​​​​​​[ቀኑን በሥራ አሳልፈው በድካም ስሜት ወደ መኖሪያ ቤታቸው የደረሱት ክቡር ሚኒስትሩ ባለቤታቸው አከታትለው የሚያቀርቡትን ጥያቄ በስልታዊ ማፈግፈግ ለማምለጥ ቢሞክሩም፣ ጥያቄው ባለማቋረጥ መዥጎድጎዱ ዕረፍት ነስቷቸዋል]

 • ደህና አይደለህም እንዴ?
 • ደህና ነኝ፣ ትንሽ ድካም ተጫጭኖኝ ነው። 
 • ጎሽ፡፡
 • ድካም ተጫጭኖኛል ነው እኮ ያልኩት፡፡ 
 • ሰምቻለሁ። 
 • ታዲያ እንዴት ጎሽ ይባላል?
 • ሕዝብን ለማገልገል መድከም መታደል ነው ብዬ ነው፣ ልክ አይደለሁም እንዴ? 
 • ሳታብራሪ ስላልሽው ግራ ተጋባሁ እንጂ እሱስ ልክ ነሽ፡፡
 • ጎሽ፡፡
 • የምን ጎሽ ነው የለከፈሽ ዛሬ? አሁን ደግሞ በምን ምክንያት ነው? 
 • ማብራሪያ የሌለው ምሥጋና እንዴት ግራ እንደሚያጋባ በአጋጣሚ ስለተረዳህ ደስ ብሎኝ ነው።
 • ምን ማለትሽ ነው?
 • ማብራሪያ የሌለው ምሥጋና እንዲህ ካደናገረ፣ ማብራሪያ የተነፈገ ጥያቄ ያለው ሕዝብ ምን ዓይነት ጨለማ እንደሚውጠው አየህ?
 • ሕዝቡ ማብራሪያ መቼ ተነፈገ? 
 • ታዲያ ምንድነው እየሆነ ያለው? ለምን አትናገሩም? 
 • ምኑን?
 • በአፋርና በሰሜን ወሎ ምን እየሆነ ነው?
 • ትንኮሳ ነው፡፡ 
 • ከተሞች ተይዘዋል እየተባለ አይደለም እንዴ?
 • አይ መያዝ ሳይሆን ትንኮሳ ነው የፈጸሙት፡፡ 
 • ከተሞቹ አልተያዙም ማለት ነው? 
 • ከተሞቹ ውስጥ አሉ፣ ግን ከተሞቹ ተይዘዋል ማለት አይቻልም፡፡ 
 • እና ምንድነው የሚባለው?
 • ነገርኩሽ አይደለም እንዴ? ትንኮሳ ነው!

[የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ መንግሥት ያወጣውን መግለጫ አንብቦ ያልገቡትን ጉዳዮች ለክቡር ሚኒስትሩ እንዲያብራሩለት እየጠየቀ ነው] 

 • ክቡር ሚኒስትር መግለጫውን አነበብኩት፣ ግን አንዳንድ ጉዳዮች አልገቡኝም።
 • አውቃለሁ ትላለህ እንጂ መቼ ይገባሃል አንተ?
 • ቆይ ክቡር ሚኒስትር በቃ መንግሥት ጦርነት አወጀ ማለት ነው?
 • የምን ጦርነት ነው የምትለው? መግለጫ አይደል እንዴ የተሰጠው?
 • መግለጫው የሚለውን አላዩትም እንዴ? 
 • ምን ይላል?
 • የመከላከያ ሠራዊቱ፣ ልዩ ኃይሎች፣ እንዲሁም ሚሊሻዎች ዕርምጃ እንዲወስዱ አቅጣጫ ተቀምጧል ይላል እኮ?
 • ታዲያ አቅጣጫ ተቀመጠ እንጂ ወደ ጦርነት ግቡ መቼ አለ? 
 • ዕርምጃ ውሰዱ ምን ማለት ነው? 
 • ጥቃት በሰነዘረው ላይ ዕርምጃ መውሰድ ነዋ፡፡ 
 • ታዲያ ወደ ጦርነት መግባት አይደለም እንዴ እንደዚያ ማለት? 
 • ተሳስተሃል፣ ጦርነት አይደለም፡፡
 • እና ምንድነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ውጊያ ነው፡፡
 • ጦርነት ያልሆነ ውጊያ ማለትዎ ነው?
 • አላልኩም፡፡
 • ምንድነው ያሉት?
 • ውጊያ ብቻ!

[ክቡር ሚኒስትሩ የማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴውን ሰብስበው በወቅታዊ የኢኮኖሚ ሁኔታዎች ዙሪያ እየመከሩ ነው]

 • ባለፈው ስብሰባ የስኳር አቅርቦት ችግር በአጭር ጊዜ መፍትሔ እንደሚያገኝ ተገልጾ ነበር፣ እጥረቱ መፍትሔ አገኘ?
 • ችግሩን ለመፍታት አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡
 • አቅጣጫ ማለት?
 • በአጭር ጊዜ ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል አቅጣጫ፡፡
 • የምርጥ ዘር አቅርቦት ለገበሬው በፍጥነት እንዲደርስ ባለፈው ተነጋግረን ነበር ከምን ደረጃ ላይ ነው?
 • ክቡር ሚኒስትር በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ወደ አፈጻጸም ለመግባት አቅጣጫ አስቀምጠናል፡፡
 • የምን አቅጣጫ?
 • ክረምቱ ከማለፉ በፊት ወደብ የደረሰውን ማዳበሪያና በመጋዘን ያለውን ምርጥ ዘር በአንድ ላይ ለአርሶ አደሩ ለማቅረብ የአፈጻጸም አቅጣጫ ተቀምጧል። 
 • አፈጻጸሙ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
 • ለአፈጻጸሙ ነው አቅጣጫ ያስቀመጥነው።
 • መቼ ነው ወደ አፈጻጸም የምትገቡት? የእርሻ ወቅት እያለፈ አይደለም እንዴ?
 • አቅጣጫ ያስቀመጥነው ለዚያ ነው። 
 • ለዚያ ነው አይደለም የሚባለው?
 • ምን ይሻላል ታዲያ ክቡር ሚኒስትር?
 • ለዛዛ ነው በል፡፡
 • እ…
 • እንዴት ያለ ነገር ነው? እሺ የሲሚንቶ እጥረትን በተመለከተ ማን ነው የሚመለከተው?
 • ከተቋሙ የተወከልኩት እኔ ነኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡ 
 • ዋናው ሚኒስትር ለምን አልተገኙም?
 • ለዚሁ ጉዳይ ከከተማ ውጪ በመሆናቸው ነው። 
 • እሺ፣ የሲሚንቶ ችግሩ በምን ሁኔታ ላይ ነው? መፍትሔ አገኘ? 
 • ጥረት እየተደረገ ነው ክቡር ሚኒስትር።
 • ምን ጥረት ተደረገ? 
 • ቀደም ብዬ እንዳልኩት ዋና ሚኒስትሩ ለዚሁ ችግር መፍትሔ ለመስጠት ፍለጋ ከከተማ ወጣ ብለዋል።
 • እየሸሹ ነው አትለኝም?
 • ምኑን ክቡር ሚኒስትር?
 • ችግሩን፡፡
 • የዘይት አቅርቦት በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል? እጥረቱ ተቀረፈ?
 • ክቡር ሚኒስትር ችግሩ እንዳለ ቢሆንም ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴዎችን ጀምረናል። 
 • ምንድነው የጀመራችሁት?
 • በዋናነት የችግሩ ምንጭ ምንድነው የሚለውን ለይተናል።
 • ከለያችሁ በኋላ ምን አደረጋችሁ?
 • አቅጣጫ አስቀምጠናል።
 • ይህ ኮሚቴ የመፍትሔ ኮሚቴ አይደለም።
 • ክቡር ሚኒስትር ነው እንጂ፡፡
 • በፍጹም፣ አቅጣጫ የጠፋበት የአቅጣጫ ኮሚቴ ነው! 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...

በስድስተኛው ዙር ጠቅላላና ድጋሚ ምርጫ የሚሳተፉ ፓርቲዎች በገዥው ፓርቲ ላይ ተቃውሞ እያቀረቡ ነው

በ2013 ዓ.ም. ስድስተኛው ምርጫ ባልተካሄደባቸው ክልሎች በጠቅላላና በድጋሚ ምርጫ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ የቢሮ ሥራቸውን አጠናቀው ከውጭ አገር የመጣ ወንድማቸውን ለመጠየቅ ያረፈበት ገስት ሀውስ ሲደርሱ ወንድማቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ፕሮግራም በመገረም እየተከታተለ አገኙት]

ውይ መጣህ እንዴ? እስኪ አረፍ በል፡፡ ምንድነው እንዲህ ያስደነቀህ? ተደንቄ ሳይሆን ግራ ግብት ብሎኝ ነው። ምኑ ነው ግራ ያጋባህ? የድልድይ ማስመረቅና የድልድይ ማፍረስ ነገር ነዋ። አልገባኝም? አለቃችሁ ድልድይ ሲያስመርቁ የተናገሩትን...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከዘመዶቻቸውና ቤተሰቦቻቸው ጋር ሆነው በዓሉን በመኖሪያ ቤታቸው እያከበሩ ነው። ባለቤታቸውም ለበዓሉ የተዘጋጀውን ዳቦ ባርከው እንዲቆርሱ ለሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

በል ዳቦውን ባርክና ቁረስልንና በዓሉን እናክብር? ጥሩ ወዲህ አምጪው... አዎ! በል መርቅ... ከዓመት ዓመት ያድርሰን... ኧረ በሥርዓት መርቅ ተው? ከዓመት ዓመት ያድርሰን አልኩኝ እኮ ...አልሰማሽም? ከዓመት ዓመት መድረሱ ብቻ ምን...

[ክቡር ሚኒስትር መንግሥት ይፋ ያደረገውን ንቅናቄ አመራሮችና ቤተሰቦቻቸው በግንባር ቀደምትነት እንዲቀላቀሉ መታዘዙን ለባለቤታቸው እያጫወቱ በዚያውም ወደተከፈተው የባንክ ሒሳብ ገንዘብ እንዲያስተላልፉ እያግባቧቸው ነው]

በይ እስኪ ሞባይልሽን አውጪና ወደዚህ የባንክ ሒሳብ አንድ ሺሕ ብር አስተላልፊ? ለምን? መንግሥት ያስጀመረውን ንቅናቄ አመራሩ ከነቤተሰቡ ግንባር ቀደም ሆኖ እንዲደግፍ ታዟል። የምን ንቅናቄ ነው መንግሥት ያስጀመረው? ‹‹ፅዱ...