Saturday, May 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገር​​​​​​​ፋታ የማይሰጠው የምጣኔ ሀብትና የኑሮ ጣጣ

​​​​​​​ፋታ የማይሰጠው የምጣኔ ሀብትና የኑሮ ጣጣ

ቀን:

በንጉሥ ወዳጅነው

በአንድ አገር ውስጥ ለመኖር አስፈላጊና ዋስትና ሰጪ ከሚባሉት ጉዳዮች አንዱ ምጣኔ ሀብት ነው፡፡ በተለይ የእኛን አገር የመሰሉ ሰፊ የሕዝብ ቁጥር ያላቸውና ገና ያልተነካ የተፈጥሮ ሀብት የሞላባቸው አገሮች ለምጣኔ ሀብታዊ ዕርምጃዎችና ማሻሻያዎች ልዩ ትኩረት ሰጥተው ካልተረባረቡ ፈጣን ዕድገትን ማረጋገጥ አይችሉም፡፡ ዘላቂ ሰላምና ዕድገት ብቻ ሳይሆን ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ ለመገንባትም መደነቃቀፋቸው አይቀሬ ነው፡፡ ስለዚህ በምንም ሁኔታ ውስጥ ቢሆኑ ፋታ አይሰጠውምና የሆድ ጉዳይ የሆነውን ምጣኔ ሀብት ቸል ማለት የለባቸውም፡፡

አሁን አገራችን ካለችበት ሁኔታ አንፃር ነገሩን በመፈተሽ እንጀምር፡፡ ወደድነውም ጠላነውም እንደ አገር ያለንበት ሁኔታ በጦርነት ውስጥ ነው፡፡ ጦርነትና የለየለት ግጭት አይደለም፡፡ ሁከትና አመፅ የሚበዛባቸው አገሮች ደግሞ ለዕድገትና ብልፅግና አመቺ አይደሉም፡፡ እንኳንስ የውጭ ባለሀብት ሊስቡና በንግድና ኢንቨስትመንት ሊራመዱ፣ ብድርናርዳታ ለማግኘትም ሲቸግሩ ማየት የተለመደ ነው፡፡ ለዚህም ነው አገራችን ተገዳም ቢሆን ከገባችበት ሕግ የማስከበር ጦርነት በሁሉም አማራጮች ወጥታ ፊቷን ወደመረጋጋትና ልማት ማዞር ያለባት፡፡

- Advertisement -

በብዙዎቹ ታዳጊ አገሮች ዕድገት ውስጥ እንደታየው ከቁርጠኛ መንግሥትና የሕዝብ ጥረት ባሻገር፣ የውጭ የገንዘብ ምንጭ መስፋትና ድጋፍ መጠናከር ፋይዳው ከፍ ያለ ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ደግሞ ትክክል ነው ባይባልም፣ የምዕራቡን ዓለም የመሰሉ ባለከፍተኛ ካፒታል መንግሥታት ከፍ ያለና የተቀናጀ የብድርና ዕርዳታ ድጋፍ የሚያደረጉት በቅድመ ሁኔታ ላይ እየተመሠረቱ ነው (የሰሞኑ የአሜሪካዊቷ የዩኤስአይዲ ኃላፊ ሰማንታ ፓወር ድራማን ያስታውሷል)፡፡

የውጭ ድጋፍ (External Resource) ከሚባሉት ሀብቶች አንዱ ብድር ነው፡፡ ሌላው የብድር (ዕዳ) ቅነሳ (Debt Relief) ሲሆን፣ ሌላኛው ከንፋስ አመጣሽ ንግድ የተገኘ ገቢ “Commodity Windfall” ነው፡፡ ከፖሊሲ ማሻሻያ የተገኘ ነው የሚባለው ደግሞ ባለፈው ሥርዓት የነበሩ አንዳንድ መጥፎ የፖሊሲ ስህተቶችንና ማነቆዎችን በማስወገድ የሚገኘው የዕድገት አስተዋጽኦ ነው፡፡ እርግጥ አገራችን በምትከተለው ዙሪያ መለስ የውጭ ግንኙነት መጠኑ ይለያይ እንጂ ከምሥራቁም፣ ከምዕራቡም ዓለም የምትቋደሰው አታጣ ይሆናል፡፡

እነዚህ የምጣኔ ሀብት እሴቶችን ለማግኘትም ሆነ በአገር ውስጥ ምርታማነትና ውጤታማነትን ለማሻሻል ግን፣ የፖለቲካ መረጋጋትና የአገር ደኅንነት መረጋገጥ አለበት፡፡ አሁን የተገባበት አገራዊ የግጭት ፖለቲካ መነሻው ምንም ይሁን ምን ፈጥኖ መጠናቀቅ ያለበት ለዚህ ነው፡፡ ለሰላም መነጋገር፣ በተለይ አመፅ ፈላጊው ኃይል ወደ ሕግና ሥርዓት የሚመጣበት መንገድ ካለም በሩ ሊዘጋ የማይገባውም ለዚህ ነው፡፡

በእርግጥ መንግሥት በተናጠል የተኩስ አቁም ስምምነትም ሆነ፣ ለረዥም ጊዜ ሕወሓት መራሹ ኃይል ወደ ግጭት ለመግባት ያደርግ የነበረውን ጥፋት በመታገስ ቅድሚያ ለሰላም መስጠቱ ይታወቃል፡፡ ሕግ ወደ ማስከበር ተገዶ እንደገባም አይዘነጋም፡፡ አገር የገጠማትን ይህን ችግር ግን ዜጎችም ሆንን መንግሥት፣ በተቀናጀና በተባባረ መንገድ መታገል ይኖርብናል፡፡ በተለይ በፐብሊክ ዲፕሎማሲና የሥነ ልቦና ጦርነቱን በመመከት ከትጥቅ ፍልሚያው ያላነሰ አስተዋፅኦ ማድረግ ይቻላል፡፡

በታሪክ እንደሚታወቀው በተለያዩ ቀውሶች፣ በመፈንቅለ መንግሥትና በእርስ በርስ ግጭቶች ውስጥ የገቡ አገሮች ፈተና አገርን ጠልፎ የሚጥለው ሲራዘምና የተቀናጀ ትግል ካልተደረገበት ነው፡፡ ይህን በቅርብ ሆነን የምንከታተለው ኢትዮጵያዊያን ደግሞ ፈጥነን ራሳችንን ማስተካከል ብቻ ሳይሆን፣ አደገኛውንና ከውጭ ጠላት የማያንሰውን ጁንታ ለሕግ ወደ ማቅረብ ካልሄደን ችግሩ ሊቃለል አይችልም፡፡

ነገሩ ‹‹መጥፎ ካለ ጥሩ አይጠጣም›› እንደሚሉት ነውና ሕወሓትና ግብረ አበሮቹ አገር ይዘው ለመሞት የጀመሩት ሴራ፣ በየትኛውም መስዋዕትነት መመከት አለበት፡፡ በተለይ ሴራው የአገራችንን መዳከም ከሚሹ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት የሚፈጸም መሆኑ ሲታይ፣ ለመንግሥትም ከዚህ የቀደመ ወቅታዊ ሥራ እንደሌለው ይታመናል፡፡ ግን የሆድ ነገርም ጊዜ ስለማይሰጥ ጎን ለጎን ኢኮኖሚውን መታደግና ምርታማነትን ማሳደግ መዘንጋት አይገባም፡፡

ቁጥሮች እንደሚያሳዩት ከሆነ በአገራችን ብቻ ሳይሆን፣ በአፍሪካ ያለው ሁኔታ ራሱ እጅግ አስደንጋጭ ነው፡፡ በብዙዎቹ አገሮች ያለውን እውነት በአማካይ ወስዶ መመልከት እንደሚቻለው፣ በፋብሪካ ሥራ የሚያገኙት አሥር በመቶ ያህል አፍሪካውያን ወጣት ሠራተኞች ብቻ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ ዘመናዊና መደበኛ በሆኑና በቂ ቴክኖሎጂ ባላቸው ኢንዱስትሪዎች ውስጥ የመቀጠር ዕድል የሚያገኙት ከአንድ በመቶ ያነሱ ናቸው፡፡

በዚህ ሳንካ የእኛን አገር ጨምሮ የሥራ አጡ ቁጥር (ያውም የተማረና የሠለጠነ ሥራ አጥ) በከፍተኛ መጠን እየጨመረ ለመምጣቱ ጥናት አያስፈልገውም፡፡ በዚህ ላይ ለዘመናት በቆየው ኢፍትሐዊ የፖለቲካ ሥሪት ምክንያት ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል አለመኖሩ፣ የመሠረተ ልማትና የማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ምጥጥን መጉደሉ የፈጠረው ክፍተት ቀላል አይደለም፡፡ ይህንን እውነት ለመቀየር አለመነሳት ነው አገርን ወደ ተጨማሪ ጫና የሚከተው፡፡

እዚህ ላይ ተያያዥነት ቢኖረውም የውጭ ምንዛሪ ዋጋ የማሻቀብ ነገር ቸል ሊባል የማይችል ችግር መሆኑን መመርመር ተገቢ ይሆናል፡፡ ፖለቲከኛውና የባንክ ባለሙያው አቶ ሙሼ ሰሙ ሰሞኑን በማኅበራዊ ድረ ገጻቸው ላይ እንደገለጹት፣ ዛሬ የአንድ ዶላር ተነፃፃሪ የጥቁር ገበያ ምንዛሪ (Parallel Market) 67 ብር እንደደረሰ በሰፊው እየተወራ ነው። ባለፉት ሦስት ዓመታት ሕገወጥ ምንዛሪው 100 በመቶ በላይ ንሯል። ሕጋዊ ምንዛሪው ደግሞ በአማካይ 36.5 በመቶ ደርሷል።

የውጭ ምንዛሪ ግብይቱ ወሳኝ በሆኑ የከተማችን አውራ ጎዳናዎች ላይ ዓይን ባወጣ መንገድ ይከናወናል፡፡ ወደ አብዛኞቹ ባንኮች ጎራ ካሉም ዶላር እንደ ሸቀጥ በደላላና በድርድር ለመሸጥ በራቸው ክፍት ነው ያሉት አቶ ሙሼ፣ የዶላር ዋጋ መናር የሚያስከትለውን መዘዝ መናገር ለቀባሪው ማርዳት ቢሆንም፣ ጫናውና ምሬቱ የሁላችንንም በር በየቀኑ እያንኳኳ ነው ነበር ያሉት። መስከረም ሲጠባና ተማሪዎች ትምህርት ቤት ሲገቡ ልብስ፣ ቁሳቁስና ፍጆታ ለማሟላት የሚጠብቀንን ፈተና ማሰብ ያስፈራል በማለት ጭምር።

ምሁሩ ሁኔታን በተጨባጭ እውነታዎች ለማሳየት ሲሞክሩም፣ በአጭር ጊዜ የዶላር ምንዛሪ 22 ብር ጭማሪ እንዴት ሊያሳይ ቻለ? ከሕጋዊ ምንዛሪው ጋር ያለው ልዩነቱስ በዚህ ደረጃ (22.5) ለምን ሊሰፋ ቻለ? ምክንያቱ ምንድነው? መፍትሔውስ? እዚህ ላይ ከሕጋዊ ገበያው ይልቅ ስለ ተነፃፃሪ ገበያው ለማንሳት የተገደድኩት፣ ተነፃፃሪ ገበያው ከጊዜ ወደ ጊዜ የኢኮኖሚያችን ወሳኝ መለኪያ እየሆነ ስለመጣ ብቻ ነው። ከሌላ ማሳያዎች (Indicators) አኳያም ማየት ይቻላል በማለት አንዳንድ ነጥቦችን ዘርዝረዋል።

 

  1. በአገሪቱ ላይ ቀስ በቀስ ሥጋትና ፍርኃት በመንሰራፋቱ በርካታ ሰዎች ንብረታቸውን እየሸጡ ብሩን በዶላር ስለሚለውጡ፣ አቅርቦቱን እያሳሳውና ፍላጎትን እያሳደገ መምጣቱ (Speculation, Holding, Hording, Short-Selling and Capital Flight)
  2. አንዳንድ ባንኮች ውስጥ ላኪና አስመጪዎች በደላላና በባንኮቹ አመራሮች ኮሚሽን ኤጀንትነት ዶላር መግዛትና መሸጥ ሕጋዊ መሆኑ፣ የተነፃፃሪ ገበያውን ዋጋ መተመን መቻሉ፣ የኮሚሽኑ ተካፋዩ እያደገ ጭማሪው መናሩ (Capital Flight, Under-Invoicing, High Premiums, Expanding Brokers Premiums)
  3. ለዝውውርናመሣሪያ ግዥ ከብር ይልቅ አስፈላጊው ዶላር ስለሆነ፣ በሕገወጥና በሕጋዊ መንገድ፣ በስፋትና በውድ ዋጋ እየተገዛ ለጦርነት አቅርቦት መዋሉ (War Economy) ይህኛው ጭብጥ ደግሞ፣ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ የተነሳበትን ግጭትን በፍጥነት የመቋጨት አስፈላጊነት ቁልጭ አድርጎ እንደሚሳይ ልብ ይሏል፡፡
  4. ሕጋዊ በሆነ መንገድ ባንክ ላይ የውጭ ምንዛሪ ማግኘትና ቢገኝም በቂ አለመሆን፣ ወደ ተጓዳኝ ገበያው ዶላር ፍለጋ ማማተር (Under Invoicing, Illegal Money Transfer, Under Cutting Supply)
  5. ላለፉት ሦስት ዓመታት እሴት ያልፈጠረና አቅርቦትን ያላሻሻለ መጠነ ሰፊ ገንዘብ በሰበብ አስባቡ ወደ ኢኮኖሚውና ግለሰቦች ኪስ መግባቱ፣ የአቅርቦትና ፍላጎት ሚዛኑን ማናጋቱ (Unbalanced Budget Deficit, White Elephant Projects, Expanding Monetary Policy) (ለአጠቃላይ ግሽበቱ እስከ 40 በመቶ ድርሻውን ይወስዳል) በማለት ያለ ይሉኝታና ማቅማማት አቶ ሙሼ አስቀምጠውታል፡፡

የባንክ ባለሙያውና ፖለቲከኛው ሙሼ ታዲያ ችግሩን አንስተው ብቻ አልቆሙም፡፡ ይልቁንም ምን ይሻላል? ምን ይበጃል? ሲሉ ተጨባጭ ዕርምጃዎችንም ነው ያመላከቱት፡፡ በእርግጥ ሥራው ፈታኝ፣ ተከታታይና ዘላቂ መሆን እንዳለበት ብቻ ሳይሆን የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ ዕቅድ እንደሚያሻ በመጠቆም።

  1. በአጭር ጊዜ ክትትልና ቁጥጥርን ማጠናከር፣ አሠራርን ማዘመን፣ የውጭ ምንዛሪ የሚጠይቁ የቅንጦት ፍላጎቶችን መገደብ፣ ገበያውን ያፈኑትን ደላሎች ከባንክም ሆነ ከጥቁር ገበያ ማስወጣትና በፖሊሲ እንዲመሩ ማድረግ (ጥቁር ገበያን ሕጋዊ እስከ ማድረግ መሄድ)፣
  2. በመካከለኛ ጊዜ የበጀት ጉድለትን (ማጥፋት ሳይሆን) በተለዋዋጭ ዓመት ሚዛን ባላንስ ማድረግ፣ እጅግ አስፈላጊ ከሆኑ ፕሮጀክቶች በስተቀር የአጭርና የመካከለኛ ጊዜ ፕሮጀክቶችን ዘመን ማራዘምና ጥብቅ ፊሲካልና ሞኒተሪ ፖሊሲ መመራት፣
  3. በረዥም ጊዜ በአጭርና መካከለኛ ጊዜ ላይ ተመሥርቶ የውጭ ምንዛሪን የሚያሳድጉ ፖሊሲዎችን መቅረፅና ኢንሴኔቲቫይዝ ማድረግ፣ መከታተልና ማጓልበት፣ ኢኮኖሚው እንዲሰፋ “De Facto Crawling Peg”  ሲስተምን በመተው፣ ሙሉ በሙሉ ወደ ተንሳሳፊ (Floating) ሲስተም መሸጋገር እንደሚያስፈልግ በማሳሰብ።

በእርግጥ በኢትዮጵያ ምድር ለተከሰተው የብር የመግዛት አቅም መድከምና የኑሮ ውድነት መባባስ በርካታ ምክንያቶችን የሚጠቅሱ ሌሎች ሰዎችም አሉ፡፡ ከማክሮ ፖሊሲ ውስንነት እስከ አቅርቦትና ፍጆታ አለመመጣጣን ወይም የፍጆታ ምርቶችን በአገር ውስጥ ካለመሸፈን ድክመት፣ ሸቀጥን በውጭ ምንዛሪ አብዛቶ እስከ ማስገባት እንቅፋቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በዚህ ላይ የሎጂስቲክና የገበያ አለመቀላጠፍ ወይም የዋጋ ህዳግ ዕጦት … እያሉ ብዙ ማለት ይቻላል፡፡

በንግዱ ማኅበረሰብ በራሱ ውስጥ የሚታየው አልጠገብ ባይነትና አግበስባሽነትንም ቀላል የማይባል ሳንካ እየፈጠረ ነው፡፡ በመሠረቱ አንዳንዱ ታች ያለው ቸርቻሪና አገልግሎት ሰጪ ነጋዴ የሚፈጽመው ሕገወጥ ተግባር፣ ለሕዝቡ ምሬትና መንገፍገፍ ትልቁን በር በመክፈት ላይ ነው፡፡ ገና ለገና የዶላር ምንዛሪ ከብር አንፃር ሲታይ ተወደደ (የብር የመግዛት አቅም ይህን ያህል በመቶ ቀነሰ) በሚል እዚሁ አገር ውስጥ በየጎሬው በሚመረተው በቆሎና ስንዴ ላይ ሳይቀር፣ ወይም በአብዛኛው ለአገር ውስጥ ፍጆታ በሚውለው የጤፍ ዋጋ ላይ ዋጋ መቆለል ከስግብግብነት ውጪ ሌላ ሊባል አይችልም፡፡

አንዳንድ ታዛቢዎች እንደሚሉት የገበያውን ብልሽት ያረጋጋሉ የተባሉት የሸማች ማኅበራት ሱቆች እንኳን ደሃውን ሊታደጉ ራሳቸውንም በሥርዓት አላዋቀሩም፡፡ አንዳንዶቹ የጥቂት ጥገኞች መፈንጫ ሲሆኑ፣ በተለይ ተከራዩን ሕዝብ በኩፖንና በመታወቂያ መለየት ስም ያገለሉ ናቸው፡፡ ጤፍና ጥራጥሬን የመሰሉ የአገር ውስጥ ምርቶችን ከአምራች የኅብረት ሥራ ገዝተው በተመጣጣኝ ዋጋ እንደሚያከፋፍሉ ብዙ የተነገረላቸው ጉደኞቹ የሸማች ማኅበራትም የሰብል ምርት ሊያቀርቡ ቀርቶ፣ በደርግ ጊዜ የተቋቋሙ ወፍጮ ቤቶችንና ምግብ ቤቶችንም ከሥራ ውጪ እያደረጉ ተቀምጠዋል፡፡

እነዚህ ማኅበራት የፖሊሲም ሆነ የመመርያ ችግር ባይኖርባቸውም በመልካም አስተዳዳር ዕጦትና በሙስና፣ እንዲሁም ከፋይናንስና ከማስፈጸም አቅም ውስንነት አንፃር ብዙዎቹ የተሽመደመዱ ናቸው፡፡ ለነገሩ ገበያ በማረጋጋት በኩል በሸማች ማኅበራት የተቋቋሙት ይቅርና ያለፈው የኢሕአዴግ መንግሥት ሰፊ ፕሮፓጋንዳ የሠራባቸው እነ ‹‹ጅንአድ›› እና ‹‹አለ በጅምላ››ም የሕዝብን የገበያ ተጠቃሚነት ከማረጋጋጥ አንፃር ውጤታቸው እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም፡፡

ለዚህ ደግሞ በቀዳሚነት ችግሩ ያለው እዚያው በየሱቆች ውስጥ ነው፡፡ ሸማቾች ሱቅ ውስጥ ብዙ ነገር አያገኝም፡፡ በተለይ አሁን እንደ ስኳርና ዘይት ያሉ መሠረታዊ ሸቀጦችን ማግኘት በጣም መክበዱ አንድ ማሳያ ነው፡፡ አብዛኛው የገበያ ዕቃ ከውጭ የሚገባ እንደ መሆኑም የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ሊያሰናዝራቸው እንዳልቻለ ደጋግመው ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ በዚህ ላይ ፖለቲካዊ አለመግባባትም ይባል የግጭት አዙሪቱ ሲመላለስ፣ የጦርነትና የግጭት ኢኮኖሚ የሚፈጥረው ጫና ቀላል አለመሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡

በእርግጥ መንግሥት የአገር ደኅንነትና ሰላምን ከመጠበቅና ከማስተዳዳር ባሻገር በኢኮኖሚው መስክም በኢንቨስትመንት ይሳተፋል፣ አቅጣጫ ያስቀምጣል፣ ዕቅድ ያወጣል፡፡ መንግሥት ብዛት ያላቸው የግል ባለሀብቶችንና ካፒታሊስቶችን ማፍራት እንደሚፈልግ ሁሉ፣ ምቹ ሁኔታን መፍጠርና ለፍትሐዊ ግብይት እንቅፋት የሚሆኑ ተግዳሮቶችንም ማስተካከል ይጠበቅበታል፡፡

ከምጣኔ ሀብት ዕድገት ማረጋጋጥ ባልተናነሰ የሸማቹን ሕዝብ ለመታደግና ከዕለት ገቢው ጋር ከማይጣጣም ጫና ለማዳን እንዲቻል የንግድ ሥርዓቱንና ግብይቱን ፈር ከማስያዝ ጀምሮ፣ በመረጃ ላይ ተመሥርቶ ሕጎችን ማስፈጸምና መቆጣጠር ለነገ የሚባል ሥራ መሆን የለበትም፡፡ ይኼ ደግሞ በሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላትና የፀጥታ ዘርፍ ሠራተኞች ተግባር ላይ ብቻ የሚወሰን አይደለም፡፡

ሕዝቡም ቢሆን ሲንቀሳቀሱ ያያቸውን ሕገወጥ የንግድ ተግባትራት ለፖሊስና ለሚመለከታቸው አካላት በመጠቆም ትብብሩን በተግባር ማሳየት ራሱን እንደ ማዳን ሊቆጥረው ይገባል፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ሕዝቡ በጋራ ጠላቱን ለመፋለም መነሳቱ፣ ልዩነቱን ወደ ጎን ብሎ ለአንድ አገር ህልውና መሠለፉ እንደ ወቅቱ መልካም አጋጣሚ መታየት አለበት፡፡ ይህን ዕድል ግን በአንድ በኩል ዘመቻውን በፍጥነትና በውጤታማነት ለማጠናቀቅ በመረባረብ ማሳየት አለበት፡፡

በሌላ በኩል ሁሉም በተሰማራበት ለምርታማነት፣ ወጪ ቆጣቢነት፣ ለመረዳዳትና ሕገወጥነትን በመታገል ማረጋጋጥ ይኖርበታል፡፡ መንግሥት በሕግ ማስከበርና በጦርነት ውስጥ ነው ብሎ በየተመደበበት የግል ጥቅሙን የሚያሳድደውን ጥገኛ መታገልም አንደኛው የትግል ሜዳ ሊሆን የግድ ነው፡፡ መንግሥትም በምጣኔ ሀብቱ መስክ የተዘረጋውን ደባ በመበጣጣስ፣ የተጀመሩ የለውጥ ተስፋዎችን በማስቀጠልና ትግሉን ወደ መልካም ዕድል ለመቀየር ይበልጥ መትጋት አለበት፡፡ የምጣኔ ሀብትና የኑሮ ጣጣ የሆድ ጉዳይ እንደ መሆኑ ፋታ አይሰጥምና!!   

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው nwodaj@yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ